በቻይናዋ ዉሃን ግዛት ስለኮሮና ቫይረስ ይዘግብ የነበረዉ ጋዜጠኛ ተሰወረ።

የAsham TV ምስል
በቻይናዋ ዉሃን ግዛት ስለ ኮሮና ቫይረስ ይዘግብ የነበረዉ የቪዲዮ ጋዜጠኛ ቼን ኩዊሽ ተሰወረ። ቼን ስለቫይረሱ የተለያዩ ዘገባዎችን በቪዲዮ እየቀረፀ 440, 000 በላይ ተከታዮች ባሉት ዩቲዩብ ቻናሉ ያሰራጭ ነበር፡፡


ከጥር 28፣ 2012 ዓ.ም ጀምሮ የተሰወረው ቼን፣ ከመሰወሩ ከቀናት በፊት በትዊተርና ዩቲዩብ በሚለቃቸዉ ቪዲዮዎች ላይ ‹ፈርቻለዉ ከፊቴ የኮሮና ቫይረስ ከኋላዬ የቻይና መንግስት እያስፈራሩኝ ነዉ። ሞትን አልፈራም በዚህ እስካለዉ ያየሁትንና የሰማሁትን ከመዘገብ አልመለስም፣ የቻይና መንግስት ሆይ አልፈራህም እታገላለሁ› በማለት እንባ እየተናነቀዉ ንግግር አሰምቶ ነበር ሲል ‹ቲአርቲ› ዘግቧል፡፡

ጠበቃና የቪዲዮ ጋዜጠኛ የሆነዉ ቼን ኩዊሽ ለሁለት ሳምንታት በዉሃን ግዛት በመገኘት፣ በቫይረሱ በተጠቁ ህሙማን የተጨናነቀዉ ሆስፒታል ላይ ቀረፃ በማድረግ የቆየ ሲሆን በቂ የአፍ መሸፈኛ ጭንብል፣ መመርመርያና መከላከያ የሚሆኑ አልባሳት የሉም፣ እንደዚሁም ህሙማን በሆስፒታሎች የሚያዙበት መንገድ ትኩረት ያነሰዉ ነዉ በማለት ጠንካራ ተቃዉሞና ትችት ሲያነሳ ቆይቷል።

የ34 አመቱ ቼን ስለ ሆስፒታሉ ሲገልፅ ‹አዳራሹ በህሙማን ሞልቶ የሚያያቸዉ ዶክተር የለም፡፡ ለዚህም ነዉ ጉዳዩ አሳሳቢ የሆነዉ› ብሏል።

በዉሃን ስለቫይረሱ መከሰት ዜናዉን በመናገራቸዉ ለእስር ተዳርገዉ የነበሩት በኋላም በቫይረሱ ተይዘዉ የነበሩትን ዶ/ር ሊ ዌንሊያንግ ህልፈት ተከትሎ ነዉ የቼን መሰወር የተሰማዉ።

ወላጅ እናቱ ልጄን ማግኘት አልቻልኩም ያሉ ሲሆን፣ ምንም እንኳን የበሽታዉ ምልክት ባይታይበትም በግዳጅ በህሙማን ማቆያ ገብቶ እንደሚሆን የቼን ጓደኛ ጥርጣሬ እንዳለው የሳውዝ ቻይና ሞርኒግ ዘገባ ያስረዳል፡፡

እስካሁን መሰወሩን አስመልክቶ ለተነሳዉ ጥያቄ ምንም ምላሽ ከባለስልጣናት ያልተሰጠ ቢሆንም፣ አለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት የሆነው ‹ሲፒጄ› በጋዜጠኛውን መሰወር የቻይና ባለስልጣናት ተጠያቂ ናቸው ብሏል፡፡

ቼን ባሳለፍነዉ አመት በሆንግ ኮንግ የነበሩ ተቃዉሞች ተሳታፊ የነበረ ሲሆን ዲሞክራሲን በመፈለግ የተደረጉ ሰልፎችን የሚያሳይ ቪድዮ በመለጠፉ የቻይና መንግስት የማህበራዊ ሚዲያ ገፆቹን በመዝጋት አፀፋዉን መመለሱ ዘገባዎች ያመለክታሉ፡፡

ምንጭ፦ አሻም ቲቪ

Post a Comment

0 Comments