በትናንትናው ዕለት ብቻ ወረርሽኙ በተቀሰቀሰባት የቻይናዋ ሁቤይ ግዛት በኮሮና ቫይረስ ተይዘው የነበሩ 242 ሰዎች መሞታቸው ተሰማ።
ይህ ቁጥር ደግሞ ወረርሽኙ ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ በአንድ ቀን የሞቱ ሰዎችን ቁጥር ከፍተኛው ነው ተብሏል።
የሟቾች ብቻ ሳይሆን በቫይረሱ አዲስ የተያዙ ሰዎች ቁጥርም በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል በማለት 14840 ሰዎች በወረርሽኙ ተይዘው መገኘታቸው ተገልጧል።
በሁቤይ ሰዎችን ለኮረና ቫይረስ ተጋልጠው ሊሆን ይችላል ተብለው የሚመረመሩበትን የበፊት አሰራር በመቀየር ሰፋ አድርጎ ማየት በመጀመሩ ቁጥሩ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር እንዳደረገው ተገልጿል።
በሁቤይ ከዚህ ቀደም ለቫይረሱ ተጋላጮች ይደረግ የነበረው ምርመራ መደበኛው የኑክሊክ አሲድ ፍተሻ ሲሆን አሁን ግን በተለየ የበሽታውን ምልክት ያሳዩና የሲቲ ስካን ውጤታቸው በሳንባቸው ላይ ጉዳት መኖሩ የታየ ታካሚዎችንም የመለየት ስራ ተጀምሯል።
እስከ ትናንትናው፣ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተጠቂ እስከተገኘበት ዕለት ድረስ ወረርሽኙ በተከሰተባት ሁቤይ ቫይረሱ መረጋጋት አሳይቶ ነበር ተብሏል።
ይህ አዲስ ቁጥር በቻይና ያለውን የሟቾች ቁጥር ወደ 1350 ከፍ ያደረገ ሲሆን አዲስ የተያዙ ሰዎችንም ቁጥር 60ሺህ አድርሶታል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ቻይና የኮሮና ቫይረስ ወረርሽንን በመከላከል ሂደት ውስጥ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ አልተወጡም ብላ ከስልጣናቸው ባነሳቻቸው ባለስልጣናት ምትክ ሌሎችን መሾሟም ተሰምቷል።
በዉሃን በቫይረሱ ተይዘው ከሞቱ 242 ሰዎች መካከል 135ቱ ተመርምረው ቫይረሱ የተገኘባቸው ነበሩ ተብሏል።
በግዛቲቱ ካሉት 14840 አዲስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች መካከልም 13332ቱ ተመርምረው የተለዩ መሆናቸው ተገልጿል።
በአሁኑ ሰዓት በአጠቃላይ በግዛቲቷ 48206 በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ይገኛሉ።
ምንጭ፦ BBC News አማርኛ

0 Comments