የክሮሽያ ዋና ከተማ ዛግሬብ በርዕደ መሬት ተመታች


የክሮሽያ ጠቅላይ ሚንስትር በርዕደ መሬቱ የደረሰውን ጉዳት ሲመለከቱ
Image copyrightAFP
አጭር የምስል መግለጫየክሮሽያ ጠቅላይ ሚንስትር በርዕደ መሬቱ የደረሰውን ጉዳት ሲመለከቱ
ክሮሽያ እንደቀሪው ዓለም በኮሮናቫይረስ ተሸብራ ከርማለች፤ ትናንት ደግሞ በመዲናዋ ሌላ ያልተጠበቀ ድንገተኛ አደጋ ተከስቶ በርካቶችን ጭንቀት ውስጥ ከቷል።
በክሮሽያ መዲና ዛግሬብ ዕሁድ በአገሪቱ ሰዓት አቆጣጠር 6 ሰዓት አካባቢ በደረሰው የመሬት መንቀጥቀጥ በርካታ ሕንጻዎች ሲደረማመሱ፤ ፍርስራሹ ብዙ ቀጥር ያላቸው መኪናዎችን ከጥቅም ውጭ አድርጓል።
አንድ ታዳጊም የአንድ ሕንጻ ጣሪያ ተደርምሶበት ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል።
በሬክተር ስኬል 5 ነጥብ ሦስት የተመዘገበው ርዕደ መሬቱ ዛግሬብ በ140 ዓመት ታሪክ ውስጥ ያስተናገደችው ከፍተኛው ነው ተብሏል።
ከታዳጊው በተጨማሪ ሌሎች 16 ሰዎችም በርዕደ መሬቱ ጉዳት ደርሶባቸዋል። በክስተቱ የተደናገጡ የዛግሬብ ነዋሪዎችም ቀደም ሲል በኮሮናቫይረስ ምክንያት ቤታቸው ውስጥ እንዲቀመጡ ቢነገራቸውም ይህኛው ድንገተኛ አደጋ ግን አደባባይ እንዲወጡ አስገድዷቸዋል።
አንድ ላይ በድንገት መሰባሰባቸው ለቫይረሱ መዛመት እድል ይፈጥራል በማለት ስጋት የገባቸው የአገሪቱ ባለስልጣናት ሰዎች በፍጥነት ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ ተማጽነዋል።
የከተማዋ ከንቲባም ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑት የዛግሬብ ቤቶች በጥንቃቄ የተሰሩ በመሆናቸው አደጋውን በመፍራት ሰዎች ወደ ውጭ መውጣት እንደሌለባቸው አሳስበዋል።
የክሮሽያ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚንስትር ዳቮር ቦዚኖቪች "አንድ ላይ አትሰባሰቡ፤ ማኅበራዊ እርቀታችሁን ጠብቁ። የመሬት መንቀጥቀጡና ወረርሽኙ ተዳምረው ሁለት አደጋ ተደቅኖብናል" ብለዋል።
በርዕደ መሬቱ የአገሪቱን የፓርላማ መቀመጫን ጨምሮ በርካታ ሕንጻዎች ወድመዋል። ይሁንና ሌኛውን ወቅታዊ ችግርን [ኮሮናቫይረስ] ለማለፍ ሲባል ሰዎች በፍጥነት ወደቤታቸው እንዲመለሱ ተነግሯቸዋል።
በክሮሽያ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ200 በላይ ደርሷል።

Post a Comment

0 Comments