የዓለም ኃያላን አገራት አፍሪካ ላይ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ የበላይነት ለማግኘት ድምፃቸውን አጥፍተው እየተፋለሙ ያሉበት ጊዜ ነው።
የአፍሪካ አገራት መሪዎች ያለ እረፍት የአፍሪካ ነክ ጉባኤዎችን ለመታደም ወደ ተለያዩ የዓለም አገራት በመጓዝ ላይም ናቸው።
እነዚህ የቻይና አፍሪካ ፣ የዩናትድ ኪንግደም አፍሪካ፣ ጃፓን አፍሪካ ጉባኤ . . . እየተባሉ የሚዘጋጁ መድረኮች በማስታወቂያ ሁለቱንም ወገን ተጠቃሚ የሚያደርጉ አጋርነቶች ተደርገው ይገለፃሉ።
እውነቱ ግን ይህ ነው? የዓለም ኃያላን ዳግም አይናቸውን አፍሪካ ላይ የጣሉት ለምንድን ነው?
እንደ አውሮፓውያኑ ባለፈው ዓመት የአፍሪካ መሪዎች የተገኙባቸው የቻይና፣ የጃፓን እና የሩሲያ የአፍሪካ ጉባኤዎች ተካሂደዋል። በባለፈው ወር የእንግሊዝ አፍሪካ የኢንቨስትመንት ጉባኤም 15 የሚሆኑ የአፍሪካ መሪዎች ተካፍለዋል።
በፈረንሳይ፣ በሳውዲ አረብያና በቱርክ በዚህ ዓመት ሊካሄዱ ለታሰቡ ተመሳሳይ የአፍሪካ ጉባኤዎችም ጥሪ ተላልፏል ተብሎ ይገመታል።
የአህጉሪቱ ከፍተኛ የማዕድን ክምችት፣ ድንግል የግብርና መሬት እንዲሁም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ አገራት 54 ድምፅ፣ በአህጉሪቱ እየጨመረ ያለው የእስልምና አክራሪነት፣ ስደት አፍሪካን ዳግም የኃያላኑ አይን ውስጥ ያስገቡ ተጠቃሽ ጉዳዮች ናቸው።
በዓለም አቀፍ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ መፅሃፍትን ለንባብ ያበቃችው እውቋ ዛምቢያዊት ኢኮኖሚስት ዳምቢሳ ሞዮ "ዓለም በቅርቡ የዓለም ችግር መሆናቸው የማይቀር የአፍሪካ ችግሮችን ለመፍታት የአፍሪካ አገራት እርዳታ ያሻቸዋል" ትላለች።
ሞዮ እንደምትለው ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አፍሪካን ለመደገፍ እርምጃ ቢወስድ እርምጃው ለዓለምአቀፉ ማህበረሰብም ትርፋማ ነው።
የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በቅርቡ አሜሪካ ላይ አፍሪካ ለቀሪው ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ የደህንነት ስጋት የምትጋርጥ እንዲሁም በስደተኞች ምዕራባውያንን ችግር ውስጥ የምትከት ብቻ ሳትሆን ለቀሪው ዓለም ሰፊ የኢንቨስትመንት እድልን የምትሰጥም እንደሆነች ተናግረው ነበር።
ኡሁሩ በንግግራቸው ቻይና፣ አሜሪካ፣ ሩሲያና ሌሎች አገሮች አፍሪካን ለመቆጣጠር የሚያደርጉትን ከፍተኛ ፉክክር እንዲያቆሙም አስጠንቅቀዋል።
አፍሪካ ምን ታስባለች?
እአአ በ2013 የአፍሪካ መሪዎች አህጉሪቱ በ2063 ያጋጥማታል ያሉትን ፈተና ለመወጣት ያስችል ዘንድ በአፍሪካ ህብረት አማካኝነት አጀንዳ 2063 የተሰኘውን እቅድ ነድፈዋል።
እቅዱ ከሁሉም በላይ በአህጉሪቱ ላይ የሚቃጡ ጦርነቶች ማስቆም፣ መሰረተ ልማት ዝርጋታ ላይ የሚያተኩር ሲሆን በአህጉሪቱ ዜጎች ከአገር አገር ነፃ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ ራዕይ የሰነቀ ነው።
ሌላው ወሳኝ ፕሮጀክት የአፍሪካ ነፃ ገበያ ምህዳርን መክፈት ሲሆን ይህ የነፃ ገበያ ማዕቀፍ በርካታ አገራትን አሳታፊ በማድረግ የዓለም ትልቁ የነፃ ገበያ ማዕቀፍ ስምምነት ነው።
ይህ የነፃ ገበያ ስምምነት በአፍሪካ አገራት መካከል የሚደረግ ንግድን ለማስፋፋት የታለመ ነው።
ከጥቂት ወራት በኋላ ተግባራዊ እንደሚሆን የሚጠበቀው ይህ የአፍሪካ ነፃ ገበያ ስምምነት አገራት የውስጥ ገበያቸውን ለመጠበቅ ባወጧቸው ቀደምት ህጎችና እንዲሁም የደካማ የትራንስፖርት መሰረተ ልማት ምክንያት ከፍተኛ ችግር እንደሚገጥመው አስተያየት እየተሰጠ ነው።
ሁሉንም የአፍሪካ አገራት መዲናዎች እና የንግድ ማዕከሎች በፈጣን ባቡር መስመር ማገናኘት፣ በአፍሪካ አገራት መካከል የሚደረግ ንግድን ማበረታታት እንዲሁም የአፍሪካ አገራት በዓለም አቀፍ የንግድ ገበያ ተሳትፎን ማጎልበት አጀንዳ 2063 ካስቀመጣቸው ግቦች መካከል ናቸው።
የአፍሪካውያን በአህጉሪቱ ነፃ የመዘዋወር፣ የመስራት እና የመኖር መብት እንዲኖራቸው ማድረግ እንዲሁም በአህጉሪቱ ያሉ ግጭቶችን ማስቆም እና ሌሎችም በርካታ ግቦች በእቅዱ ላይ ተቀምጠዋል።
ነገር ግን የአፍሪካ ሕብረት እነዚህን አጀንዳዎች ለማስፈፀም በእጅጉ እየተፈተነ ሲሆን ችግሩ ሕብረቱ አባል አገራት በገቡት ስምምነት መሰረት ነገሮችን ተግባራዊ እንዲያደርጉ ማስገደድ አለመቻሉ ነው።
ተንታኞች እንደሚሉት የአፍሪካ አገራት ያለባቸውን ከፍተኛ የእዳ ጫና ለመክፈል የሚያደርጉት ትግል ትልቁን አህጉራዊ አጀንዳ ችላ እንዲሉ ግድ ብሏቸዋል።
ቢሆንም ግን የአፍሪካ አገራት በየጊዜው እየናረ ከመጣው የኃያላኑ ፍላጎት አትራፊ ለመሆን ጠንካራ ድርድር ማድረግ የሚያስችላቸውን የፖሊሲ አቅጣጫ በማስቀመጥ የዚህ/የዚያ የሚባሉ የአፍሪካ ጉባኤዎች ላይ የሚቀርቡ የአጭር ጊዜ ስምምነቶችን ከመቀበል ይልቅ ትልቁን አህጉራዊ አጀንዳ ታሳቢ ያደረጉ ስምምነቶችን ማድረግ እንደሆነ ተንታኞቹ ምክረ ሃሳባቸውን ያስቀምጣሉ።
ምንጭ፦ BBC News አማርኛ

0 Comments