አያሌው ደጀኔ
ከዚህ ፅሁፍ ጋር ባያያዝኩት ፎቶ የምትመለከቷት እህታችን በሰይፉ ፋንታሁን ሾው ላይ እንግዳ ነበረች። እንግድነቷ አዲሱን ፊልሟን ለማስተዋወቅ ቢሆንም፣ 'ከመጣሽ ማርያም ታምጣሽ' እንዲሉ ሁኖ ሰይፉ የግል የህይወት ማህደሯን ገለጠው። ከአንድም ሁለት ልጆች ወልዳ ለብቻዋ ያለ አባታቸው እያሳደገች ያለችበትን ውጣ ውረድ አክብዳም፣ አኮስሳም አወራች።
'ሲንግል ማምነት' ወይም ልጅ ወልዶ ከአባት ውጭ ለብቻ ማሳደግ ለብዙዎች ምርጫ አይደለም። ነገሩ ግን በልዩ ልዩ አጋጣሚ የተነሳ ወደ እናቶች ህይወት ይመጣል። ወይ ከትዳር ውጭ በልዩ ልዩ አጋጣሚ መውለድ፣ ወይ በትዳር ውስጥ ወልደው ትዳር ፈርሶ ለብቻ ልጅ ማሳደግ የተለመደ ነው። ለዚህ አባትም፣ እናትም የሚወስዷቸው ድርሻዎች ሳይዘነጉ፣ ነገሩ ግን ቀላልና 'celebrate' የሚደረግ አይደለም።
ቢሆንም ነገሩ ቀላል አይሆንም። እናቶች ልጆቻቸውን ለማሳደግ ሲሉ ስንት የመከራ ሸለቆ ይሻገራሉ። መሆን የማይገባቸውን ለመሆን ይገደዳሉ። ልጆችም እንደ 'ወፍዘራሽ'፣ እንደ 'የሴት ልጅ' ያሉ የማህበረሰብ አስተሳሰብ አለመዳበር የፈጠራቸው 'ስድቦች'ን እየተጋቱ፣ እየተገለሉ፣ እየተሸማቀቁ፣ እየቆሰሉ ያድጋሉ። ያ በጊዜ ካልታከመ ኋላ በእራሳቸው ህይወትም ያመረቅዛል።
እኔ እራሴን እንደ አብነት ጠቅሼ ለቀጥል። የግል ጉዳዬን እዚህ በአደባባይ ማንሳቴ ካስተማረ በሚል ነው። በተበተነ ትዳር፣ እናትና አባት በአንድ ጣራ በሌሉበት፣ ከእናት ጋርም ይሁን ከአባት ጋር ብቻ ማደግ ምን እንደሆነ፣ ምን አይነት የስነልቦና፣ የስሜት፣ የአስተሳሰብ ጣጣና ቁስል ይዞ ማደግ እንደሆነ በዚህ መልኩ ተወልደው ያደጉ ሰዎች ያውቁታል። እኔ እራሴም ጭምር ትልቅ አብነት ነኝ። ነገሩ እንዲህ ነው።
ያደግኹት ከእናቴ ጋር ነው። እኔን ለማሳደግ የሆነችውን መሆን ሳስብ ስለ እሷ ሁሌም ጥልቅ ሀዘን ይሰማኛል። እንደ ተለኮሰ ሻማ በዐይኔ ስር ነው እየቀለጠች የበራችልኝ። እናቴ 'ሲንግል ማምነት' ምርጫዋ ያልነበረ ቢሆንም ከአባቴ በኩል በመጣ ጫና ሁናዋለች። አማራጭ አልነበራትም።
በዚያ ላይ ገጠር መኖር ደግሞ የሲኦል ቅርብ መሆን ነው። ገጠር ነው የኖረችው። የከተማው ቢያንስ ብዙ የህይወት ሸክም ማቅለያ የግንዛቤም፣ የማህበረሰባዊ እሳቤ ንቃትም፣ የኢኮኖሚ እድልም አለው።
እኔ በእርግጥ ከእናቴ ጋር ሁኜ ሳድግ የአባትንም፣ የእናትንም ሚና ተክታ፣ ሞልታ ለማሳደግ ስትል በህይወት መስመሯ የሚመጡላትን እድሎች ሁሉ 'ለእኔ ስትል'፣ ቅድሚያ ለእኔ ምቾት ተጨንቃ አምክናቸዋለች። ለእራሷ አልኖረችም። ያለ እድሜዋ በበረሃ ተገኝታ በጠዋት እንደጠወለገች አበባ ናት።
ግን እሷ ቤት ውስጥ የአባቴ አለመኖር ክፍተት እንዳይሆን፣ እንዳልብሰለሰልበት ማድረጉ ቢሳካላትም ከቤት ስወጣ ግን ከሰፈሩ ልጆች፣ ሰዎች፣ ትምህርት ቤት የሚመጡ ጥያቄዎችን እንዳያገኙኝ መሸፈን አልሆነላትም። ከማህበረሰቡ ነቀፋና ሽሙጥ ልትከልለኝ የምትችልበት ስልጣን የላትም። ያም የእሷ ጥፋት አልነበረም።
የምጠራው በአያቴ ነው። በእናቴ አባት። ያን ዛሬም መቀየር አልፈለኩም። ምክንያቴ ይቆይና ወደ ተጋፈጥኩት ጫና ላተኩር። ከየሰው አፍ የሚወጣ "አባት የለህም?" የሚለው ጥያቄ እየተከተለ ያሳድደኝ ነበር። እሸሸዋለሁ። ይከተለኛል። አንዳንዱ ስድ ደግሞ ድንገት ተናዶ ከሆነ "አንተ ወፍዘራሽ" የሚል ስድብ በአእምሮዬ ላይ ይዘራብኛል። ያም ነበር!
በዚህ ሳቢያ በልጅነቴ ከእድሜ አኩየቼ ጋር እንደ ልጅ ተጫውቼ ያደኩባቸው ጊዜያት ለቁጥር አይበቁም። ገለልተኛ ነበርሁ። የምሸሽ፣ የምተክዝ፣ የምርቅ ነበርሁ። ውሎዬ ከሽማግሌዎች ስር ነበር። 'አትጫወትን?' ስባል መልስ አልሰጥም–ዝም! ... መጫዎት እፈልግና ግን በጨዋታ መካከል በሚኖር የተለመደ የልጆች ጭቅጭቅ ወቅት አባትን ተንተርሰው የሚመጡ ስድቦችን ሽሽት የጨዋታ ፍላጎቴን ቀጥቼ ነው ያደኩት።
አባቴ በህይወት ያለ ቢሆንም፣ ከእኛ የራቀ ቦታ ነበር። የ3 አመት ልጅ እያለሁ ካየኝ በኋላ አልተያየንም። አልተጠያየቅንም። እያደግኹ ስመጣ፣ ወደ ዓለም የበለጠ ስጋለጥ፣ ወደ ሰው መስተጋብር የበለጠ ስቀርብ በአባቴ አለመታወቅ (ለሌላው ሰው) እና አለመኖር የተነሳ የሚመጡ ጫናዎች በረከቱ። ስለሆነም እንደ ህፃንነቴ ገለል በማለት አላመልጠውምና ወሰንሁ። አባቴን ልፈልገው።
እናቴን ቀስ እያልሁ ስለ እሱ፣ ስለሚኖርበት አካባቢ፣ በዚያ አካባቢ ስለሚዮሩ ሌሎች የእናቴ ዘመዶች በጨዋታ መካከል እየጠየቅሁ መረጃ ሰበሰብሁ። ያገኘኋቸው መረጃዎች ሲበረክቱ አንድ ቀን ጧት ከቤት ወጣሁ። ማንነትን ፍለጋ!
ጊዜው 1997 ዓ.ም ነበር–ወቅቱ ክረምት። ከቤት መውጣቴ የተለመደው የስራ ወይ የጨዋታ አወጣጥ አልነበረም። እኔ ማነኝ? አባቴ ማነው? ሌሎች ያላቅዃቸው ልጆችስ አሉት? እህትና ወንድም የሚሆኑኝ? የሚሉ ጥያቄዎቼን ለመመለስ፣ 'አባት የለሽ' አድርጎ ለሚነቅፈኝ ማህበረሰብ መልስ ለመስጠት ወጣሁ። ፍለጋ!
ከቤት ስወጣ ለእናቴ አልተናገርሁም። ከዚያ ሁሉ በመከራ የማሳደግ አመታት በኋላ፣ እሱ ያልጠየቀኝ እኔ "አባቴ" ብዬ ፍለጋ መውጣቴ እሷን ትቶ፣ ከድቶ እንደመሄድ እንዳይሰማት በሚል ለሰዎች ዘመድ ዘንድ እንደሄድሁ ንገሯት ብየ ወጣሁ። ከስንት አድካሚ ፍለጋና ጉዞ በኋላ አባቴን አገኘሁ። ልጆቹን (እህትና ወንድሞቼን) አገኘሁ። እነሱ ሊጠይቁኝ ሳይሞክሩ እኔ አድጌ እነሱን ፍለጋ በመሄዴ አፍረትም ሳይሰማቸው አልቀረም።
የእኔ አባቴን ፍለጋ መሄድ እናቴ በምትኖርበት አካባቢያችን ዘንድ ተጠረጠረ። "ውፍዘራሽ" ያለኝ የማህበረሰብ ክፍል መልሶ በሽሙጥ "ልጅ ይሄው ነው፤ አንገት ሲያወጣ ጥሏት 'አባቴ' ብሎ ሂዴ" ብለው እናቴን በሽሙር አሳቀቋት። እናቴ በመከራ ያሳደገችኝን እኔን ፍለጋ ወጣች። ጣጣው ብዙ ነው!
ሳምንት ሳይሞላው እናቴ እኔን ፍለጋ ዘመድ ዙራ ስታጣኝ ጠርጥራ ኑሮ መጣች። እኔ የሶስት አመት ልጅ ሁኜ ጥላው የሄደችውን አካባቢ በእኔ ምክንያት ዳግም ጎበኘችው። በአባቴ ቤት ከዘመድ መካከል አገኘችኝ። አቅፋኝ ተላቀስን።
ተቃቀፈን እንባዋን ሳይ ውስጤ 'አስለቀስኳት' የሚል የጥፋተኝነት ህመመም ሲሰቅዘኝ ይታወቀኝ ነበር። አላማዬ ማንነቴ ውስጥ የተፈጠሩ ክፍተቶችን መሙላት፣ ጠባሳውችን መጠገን ነበርና ከእናቴ ጋር ያኔውኑ ወደ ቤታችን ተመለስን። ከዚያ ወዲህ እናቴ ጋ አልተለያየንም።
ሆኖም ዛሬም ድረስ ከአባቴ ጋር ይህ ነው የሚባል መስተጋብር (emotional attachment) አይሰማኝም። ግን የተሰበረውን ጠግኜ ግንኙነታችንን ለማዳበር ትግል ላይ ነኝ። በህይወቴ ያለፍኩባቸው መልካም ስኬቶቼ ውስጥ ፈልጌ አላገኘውም። በተቻለ መጠን ደግሞ የህይወት መከራዎቼ ውስጥ ግን ከስበቦቹ አንዱ ሁኖ እንዳላገኘው እጠነቀቃለሁ–ጭራሹኑ ግንኙነቴን ላለማበላሸት ብዬ።
ይሄን ቀለል አድርጌ ለማስቀመጥ ያህል እንጅ ነገሩ "ሲንግል ማም ነኝ" ያሉ እህቶቻችን አቅልለው እንደሚሉት ቀላል አይደለም። ጥቂቶት ፈልገውት ቢሆኑም፣ በአስገዳጅ ሁኔታ ከዚህ እውነት ጋር የሚጋፈጡ ብዙዎች ናቸው። የእነሱን ህመም ቢደቀብቁት ይሁን።
በቤተሰብ መካከል ያላደጉ ልጆች ውስጥ የተቀበሩ ስንት መራራና ህመመም የሞላባቸው ታሪኮች ግን አሉ። ገጠመኞች ግን አሉ። experiences ግን አሉ። አይደበቁም። ተስለክልከው ያመረቅዛሉ። እራስን፣ ቤተሰብን፣ ማህበረሰብን እየሰረሰሩ ይበላሉ።
እነዚህ እውነቶች የበለጠ በተደበቁ፣ በታመቁ ቁጥር በልጆቹ የወደፊት የፍቅር፣ የትዳር ህይወት ላይ፣ የቤተሰብ ጉዳይ ላይ ቀስ እያሉ የሚያመረቅዙ ቁስሎች ይተዋሉ። ነገሩ ለሰው አፍ ሲሳይ ላለመሆን "enjoy አድርጌው ነው" ይባላል እንጅ እውነቱ እሱ አይደለም። ለማንኛውም በተቻለ አቅም ልጆች መቼም ቢሆን በአባትና እናት መካከል በጋራ ቢያድጉ የተገባና የተመረጠ ነው ለማለት ነው።
0 Comments