
የግብርና ሚኒስቴር ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንዳስታወቀዉ ከዉጪ የሚገባዉ የበረሃ አንበጣ ካለመቆሙም በተጨማሪ በኢትዮ ኬንያ ድንበር አካባቢዎች በመፈልፈሉ ለመከላከል አስቸጋሪ ሆኗል፡፡
በግብርና ሚኒስቴር የእፅዋት ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ ዘብዲዮስ ሰላቶ እንዳሉት በአሁኑ ወቅት የበረሃ አንበጣ ለምስራቅ አፍሪካ ወረርሽኝ ሆኗል ብለዋል፡፡
የአንበጣ መንጋዉ ከዚህ ቀደም በምስራቁ የአገሪቱ ክልል በኩል ወደ አገር ይገባ እንደነበር የገለፁት ዳይሬክተሩ፤ አሁን ደግሞ በደቡብ ክልል በተለይም በኬንያ ድንበር አካባቢ በስፋት መስተዋሉን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ እና በምስራቅ አፍሪካ አገሮች ላይ እየተስፋፋ የመጣዉን አንበጣ ለመከላከል የአለም አቀፍ ተቋማት እና ግብረሰናይ ድርጅቶች ድጋፍ ሊያድርጉ እንደሚገባም አቶ ዘብዲዮስ ጠይቀዋል፡፡
የአለም አቀፉ የእርሻ እና ምግብ ድርጅት ለኢትዮጵያ ሁለት አዉሮፕላኖችን ድጋፍ ማድረጉን እና አንደኛዉ አዉሮፕላን ወደ አርባምንጭ መሰማራቱን ሚኒስቴሩ አስታዉቋል፡፡
ድርጅቱ ተጨማሪ አዉሮፕላኖችን እና ለመስክ ስራ የሚያገለግሉ ተሸከርካሪዎችን በቅርቡ ድጋፍ እንደሚያደርግም ዳይሬከተሩ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ እስካሁን ባደረገችዉ የመከላከል ስራ ከ300 በላይ መንጋዎችን ላይ ዘመቻ መደረጉን የተናገሩት አቶ ዘብዲዮስ፣ከእዚህ ዘመቻ ያመለጡ የአንበጣ መንጋ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ተበታትነዋል ብለዋል፡፡
በተለይም በጎንደር አካባቢ አንበጣዉ ይከሰት እንጂ ያረፈበት አካባቢ ብርዳማ በመሆኑ በቅርብ ጊዚያት ዉስጥ የሚጠፋ እንደሆነም አንስተዋል፡፡
አሁን ላይ ኢትዮጵያ አንበጣዉን ለመከላከል አምስት አዉሮፕላኖችን በባሌ፤ በአርሲ ፤ በአርባ ምንጭ እና በኮንሶ አካባቢዎች እየሰሩ ይገኛሉ ተብሏል፡፡
የወቅቱ የአየር ሁኔታ የበረሃ አንበጣዉ እንዲስፋፋ ምቹ ሁኔታን እንደፈጠረለትም ተሰምቷል፡፡
የግብርና ሚኒስቴር ከባለፈዉ አመት ሰኔ ወር ጀምሮ ከሚመለከታቸዉ አካላት ጋር በመሆን መከላከል ስራዉን እየሰራ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡
በአባቱ መረቀ
መጋቢት 2 ቀን 2012 ዓ.ም
0 Comments