ሙስሊም ጠልነት በኢትዮጵያ አለን ካለስ ለምን - ክፍል ሁለት



እስኪ መጽሓፉን በበረራ ላስቃኛችሁ፡፡
የመጽሐፉ ርእስ፡- ሙስሊም-ጠልነት በኢትዮጵያ፤ የሰሜኑ ፖለቲካና አፈታሪክ ውርስ?
ጸሓፊ፡- ፋኢዝ መሐመድ
የኅትመት ዘመን፡- 2019
አታሚ፡- አልተጠቀሰም
የገጽ ብዛት፡- 314
የምእራፍ ብዛት - ዘጠኝ
መጽሐፉ በውስጥ ገጾቹ፡-
ማስታዎሻነቱ፡- ለአራት ወገኖች እንደሆነ ይገልጻል

በመግቢያው፡-

የኢትዮጵያ የጥንት ሥልጣኔ እና የአሁን የዜጎቿን ሁኔታ ያትታል
የፖለቲካዋ ባሕሪ መጠላለፍና በራስ ወዳድነት የተተበተበ እንደሆነና ለዚህ ተጠያቂዎቹ የሰሎሞናዊው ሥርወ መንግሥት እንደሆነ ያለውን እምነት እንዲህ በማለት ይገልጻል፡-
"…. ለዚህ ደግሞ የሰለሞናዊ ሥርወ መንግስት ትርክት አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ይኸው ሥርወ መንግስት አገሬን በችግር ተብትቧት ሄዷል የሚል እምነት አለኝ፡፡"1
ፋኢዝ የዚህን ሥርወ መንግሥት አስተሳሰቦች ለመተቸት በቁርጠኝነት እንደተነሣሣ፤ ለዚህ ደግሞ ከቤተሰብ የወረሰው አገራዊ አደራ እንዳለበትና ግድ እንደሚለው ይገልጻል፡-
"እኔም ታዲያ እንደ አንድ አገሩን እንደሚወድ ዜጋ በተለያዩ ዘርፎች ወደፊት ወገኔን ለማገልገል ካለብኝ ኃላፊነት በተጨማሪ ይህን "አግላይ" ትርክት በመተቸት ዳግም እንደዚህ አይነት ትብታብ ተከስቶ ትውልዱን መቀመቅ ውስጥ እንዳይገባ የምችለውን ለማድረግ ኃላፊነት እንዳለብኝ ይሰማኛል፡፡ እንደዚሁም ከቤተሰብ የተረከብኩት አገራዊ አማና (አደራ) ሁሌም እንቅልፍ የሚያስተኛ አይደለም"

መጽሓፉ የተጻፈበት ዐላማ፡-

1. በአገሪቱ ጉዳይ ወሳኝ የሆኑት ውስን ግለሰቦች ወይም ስብስቦች (ሙስሊም ያልሆኑ ማለቱ ነው) ብቻ ሲወስኑ ስለተመለከተና ይህ ደግሞ አገርን ሊሰነጥቅ የሚችል ቁርሾ በመሆኑ እርሱን ለማከም
2. እስልምናን እና ሙስሊሞችን በተሳሳተ መንገድ በመረዳት ለዘመናት በማግለል ላይ የተመሠረተ ትርክትና ፖሊሲ በመኖሩ ተባብረንና ተፈቃቅረን ሁላችንም የምንኖርባት ሰፊ አገርን እንጂ የምንናቆርባት ጠባብ ኢትዮጵያን ላለመገንባት በትርክት ደረጃ ቀድመን ማስተካከል ያለብን ለመጠቆም
3. በአገር በቀል ደረጃ ሙስሊም-ጠልነት መኖሩን ለማብራራት የሚሉት ያየኋቸው ናቸው
ምዕራፍ አንድ፡-
በምዕራቡ ዓለም ሙስሊም ጠልነት መቼ እንደ ተጀመረ
1 የመጽሐፉ ገጽ 2
ለምዕራቡ ዓለም ሙስሊም-ጠልነት እንዲስፋፋ ደግሞም ሙስሊም-ጠልነትን በመቃወም የምሁራን ሚና ምን እንደሚመስል፤ ለሙስሊም-ጠልነት አስተዋጽኦ ያደረጉ አስተሳሰቦች
እስልምና አሃዳዊ ባህልን የሚያራምድ ሃይማኖት ተደርጎ መታመኑ
እስልምና ከሌሎች ሃይማኖቶች አንጻር ፍጹም የተለየ (የተቃረነ) ተደርጎ መገመቱ
የጥላቻ ሃይማኖት ተደርጎ መለፈፉ
የጅሃድ ጽንሰ ሐሳብ ከአክራሪነትና ሽብርተኝነት ጋር መያያዙ
እስልምና በአጠቃላይ ሴቶችን ይጨቁናል ተብሎ መታመኑ፤ በተለይ ሒጃብ ሴቶችን መጨቆኛ መሳሪያ ተደርጎ መታየቱ
እስልምና ለምዕራቡ ዓለም የማይመጥን የበታች፣ የኋላ ቀርነትና የፀረ-ሥልጣኔ መገለጫ ተደርጎ መታየቱ
እስልምና በፖለቲካውው ረገድ አማራጭ የሌለውና ታጋሽ አይደለም መባሉ ናቸው ሲል የዘረዝራል
በሙስሊም-ጠልነት ላይ የአገራችን ልሂቃን ሚናም ተጠቅሷል፤ ለምሳሌ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ፣ / መስፍን /ማርያም ሌሎችም
ሙስሊም-ጠልነት በኢትዮጵያ ሊኖር አይችልምን? ብሎ በመጠየቅ "በኢትዮጵያ እንዴታ" ለማለት ይመስላል ሙስሊም ብዝሃ በሆነባቸውም አገራትም ጠልነቱ እንዳለ ማስረጃዎችን ይመዛል፡፡
ምዕራፍ 2-
"አገር-በቀል ሙስሊም ጠልነት በኢትዮጵያ" በማለት መዘርዝሩን ይጀምራል፤ የሙስሊም ጠልነቱ አንዱ ማሳያ ከትምህርት ማግለል እንደሆነ ይገልጻል፡፡ በመቀጠልም በአገራችን ለሙስሊም-ጠልነት መስተዋል አስተዋጽኦ ያደርጋሉ ያላቸውን እንዲህ ይዘረዝራል፡-
• "ያልተፈተነ" መስተጋብር እና "ያልጠራ" ትውውቅ
ኪነ-ጥበብ፡- ቀዳማዊ "መሐጀባ"
ዘመናዊ መሐጀባ
o ዓለማዊ መምህራን
o ሃይማኖታዊ መምህራን
ፖለቲከኞች
ታሪካዊ ውርስ
እነዚህ እስከ ምዕራፍ 6 ድረስ እንዴት ሙስሊም-ጠልነትን እንደታየባቸው ተዘርዝሯል፡፡
ያልተፈተነ መስተጋብርና ያልጠራ ትውውቅ የሚለውን በሦስት ከፍሎ ለማየት ሞክሯል፡-
ያለተፈተነ ክርስቲያን-ሙስሊም ተሞክሮ
ያልተፈተነ ሙስሊም-ክርስቲያን ተሞክሮ
የዳበረ ሙስሊም-ክርስቲያን (ክርስቲያን-ሙስሊም) ተሞክሮ
ምዕራፍ 7-
ስለ ዕውቁ እስራኤላዊ የታሪክ ተመራማሪ / ሐጋይ ኢርሊኽ በአገራችን ስላለው ሙስሊም-ጠልነት ያሳደረው ተፅእኖና በእርሱ ተፅእኖ ሥር ስለወደቁ አካላት ይተነትናል፡፡
ምዕራፍ 8-
ለሙስሊም-ጠልነት ማኅበረ ቅዱሳን ተፅእኗቸው እስከምን ድረስ እንደሆነ በአራት ንኡሳን ክፍሎች በመክፈል መረጃውን ያስነብባል፡፡
ምዕራፍ 9-
ያልተገራ ዓረብ-ጠልነት እና ያልተጠቀምንባቼው ትሩፋቶች እንዳሉ ከትዝብት ጋር ለማሳየት ይሞክራል፡፡
እኔም እንዲህ በሚል መጠይቅ ወደ ምልከታዬ አለፍኩ፡- "ሙስሊም ጠልነት በኢትዮጵያ አለን? ካለስ ለምን?"
ምልከታ፡-
ከምከታተላቸው የፌስ ቡክ ገጾች መካከል አንዱ "ሂጅራ ቲዩብ" ነው፡፡ ጥቅምት 11/2012 . ላይ "የዘር ካርድ" ከተሰኘው የመሐመድ አሊ (ቡርሀን) መጽሐፍ ላይ ኢብን ኻልዱን ቀንጭቦ የወሰደውን ጽሑፍ አነበብኩ፡፡ የፋኢዝን መጽሐፍ ካነበብኩ በኋላ ቡርሀን "ኢትዮጵያ ትልቅ ናት ብዬ ፍጹም አልነሳም…" ማለቱ እውነት ነው አልኩ፡-
"ኢትዮጵያ ትልቅ ናት ብየ ፍጹም አልነሳም፡- ኢትዮጵያ የዓለም ደሃ ናት፤ ኢትዮጵያ ኋላ ቀር ናት፤ ብዙ እየተማረ የማያስተዉልባት ሀገር ናት፡፡"
እውነት ብሏል፡፡ ፋኢዝንና መሰሎቹን በትክክል የገለጸልኝ አባባል ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ በውረፋ ነገሬን ለመጀመር ወይም እርሱን ለማቃለል አስቤ አይደለም፤ የማቀርባቸው ማስረጃዎችና መረጃዎች ወደፊት ያስረዱልኛል፡፡ መደምደሚያ ላይ እናንተውም ትፈርዳላችሁ፡፡ "ሙስሊም-ጠልነት በኢትዮጵያ" የተሰኘው መጽሐፍ ጉድፉ እጅግ ብዙ ነው፡፡ ምናልባት አጀብ ያሉለት ወገኖች ሊኖሩ ይችሉ ይሆናል፤ አሉም፡፡ እኔ ግን እጅግ ለምድሪቱ አዘንኩ፡፡ ቡድንተኛ እና እውነትን የሚሸቃቅጥ እንጂ እውነትን የሚወድድ ሰው አይብቀልብሽ ተብላ የተረገመች ይመስላል፡፡ ፋኢዝ እውነትን በወገንተኝነት፣ በቡድነኝነት፣ ምናልባትም በአንድ ብሔር ጥላቻ ትብታብ ውስጥ ሆኖ እውነትን ደብቋል፣ እውነትን ሸሽጓታል፤ እውነትን አታስፈልጊም ብሎ ጥሏታል፡፡ አሁን በምድሪቱ ያለው የሃይማኖት፣ የዘርና የጎጥ ፖለቲካ እድፍ ልቡናውን ተጭኖት ይታያል፡፡ ያንን ለመሸፋፈን "አገር፣ አገሬ" የሚሉትን ቃላት ለመጠቀም ቢጣጣርም ጽሑፉ ያሳብቅበታል፡፡ ይሁንና እውነትን ብዙ ውሸቶች ተሰባስበው በጨለማ ጥላቸው ሊጋርዷት ቢሞክሩም ተጣጥራ ብርሃኗ እንደ ቀትር ብርሃን እስከሚሆን ድረስ ልታበራ ጨለማውን ማሸነፏ አይቀርም፤ የጊዜ ጉዳይ ነው፡፡ እርሱንም አሁን እኔ አግዛታለሁ፡፡
"ሙስሊም-ጠልነት በኢትዮጵያ" መጽሓፍ ጉድፍ አንድ በአንድ ላሳይ ካልኩ ከመጽሓፉ በላይ የሆኑ ሌሎች ዳጎስ ያለ ገጾች ያሏቸው መጽሓፍት ለመጻፍ መዘጋጀትን ይጠይቃል፤ እርሱ ይቆይ፡፡ በዚህ ጽሑፍ ሊጠቀሱ ያስፈልጋል ብዬ ያመንኩባቸውን ግን አንድ ሁለት እያልኩ ማቅረቤን ጀምሬያለሁ፡-
ጉድፍ አንድ፡-
የመጀመሪያው ጉድፍ ያለው ማስታወሻው ላይ ነው፡፡ አራት ወገኖች በመጽሓፉ ይታወሱልኝ ብሏል፡-
1. አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ
እርሳቸው አሉ ተብሎ ከመጽሐፋቸው የተቀነጨበውን አንብቤያለሁ፡፡2 ያንን ያሉት ስለ እስልምና ምንም ዐይነት ዕውቀት ስለሌላቸው ብቻ ነው፡፡ በጽሑፋቸው ለፋኢዝ ግብአት ሆኖለታል፡፡ ስለሆነም ማስታወሻነቱ ሊመጥናቸው ይችል ይሆናል፤ ያም እውነታውን እስከሚያውቁ ድረስ ብቻ ይሆናል፡፡
2 ስለ እስልምና ዕምነትና ስለ ተከታዮቹ ራሳቸው ሙስሊሞቹ ካልሆኑ በስተቀር ብዙዎቻችን ከክርስቲያን ቤተሰቦች የመጣነው ወጣቶች ብዙ የምናውቀው ነገር አልነበረም፡፡…" (ሙስሊም-ጠልነት በኢትዮጵያ ገጽ 70)

Post a Comment

0 Comments