የአውሮፓ ኅብረት አገራት በአንድ ቀን ብቻ ከፍተኛ የተባለውን የሞት ቁጥር አስመዘገቡ

የኮሮናቫይረስ ስርጭት በአውሮፓ

Image copyrightREUTERS
አጭር የምስል መግለጫየኮሮናቫይረስ ስርጭት በአውሮፓ
ሦስት የአውሮፓ ኅብረት አገራት እስከ ዛሬ በኮሮናቫይረስ ምክንያት በቀን ከተመዘገበባቸው የሞት መጠን አንጻር ትናንት ከፍተኛ የተባለውን የሞት አስመዝግበዋል።
ጣሊያን በትናንትናው ዕለት 368 ዜጎቿን ስታጣ አጠቃላይ የሟቾች ቁጥር ወደ 1 ሺህ 809 አሻቅቧል። ስፔን 97 ዜጎቿ የሞቱባት ሲሆን አጠቃላይ የሟቾች ቁጥር 288 ደርሷል። በፈረንሳይም በትናንትናው ዕለት 29 ሰዎች ሲሞቱ በአጠቃላይ 120 ዜጎቿን በኮሮናቫይረስ ተነጥቃለች።
የዩናይትድ ኪንግደምም ትናንት ብቻ 14 ሰዎች የሞቱባት ሲሆን በአጠቃላይ ደግሞ የሟቾች ቁጥር ወደ 35 አድጓል።
በአውሮፓ መንግሥታት መመሪያዎችን በማጠናከርና የድንበር ቁጥጥሮችን በመጨመር ላይ ናቸው። ኦስትሪያ ከአምስት ሰው በላይ መሰባሰብ የተከለከለ መሆኑን አውጃለች። በብዙ የኅብረቱ አገራትም ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል።
ኮሮናቫይረስ መነሻውን ቻይና ቢያደርግም አሁን ባለው ሁኔታ ግን ወረርሽኙ ዋነኛ ማዕከሉ አውሮፓ መሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል።

ቫይረሱ እንዴት እየተስፋፋ ነው?

ስዊትዘርላንድ በ24 ሰዓታት ውስጥ ብቻ 800 ሰዎች በበሽታው እንደተጠቁባት የታወቀ ሲሆን አጠቃላይ የቫይረሱ ተጠቂ ዜጎቿ ቁጥር 2 ሺህ 2 መቶ የደረሰ ሲሆን 14 ሞት ደግሞ ተመዝግቧል።
በከፍተኛ ደረጃ የተጠቃችው ጣሊያንም በበሽታው የተያዙት ሰዎች ቁጥር ወደ 25 ሺህ ከፍ ብሏል።
ፈረንሳይ ወደ 7 ሺ 8 መቶ የሚጠጉ ህሙማን ሲኖሯት ስፔንም ወደ 5 ሺ 4 መቶ ሰዎችን መዝግባለች።
የስፔን መንግሥት ዜጎች ሸቀጦችን ለመግዛት ወይም ለሥራ ካልሆነ ከቤት እንዳይወጡ አዟል። ፈረንሳይም ካፍቴሪያ፣ ሬስቶራንት፣ ሲኒማና በርካታ ሱቆችን ቆላልፋለች።
የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ቮን ዴር ሌዬን ወረርሽኙን ተከትሎ ኅብረቱ የመከላከያ መሳሪያዎችንና መመርመሪያዎችን ማምረቱን ይቀጥላል ብለዋል።

ቀሪው ዓለምስ ምን እያደረገ ነው?

  • እስካሁን ባለው መረጃ 162 ሺህ 687 ሰዎች በመላው ዓለም በኮሮናቫይረስ መጠቃታቸው ተረጋግጧል። ከዚህ ውስጥ ከግማሽ በታች የሚሆኑት ብቻ በቻይና ይገኛሉ (81 ሺህ ሦስት ተጠቂዎች ብቻ)።
  • በመላው ዓለም 6 ሺህ 65 ሰው እንደሞተ የሚገመት ሲሆን 3 ሺህ 85 የሚሆኑት ቻይና ውስጥ የሞቱ ናቸው።
  • ደቡብ አፍሪካ ቫይረሱ በብዛት ከተሰራጨባቸው አገራት የሚመጡ የውጭ አገራት ዜጎችን ከረቡዕ ጀምሮ ለማገድ ወስናለች።
  • ደቡብ አፍሪካ 61 ሰዎች የተጠቁባት ሲሆን በአገር ውስጥ በስፋት እየተስፋፋ በመሆኑ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ "አገራዊ አደጋ ላይ ነን" ብለዋል።
  • የቫይረሱን ሽርጭት ተከትሎ የአሜሪካ የፌደራል መጠባበቂያ መስሪያ ቤት የአገሪቱን ምጣኔ ሃብት ለመታደግ በሚል የወለድ መጠኑን ዜሮ ሊባል በሚችል ደረጃ ዝቅ አድርጓል።
  • አሜሪካ ከውሮፓ የሚመለሱ ዜጎቿን በአውሮፕላን ማረፊያች ምርመራ በመጀመሯ ግርግርን ፈጥሯል።
  • የትራምፕ አስተዳደር ከ26 የአውሮፓ አገራት የሚመጡ ተጓዦችን ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ አግዷል፤ ይህ እገዳ ታላቋ ብሪታኒያንና አየር ላንድንም ያካትታል።
  • አሜሪካ 3 ሺህ 244 ዜጎቿ በቫይረሱ የተጠቁባት ሲሆን 62 አሜሪካዊያን ደግሞ ለሞት ተዳርገዋል።

Post a Comment

0 Comments