በዶ/ር አረጋ አባተ
ተሐድሶ ቤተ ክርስቲያንን የመክሰሻ ስልቱ
የፕሮቴስታንትና የተሐድሶ ትልቁ ችግራቸው ያልተባለን፣ ዋና ጉዳይ ያልሆነን፣ ወይም አንዳንዶች የሚያደርጉትን ልማድ ይወስዱና ቤተ ክርስቲያን የምታደርገው፣ ኦርቶዶክሳውያን በሙሉ የሚያምኑትና የሚከተለው አስመስለው በመነሣት ለዚያ መልስ ሲሰጡ ይታያሉ፡፡ ይኸ ከጥንት ጀምሮ የሚያደርጉት ማደናገሪያና ስልታቸው ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያንን ለማጥቃት የሚመርጧቸው ክሶች፣ በአንድ በኩል ከዐውዱ የተነጠሉ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የአንድ ዐሳብ ማጎልበሻዎች ተደርገው የሚወሰዱ ጥቃቅን መገለጫዎችን እንደ ዋና ቁም ነገር አስመስሎ በማቅረብ ነው፡፡
በነገራችን ላይ ቤተ ክርስቲያን ልትጠየቅ የሚገባት በመሠረታዊው አስተምህሮዋ፣ በሥርዓት አፈጻጸሟ፣ በቅዳሴዋ፣ በአገልግሎቷ እንጂ አንዳንድ ክርስቲያኖች በሚጽፉትና የገባውም ያልገባውም በሚናገራቸው ዋና ባልሆኑ ግለሰባዊ ዐሳቦች ሊሆን አይችልም፡፡ ሁላችንም ልብ ማለት ያለብን ነገር ግን ቤተ ክርስቲያን የምትፈጽማቸው አገልግሎቶች ሁሉም ከድኅነት ጋር በአንድም በሌላም በኩል የሚገናኙ መሆናቸውን ነው፡፡ ለመረዳት ጥረት ማድረግ ያለብን ያንን ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን የማይጠቅምን ነገር ልትፈጽም አትችልም፡፡ ነገረ ቅዱሳ፣ ነገረ መላእክት፣ ነገረ ሰብእ፣ ቅዳሴው፣ ማኅሌቱ፣ ገድሉ፣ ተአምራቱ ሁሉም ከአምልኮና ከነገረ ድኅነት ጋር ይገናኛል፡፡ ታዲያ እነዚህ ሁሉ አገልግሎቶችና ሥርዓቶች ከነገረ ሥላሴ፣ ከነገረ ክርስቶስ፣ ከነገረ ምሥጢራት ብሎም ስለ ትንሣኤ ዘጉባኤ ካላት አስተምህሮ ጋር የሚሰናሰሉ ናቸው፡፡ ከእነዚህ የሚቃረን ሥርዓትም፣ አገልግሎትም ሆነ የአምልኮ ሥርዓት የላትም፡፡ ለሁሉም ባለሥልጣኗ ቤተ ክርስቲያን ስትሆን ሥልጣኗ የሚቀዳው ደግሞ ከመሠረቷና ከራሷ ከክርስቶስ እንዲሁም ከሕይወቷ ከመንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ ምስክሮቿ ደግሞ ቅዱሳት መጻሕፍት፣ ትውፊትና ሥነ ፍጥረት ናቸው፡፡
በጠቅላላው ኦርቶዶክሳዊነት በምልዓት በመረዳት የሚቀበሉት ሙሉ እውነት እንጂ የወፍ በረር አጉል ልማዶችን ወስዶ ቤተ ክርስቲያንን ለመክሰሻነት የምንጠቀምበት ወይም የምንመጻደቅበት ግማሽ እውነት አይደለም፡፡ የፕሮቴስታንና የተሐድሶ መሠረታዊ ችግር የሚመነጨው ይኸን ከሚያንሸዋረር እይታ ነው፡፡ ይኸንን ሸውራራነት የሚፈልገው ደግሞ ክርስትና የሚጠይቀውን ተጋድሎ (ገድል) ለመሸሽ ከሚፈልግ ማጭበርበሩ የተነሣ ነው፡፡
በአጭሩ በሐዲስ ኪዳን በክርስቶስ ስለሆነው ድንቅ ማዳንና ስለከፈለልን ካሳም ስንናገር ክርስቶስ ያዳነን እኛ ማድረግ ከማንችለውና ከአቅማችን በላይ ከሆነው እንጂ እኛ ማድረግ ከምንችለው ገድል፣ በጎነት፣ ፍቅርና መልካም ምግባራት ሁሉ ርቀን ‘አንዴ ስለዳንን ምንም መሥራት አያስፈልገንም’ ብለን እንድንዘረፈጥ አለመሆኑን ቤተ ክርስቲያን ታስተምራለች፡፡ ቅዱስ ወንጌል የሚነግረን ‘የሚወደኝ ቢኖር ትእዛዜን ይጠብቅ፣ ራሱን ይካድና መስቀሌን ይሸከም’ በማለት ነው፡፡ ይኸ ነው ገድል የሚባለው፣ መልካም ሥራ፣ ምግባር፣ መከራ የሚባለው ይኸን የመሰለው ጥብዓትን የሚጠይቅ አገልግሎት ሁሉ ነው፡፡ እንዲያውም ክርስቲያኖች የተጠየቁት ዓለሙን ትተው እርሱን ይከተሉትና ይመስሉት ዘንድ እንጂ በዓለም ያሸበርቁ ዘንድ አይደለም፡፡ ሰዎች ዘላለማዊውን መንግሥትና ጽድቁን ሲሹ ሌላው ሁሉ ይጨመርላቸዋል ነው የተባለው፡፡ ገድል ትሩፋት ማለት ይኸ ነው፣ መልካም መዓዛ ያለው ሥነ ምግባር ማለት አስቀድሞ ጽድቅና መንግሥቱን መሻትን ያንንም በመታመን መግለጥን ነው፡፡ ቸር የሚያሰኝ ይኸ ነው እንጂ ‘አይ ክርስቶስ ስለሞተልኝና አንዴ ስለጸድቅኩ ሥራ፣ ገድል ትሩፋት የሚባል ነገር አያስፈልገኝም’ ብሎ መኖርም ሆነ መስበክን አይመለከትም፡፡ ይኸን መሰሉ የተሳሳተና በምልዓት ያልሆነ ምልከታ ከቅዱሳት መጻሕፍት የወጣ፣ ምስክር የማይገኝለት ዘመን አመጣሽ ትምህርት ነው ተሐድሶና ተረፈ ተሐድሶዎች የሚያቀነቅኑት፡፡፡
የተረፈ ተሐድሶ ትርፍ ጩኸት
ይኸንን ጽሑፍ ለመጻፍ ያነሣሣኝ ሰሞንኑ አክሊለ የሚባል ልጅ በቴሌግራም ላይ ያስቀመጠውን ‘ተአምረ ማርያምን መስማት ሥጋ ወደሙን ከመቀበል ጋር ይስተካከላል’ የሚለው የተሐድሶ ጩኸት፤ በተጨማሪም ስለ ቅዱሳን ቃል ኪዳን የተሳለቀውን እና ታሪኩ አበራ የሚባል ሰው ‘አንዳንድ ወገኖቻችን ዕውቀት ከማጣት የተነሣ ከኢየሱስ በላይ ለመላእክት የተለየ ክብርና ከፍታ ሲሰጡ እንመለከታለን እንዲህ ዓይነቱ አመለካከት ሊታረም ይገባል’ በማለት ከረጅም ማብራሪያ ጋር የጻፈውን አሉባልታ ተመልክቼ ነው፡፡ ሁለቱም ‘ኦርቶዶክሳውያን ነን’ የሚሉ ነገር ግን ቤተ ክርስቲያንን በተደጋጋሚ በተሐድሶዊና በፕሮቴስታንታዊ ጉንተላዎች ሲከሱ የሚታዩ ሰዎች ናቸው፡፡ ከድርጊታቸው መታዝብ የሚቻለው ‘ውስጥ ሆነን፣ ኦርቶዶክስ ነን ብለን ማደስ አለብን’ ከሚሉት ወገኖች መካከል መሆናቸውን ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ተሐድሶ መሆናቸውን የማይቀበሉ ስለሆነ ስማቸው ተረፈ ተሐድሶ (Latent Reformists) ይባላሉ፡፡ ተሐድሶነታቸው ልቡጥ ነው፣ ሽፋን አለው፣ በትምህርት ስም፣ ‘በጠራ ዶግማ’ ስም ነው የሚያቀርቡት፡፡ ክሳቸውም ‘ቤተ ክርስቲያን ግብስብሱ ሁሉ የተጫነባት፣ ያልጠሩ ነገሮች ስላሉ ብዙዎች ዋጋ እየከፈሉ’ አስመስለው በማቅረብ፣ ከዚያም የምትሳሳትና ኩላዊት ያልሆነች አድርጎ ማሳየት ነው፡፡
ለአንድ ቅዱስ ‘ተዝካርህን ያወጣ፣ በስምህ ለለመነኝ፣ ለሽህ ትውልድ እምርልሃለው የሚል ቃል ኪዳን ከፈጣሪው ተሰጠው’ መባሉ የአንድን አማኝ ሕይወት የሚመሳቀልበት ምክንያት ምን እደሆነ ሲያብራሩ አታዩአቸውም፡፡ አክሊለ የሚባለው ልጅ ግን ሰሞኑን በዚህ ቃል ኪዳን ሲሳለቅ ነበር፡፡ ጥያቄው ‘አምላካቸው የሰጣቸውን ቃል ኪዳንና እምርልሃለሁ ያላቸውን ትውልድ አበዛው’ ነው? ወይስ ‘ጨርሶ ቃል ኪዳን መግባት የለበትም’ ነው እያሉ ነው? ሁለት ትውልድም ይማር አንድ ሚልዮን ትውልድ ይኸ የፈጣሪ ሥራ እንጂ አንድን ግለሰብ የሚያሳስብና ሕይወቱን ፈተና ውስጥ ሊጥል የሚችል ጉዳይ አይደለም፡፡ ይኸ የፈጣሪን አሠራር አለማወቅ ነው፡፡ ይኸን መሰል ስላቅ ‘ለእኛ ከባድ የሆነ ሁሉ ለእግዚአብሔርም ይከብደዋል’ ብሎ ከሚያስብ ክህደት የሚመነጭ ነው፡፡ ፈጽሞ ‘ቃል ኪዳን መግባት የለበት' የሚሉ ካሉም ክርስቲያኖች አይደሉም ማለት ነው፡፡ ክርስቶስ ሰዎችን ያዳነው ‘ከ 5500 ዘመን በኋላ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ’ ተብሎ ለአዳም በተገባ ቃል ኪዳንና ተስፋ ነው፡፡ እግዚአብሔር ለኖኅ፣ ለአብርሃም ለሌሎችም አባቶችም ቃል ኪዳን ሲገባላቸው ኖሯል፡፡ የሚያስገርመው ሲያድንም አንድ ሽህ ትውልዳቸውን ብቻ ሳይሆን ዓለምን በመላ ነው ያዳነው፡፡ ይኸን የእግዚአብሔር ድንቅ ሥራ በዛ ያለ፣ ርካሽም ነው ያለ የለም፡፡ ለቅዱሳን በተገባ ቃል ኪዳን የሚያላግጡም፣ እግዚአብሔር ቃል ኪዳን ሊገባ አይችልም ብለው የሚያስቡም ሰዎች ተረፈ ተሐድሶ ካልሆኑም እንኳን የዳኑበትን መንገድ አይረዱትም ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር እንደ እንግዳ ደራሽ እንደ ውኃ ፈሳሽ ሆኖ አላዳናቸውም፡፡ ይኸን መሰሉን የእግዚአብሔርን ቸርነት ሲያደንቁ የሚውሉ ቅዱሳን ሰዎች ሌሎች ወንድሞቻቸው የሚሠሯቸውንም ኃጢአቶች ይቅር ብሎ ያድናቸው ዘንድ ፈጣሪያቸውን መለመናቸው፣ ለዚያም ልመና ሽልማት ይሆን ዘንድ ከፈጣሪያቸው ቃል ኪዳን መቀበላቸው የቤተ ክርስቲያንን አስደናቂነት፣ የክርስትናን ረቂቅነት የሚያሳይ እንጂ ከወንጌል የወጣ ትምህርት አይደለም፡፡ የማንንም አማኝ መብትም የሚገፋና ሰዎችን ወደማመሰቃቀል የሚውስድ አይደለም፡፡
አክሊለ እያደረገ ያለው ምንድነው?
ተረፈ ተሐድሶዎች ቅዱሳት መጻሕፍትን በምልዓት ሳይረዱ ቤተ ክርስቲያንን የሚከሱት፣ ስለ ገድላት፣ ቃል ኪዳን፣ ተአምራት፣ በአጠቃላይ ስለሚታየውና ስለማይታየው ምሥጢር እና ነገረ እግዚአብሔር ያላቸው አረዳድ በግል መረዳታቸው የሚወሰን ስለሚመስላቸው ነው፡፡ አክሊለ በተደጋጋሚ ተአምርና ገድል እየጠቃቀሰ ቤተ ክርስቲያንን በመጎንተል የሚያቀርበው ክስ መሠረተ ቢስ ብቻ ሳይሆን ከጥንት አባቶች ምስክር የማይገኝለት ዐዲስ አረዳድ መሆኑን ተከታዮቹ ሊረዱት ይገባቸዋል፡፡ አክሊለ ሲናገር በሰማሁት ቁጥር ያልገባውን ነገር የገባው አስመስሎ በመናገርና አስደንጋጭ ድምዳሜ ላይ ሲደርስ በተደጋጋሚ ታዝቤለሁ፡፡ ለዚህ ሁሉ ችግሩና ኃይል የሆኑት ደግሞ ‘ጋይስ’ የሚላቸው ተከታዮቹ መሆናቸውን ባለፈው ተናግሬአለሁ፡፡ በዚያ ልጥፍም ጭምር ያረጋገጡት ሐቅ የተናገርኩት እውነት መሆኑን ነው፡፡ አክሊለ ‘ከቤተ ክርስቲያን ውስጥ ትክክል የሆነውን፣ ከጥንት አባቶች ምስክር የምናገኝለትን ብቻ፣ በሌሎችም አብያተ ክርስቲያናት የሚከናወነውን ብቻ ማመን እንችላለን፣ ይኸም ድኅነታችን ላይ ችግር ያለው አይመስለኝም’ በማለት በመሰለኝና በደሳለኝ የሚናገር ደፋር ልጅ ነው፡፡ ላለፉት ጥቂት ወራት ሊቃውቱ ሁሉ እርሱ ያጠፋውን ሲያርሙ፣ እርሱንም ወደተሟላ መረዳት ለማምጣት ሲረባረቡ ነው የከረሙት፡፡ ከዚያም በላይ የሊቃውንት ጉባኤ ሳይቀር ልጁ የፈጠረውን ቀውስ ለማስተካከልና ያሳመጻቸውን ተከታዮቹን ለማረቅ ሲለፋ ነው የሰነበተው፡፡ ይኸ ሁሉ እየተደረገም ልጁ አስቀድሞ ከሚይዘው ግማሽ እምነትና አቋም አንድም ቀን ንቅንቅ ሲል ታይቶ አያውቅም፡፡ ‘ያላወቅኩት ነገር ይኖራልና ልጠይቅ’ ሲል ተሰምቶ አይታወቅም፡፡ እርሱ ከሚያውቀው ውጭ ያለውን ሁሉ በተደጋጋሚ ‘በጥንት ቤተ ክርስቲያን የማይታወቅ፣ ሎካል፣ የአባቶች ስሕተት’ ወዘተ አድርጎ ለማቅረብ ሲሞክር ይታያል፡፡ በአጭሩ የጎሉን ቋሚ እየቀያየረ ነው ይከሰታል በተደጋጋሚ እንጂ ወደ ቤተ ክርስቲያን መረዳት ሲቀርብ አይታይም፡፡
የሚያሳዝነውም፣ ‘አመለካከትህ ስሕተት ነው፣ ረጋ ብለህ ተረዳ፣ ቤተ ክርስቲያንህን እወቅ፤ አንድ መጽሐፍ ብቻ አንብበህ ለድምዳሜ አትድረስ፣ የሚሉትን ሊቃውንትና አባቶች ሁሉ ወይ ጠላይ አድርጓቸዋል ወይም በዱርየ ቃላት እየጎነተለ ለመንጋው ስድብና እሱ ‘ረገጣ’ ለሚለው ብልግና ዳርጓቸዋል፡፡ በሚደረጉ ውይይቶችም ለመምህራን ያለውን ንቀት ቢያንስ በሁለት ውይይቶች ላይ ተሳትፌ ለመታዘብ ችያለሁ፡፡ ይኸንን ስለሚፈሩ ይመስላል ሲያግዙት የነበሩት አባቶች በጥፋቱ ሲቀጥልም ጭምር አሁን አሁን እየተዉት ናቸው፡፡ በአጭሩ ልጁ እያደረገ ያለው ‘ቤተ ክርስቲያንን ማረም እችላለሁ’ በሚል ትዕቢት ባልታረመ የቃላት አጠቃቀሙ አባቶችንና መምህራንን የማይሰማና የማይታዘዝ ትውልድ መፍጠር ነው፡፡ ይኸ አደጋ ነው፡፡ ይኸንን ተረፈ ተሐድሷዊ ዐሳብ ሳይቃጠል በቅጠል ማጥፋት ያስፈልጋል፡፡
ታሪኩ አበራስ ምን እያደረገ ነው?
****************************
በዚህ ሁለት ቀናት ወደ ቤተ ክርስቲያን ከተኮሱት ተረፈ ተሐድሶዎች መካከል ሌለኛው ታሪኩ አበራ የሚባለው ግለሰብ ነው፡፡ ስለዚህ ግለሰብ ስሰማ የነበረው ያኔ በጋሻውና ቡድኑ ቤተ ክርስቲያንን በሚያምሱበት የቡድኑ አባል በነበረበት ጊዜ ነበር፡፡ ትናንት ደግሞ የሆነ አደናጋሪ ጽሑፍ ጽፎ ሰዎች ልከውልኝ ሳላይ አልፌው ነበር፡፡ ዛሬ የቀሲስ ዲበ ኩሉን ጽሑፍ ሳይ ነው ሰውየው አሁንም እንደ ቤተ ክርስቲያን አባል የሚቆጠርና ተሐድሶነቱን አስቀጥሎ ያለ መሆኑን የተረዳሁት፡፡
እኔ ያነበብኩትና ሰሞኑን ስለ መላእክት የጻፈው በአጭሩ እንቶ ፈንቶና ልብወለድ አለ፡፡ መነሻ ላደረገው ("ሁሉ፡መዳንን፡ይወርሱ፡ዘንድ፡ስላላቸው፡ለማገዝ፡የሚላኩ፡የሚያገለግሉም፡መናፍስት፡አይደሉምን ?"ዕብ 1፥14) ምክንያተ ጽሕፈት ብሎ ያቀረበው ኋላ ላይ ‘ቤተ ክርስቲያን ከክርስቶስ ይልክ ለቅዱሳንና ለመላእክት ክብር ትሰጣለች’ ለሚለው ተሐድሶዊ አሉባልታና ክስ ታሪካዊ ዳራ ለመስጠት ነው፡፡ ታሪኩ አበራ እንደሚለው ቅዱስ ጳውሎስ በሚያስተምርበት ጊዜ ከአይሁድ ወገን ከፈጣሪ በላይ መላእክትን ያመልኩ የነበሩ የአይሁድ ቡድኖች አልነበሩም፡፡ ፈሪሳውያንም፣ ሰዱቃውያንም፣ ጸሐፍትም፣ መነናውያንም በዚህ አይታሙም ነበር፡፡ በሌላ በኩል ንባቡ የመላእክትን አገልግሎት ማስረዳት እንጂ የመላእክትን አማልእክት አለመሆን ለማመልከት አይደለም፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ስለ መላእክት አምልኮ በቀጥታ ነው የሚነቅፈው እንጂ ጨርሶ ፍንጭ በሌለው ንባብ ውስጥ የአምልኮ ነቀፋ መልእክት ሊያስተላልፍ አይችልም፡፡ ለምሳሌ ‘ትሕትናንና የመላእክትን አምልኮ እየወደደ፣ ባላየውም ያለ ፈቃድ እየገባ በሥጋዊ አእምሮ በከንቱ እየታበየ ማንም አይፍረድባችሁ ቆላ 1፡18’ በማለት በቀጥታ ሲናገር እናገኘዋለን፡፡ በአጭሩ ይሁዲነት የመላእክት አምልኮ ችግር ኖሮበት የሚጻፍለት ሃይማኖት አልነበረም፡፡ ‘የዕብራውያን መልእክቱ መላእክትን ከፈጣሪ በላይ ሲያመልኩ ለነበሩ አይሁድ የጻፈውን ነው’ የሚለው ኋላ ለሚያስቀምጠው ለመደምደሚያው ማቀባበያ እያዘጋጀ ነው፡፡ ታሪኩ ሌላም ከነገረ ድኅነት ጋር የሚያያዝ ተሐድሶዊ ክስ አቅርቧል፡፡
‘ልክ ዛሬ አንዳንድ ክርስቲያኖች በክርስቶስ ደም ጽድቅን ያለዋጋ በጸጋ አግኝተሃል የምትጸድቀው ክርስቶስ በመስቀል ላይ በሠራልህ የማዳን ሥራ ነው።ከአንተ የሚጠበቀው ይህንን በእምነት መቀበልና ይህ እምነትህን በመንፈስ ፍሬ መግለጥ ነው ሲባል አይደለም የምጸድቀው በራሴ ሥራ ነው እያለ የክርስቶስን ድካም ከንቱ ለማድረግ እንደሚሟገት ሁሉ አይሁድም በወንጌልና በክርስቶስ ላይ ያላቸው መረዳት ከኦሪቱ የቀደመ ዕውቀታቸው ጋር እየተደበላለቀ ይቸገሩ ነበር።’
ታሪኩን ‘የምጸድቀው በራሴ ሥራ ነው እያለ የክርስቶስን ድካም ከንቱ ለማድረግ የሚሟገት ክርስቲያን በምድር ላይ ይገኛል ወይ?’ ብላችሁ ብትጠይቁት ወይ መልስ የለውም አልያም የተለመደውን የተሐድሶን ክስ መምዘዙ አይቀርም፡፡ ‘በሥራ ነው የምጽድቀው’ የሚልም ይሁን ‘አንዴ ጸድቄአለሁና ሥራ አያስፈልገኝም’ የሚሉት ከክርስትና ጋር የተቃረኑ ናቸው፡፡ በነገራችን ላይ ትኩረት ስላልተሰጠው እንጂ በርካታ የተሐድሶና የፕሮቴስታንት ክሶችን ሲሰነዝር መኖሩን ወንድሜ መምህር ዮሴፍ ፍሥሓም ጽፎ ተመልክቻለሁ፡፡ ስላነሣቸው አብዛኛው ክሶች በተደጋጋሚ መልስ ስለተሰጠባቸው እነሱን በመዘርዘር አንባቢን አላሰለችም፡፡ በተደጋጋሚ ያነሣቸውን ተሐድሶዊ ትምህርቶቹን ከ Yosef Fiseha ገጽ ማንበብ ትችላላችሁ፡፡
የመፍትሔው ዐሳብ
*****************
የማቀርበው የመፍትሔ ዐሳብ አክሊለ የሚያስተጋባውን የተሐድሶና የተረፈ ተሐድሶ ክስ ረስቶ፣ ልክ በዐርብ ዓርብ ምሽት በቲክቶክ መርሐ ግብራችን ላይ እንደምናደርገው መሠረታዊውን ትምህርት ማስተማሩ ላይ መበርታት፣ በጽሑፍ ለሚለቋቸው ስሕተቶቹ ደግሞ ጠብሰቅ አድርጎ መመለስ ያስፈልጋል፡፡ አኬን በተደጋጋሚ ተመክሮ ከመመለስ ይልቅ አንገቱን እያደነደነ በመሆኑ ስሕተቱ ላይ ብቻ በማተኮር ማረም የሚያስፈልግበት ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡ ያኔ መንጋው ሲለየው ባያምንበትም እንኳን ቢያብንስ ላነገሠው መንጋ ሲል አፉን ዝም ያደርጋል ወይም ለይቶለት ‘ቤተ ክርስቲያንን በአፍ ጢሟ እንደፋታለን’ ብለው ሲያምሱ እንደነበሩት እንደነበጋሻው ጸጋው ተገፎ ብቻውን ይጨፍራል፡፡ በመንጋቸው ስድነት የሚመኩ ተረፈ ተሐድሶዎችን ሳይቃጠል በቅጠል ማስተካከል ካልተቻለ ኋላ ጥፋታቸውን ለማቃናት ውድ ዋጋ የሚጠይቅ ነው የሚሆነው፡፡
በጠቅላላው መሰል ክሶችን የሚያነሡ ሰዎችን ፍላጎት እና ምን እያሉ መሆኑን በመንቀስ ስሕተታቸው ላይ ብቻ በማተኮር ለተከታዮቻቸው እውነትን በምልዓት የመግለጥ አገልግሎታችንን ማጠናከር አለብን፡፡ እንደ ግለሰብ ማድረግ የምንችለውም ያንን ነው፡፡ ማስተማሩ ላይ መበርታት ነው፡፡ ከዚያ ውጭ የማይድነውን የመለየትና የመነጠል ሥራ ደግሞ የቤተ ክርስቲያን መዋቅር ኃላፊነት ይሆናል፡፡ የጠላትን ክስ እውነት አስመስሎ ከውስጥ ወደ ውጭ ወይም ከውጭ ወደ ውስጥ የሚያንባርቅን ፕሮቴስታንት፣ ተሐድሶና ተረፈ ተሐድሶ ቤተ ክርስቲያን ላይ በሐሰት መፈትፈቱን ማስቆም ግዴታችን ነው፡፡ የታሪኩ አበራ እና የመሰለ ተረፈ ተሐድሶዎች በመርዝ የተለወሰ ትምህርታቸውም ለወጣንያን ፈተና መሆኑ ስለማይቀር ከሥር ከሥር የማረምና የማቃናት ሥራ ይጠይቀናል፡፡ ‘በራሱ ጊዜ ይስተካከላል’ ብለን የምናልፈው ክስ ወይም የስሕተት ትምህርት አይኖርም፡፡ ባይሆን ለመታረም ፈቃዱ ያላቸውን ችኩል ተሳሳቾችን ለማገዝምና ለመርዳት መዘጋጀት አለብን፡፡ የተለመደውንና ‘ተገፋን’ የሚለውን ክሳቸውንም በቻልነው መጠን ምክንያት ምንጩን ልናደርቀው ይገባል፡፡ ይኸንን ስናደርግ ተሐድሶ ስልት ቀይሮ በተረፈ ተሐድሶዎች በኩል ለመንሰራራት የሚያደርገውን ሙከራ ከንቱ ማድረግ እንችላለን፡፡
ይኸው ነው፡፡
0 Comments