ቻይና ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን በአግባቡ አልያዙም ያለቻቸውን ከፍተኛ ባለስልጣናት ከሥልጣን ያነሳች ሲሆን በበሽታው ተይዘው የሞቱ ሰዎች ቁጥርም 1ሺህ መድረሱ ተሰምቷል።
የሁባይ ጤና ኮሚሽን የፓርቲው ጸኃፊ እንዲሁም የኮሚሽኑ የበላይ ኃላፊ ከስራቸው ከተነሱ ባለስልጣናት መካከል ናቸው።
እነዚህ ከፍተኛ ሹማምንት በቻይና ከበሽታው ጋር በተያያዘ ከስልጣናቸው የተነሱ የሙጀመሪያዎቹ ከፍተኛ ባለስልጣናት ናቸው።
የአካባቢው የቀይ መስቀል ምክትል ኃላፊም የመጣውን እርዳታ በአግባቡ ካለማድረስ ጋር በተያያዘ " ኃላፊነትን በተገቢው ሁኔታ አለመወጣት" በሚል ከስራቸው ተሰናብተዋል።
ሰኞ እለት በሁቤይ አውራጃ ብቻ 103 ሰዎች የሞቱ ሲሆን በአጠቃላይ በሀገሪቱ ደግሞ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 1,016 ደርሷል።
ነገር ግን በቻይና በበሽታው አዲስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ መሆኑ የተነገረ ሲሆን የሁቤይ አውራጃ የጤና ኮሚሽን በግዛቱ 2,097 ሰዎች መያዛቸውን ሰኞ ዕለት አስታውቋል።

እንደ ሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኀን ዘገባ ከሆነ በሁባይና በሌሎች ግዛቶች በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከኮረና ቫይረስ ወረርሽን ጋር በተገናኘ ከስራቸው የተሰናበቱ ሲሆን ምርመራ እየተደረገባቸው ያለ ማስጠንቀቂያ እንዲደርሳቸው የተደረጉም መኖራቸው ተገልጿል።
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የቻይና ባለስልጣናት ወረርሽኙን የያዙበት መንገድ እያስተቻቸው ይገኛል።
የኮረና ቫይረስን አስቀድሞ በመለየት ያስጠነቀቀው ዶክተር መሞቱን ተከትሎ ከፍተኛ ቁጣ ተቀስቅሶ እንደነበር ይታወሳል።
በአሁኑ ሰአት በቻይና 42,200 ሰዎች በበሽታው መያዛቸው የታወቀ ሲሆን እህም ከዚህ ቀደም ከነበረው የሳርስ ወረርሽን ቀጥሎ ከፍተኛ የጤና ቀውስ መሆኑ ተገልጿል።
የሁቤይ ጤና ኮሚሽን እንዳለው ከሆነ በአውራጃዋ ብቻ 31,728 ሰዎች በበሽታው መያዛቸው የተመዘገበ ሲሆን ከእነዚህም መካከል 974 ሰዎች መሞታቸው ተገልጿል።
አብዛኞቹ ሟቾች በሁቤይ ግዛት ዋና ከተማ ዉሃን የተከሰተ ነው። ይህች 11 ሚሊየን ነዋሪዎች ያሉባት ከተማ አሁን ድረስ እንቅስቃሴ ተገድቦባት ትገኛለች።
ከቻይና ውጪ በዩኬ ስምንት ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ሐየተረጋገጠ ሲሆን መንግሥትም ይህንን የጤና ስጋት በሚመለከት ማስጠንቀቂያ ለዜጎቹ አስተላልፏል።
የኮሮና ቫይረስ ከቀላል እስከ ከባድ የመተንፈሻ አካል ሕመም የሚያስከትል የቫይረስ ዝርያ ሲሆን ሞትን ሊያስከትል የሚችል ህመም ነው።
በሽታው ያለበት ሰው ሲያስነጥስ፣ ባልበሰሉ ምግቦች፣ ከታማሚው ሰው ጋር በሚደረግ የቅርብ ንክኪ ይተላለፋሉ።
በበሽታው የተያዙ ሰዎች ትኩሳት፣ ሳል፣ የትንፋሽ መቆራረጥ እና የመተንፈስ ችግር ምልክቶች ይታይባቸዋል። በሽታው የጠናባቸው ሰዎች ላይ ደግሞ እንደ የሳምባ ምች እና ከባድ የመተንፈሻ አካላት ህመም ይስተዋላል።

0 Comments