ሙስሊም ጠልነት በኢትዮጵያ፤ የሰሜኑ ፖለቲካና አፈታሪክ ውርስ የተሰኘው መጽሐፍ ምልከታ
በሳሂህ ኢማን
መንደርደሪያ፡-
እለቱ ሐሙስ ነው፤ ለአንድ ጉዳይ እግሮቼ እየመሩ አንዋር መስጊድ አካባቢ ወዳሉ ሱቆች አደረሱኝ፡፡ ዐልፎ ዐልፎ መጽሐፍት መግዛት ሲያሰኘኝ የምሄደውና የምገዛው እዛ ነው፡፡ በእግረ መንገድ ወደ አንዱ ኢስላማዊ መጽሐፍት ወደ ሚሸጡበት ሱቅ ጎራ ስል "ሙስሊም-ጠልነት በኢትዮጵያ፤ የሰሜኑ ፖለቲካና አፈታሪክ ውርስ" በሚል ርእስ በፋኢዝ ሙሐመድ የተጻፈው መጽሐፍ እይታዬ ውስጥ ገባ፡፡ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ማስታወቂያውን ዐይቼ ነበር፡፡ እኔ አንዋር መስጊድ የደረስኩት በማስታወቂያ ከተነገረው መውጫ ቀን አንድ ቀን ቀደም ብዬ በመሆኑ መጽሓፉ ለሽያጭ የወጣበት የመጀመሪያው ቀን ላይ የደረስኩ ይመስለኛል፡፡ ወዲያው አነሣሁት አገላበጥኩት፤ በጀርባው ሽፋን ላይ የጸሐፊውን "ፊደል ዘለቅነት" ስመለከትማ ምን እንደሚል ለማየት ጉጉቴ ጨመረ፡፡ ለመጽሓፉ የተጠየኩትን ዋጋ ሳላቅማማ ከፍዬ የሄድኩበትን ጉዳይ ሳላከናውን ወደ ድንኳኔ ለመመለስ ታክሲ ውስጥ ገባሁ፡፡ አላስቻለኝም እዛው ንባቤን ጀመርኩ፡፡
የመጽሓፉን ርእስ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ባየሁበት ወቅት አግራሞትን ፈጥሮብኛል፤ አበው "ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም" እንደሚሉት ጉድ እየሰማሁ እንዳለሁ ነበር የተሰማኝ፡፡ "በእርግጥ ሙስሊም ጠልነት ኢትዮጵያ ውስጥ አለን?" ብዬ ነበር ራሴን የጠየኩት፡፡ በእኔ ዕውቀት ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩ ሙስሊምና ክርስቲያን አንድም በዝምድና፣ እልፍ ሲል ነፍስ ለነፍስ የተጋመደ ጓደኛማችነት፣ ሥራ፣ አገራዊ መልካም እሴቶች ያስተሳሰሩት ሕዝብ ነው፡፡ ለዚህ እንደ ምሳሌ ስለራሴ ብናገር ቅድመ አያቴ አባባ አሊ ይባላሉ፡፡ እንዴት ቢሆን በየትኛው አንጀቴ እኒህን የመገኛዬን ሥር ልጠላ እችላለሁ? እንደኔ ክርስቲያን ያልሆኑትን የእርሳቸውን ልጆችና የልጅ ልጆች እንዴት ቢሆን መጥላት ይቻለኛል? ከወንድም የሚጠጋጋኝን ውድ ጓደኛዬን ሐሰንን በየትኛው ልቤ ልጠላው እችላለሁ? የአባቴ የልብ ጓደኛ የሆኑትን አባባ ኢብራሒምን ከአብራካቸው እንደተከፈለ ልጃቸው ያሳደጉኝን እንዴት ልጠላ እችላለሁ? ባደኩበት አካባቢ ቤተ ክርስቲያን ሲገነባ ሙስሊሙም ሲያዋጣ፣ መስጊድ ሲታደስና አዲስ ሲገነባ፤ ክርስቲያኑ አብሮ ሲያዋጣ ነው እያየሁ ያደኩት፤ የምነግራችሁ በመጽሐፉ እንደ ምሳሌ ስለተጠቀሰው ስለ ወሎ ሳይሆን፤ ስለ ጎንደር ነው፡፡ ይህ ነው ጉድ ሳይሰማ ያሰኘኝ፤ ለእኔ ጉድ ነውና፡፡ ለነገሩ ጊዜው ብዙ ጉዶች የምንሰማበት ሆኖ ካረፈው ቆየት አለ አይደል?
በእነዚህ ሐሳቦች ተጠፍንጌ ተይዤ ማንበብ ጀመርኩ፤ ምስጋናውን አንብቤ ወደ ማስታዎሻነቱ አለፍኩ፤ በዚህ ወቅት የመጽሐፉ ይዘት ምን ሊሆን እንደሚችል የጸሓፊውንም ስነ ልቡና መገመት አልከበደኝም፡፡ ሚዛናዊነቱን ተጠራጠርኩት፡፡ የጸሓፊው ፊደል ዘለቅነት (ለጸሓፊው ፊደል ዘለቅ በሚል ለመጥራት የተገደድኩት ከዛ በኋላ ነው፡፡ ምክንያቴም ዕውቀትና ትምህርት የዘለቀ ሰው ይለወጣል ብዬ ስለማምን ነው፤ እውነት ለመናገር ከሆነ ግን በፋኢዝ ለውጥን አላየሁም፡፡) በሃይማኖታዊ ቅንአት የእብለት ዳዋ እንደተዋጠ አመላከተኝ፡፡ መጽሐፉ በዘጠኝ ምዕራፎች እንደተዋቀረ እወቁልኝ የሚለውን ማውጫ አወራርጄ መግቢያውን፣ ምእራፍ አንድ፣ ሁለት እያልኩ ዘለቅሁ፡፡ ግምቴም ትዝብቴም ትክክል ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ ፋኢዝን እንድናውቀው፣ በዚህ ርእስ እንድንወያይና ሐሳባችንንም እንድንሰጥ መንገድ ስለሆናችሁን በምስጋናው ሥፍራ የተመሰገናችሁትን ወገኖች በሙሉ እኔም ከመቀመጫዬ ብድግ በማለት ክበሩልኝ ብያለሁ፡፡
የመጽሐፉን መግቢያ ሳነብ እንዲህ የሚል አንብቤ እንደነበር ትዝ ሲለኝ ብዕሬን አነሣሁ፡- "…ዋናው ሐሳቤ ተወያይተን ችግሮቻችንን እንድንፈታ ነውና የጎረበጣችሁን ወይም ያላሳመናችሁን ነገር ብትጠቁሙኝ ለማስተካከል ወይም ለመወያየት ዝግጁ መሆኔን እወቁልኝ፡፡" እናም በዚህ መጽሐፍ የጎረበጠኝንና ያላመንኩበትን እነሆኝ ለማለት ብዕሬን ሰድሬያለሁ፡፡
ወንድማችሁ ሳሂህ ኢማን ነኝ!
ይቀጥላል…
0 Comments