
ከሟቾች በተጨማሪም ከ700 በላይ ሰዎች በበሽታዉ መጠቃታቸዉ ተገልጧል፡፡
የኩፍኝ ወረርሽኙ ካሳለፍነዉ የጥር ወር አጋማሽ ጀምሮ በሀገራችን በተለይም በምስራቅ ወለጋ ዞን መከሰቱ መነገሩ ይታወሳል፡፡
ከዛ ጊዜ ጀምሮም እስካሁን ድረስ አምስት ሰዎች ሲሞቱ ከ700 በላይ ሰዎች በበሽታዉ መጠቃታቸዉ የተነገረ ሲሆን የተደራጀ መረጃ ባለመኖሩ እንጂ የተጠቂዎች ቁጥር ከዚህም ከፍ ሊል እንደሚችል የዓለም አቀፋ የስደተኞች ድርጅት አይ ኦ ኤም ለኢትዮ ኤፍ ኤም አስታውቋል፡፡
ድርጅቱ እንዳለዉ በአሁኑ ወቅት በሽታዉን ለመከላከል ጠንካራ ስራ እየተሰራ መሆኑንና በበሽታዉ ምክንያት ሰዎች ህይወታቸዉን እንዳያጡ የሚደረገዉ ትግል መልካም ፍሬ እያፈራ መሆኑን ገልጿል፡፡
በተለይም በሽታዉ በስፋት ታይቶባቸዋል የተባሉ አዳሬና ብሪንቃስ በተባሉ ቀበሌዎች ከ15 ሽህ በላይ በሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን ማከናወኑን ድርጅቱ አስታዉቋል፡፡
በዚህም ህብረተሰቡ የበሽታዉ ምልክቶች የሚታይባቸዉን ሰዎች በአፋጣኝ ወደ ጤና ተቋማት እንዲሄዱ እያደረጉ መሆኑንና በሽታዉ በብዛት እንዳይስፋፋ ለማድረግ እየተባበሩ መሆኑን ገልጿል፡፡
ከዚህ በሻገርም ድርጅቱ ዉሃና ሌሎች የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን በማሰራጨት በሽታዉን ለመከላከል ትልቅ እገዛ እያደረገ መሆኑ ነዉ የተነገረዉ፡፡
አሁንም ቢሆን ግን በአካባቢዉ በሽታዉን ለመከላከል የተሰማሩ የጤና ባለሙያዎችን አቅም ይበልጥ መገንባትና ተቀናጅቶ መስራት ያስፈልጋል ተብሏል፡፡
የኩፍኝ በሽታዉን የመከላከል ስራዉ እየተከናወነ የሚገኘዉ፣በኢትዮጵያ የሰብአዊ ድጋፍ ፈንድና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ ሰጭ ፈንድ ትብብር ነዉ፡፡
በሙሉቀን አሰፋ
የካቲት 16 ቀን 2012 ዓ.ም
0 Comments