የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ ባለቤት ሶፊ ግሪጎሪ ትሩዶ በተደረገላቸው ምርመራ በኮሮናቫይረስ መያዛቸው መረጋገጡን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት አስታውቋል።
"የሚመከሩ ጥንቃቄዎችን ሁሉ እየወሰደች ለጊዜው ተገልላ የምትቆይ ይሆናል፤ ደህና ነች የሚታዩባት ምልክቶችም ቀላል የሚባሉ ናቸው።" ይላል የጽሑፉ መግለጫ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ትሩዶ ጤናማና ምንም የኮሮናቫይረስ ምልክቶች የማይታዩባቸው ቢሆንም ለ14 ቀናት ራሳቸውን አግልለው እንደሚቆዩም ተገልጿል።
ነገር ግን ምንም የሚታይባቸው ምልክት ስለሌለ የኮሮናቫይረስ ምርመራ አያደርጉም ተብሏል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለቤት ግሪጎሪ ትሩዶ ረቡዕ እለት ማምሻውን ከለንደን ወደ ካናዳ መመለሳቸውን ተከትሎ የጉንፋን ምልክት ማሳየታቸው ታውቋል።
"ምንም እንኳ በቫይረሱ ምቾት የሚነሱ ስሜቶች ቢኖሩኝም አሁን በቅርቡ በጣም ደህና እሆናለሁ" ብለዋል ግሪጎሪ ትሩዶ።
የጤና ባለሙያዎች ግሪጎሪ ትሩዶ ባለፉት ጥቂት ቀናት ያገኟቸውን ሰዎች በሙሉ ፈልገው እንደሚያገኙ ተገልጿል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምንም እንኳ ራሳቸውን ለቀጣዮቹ 14 ቀናት አግልለው የሚቆዩ ቢሆንም መደበኛ ስራቸውን እየሰሩ ሃላፊነታቸውን እንደሚወጡ በመግለጫው ተመልክቷል
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትሩዶ ዛሬ ለካናዳዊያን በቴሊቪዥን መግለጫ እንደሚሰጡም ጽ/ቤታቸው አስታውቋል።
በአሁኑ ወቅት በካናዳ 103 ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ተረጋግጧል።

0 Comments