ገንዘብ ተፈጥሮአዊ አይደለም፤ በባሕርያችን አይታወቅም

በናትናኤል ሰለሞን

ገንዘብ ተፈጥሮአዊ አይደለም፤ በባሕርያችን አይታወቅም። ሰው በመኾን እውነት ውስጥ ምንም ስፍራ የለውም። ገንዘብ የሰው ሀሳብ ውጤት ብቻ ነው፤ ሰው ከመጣ በኋላ ያመጣው ነው። የገንዘብ ፈጣሪው ሰው ነበረ፤ አኹን ግን ገንዘብ የሰው ፈጣሪ ወደ መኾን ተሻሽሏል። የፈጠርነውን እያመለክነው ነን።

ገንዘብ በአጭሩ የዋጋ ተመን ወይም ስምምነት ማለት ነው። ለዚህ ነው እኛው ፈጠርነው የሚባለው። ገንዘብን ገንዘብ አድርጎ ያቆየው የእስካኹኑ የእኛ የአእምሮ ስምምነት ብቻ ነው፤ ሰዎች ተሰማምተን በላያችን እንዳነገሥነው መጠን፣ ተስማምተን ስናወርደው ደሞ እየተነነ እንደሚወጣ ጭስ የገባበት ይጠፋል። ይኼ ለአኹን ጊዜው አኗኗር የማይመስል ወሬ ይመስላል፤ በጣም ሊደንቀን ይገባ የነበረው ግን ተቃራኒው ነበረ፡፡ የተፈጥሮ አየርና ውኃ ይመስል ያለ ገንዘብ "እንዳንኖር" መኾናችን ይገርማል፡፡

የዚህን ዓለም ሥርዓት በደንብ ለሚታዘብ ሰው፣ ገንዘብ የባርነት ሀሳብ ባለአደራዎች መሣሪያ እንደኾነ ያስተውላል። በዓለም ያለው እጅግ ሰፊና ውስብስብ አጠቃላይ የገንዘብ እንቅስቃሴ አድራሻው ወደየት መድረስ ነው ቢባል መልስ የለም። ቢኖርም ልብ አይደርስም። የልብ ነገር አይመለከተውምና፤ ገንዘብ የተሠራው የሰውን ውጪያዊ ቅጥር (ሥጋ) ብቻ ለማገልገል ነው፤ ወደ ውስጥ ቅጥሩ መዝለቅ አይችልም። ለምሳሌ ቃል ኪዳን ለገንዘብ ምንድነው? ናፍቆት በገንዘብ እንዴት ይበየናል? ተስፋ ምን ያህል ገንዘብ ያወጣል? አደራና ገንዘብ ምንና ምን ናቸው?

ገንዘብ በሥጋ ቅጥር ውስጥ ብቻ የሚንቀሳቀስ የሥጋ አገልጋይ ነው፤ እርግጥ እንዳልነው አኹን አኹን ተገልጋይ ኾኗል። ገንዘብ እስከ መብላት፣ እስከ መጠጣት፣ እስከ መልበስ፣ ቤትና መሳሰሉን እስከ መገንባት ድረስ የሚረዝም ትንሽዬ ነው። እኔ እንደውም መብላትና መጠጣቱም ድረስ መዝለቁ ይቆጨኛል፤ ትል እንኳ በፍጥረት ሥርዓት ውስጥ ስለምትበላውና ስለምትጠጣው ዋጋ በማትጠየቅበት ዓለም ውስጥ የሰው ልጅ ለቁርስ ምሳ እራት የዕድሜውን አብዛኛ መገበሩ ያሳዝናል። ለራሱ እጆች ሥራ ምን ያህል መልሶ እንደተገዛ ለማየት እንኳ አለመፈለጉ ደሞ ይልቁን ተስፋ ያስቆርጣል። ከሥጋ የተወለደ ሥጋ የገንዘብ እስረኛ ነው።

'አሌሃንድሮ ጆዶዉስኪ' የሚባል አንድ የፊልም ባለሙያ 'በታሰረ ጎጆ (ድፊት?) ውስጥ የተወለዱ ወፎች መብረር የሚባለው ነገር ዕብድት ይመስላቸዋል' ይላል። ዳዊት በበኩሉ 'ሰው ክቡር ኾኖ ሳለ አያውቅም እንደሚጠፉ እንስሳት መሰለ' እንዳለው መኾኑ ነው። ገንዘብ በዛሬ ዘመን ትርጓሜው ሰው የገዛ ተፈጥሮዉን እንዲረሳ፣ ሲብስም እንዲንቅ አድርጎታል። ኾን ተብሎ እንደዚህ መደረጉ እንዳለ ኾኖ እያንዳንዱ ሰውም ለዚህ የባርነት ነገር አንዳንድ ሰንሰለት አቀብሏል። ገንዘብን ለተሻለ ሰውነት መገለጫ አድርገን ያፀደቅነው ሰሞን በጥልቅ ለተሳሰረ ባርነት ተላልፈን ተሰጥተናል። አኹን ከገዛ ራሳችን የሚፈታንን መሲሕ እየጠበቅን ነን።

ሆኖም ማንም አይፈታንም። የገንዘቡ ዓለም ሥልጣን የሚወድቀው በተገነባበት ቦታው በእያንዳንዳችን አእምሮ ውስጥ እንጂ በእጅ ተገፍቶ አይደለም። ግን ከባድ ነው። እንደተባለው መብረር መቻላቸውን በትውልድ ሂደት እየረሱ ለመጡ ወፎች ማስረዳት እንደ ቁም ቅዠት ይቆጠራል። መሥዋዕትነትም ይፈልጋል። የዚህ ዓለም የሥጋ ሰው ደሞ ከራሱና በዙሪያው ካለው ደህንነት ውጪ ደንታው አይደለም፤ በጊዜና በቦታ ስለራቀው ስለሌላው ሰው ከልብ የሚገደው መዝናናት ወይ ዜና መስማት የፈለገ እንደኾነ ብቻ ነው። በተረፈ እሱና ቤተሰቡ ብቻ በዓለም ላይ ቢኖሩ ምንም የማይመስለው ብዙ ሰው አለ፤ ይህም ብዙ ሰው በየሀገራቱ ኾኖ ሐይማኖት ኾኗል፣ ፖለቲካ ኾኗል፣ ትምህርት ቤት ሰርቷል፣ ኢንደስትሪ ተክሏል፣ .. ። በዚህም ብዙ ሰው ላይ ገንዘብ በገዛ ፈቃዱ ስለሠለጠነ፣ ከገንዘብ ውጪ ማሰብ ለብዙሃኑ የማይታሰብ ይኾንበታል። መጥፊያው ኹሉ ይመስለዋል። ግን አልነበረም።

ለማንኛውም አንዳንድ የፖለቲካው ዓለም ሰዎች ድህነትን ከዚህ ዓለም ጠራርጎ ለማጥፋት ሌተቀን እንሰራለን እያሉ ይሰልቁብናል (መቼም አይጠፋም፤ ድህነት ከጠፋ እነሱም ይጠፋሉ)። እኔ ግን በእውነት የምመኘው ሐብታምነትም ድህነትም ተያይዘው የሚጠፉባትን (ትርጉማቸው በመቀየር ሊኾን ይችላል) ዓለም በቁሜ ሳለኹ ማየት ነው።

Post a Comment

0 Comments