
በ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መሐመድ ኢብን አብደል ዋሂብ በተባለ ሰው የተመሠረተ የእስልምና ርእዮተ ዓለም ወይም እስላማዊ የተሐድሶ እንቅስቃሴ (religious movement) ነው፡፡ መሐመድ ኢብን አብደልዋሂብ የብዙ እስላሞችን ቀልብ የሳበውን አዲሱን አክራሪ እስልምናን መሠረት የጣለ ነው፡፡ መሐመድ አብደልዋሂብ በማእከላዊ አረብያን ከሪያድ በስተሰሜን አካባቢ ስፍራ ከወግ አጥባቂ ቤተሰብ የተወለደ ነው፤ ይህ ሰው በተለያዩ የአክራሪ እስልምና ተቋማት ተኮትኩቶ ያደገ ሰው ነው፡፡
ወሀቢዝም ከ1970ዎቹ ጀምሮ ከሳወዲ የነዳጅ ኤክስፖርቶች ድጋፍ የሚንቀሳቀስ በአሁኑ ሰዓት በዓለም ዙሪያ ከፍተኛ ተፅዕኖ እያሳደረ ያለ አክራሪ የእስልምና እንቅስቃሴ ነው፡፡
በእስልምና ሁለት ታላላቅ ርእዮተ ዓለሞች አሉ፤ እነዚህም ሱፊዝምና ወሀቢዝም ይባላሉ፡፡
ሱፊ ሙስሊሞች ብዙውን ጊዜ መንፈሳዊ መሪዎችን ወይንም ቅዱሳንን ይከተላሉ፤ ወደ ሞቱ ቅዱሳን መቃብር ቦታ ረጅም ጉዞ ያደርጋሉ፡፡ ቅዱስ ነው ከሚሉት የሞተ ቢሆንም እንኳን በጤንነትና በቤተሰብ ችግር ጊዜ ከእርሱ እርዳታን ለማግኘት ይሞክራሉ፤ ለእርሱም በጸሎት ጥያቄ ያቀርባሉ፡፡ በሱፊዝም አስተሳሰብ ቅዱሳን የሚታዩት ከክፉ ነገር ጠባቂዎችና የመለኮታዊ ኀይል ምንጭ ተደርገው ነው፡፡
ሱፊዎች የቅዱሳንን መቃብር ቦታዎች ይጎበኛሉ ይህም በየዕለቱ ላለው የሕይወት ችግር እርዳታን ለማግኘት ለፈውስና ለመንፈሳዊ ጥበቃ ነው፡፡ ሱፊዎች ታላቅ ሚሽነሪዎች ናችው ስውን አሳምኖ እንጂ አስገድዶ በማስለም አያምኑም፡፡
ወሀቢዝም ግን ከዚህ በተቃራኒ የቆመ የእስልምና ርእዮተ ዓለም ነው፤ መንግሥትና ሃይማኖት በመለያየት አያምንም፤ ከእምነቱ ውጭ ካሉት ጋር በግልም ይሁን በማኅበር ሰላማዊ ግንኙነት ማድረግን አይቀበልም፤ የተቀደሱ ሰዎች የሚባል ነገር አያውቅም፤ ከእስልምና ያፈነገጡ በሞት እንዲቀጡ የሚያምን ነው፤
ከቁርአንና ከሱኒ በስተቀር ሌላ የእስልምና መጻሕፍትን አይቀበልም፤ እስልምና ብቸኛ የመዳን መንገድ ነው፤ ስለዚህ ሰዎች በውድም በግድም እስልምናን መቀበል አለባቸው ብሎ ያምናል፤ በዚህ ምክንያት የተቀደሰ ጦርነት እንዲደረግ ይሰብካል፡፡ በየሀገራቱ ፍርሃት፣ ሽብር፣ ዐመፅና ነውጥ የሚያስነሡት እነዚህ የወሀቢዝም አቀንቃኞች ናቸው፡፡
በሀገራችንም አያሌ ክርስቲያኖች እየተቀጠቀጡ የተገደሉት በርካታ አብያተ ክርስቲያናት የተቃጠሉት በወሀቢያዎች ስብከት ነው፡፡ ወሀቢዝም በሁለት መንገድ ኢትዮጵያን በእስልምና ለማጥለቅለቅ አቅዶ ተነሥቷል፡፡ የመጀመሪያው ወጣቶችን ወደ ተለያዩ የእስላም ሀገሮች በተለይ ደግሞ ወደ ሳውዲ አረቢያ፣ ወደ ፓኪስታንና ወደ ማሌዢያ በመውሰድ የወሀቢዝምን አስተሳሰብ ማሠልጠን ነው፡፡
እነዚህ ወጣቶች ተምረው ከተመለሱ በኋላ ወንዶቹ አጭር ሱሪ ለባሾች፣ ጢም አሳማሪዎች ሲሆኑ፤ ሴቶቹ ደግሞ ከእግር ጥፍራቸው እስከ ራስ ጸጉራቸው ሂጃብ የሚሸፋፈኑ ናቸው፤ እነዚህ ወሀቢዎች ሙስሊሞች ከክርስቲያኖች ጋር በሰላም አብረው እንዳይኖሩ የሚለያዩ፤ ከእስልምና ውጭ ያሉትን የሚጸየፉ ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ እንደ ሱማሊያና እንደ ሳውዲ አረቢያ እስላማዊ መንግሥት ሊኖራት ይገባል እያሉ ነውጥ ይፈጥራሉ፡፡ ወሀቢያዎች በአሁኑ ሰዓት ከሳውዲ አረቢያ በሚረጨው በሚሊዮኖች በሚቆጠር ገንዘብ እየታገዙ በሙስሊሙና በክርስቲያኑ መካከል ለዘመናት ነባር ሆኖ የቆየውን የአብሮነትን ባህል ለማፍረስ ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ናቸው፡፡
ወሀቢያዎች በሚሰጡት የተዛባና የከረረ ትምህርት አማካኝነት ሕዝቡ ተረጋግቶና ተከባብሮ እንዳይኖር ሽብር ይፈጥራሉ፤ የሙስሊሞችን እድር ከክርስቲያኖች የማለያየት
ሥራ ይሠራሉ፤
በንግድ፣ በሥራና በማኅበራዊ ጉዳይ ከክርስቲያኖች ጋር አትገናኙ እያሉ ይሰብካሉ፤ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ክርስቲያኖችን በመክሰስ
በሙስሊሙ ማኅበረሰብ
እንዲጠሉ ያደርጋሉ፤
ክርስቲያኖችን ለማስለም
ኀይል የተሞላበት
እንቅስቃሴ ያደርጋሉ፡፡
ሆኖም ምንም እንኳን አንዳንዶች የወሀቢያ እስላሞች አጋጣሚውን እየተጠቀሙ ብሔራዊ ክፍተትን እየጠበቁ ጥቃትና ወረራ ቢያደርጉም በአመዛኙ ግን በኢትዮጵያ ለረጅም ዘመናት ከቆየው የአብሮነት ባህል የተነሣ ሙስሊሙና ክርስቲያኑ ተከባብሮ ተዋዶ መኖሩ አይካድም፡፡
በኀዘንም ሆነ በሰርግ እንዲሁም በተለያዩ ማኅበራዊ ግንኙነቶች እየተረዳዳ፤ ቤተ ክርስቲያን ሲሠራ ሙስሊሙ ማኅበረሰብ እያገዘ፤ መስጊድ ሲሠራ ክርስቲያኑ እያገዘ ሁሉም በየቤተ እምነቱ የሚያምነውን አስተምህሮ በሰላማዊ መንገድ ይሰብካል እንጂ አንዱ የአንዱን ሃይማኖት ማጠልሸት አልነበረም፡፡
መላው የኢትዮጵያ የሙስሊም ማኅበረሰብ በጉልበትና በሰይፍ የማስለም የአረቡን ጠባይና ባህል ሳይወርስ ከሌሎች እምነቶች ጋር ተከባብሮ መኖር የለመደ መሆኑን መዘንጋት አይገባም፡፡ በወሀቢያ አቀንቃኞች ዘንድ ግን በየጊዜው ምእመናንን በሚዘገንን መልኩ ማረድ፤ ቤተ ክርስቲያንን ማቃጠል የክርስቲያኖችን ንብረት መዝረፍ እየተለመደ ከመጣ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ የዚህ ጽሑፍ ዋና ዐላማ በሰይፍ የሚያምኑ ወሀብያዎችን የሚያደርጉትን ኢሰብአዊ
ተግባር መቃወም እንጂ የመላውን የእስልምና ተከታዮችን አስተሳሰብ እንደማይመለከት ውድ አንባብያን እንድትረዱልኝ እፈልጋለሁ፡፡
0 Comments