የኮሮና ቫይረስ ተመሳሳይ ምልክት የታየባቸው ሁለት ሰዎች በለይቶ ማቆያ ክፍል ክትትል እየተደረገላቸው ነው

የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የኮሮና ቫይረስ ተመሳሳይ ምልክት የታየባቸው ሁለት ሰዎች በለይቶ ማቆያ ክፍል ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑን አስታወቀ።

ኢንስቲትዩቱ የኮሮና ቫይረስ ወቅታዊ መረጃን በተመለከተ ለጣቢያችን በላከው መግለጫ ከየካቲት 24 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ 14 ሺህ 140 መንገደኞች በሙቀት መለያ እንዲያልፉ መደረጉን አስታውቋል።
ከእነዚህ ውስጥም 382ቱ ቫይረሱ ሪፖርት ከተደረገባቸው ሃገራት የመጡ መሆናቸውን ጠቅሶ፥ ለ93ቱ የጤና ክትትል ተደርጎላቸው ማጠናቀቃቸውን ገልጿል።
በተጨማሪም ለ910 ሰዎች የጤና ክትትል እየተደረገ ነው ያለው ኢንስቲትዩቱ፥ ስምንት አዳዲስ ጭምጭምታዎች ደርሰውት በኢንስቲትዩቱ የድንገተኛ ህብረተሰብ ጤና አደጋዎች ምላሽ ማጣራት ተደርጓልም ብሏል።
ከእነዚህ ውስጥ ሁለቱ ከኮሮና ቫይረስ ጋር ተመሳሳይነት ያለው ምልክት በማሳየታቸው በለይቶ ማቆያ ክፍል ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑንም ነው የገለጸው።
በተጨማሪም ከጥር 15 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ቫይረሱ ሪፖርት ከተደረገባቸው ሃገራት የመጡና የቫይረሱን ተመሳሳይ ምልክት ያሳዩ 27 ሰዎች በተለያየ ጊዜ በለይቶ ማቆያ ክትትል ተደርጎላቸው በላቦራቶሪ ምርመራ ነጻ መሆናቸው በመረጋገጡ ወደ ህብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ ተደርጓልም ነው ያለው።
አሁን ላይም ቫይረሱ ወደ ሃገር ውስጥ እንዳይገባ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራዎችን ጨምሮ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑንም በመግለጫው አመላክቷል።

Post a Comment

0 Comments