የአገሪቱ 45 ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ባሉበት ትምህርታቸውን ይቀጥላሉ ተብሏል።
የጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ከውሳኔው የደረሰው አራት ሰዎች በኮሮና ተህዋሲ መያዛቸው ከተረጋገጠ በኋላ ነው። ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ በዛሬው ዕለት በሰጡት መግለጫ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ባሉበት ሆነው አስፈላጊው ክትትል ይደረግላቸዋል ማለታቸውን የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት እና የጤና ሚኒስቴር የበሽታውን ስርጭት ለመቆጣጠር እና በተህዋሲው የተያዙ ሰዎችን ለመለየት እና ርምጃ ለመውሰድ ከተለያዩ አጋሮች ጋር እየሠራ መሆኑን የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ እሁድ ዕለት በሰጡት ገልጸዋል። ማህበረሰቡም የበሽታውን ስርጭት ለመግታት የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ አሳስበዋል። የኮሮና ተህዋሲ እስካሁን በ 26 የአፍሪቃ ሀገራት መሰራጨቱ የተረጋገጠ ሲሆን በርካታ ሀገራት የዓለም አቀፍ በረራዎችን እየሰረዙ እና የትምህርት ተቋማትን እየዘጉ ይገኛሉ። በሳምንቱ መጨረሻ በኢትዮጵያ በርካታ ሰዎች የተሰበሰቡባቸው እንደ «ቅድሚያ ለሴቶች» ሩጫ እንዲሁም የብልፅግና ፓርቲ የገቢ ማሠባሰቢያ ዝግጅቶች በሚሊኒየም አዳራሽ ተካሒደዋል። መርሐ ግብሮቹ የተካሔዱት በአአገሪቱ በኮሮና የተያዘ አንድ ሰው መገኘቱ ከተረጋገጠ በኋላ ነው።

0 Comments