የኮሮና ቫይረስ ምልክቶችን ያሳዩ 5 ግለሰቦች በለይቶ ማቆያ ማዕከላት ገብተው የህክምና ክትትል እየተደረገላቸው ነው ተባለ፡፡


የcorona virus ምስል ውጤት

የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ወቅታዊውን የኮሮና ቫይረስ ሁኔታ አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
ሶስት ኢትዮጵያዊያንና 2 ቻይናዊያን የኮሮና ቫይረስ ምልክቶችን በማሳየታቸው ቫይረሱ ይኖርባቸዋል በሚል ተጠርጥረው ወደ ማቆያ ማዕከላት እንዲገቡ መደረጉ በመግለጫው ተነግሯል፡፡
የእነዚህ ተጠርጣሪዎች የላብራቶሪ ናሙና ተወስዶ ውጤታቸው እየተጠበቀ መሆኑን የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ኤባ አባተ ተናግረዋል፡፡
እስካሁን ኢትዮጵያ ውስጥ በኮሮና ቫይረስ የተያዘ ሰው እንደሌለም ዶ/ር ኤባ አረጋግጠዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ቫይረሱ ከተከሰተባቸው አገራት የገቡ 958 ተጓዦች የ2 ሳምንት ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑን ከመግለጫው ሰምተናል፡፡
1224 ተጓዦች ደግሞ ሲደረግላቸው የነበረውን የ2 ሳምንት ክትትል አጠናቅቀዋል ተብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ህብረሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እስካሁን ከሰማኋቸው ኮሮናን የተመለከቱ 131 ጭምጭምታዎች 54ቱ የቫይረሱን ተመሳሳይ ምልክቶች ያሳዩ በመሆናቸው ክትትል አድርጌባቸዋለሁ ብሏል፡፡
49ኙ ተጠርጣሪዎች ደግሞ በተደረገላቸው ምርመራ ከቫይረሱ ነፃ መሆናቸው ተረጋግጧል ተብሏል፡፡
ቀሪዎቹ 5 ተጠርጣሪዎች አሁንም በማቆያ ማዕከላት ሆነው የላብራቶሪ ውጤታቸው እየተጠበቀ ነው ተብሏል፡፡
ኮሮና እስካሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ባይገባም ህብረተሰቡ ራሱን በመጠበቅና አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ በኩል እንዳይዘናጋ ዶ/ር ኤባ አሳስበዋል፡፡
በዓለም የጤና ድርጅት መረጃ መሰረት ከ113 ሺ በላይ ሰዎች በኮሮና ቫይረስ ተይዘዋል፡፡
ከ4 ሺ በላይ የሚሆኑት ደግሞ በቫይረሱ ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡
ኮሮና እስካሁን ከ110 በላይ አገራት ላይ ተከስቷል፡፡
ከቻይና ውጪ ብዙ ሰዎች በቫይረሱ የተያዙባት አገር ጣሊያን ስትሆን ከ10 ሺ በላይ ዜጎቿ በኮሮና ተይዘዋል፡፡
(ማህሌት ታደለ)

Post a Comment

0 Comments