ሁለት ኢትዮጵያዊያን ጣሊያን ውስጥ በኮሮናቫይረስ መሞታቸው ተረጋገጠ

የጣሊያን የህክምና ባለሙያዎች በኮሮናቫይረስ ለተያዙ ሰዎች የህክምና ድጋፍ ሲያደርጉ

Image copyrightANTONIO MASIELLO
አጭር የምስል መግለጫየጣሊያን የህክምና ባለሙያዎች በኮሮናቫይረስ ለተያዙ ሰዎች የህክምና ድጋፍ ሲያደርጉ
አውሮፓ ውስጥ በኮሮናቫይረስ [ኮቪድ-19] ክፉኛ ከተጠቁት አገራት መካከል ቀዳሚዋ በሆነችው ጣሊያን ውስጥ ሁለት ኢትዮጵያዊያን በበሽታው ምክንያት ህይወታቸው ማለፉን ቢቢሲ አረጋገጠ።
ኢትዮጵያዊያኑ እዚያው ጣሊያን ውስጥ በበሽታው ተይዘው ህክምና ሲደረግላቸው ቆይተው ህይወታቸው ማለፉን ቢቢሲ ያናገራቸው የውጪ ጉዳይ ምንጮች አረጋግጠዋል።
በወረርሽኙ የሞቱት ሁለቱም ሰዎች ዕድሜያቸው ከ40 ዓመት በላይ የነበረ ወንድና ሴት ኢትዮጵያዊያን እንደሆኑ የታወቀ ሲሆን አንደኛው ለረጅም ዓመታት ጣሊያን ውስጥ የኖሩ መሆናቸውም ቢቢሲ ለመረዳት ችሏል።
ሁለተኛዋ ሟች መቼ ወደ ጣሊያን እንደሄዱ በትክክል ባይገለጽም ቤተሰብ ለመጎብኘት ወደ ጣሊያን በመሄድ እዚያው የቆዩ እናት እንደሆኑ ታውቋል።
ሁለቱም ሟቾች ህመሙ ከታየባቸው በኋላ አስፈላጊውን የህክምና ክትትል ሲያደርጉ እንደቆዩና በመጨረሻም ለህልፈት መብቃታቸው ተገልጿል።
ባለሙያዎች እንደሚሉት የኮሮናቫይረስ በሽታ በእድሜ በገፉና ሌሎች የቆዩ የጤና ችግሮች ባሉባቸው ሰዎች ላይ እስከ ሞት የሚያደርስ ከባድ ጉዳትን ያስከትላል።
ጣሊያን ውስጥ በኮሮናቫይረስ ህይወታቸው እንዳለፈ የተነገረው ሁለቱ የኢትዮጵያዊያንም ሞት የተፋጠነው ቀደም ባለ የጤና ችግር ምክንያት ሊሆን ይችላል ተብሎ ተጠርጥሯል።
ከቻይና ቀጥሎ በኮሮናቫይረስ ወረርሽን ክፉኛ በተጠቃችው ጣሊያን ውስጥ እስካሁን በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ31 500 በላይ የደረሰ ሲሆን 2503 ሰዎች ደግሞ መሞታቸውን የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ መረጃ ያመላክታስ።

Post a Comment

0 Comments