ሁሉ ተፈቅዶልኛል ሁሉ ግን አይጠቅምም።
ሁሉ ተፈቅዶልኛል በእኔ ላይ ግን አንዳች አይሰለጥንም።
1ኛ ቆሮ 6፣12
መጥፎ ልምድ ወይም ሱስ ጊዜ፣ ገንዘብ እና አቅም የሚያባክን፤ ትኩረት የሚሰርቅ፤ ጤና እና ክብርን የሚቀማ ....ነው፡፡
መጥፎ ልምድ /ሱስ የአልኮል፣ የሲጋራ፣ የጫት፣ የአደንዛዥ ዕፆች...ብቻ አይደለም፡፡ ሌሎች የኃጢአት ልምምዶችንም ያጠቃልላል፡፡ ሱስ በቀልድ ልንጀምረው እንችላለን፤ መውጫው ግን እንደምናወራው ቀላል አይደለም፡፡ የትውልዳችን አንዱ ሕመም ሱስ ነው፡፡
ሱስ በዘመናዊነት ካባ ተሸፍኖ የብዙዎችን ሕይወት እያጨለመ ነው፡፡ ጤናን ከስሮ መዝናናት ያዋጣል? ሱስ ለጊዜው የሚሆን ደስታ በመስጠት መርዙን በውስጣችን ይዘራል፡፡ በሱስ የሚሠራው የቅድስና መንፈስ አይደለም፡፡
መርቅኖ መጋጨት፣ ሰክሮ መደባደብ፣ ወዶ ራስን መጉዳት ................... ከእግዚአብሔር ሊሆን አይችልም፡፡ አንዳንድ ጊዜ መርሳት የምንፈልገውን ጉዳት/ ጉዳይ ለማስታመም ብለን ጉዳት መጨመር የለብንም፡፡ የደረሰብንን መከራ መርሳት የምንችለው የሚደርስልንን እግዚአብሔርን በማሰብ ነው፡፡ ሱስ አስከፊ መሆኑን ሱሰኞችም ያምናሉ፤ ነፃ መውጣት ነው ያልተቻለው። ጥቂት የመፍትሔ አሳቦችን ልጠቁም
ከሱስ እንዴት መውጣት ይቻላል?
1) ጉዳቱን መገንዘብ፦ በጊዜያችን፣ በጤናችን፣ በገንዘባችን፣ በማህበራዊ ሕይወታችን፣ በመንፈሳዊ ሕይወታችን የደረሰውን ወይም የሚደርሰውን ጉዳት/ ኪሳራ ማሰብ አለብን፡፡ የሱስን ጉዳት በሚገባ ካሰላሰልነው ጥላቻ ይኖረናል፡፡ ለመውጣት ሞክረን ሲያቅተን እልህ ውስጥ ልንገባ እንችላለን፡፡
2) እንደ ችግር መቀበል፦ ጉዳቱን መዝነን ችግር እንደሆነ አምነን መጸለይ እንጀምር፡፡ የጸጋው ችሎት እንዲያግዘን ወድጄ የተያዝኩበት ሰንሰለት ቁረጥልኝ ብለን እንጩህ፡፡ እንደ ችግር ካልተቀበልነው ግን ስንጎዳ ስንታመም ነው ጸሎቱ ትዝ የሚለን፡፡ ብዙዎች እንደ ችግር ስላልተቀበሉት ዘመናዊነት ነው፣ ለመዝናናት ነው እያሉ ስም ይሰጡታል በሞት ዋዜማ ናችሁ ብሎ ዶ/ር ካላወጀላቸው አይነቁም
3) መወሰን፦ ውሳኔ ቁርጠኝነት ካለበት የኃይል ምንጭ፣ የኑሮ መሪ አቋም ነው፡፡ አምነን ወደን ከሱስ ለመውጣት መወሰን ያስፈልጋል፡፡ በተያዝንበት ክፉ መያዝ ላለመያዝ ደግመን ጤናችንን ላለመጉዳት ጨክነን ለመውጣት መወሰን እና የመፍትሔ አሳቦችን መፈለግ አለብን፡፡ የእግዚአብሔር ቃልና መንፈስ ከየትኛውም ሱስ ለመውጣት ትልቅ ኃይል ነው፡፡
4) ከመቀነስ መጀመር፦ ከሱስ ጋር ብዙ ለተዛመዱ የሚመከረው ከመቀነስ መጀመር እንዲለማመዱ ነው፡፡ በየቀኑ እንደ ሥራ ቁጥሮ በመቀነስ ወደ መተው/ ማቆም መምጣት ይቻላል፡፡
5) በጎ ልምድ መተካት፦ ሱስ በሂደት የሚለመድ አውሬ ነው፡፡ ስለዚህ ልምድን በልምድ መተካት ያስፈልጋል፡፡ የማንበብ ልምድን ማሳደግ እና ሌሎች በጎ ልምምዶችን ማብዛት አለብን፡፡ በጎ ልምድ ወደ በጎ ይስበናል፡፡
6) ከሚፈትኑን ሰዎች፣ ሁኔታዎች እና ቦታዎች ራስን ማግለል፦ ሱስ የሌለባቸው ወይም ወደ ሱስ የማይገፋፉ ሰዎች ጋር መሆን፡፡ ከሱስ ነፃ አካባቢዎችን መምረጥ፡፡ ለሱስ የሚዳርጉ ዝግጅቶችን፣ ሁኔታዎችን፣ አጋጣሚዎችን መሸሽ ያስፈልጋል፡፡
7) ራስን በሌሎች ነገሮች/ በሥራ መጥመድ፦ ለምሳሌ ሳይጠጣ ማደር የማይችል ቢሮ/ ሥራ ቦታ ራሱን በሥራ ቢዚ አድርጎ ማቆየት ቢችል ወይም ለቤተሰብ ጊዜ ቢሰጥ በአይምሮው ትኩረት ይነሳዋል፡፡ ትውልድ ሱስን እንደ ሥራ ይዞት ማየት ግን ከባድ ነው፡፡
8) መንፈሳዊ ተግባራትን ጨክኖ መያዝ፦ ጸሎተ፣ ቃሉን ማንበብ መስማት፣ ጾም፣ ንስሐ፣ ወደ ገዳማት ለበረከት መውጣት ....እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡
9) ቆርጦ መውጣት፦ በጸሎት መስነን ቆርጠን ከሱስ ግዛቶች መውጣት ያስፈልጋል፡፡ ልባችን ጋ ጥቂት እንኳ የሱስ ፍቅር ቅሪት መኖር የለበትም፡፡
10) በመጥፎ/ በጥሩ አጋጣሚዎች ሰበብ ወደ ኋላ አለመመለስ፦ ወደ ድሮ የሱስ ሕይወት የሚመልሱንን ሁሉ እምቢ ማለት ያስፈልጋል፡፡
የእግዚአብሔር ጸጋ ትውልድን ያግዝ!(አሜን(3)

0 Comments