የወሲብ ፊልምና ጠንቆቻቸው (ክፍል - 2)


ክፍል - 2

በስመ አብ፥ ወወልድ፥ ወመንፈስ ቅዱስ፥ አሐዱ አምላክ፥ አሜን፡፡

የወሲብ ፊልምና የስነልቦና ጉዳት 

የሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን የትውልድ ፈተና ሆኖ ከገዳይ በሽታዎችና ከትራፊክ አደጋዎች ባልተናነሰ የወጣቱን ማኅብረሰብ ውስጠኛ ሕይወት ክፉኛ እያጠቃና እያኮለሸ የሚገኘው የወሲብ ፊልም ሱስ ነው፡፡ 

በመናፍስቶችና የመናፍስት አጀንዳ ባለቸው ሰዎች የሚመራው የወሲብ ፊልም ኢንደስትሪ ከሚፈልጉት መጠንና ፍጥነት በተሻገረ መልኩ ብዙ የዓለምን ትውልዶችን የስነልቦና ጤናማነትና መንፈሳዊ ኑሮ በእጅጉ ጎድተዋል፡፡ አልፎም ተርፎም ወጣቶች ከራሳቸው ባሕሪይና አመል ጋር መስማማት በማጣታቸው ምክንያት ለተለያዩ የአእምሮ መታወኮችና የግል ጭንቀቶች የታደረጉ ሲሆኑ፤ ለብዙ ራስን በራስ የማጥፋት መንስኤዎችም ግብአት የሆነ የርኩሳን መናፍስት የግብር እስረኛ የሚያደርገው የወሲብ ፊልም ያልተጠና ነገር ግን ከፍተኛ ውድመት ለማስከተል የቻለ ተጽዕኖ በአገራት ላይ አስከትሏል፡፡ ብዙ ወጣቶች ከቤተሰብና ቤተሰብ አዝማድ ጧሪነት ተነጥለው የወሲብ ፊልም ሱስ ጧሪ በመሆን፤ ከሌሎች እንደነርሱ እስረኛ ከሆኑ ወጣቶች ጋር ብቻ በሚያገኟት ክፍተት በፌዝና እንደ ችግር ባልተቆጠረ መልኩ የውስጥ ስቃያቸውን ሲተነፍሱ፤ በተናጠል በተናጠል ግን ከራሳቸው ጋር የሚጣሉበትን መንገድ መንፈሱ እየቀረጸላቸው አልለቅ ያለ ጥገኛ ሆኖባቸው በዝምታ እየተቸገሩ የቆዩ በመሆኑ ስቃዩን ለምደውት ዛሬ እንደ አንድ የጠባያቸው ገጽታ አስተናግደውት ይገኛሉ፡፡ 

የወሲብ ፊልም ጥገኝነት ለመናፍስታዊ ማነቆ ቁራኛ የሚያደርግ ሲሆን፤ ወጣቶችና ጎልማሶች ለፍትወት የተፈጥሮ ስሜት መልስ መስጠት የሚችል አድርገው በመቁጠር እንዲገቡበት ከሆነ በኋላ፤ ከቁጥጥር አልፎ በሳምንት ውስጥ ለተደጋጋሚ ቀናት ከዛ በየቀኑ በመቀጠልም በቀን ሦስት አራቴ እንዲመለከቱና ራሳቸውን በራሳቸው በማስደሰት ግለ-ሩካቤ በመጥመድ ጠፍንጎ በሚያስራቸው ጊዜ ከጥገኘነቱ ልላቀቅህ ቢሉት 'እምቢ!' የሚል፤ እየመላለሰም በፍትወት ንዳደ ስሜት በኩል እያቃጠለ ከተነሱበት ነጥብ እንዲጀምሩ በማድረግ ውስጣዊ ሰላምን የሚያናጋ፣ እረፍትን የሚበጠብጥ፣ ትዳርን የሚያኮስስ፣ የተፈጥሮ ስሜትን የሚያደበዝዝና ከራስ ልማድ ጋር ሙግት በመግጠም ሂደት ውስጥ የአእምሮ ብሎም የአካል መድከምን የሚያመጣ እጅግ ክፉ የመናፍስት እስራትን የሚገልጥ የክፉዎች መሣሪያ ነው፡፡

የወሲብ ፊልም ሱስኝነት የሚፈጥራቸው መናፍስታዊ የስነልቦና ጉዳቶች 

1) ጭንቀት

ዓለም በቴክኖሎጂውና በሳይንሳዊ ልቀት ጥልቅ የሆነ ለውጥ ማምጣት ከቻለችበት አንደኛው ዘርፍ መካከል የመገናኛ አውታሮች የሆኑት የእጅ ስልኮቻችን ይጠቀሳሉ፡፡ ዛሬ በእጅ ስልኮቻችን አማካኝነት በቀላሉ የምንፈልገውን ሃይማኖታዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና የመዝናኛ መረጃዎችን ማግኘት ከመቻላችን በላይ፤ እንደ ቀድሞ ዘመን መልእክት ይዞ መንከርፈፍ ቀርቶ በፍጥነትና በጥራት ርቀት ላይ ለሚገኝ ሰው መልእክትን ማቀበል የሚቻልበት መልካም አጋጣሚ ተፈጥሯል፡፡ ጥሩ ነው እግዚአብሔር ይመስገን፡፡ ነገር ግን በአጽንዖት ልናስተውልና ልንገነዘበው የሚገባው ጉዳይ በእጅ ስልኮቻችን አማካኝነት መናፍስታዊ መረጃዎች በቀላሉ ወደ ሕይወታችን ለመግባት የሚችሉበት ዕድል በዛው የመገናኛ አውታሩ ብዛትና ስፋት መጠን ልክ እንደሚፈጠር መረዳት ይገባናል፡፡ ከነዚህም በቴክኖሎጂ ጀርባ ከሚደበቁ መናፍስታዊ የመረጃና የመዝናኛ ደባዎች መካከል ዓለምአቀፋዊ ሴራ ያለበት የወሲብ ፊልም ኢንደስትሪ በወጣቶችና በጎልማሶች የአኗኗር ሁነት ጥልቅ አደጋን በመፍጠር ብዙ ተመሳሳይ ይዘት ያለውን ችግር ካስከተለበት መንገድ አንደኛው ጭንቀት ነው፡፡ 

ብዙ ወጣቶች የዘመኑን ፋሸንና አለባበስ ተከትለው በአንድ ላይ ታጅበው እየተሳሳቁና እየተፏገሩ ሲታዩ ደስተኞች ቢመስሉም፤ ቤታቸው ከገቡ በኋላ ግን በከፍተኛ ጭንቀት የሚባትቱ፣ የሚናገሩትና ይሄ ነው ብለው የማይለዩት ሽብር ሕሊናቸውን የሚንጣቸው፣ በእምነትና መንፈሳዊ እንድምታ በኩል ራሳቸውን ለማስቀመጥ የሚቸገሩና በዚህም ምክንያት የነፍስ መጨነቅ ውስጥ የሚገቡ ትውልዶች ቤቱ አይቆጥራቸውም፡፡ 

ይሄ የውስጣዊ ሕይወት ጭንቀት እንዲከተል ካደረገው መነሻ ምክንያቶች መካከል ብዙ ቤተሰባዊና አከባቢያዊ ችግሮችን መዘርዘር ቢቻልም አንደኛው የመከራ መዋጮን በማዋጣት ለተባባሰ መረበሽና ብቸኝነት የመዳረግ ሚናን የሚጫወተው የወሲብ ፊልሞችን እና ምስሎችን አዘወትሮ የመመልከት አባዜ ነው፡፡ ወጣቶቹ ገና ሲጀምሩት የሚያስደስትና ለአእምሮ የሚያዝናና ሆነው ቢያገኙትም፤ ከጊዜያት ቆይታ በኋላ መናፍስታዊ ግብሩ በሚጠነክርበትና ሱስ የመሆን እስራቱ በሚጠብቅበት ጊዜ፤ ደጋግሞ የመመልከት ፍላጎቱ በግፊት ሰለሚያይል፤ ከዚህ ስሜት ለመውጣት በየቀኑ በሚኖረው ትግል ውስጥ ዘወትር ጥቂት ጥቂት እያለ የሚጨምር የጭንቀትና የመድከም ኃይል ከውስጥ ይኖራል፡፡ 

በአእምሮና በልቦናም ውስጥ እየጨመረና እየገዘፈ የሚመጣው ጭንቀት እየተባባሰ ከሚሄድባቸው ምክንያቶች ዋነኛው ምንድነው፤ የወሲብ ፊልም የብልጭታ ያህል መነሻን አሳብ ብቻ መንፈሱ የሚፈልግ በመሆኑ፤ በየቀኑ ወጣቶች ከሚያዩት፣ ከሚሰሙትና ከሚያነቡት ላይ በመንተራስ የሩካቤ ጫናን በመቀስቀስ ልቦናቸውን በቀጭን መስመር ላይ በማጥበብ እንዲመለከቱ በዙሪያቸው ከወሲብ ነክ እይታ ውጪ የሆነውን ያደበዝዘዋል፡፡ ከዛ በኋላ በመንፈሱ በተከፈተው ቀጭን መስመር ላይ ሲቆም ሌላ አሳብን ማመላለስ እጅግ አዳጋች ይሆናልና ወጣቶች በግፊት በመጣው የመንፈሱ ጤናማ ያልሆነ የግንኙነት ስሜት ተቃጥለው ከተመለከቱ በኋላ ልቦናቸውን #ለጊዜው ለቀቅ ስለሚያደርገው፤ መልሰው በራሳቸው ጊዜያዊ ስሜት ግራ በመጋባት የፊልም ሱሱን ለማቆም ለራሳቸው ከሕሊናቸው የገቡትን ቃል አፍርሰው ደግመው በዝሙት ግብር በመውደቃቸው ይጸጸታሉ፡፡ ራሳቸውን የስሜት ተገዢና የፍትወት ምርኮኛ አድርገው እንዲቆጥሩ መናፍስቱ አሳብ ስለሚያቀርቡ፤ በቁጭትና በንዴት በመብሰክሰክ ከራሳቸው ጋር እንዲጣሉ ስለሚገደዱ ይሄ ልማድ በሚደጋገምበት ጊዜ ከፍተኛ የስነልቦና ጭንቀት ይፈጥራል፡፡ ይህም ጭንቀት ለዓመታት በሚቀጥልበት ጊዜ ወደሌሎች የአሳብ አመለካከቶችና ማኅበራዊ ግንኙነቶች በቀላሉ በመሻገር ሁሌ ድበታ ያልተለየው፣ ለምንም ነገር ስሜት ያጣና ደንታ ቢስ የሆነ፣ በየቀኑ ድካምና መልፈስፈስ የሚሰማው ሰው እንዲሆን የኑሮ አካሄዱ በመናፍስቱ የጥፋት አካሄድ መሠረት እየተቀረጸ ይሄዳል፡፡ 

2) ብቸኝነት

በመናፍስት እስራት ውስጥ የገባ የወሲብ ፊልም ጥገኝነት ባሕሪያችንን ቀስ በቀስ ቤተሰባዊና ማኅበራዊ ግንኙነቶችን በመቧጠጥና በማሻከር የብቸኝነት ሰዓትን በመጨመር ለሱሱ ብቻ ተገዢ እንድንሆን ያስገድዳል፡፡ በተለይ የልማዱን ጥማት ለመወጣት የሚመቸው ለብቻ በመሆን ስለሆነ፤ የብቻ ጊዜያትን በሕይወት ውስጥ በመጨመር በር ዘግቶ ለረጅም ሰዓታት በወሲብ ፊልም ውስጥ ኑሮን በመደበቅ ከመናፍስቱ ጋር ግንኙነት(ግለ-ሩካቤ) በማሰልጠን የግለሰቦችን የዕለት ተዕለት የኑሮ አቅጣጫ ሳያሳውቅ የሚያበላሽ ይሆናል፡፡ አንድ ሥራ ለመሥራት፣ ጥናት ለማጥናት፣ መጽሐፍ ለማንበብ ስንሞክር የወሲብ ፊልሞቹ ትውስታ በመናፍስቱ ግፊት በኩል ምናብ እየሆኑ የአእምሮአችን ግድግዳ ላይ ስለሚሳሉ፤ የግለ ሩካቤውን ግብር እስከምንፈጽመበትና መንፈሱን እስከምናስደስትበት ደቂቃ ድረስ ይሄ የምናብ ግፊት አይለቅም፡፡

በመሆኑም የጀመርነውን ሥራ፣ ጥናት አሊያ ንባብ አቋርጠን የወሲብ ፊልም መመልከት ወይንም በመናፍስቱ እገዛ በኩል ወደ ውስጠኛ የምናበ ክፍላችን በመመሰጥ ያየነውን የወሲብ ምስል ደግመን በሕሊና እያየን የመናፍስቱን ጥያቄ ለመመለስ በመናፍስቱ እንገደዳለን፡፡ ይሄም በእግዚአብሔር የአምልኮት ሕይወትና የዘወትር መንፈሳዊ ልምምድ ብቻ የምንዋጋው የጠላት ክንድ ስለመሆኑ መረጃው ብዙ ጊዜ ስለማይኖረን፤ ከልማደ ግብሩ ከመላቀቅ ይልቅ አብዝተን እየገባንበት ወደ ብቸኝነት አቅጣጫ ሳናስተውል ርቀን በመጓዝ ቤት ስንገባ ብቸኛ፤ ከሰው ጋር ስንሆን ብቸኛ፤ ከቤተሰብ ጋር ስንጨዋወት ብቸኛ እየሆንን ስውር የመናፍስቱን ትዳር አግብተን እንኖራለን ማለት ነው፡፡

3) ልቅነት እና ግዴየለሽነት

የወሲብ መናፍስቶች ሌላው በትውልድ የሰው ልጆች ልቦና ላይ የሚያስከትሉት ከፍተኛ ተጽዕኖ መረን የለቀቀ ስድነትና ቸልተኝነት ነው፡፡ በዝሙት ፊልምና በግለ ወሲብ ሱስ የተጠመዱ ብዙ ሰዎች ያፈነገጠና ከተፈጥሮአዊው ሁነት የተጣላ የሩካቤ ስሜትና ፍላጎት የሚኖራቸው ሲሆን ማለትም ዓይናውጣነትና ምንም የነውር ስሜት የማይገኝበት የወሲብ ልምምድና አኗኗር በመያዝ የሴሰኝነት ጠባያትን ከአጉል አመል ገጽታ ጋር መላበስ ዕድል ፈንታቸው ነው፡፡ በአንፃሩ ደሞ ጭራሽ ከተፈጥሮአዊው ስሜት የተጣረሰ የሩካቤ ፍላጎት መቀዛቀዝ በመከተል፤ ከፊልሞቹና ከግለ እርካታው ልምምድ ውጪ የትዳር አጋርን በመሸሽና በመጥላት በዚህም ሳቢያ የአብራክ ክፋይ ልጅ በማጣት የሌሎችን ሕይወት እያዩ እንዲማረሩና ራሳቸውንም ሆነ ትዳራቸውን እንዲጠሉ መንፈሱ ይገፋፋቸዋል፡፡ ይህ ሁኔታ ራስን በራስ እስከመቅጠፍ ደረጃ ሊደርስ ይችላል፡፡ 

ገና ከመነሻ ዓላማቸውም የወሲብ ፊልሞቹ ሲሠሩና ሲበተኑ ራእያቸው ራሱን፣ ጊዜውንና ኑሮውን የማይገዛ ትውልድን ለመፍጠር ግብ ተደርገው የተለቀቁ ስለሆኑ፤ መናፍስቶቹ የባለቤቶቹን ፍላጎት በተገበረላቸው ጭዳ በኩል ለማሟላት የሚቆራኙትን ግለሰብ ደንታ ቢስ፣ ለእውነትና ለቁም ነገር ቦታ የማይሰጥ፣ ኑሮውን ቀጥ አድርጎ መምራት የማይችልና ሁልጊዜ መዝናናት የሚያምረው በማድረግ በሁሉም የሕይወቱ አቅጣጫ የማይከናወንለት ከንቱ ያደርጉታል፡፡ 

በዝሙት መናፍስት የታሰረ ሰው ራእይ፣ ዓላማ፣ ስኬትና የሕይወት የበረከት ውጣ ውረድ በፍጹም አይገቡትም፡፡ ስለዚህ ለምንም አይነት አጋጣሚና ዕድል የሚያሳየው ፍላጎትና እቅድ የተዝረከረከ ስለሚሆን፤ ከወሲብ በቀር በምድር ላይ የሚያስደስተው ነገር አይኖርም፡፡ በዚህም ባሕሪው በየጊዜው ከነፍሱ ማንነት ጋር ስለሚጋጭ፤ ይህንን ውስጣዊ ፍጭት ለማስታገስ ሁሌ መዝናናት፣ መደሰት፣ ነገሮችን መርሳት፣ በሱስና አደንዣዥ ዕፅ መደበቅ የሚመርጥ ችግሩንም ለይቶ መናገር የማይችልና ቢችልም የሚያሳፍረው የውጭ ሳቂታ የውስጥ አልቃሽ ይሆናል፡፡ 

ብዙ ወጣቶች በዘመናችን አንደበታቸው በወሲብና ልቅ በሆኑ ቃላት የተጀቦነ፤ በስድብም፣ በነቀፋም፣ በምክርም፣ በውይይትም፣ በጽሑፍ ልውውጥም መካከል የዝሙት ስሜቶችንና ፍላጎቶችን የሚያንጸባርቁ ድምፆችን እያሰሙ፤ የነውር ኃላፊነት የራቃቸው ቋንቋዎችን መናገር የዘመናዊው ባለ ቴክሎኖጂ ትውልድ መገለጫ ሆኗል፡፡ የዚህ የስነምግባርና የእምነት እሴት መጨንገፍ ምክንያቱ እነዚህ በህቡዕ ድርጅቶች አማካኝነት የሚሰራጩት የወሲብ ፊልሞች የርኩሰት ውጤት አንደኛው ሲሆን፤ ሰው ያስገባውን የውስጥ መረጃ ወደ ውጪ በሚገልጥበት ጊዜ ያንኑ የተመለከተውን ጸያፍ ድርጊትና የላሸቀ ምግባር ይገልጣል፡፡ በዚህም ምክንያት ከአፉ እሳት የሚተፋ፣ ያመጣለትን ቃላት የሚናገር፣ አንደበቱን ከዝሙት ቃላት ማሸሽ የማይችል እና በየሄደበት ቦታ የቀልድና የፌዝ ወሲባዊ ገጽታዎችን የሚያንጸባርቅ የሰይጣን ገጸ ባሕሪይ የሆነ ትውልድ እንዲፈጠር የተዘራው የመናፍስትና የክፉዎች ዘር አፍርቶ በኛም ትውልድ ሁለንተናዊ መጣረስና መፋለስ የሚስተዋልበት የሰው ልጆች ዘመን ይገኝ ዘንድ ተገድደናል፡፡ 

4) መፍዘዝና መደንበዥ

የወሲብ ፊልምን አዘወትሮ የመከታተል ሌላኛው ስነልቦናዊ ጠንቁ፤ መናፍስታዊ አዚም የተጫነው የውስጥ ሕይወት መደንዘዝና ዝምታ በመሆኑ በየቀኑ ከዚህ ስሜት ለመላቀቅ ተጨማሪ ፊልሞችንና ምስሎችን ለማየት የሕሊና አሳብ ግፊት ሲኖር፤ ዘወትር መደብዘዙና መፈዘዙ እየጨመረ የሚሄድ ይሆናል፡፡ የወሲብ ፊልም ሱስ የመሆን አቅሙ እንደ ጫት፣ ሲጋራና ሐሺሽ በመሆኑ፤ የሱስ ግብሩን በመናፍስቱ ጫና በኩል በሚጠይቅበት ጊዜ፤ ግብሩ በወቅቱና በሰዓቱ ካልተሰጠው የአእምሮ ዝለትና መዳከምን መናፍስቱ ከውስጥ ይለቃሉ፡፡ ልክ በሲጋራ ሱስ መላልሶ እንደሚያፋሽክ ሰው፤ የወሲብ ፊልም ሱስ ያየዘው ልቦናም ደጋግሞ በስሜት ስለሚያፋሽክ የሱስ ግብሩ ርሃብ ካልታገሰለት በቀር ግለሰቡ እረፍት አይሰማውም፡፡ በዚያ ቀን እንደምንም ተቋቁሞ ቢያልፍ፤ ወይንም ከሌሎች ሰዎች ጋር በመቆየት ጭንቅላቱን ለማረሳሳት ቢሞክርም፤ በሌላ ቀን አዘናግቶ መልሶ ይህንኑ የአእምሮ ማፋሸክ ስለሚፈጥር፤ ባለፉት 'የአምጣ' ጥያቄ ቀናት ትግል የተዳከመው ሕሊና በሌላ የሚከተለውን የመናፍስቱን ጫና መቋቋም ያቅተውና ይወድቃል፡፡ ይሄም የውስጥ ጭንቅላት የኃይል አቅም እጥረትና መልፈዝፈዝ የሚያስከትል ስለሆነ መፍዘዝና መደንገዝ በወሲብ ፊልም መናፍስቶች የተያዙ ሰዎች የሚሰማቸው ማንም የማይረዳላቸው የውስጥ የባሕሪይ እከል ይሆናል፡፡ 

ይቀጥላል..



Post a Comment

0 Comments