
ለመጀመሪያ ጊዜ ባለፈው ታኅሣስ በቻይና የተከሰተው የኖቨል ኮሮና ቫይረስ የዓለማችን የጤና ስጋት መሆኑን የዓለም የጤና ድርጅት ባስታወቀ ማግስት ከቻይና ወጥቶ በበርካታ ሀገራት ተዛምቷል፡፡ ችግሩን በተለያየ መንገድ ለመከላከል የሞከሩ ሀገራት ሳይቀሩ ዜጎቻቸው በቫይረሱ እየተያዙ መሆኑን እና ቫይረሱ ወደየሀገሮቻቸው መግባቱን እያስታወቁ ነው፡፡
ሴኔጋል ትናንት ሰኞ በዋና ከተማዋ ዳካር በኮሮና ቫይረስ የተያዘ ሰው ማግኘቷን አረጋግጣለች፡፡ የፈረንሳይ ዜጋ የሆነው እና በቫይረሱ የተጠረጠረው ግለሰብ ትናንት በዳካር ኢንስቲትዩት ኦፍ ፓስተር በቫይረሱ መያዙ በሕክምና ምርመራ ተረጋግጧል ተብሏል፡፡ ሴኔጋል የኮሮና ቫይረስ የተከሰተባት አራተኛዋ ሀገርም ሆናለች፡፡ ከዚህ ቀደም ግብፅ፣ አልጀሪያ እና ናይጀሪያ ቫይረሱ የተከሰተባቸው አፍሪካዊ ሀገራት ናቸው፤ በእርግጥ ደቡብ አፍሪካም ከጃፓን የመጡ መርከበኞች በቫይረሱ እንደተያዙ ማረጋገጧ ተዘግቦ ነበር፡፡
ሳዑዲ ዐረቢያም ለመጀመሪያ ጊዜ ቫይረሱ በግዛቷ መከሰቱን አረጋግጣለች፡፡ ባለፉት ሦስት ወራት በቻይና እና ሌሎች 66 የዓለም ሀገራት ላይ ከተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ነፃ ሆና የቆየችው ሳዑዲ ዐረቢያ ለመጀመሪያ ጊዜ ቫይረሱ በግዛቷ መከሰቱን ትናንት አስታውቃለች፡፡
የሀገሪቱ የጤና ሚኒስቴር ትናንት እንዳስታወቀው በቫይረሱ የተያዘው ግለሰብ ከኢራን በባሕሬን አድርጎ ወደ ኪንግ ፉሃድ ጉዞ አድረጓል፡ ግለሰቡ በተለየ የሕክምና መስጫ ማዕከል ውስጥ ሆኖ ሕክምና እየተከታተለ ነውም ተብሏል፡፡
ምንጭ፡- ዐረብ ኒውስ እና ሲ ጂ ቲ ኤን
በታዘብ አራጋው
0 Comments