የኢትዮጵያ አየር መንገድ መቀሌና ላልይበላ ጨምሮ በሰሜናዊ የአገሪቱ ክፍሎች ዛሬ ሊያደርጋቸው የነበሩ በረራዎችን ባጋጠመው አስቸጋሪ የአየር ጠባይ ምክንያት መሰረዙን አስታወቀ።
አየር መንገዱ ጨምሮም በተመሳሳይ ወደ ጎንደር፣ አክሱምና ሽሬ ሊያደርጋቸው የነበሩ በረራዎችም ዛሬ ጠዋት በነበረው አመቺ ያልሆነ የአየር ሁኔታ ሳቢያ መስተጓጎሉን አመልክቷል።
በዛሬው ዕለት የተሰረዙትን በረራዎች ያለው የአየር ሁኔታ መሻሻሉን በተመለከተ ከብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ አገልግሎት የሚገኝን መረጃ መሰረት በማድረግ እንዲቀጥል የሚደረግ መሆኑን ገልጿል።
ነገር ግን አሁን ከብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ አገልግሎት የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው በረራዎችን ያስተጓጎለው የአየር ሁኔታ በቀጣዮቹ ሁለት ቀናት ውስጥም ሊቀጥል እንደሚችል አመልክቷል።
በተያያዘ ዜና ከአርብ ከሰዓት ጀምሮ ቅዳሜ ዕለትም የባህር ዳር ከተማ ሰማይ በአቧራ ጭጋግ ተሸፍኖ እንደነበር ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ይህንን ክስተት በተመለከተ የምዕራብ አማራ የሜቲዮሮሎጂ አገልግሎት ማዕከል የትንተናና ትንበያ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ቡድን አስተባባሪ የሆኑት አቶ ጥላሁን ውቡ ለቢቢሲ እንዳረጋገጡት "ጠንካራ የአቧራ ጭጋግ ተከስቷል።"
ይህ የአቧራ ጭጋግ የሚከሰተው በደረቅ አካባቢዎች የሚከሰትን አውሎ ነፋስ ተከትሎ ነው የሚሉት ባለሙያው፤ በባህር ዳር ላይ የታየው የአቧራ አውሎ ነፋስ ሱዳን ላይ በተከሰተ ዝቅተኛ የአየር ግፊት ምክንያት መሆኑን ይናገራሉ።
ይህ የአቧራ ጭጋግ የተከሰተው በባህር ዳር ከተማ ብቻ አለመሆኑን የሚናገሩት ባለሙያው ጎንደር ላይም መታየቱን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ክስተቱ ብዙ ጊዜ ለረዥም ሰዓት አይቆይም የሚሉት አቶ ጥላሁን ቶሎ ሊጠፋ እንደሚችል ያስረዳሉ። ነገር ግን በእንዲህ ዓይነት የአየር ሁኔታ አውሮፕላኖች ለመነሳትም ሆነ ለማረፍ እይታን ስለሚጋርድ ለበረራ አስቸጋሪ እንደሚሆን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ላይ ግን በረራዎች ከተስተጓጎሉባቸው ከተሞች ውስጥ የአቧራ ጭጋጉ የተከሰተባት የባህር ዳር ከተማ የለችበትም።
ባለሙያው ጨምረውም እንዲህ አይነት አቧራ ጭጋግ የመተንፈሻ አካል ችግር በተለይ አስም ላለባቸው ሰዎች አስቸጋሪ እንደሚሆን አስታውሰው፤ እንዲሁም ክስተቱ የማጅራት ገትር በሽታ መንስዔም ሊሆን እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።
ባህር ዳር የሚገኘው የቢቢሲ ዘጋቢ እንዳረጋገጠው የአቧራ ጭጋጉ ዛሬ በከፍተኛ ሁኔታ የቀነሰ ቢሆንም የተወሰኑ ምልክቶች ግን እንዳሉ አመልክቷል።

0 Comments