በቅርቡ በቻይና ሁቤይ ግዛት ውሃን ከተማ የተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ወደ ተለያዩ የዓለም ሀገራት በመዛመት ላይ ይገኛል።
አሁን ላይም ቫይረሱ ከ150 በላይ በሆኑ የዓለም ሀገራት ውስጥ መስፋፋቱን የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያሳያል።
በዚህ መሰረትም በአፍሪካ ኢትዮጵያን ጨምሮ 26 የሚሆኑ ሀገራት ቫይረሱ የተገኘባቸው መሆኑ ተረጋግጧል፡፡
በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ በቫይረሱ ከ5 ሺህ 300 በላይ ሰዎች ለህልፈት ሲዳረጉ፥ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር ደግሞ ወደ 156 ሺህ 400 ከፍ ብሏል።
ከዚህ ውስጥ በቻይና ብቻ እስካሁን 80 ሺህ 844 የሚሆኑ ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን፥3 ሺህ 119 ዜጎች ደግሞ ህይወታቸው አልፏል።
በተመሳሳይ በአፍሪካ በአጠቃላይ በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር 273 የደረሰ ሲሆን፥ስድስት ሰዎች ደግሞ ህይወታቸው አልፏል።
በበሽታው ከቻይና በመቀጠል ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባት አውሮፓዊቷ ሀገር ጣሊያን ደግሞ 1ሺህ 440 የሚሆኑ ዜጎቿን በቫይረሱ ተነጥቃለች።
የቫይረሱ ስርጭት ከቀን ወደ ቀን በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎም በርካታ የአለም ሀገራት የቫይረሱን ሥርጭት ለመግታት የተለያዩ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ናቸው።
በዚህ መሰረትም አንዳንድ ሀገራት የተወሰኑ ዓለም አቀፍ በረራዎችን ከማገድ ጀምሮ ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ፣ ሰዎች በብዛት የሚሳተፉባቸው ስፖርታዊ ውድድሮች እና የእምነት በዓላት እንዳይካሄዱ መወሰናቸው ተመላክቷል።
አሜሪካ የበሽታውን የስርጭት አድማስ ለመግታት 26 በሚሆኑ የአውሮፓ ሀገራት ላይ የጉዞ እገዳ ከመጣል ባለፈ በመላ ሀገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጃለች።
ከአውሮፓ ሀገራት ውስጥ ጣሊያን፣ ስፔን እና ፈረንሳይ የምግብ ቁሳቁሶችንና መድሃኒቶችን ለመግዛት ወይም ወደ ስራ ለመሄድ ከሚደረግ እንቅስቃሴ ውጪ ዜጎች ከቤት እንዳይወጡ ከልክለዋል።
ብሪታኒያ ደግሞ ዕድሜያቸው ከ70 በላይ የሆኑ ዜጎች ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ከቤታቸው እንዳይወጡ ልታደርግ መሆኑን የሀገሪቱ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
ህንድ በበኩሏ ከዲፕሎማቶች እና ከመንግስት ባለስልጣናት ውጪ ለአንድ ወር ያህል ለማንኛውም ዜጋ ቪዛ የማትሰጥ መሆኑን ይፋ አድርጋለች።
ምንጭ፦ ቢ ቢ ሲ እና ሲ ጂ ቲ ኤን

0 Comments