
አምስተኛው ሰው በተሕዋሲው መያዛቸው በትናንትናው ዕለት መረጋገጡን የጤና ምኒስትር ሊያ ታደሰ በትዊተር ገፃቸው አስፍረዋል።
ተሕዋሲው የተገኘባቸው ሶስት የውጭ አገር ዜጎች እና ሁለት ኢትዮጵያውያን «ለሞት የሚያሰጋ» ነገር የለባቸውም ያሉት ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ «ሕዝቡ ጥንቃቄ ከማድረግ ያለፈ የተጋነነ ፍራቻ» ውስጥ እንዳይገባ አሳስበዋል።
ዜጎች ከሚያስሉ፣ ከሚያስነጥሱ እና ትኩሳት ካላቸው ሰዎች ቢያንስ ለሁለት እርምጃ እንዲርቁ የኢትዮጵያ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እና የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት አሳስበዋል።
እጅን በሳሙና እና በውኃ አዘውትሮ መታጠብ፣ ወይም አልኮል ባለው ማፅጃ እጅን ማፅዳት ራስን የኮሮና ተሕዋሲን ለመከላከል ያግዛሉ። እጅን ሳይታጠቡ አይንን፣ አፍን፣ አፍንጫን አለመንካት መጨባበጥን ሙሉ በሙሉ ማቆም በባለሙያዎች የተጠቆሙ እርምጃዎች ናቸው።
የኢትዮጵያ መንግሥት ትምህርት ቤቶች፣ ቁጥሩ በዛ ያለ ሕዝብ የሚሳተፍባቸው ስብሰባዎችና የውይይት መድረኮች እና ስፖርታዊ ክንውኖች ለሚቀጥሉት አስራ አምስት ቀናት እንዲታገዱ ወስኗል።
በሺሕዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች የሚገኙባቸው 45 ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ግን አልተዘጉም። የሳይንስ እና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢዎች እና በተማሪዎች ማደሪያ ክፍሎች ለሚገኙ ተማሪዎች ለየኮርሱ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን በኢንተርኔት ለማሰራጨት እየተዘጋጀ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
የጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት የአፍ መሸፈኛ ጭምብሎች፣ ሳሙናዎች፣ ፈሳሽ የመድኃኒት አልኮል እና ሌሎች አስፈላጊ ግብዓቶች አስፈላጊ በሆኑባቸው ሥፍራዎች ተጨማሪ በጀት እንደሚመድብ አስታውቋል። ከትናንት በስቲያ 1.5 ቢሊዮን ብር የሰበሰበው የጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ ብልፅግና ፓርቲ 100 ሚሊዮን ብር ለዚሁ ዓላማ እንደሚሰጥ አስታውቆ ነበር።
ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ የአዲስ አበባ ከተማ ከጤና ሚኒስቴር ጋር ከዛሬ ጀምሮ «ወሳኝ ወሳኝ በሆኑ ቦታዎች ላይ በተለይ በከተማ አካባቢ የአልኮል፣ የሳሙና እና የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች» ያቀርባል ብለዋል።
ጠቅላይ ምኒስትሩ የመንግሥት ተሽከርካሪዎች ሕዝብ እንዲያጓጉዙ መወሰኑን ተናግረዋል። ጠቅላይ ምኒስትሩ እንዳሉት ውሳኔው በመጓጓዣ አገልግሎት እጥረት የሚፈጠረውን መጨናነቅ ለመቀነስ የተላለፈ ነው።
0 Comments