ክፍል - 3
በስመ አብ፥ ወወልድ፥ ወመንፈስ ቅዱስ፥ አሐዱ አምላክ፥ አሜን፡፡
የወሲብ ፊልም የቱን ያህል በዘመኑ ፋሽን ዘልቆ ሄደ?
የዝሙት ፊልሞችና ምስሎች በዓለም አህጉራት በከፍተኛ ደረጃ የመሰራጨታቸው ሚስጢር ከጀርባው በተቀናጀ አደረጃጀትና ህቡዕ በሆነ አካሄድ ውስጥ የተሰለፉ የሚስጢር ማኅበራት ተጽዕኖ እና አቅም አማካኝነት ነው፡፡ አብዛኛው የወጣቱ ትውልድም በቀላሉ በሚያገኘው የእጅ ስልኮቹና የመገናኛ አውታሮች በኩል የሚለቀቁት እነዚህ የርኩሳን መናፍስት አዚማዊ መሣሪያ የሚሆኑ ፊልሞች፤ ወደኑሮና ልማድ የመቀላቀል ፍጥነታቸው ከፍተኛ የሆነ ሲሆን ያለ ውጣ ውረድና ተጨማሪ ጉልበት የተፈጥሮ ስሜት ላይ በመመርኮዝ የአእምሮ ክፍልን ተቆጣጥሮ በፍላጎት ስሜት አነሁልሎ በማደንዘዝ ወደ ልክፍት የሚመራ ስውር የማይነገርለት ጠፍናጊ ሱስ የመሆን ባሕሪይ ያለው የክፍለ ዘመናችን ማፍዠዣና ትውልድን ማሰሪያ ወጥመድ ነው፡፡
ፊልሞቹ በጥንቃቄ ታቅደው ሲዘጋጁ ከኋላቸው እንዲያሳኳቸው የተቀመጡላቸው መናፍስታዊ ራእይና ግብ አላቸው፡፡ ከነዚያም መካከል ትውልዱ በሚከተላቸው የፋሽን፣ የአለባበስ፣ የመዝናኛ እና ሌሎች ዘርፎች በኩል ተዘዋዋሪ የሚመስል ነገር ግን በቀጥታ የተቆራኘ ዲያቢሎሳዊ ስብከቶችንና መገለጫዎችን ማስፋፋት አንደኛው ሲሆን፤ በእውነትም ታዲያ በዚህ በኩል ያለውን ግፊትና ያመጣውን ግልጽ ጫና ከትውልዳችንና ዘመኑ ጋር አሰናስለን ስንመለከተው በእጅጉ ተሳክቶላቸው በድሉም ከፍተኛ እርካታንና ድል አድራጊነት የሚያመጣላቸውን ስራ እንደፈጸሙ ማገናዘብ እንችላለን፡፡
እነዚህ የዝሙት ኢንደስትሪዎች ጥፋት አድራሽነታቸውና የትውልድ ልክፍትነታቸው ገሃድ በወጣ እውነታ ያለ ማስረጃና ሰነድ አስፈላጊነት የተረጋገጠ ሲሆን፤ ነገር ግን "ተዉ" የሚላቸው ጠንካራ የመንግሥትና የግለሰቦች ተቋም እምብዛም አለመኖሩን ስናጤን፤ ከዓለም መንግሥታት ጀርባ ያሉት መናፍስታዊ መዋቅር ያላቸው ድርጅቶች ባለ ጠንካራ ሰንሰለታማ አሳሪዎቹ የሚስጢር ማኅበራት ክንድ የቱን ያህል እግዚአብሔር በረሳ ትውልድና ዘመን ላይ በርትቶ እየደቆሰ፣ እየጠመዘዘና እየገፈተረ እንዳለ መረዳት ያስችለናል፡፡ የወሲብ ፊልሞች አደገኝነት በንጽጽር ሲታይ ጥቂት የሚሆኑ ተመራማሪዎችና አጥኚዎች ጉዳቱንና ሁለ ገብ እከሉን በሰዎች ቋሚ ምስክርነት እያረጋገጡ ትምህርትና መረጃ ቢሰጡበትም፤ የወሲብ ኢንደስትሪዎቹ ከተሰራጩበት ጥልቀትና ስፋት አንፃር፤ እንዲሁ ትውልዱ ውስጥ ሥር ሰደው ካሉት የመናፍስት አገዛዝና አሠራር ምክንያት በቀላሉ ለኃጢአትና ለእርግማን አሳቦችና ድርጊቶች የመሳብ አዝማሚያው ከፍተኛ በመሆኑ፤ እዚህ ግባ የማይባል ለውጥ ሳያመጡ ቀርቶዋል፡፡
የወሲብ ኢንደስትሪና የፋሽን ኢንደስትሪ ጣምራ ሂደት
ከላይ በተገለጸው መልኩ እንደተቀመጠው ጉልህ የሆነና በቁጥርም የበዛ ጥናትና ምርምር ባለመካሄዱ እንጂ በዛሬው ትውልድ እውነታ ውስጥ የዝሙት ኢንደስትሪ ተቋማት የአሻራ ተጽዕኖ ያልነካካው የሕይወት ዘርፍ ፈልጎ ማግኘት የሚያዳግት ይሆናል፡፡ ከነዚህ በታላቅ ተጽዕኖ ውስጥ ውድቀው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚስጢር ማኅበራቱ ተልዕኮና እቅድ ተፈጻሚ ከሆነባቸው የትውልዱ ገጽታዎች መካከል የፋሽን ኢንደስትሪው ይጠቀሳል፡፡
ዛሬ በፋሽን ኢንደስትሪው በኩል በየቀኑ እየተመረቱ የሚወጡት የልብስ ቅርጾችና ይዘቶች፣ የመዋቢያ መሳሪያዎች፣ የተለያዩ ቁሳቁሶች በአብዛኛው ራቁት ገላን የሚያበረታቱና ዝሙት ነክ እንድምታ የሚነበብባቸው ናቸው፡፡ ርጉማን መናፍስት፤ የዘመኑን ትውልድ የቀልብ አሳብ አዎንታዊ በሚመሰል ስሜት አነሁልሎ በራቁትነት ገጽታ በመሳብ፤ የፋሽንና የአለባበስ ሴሰኝነትን የሚያንጸባርቅ ፍላጎት በመፍጠር፤ በዓይን በመመልከት ብቻ የሕሊናን እምነት መስመር በማሳት፤ ውስጣዊ ዝንባሌን ከመናፍስት ትዕዛዝ በሚመነጭ ግፊት በማስቀልበስ ወሲብ ናፋቂ እንዲኮን ያደርጋሉ፡፡
ዘመናት አስቀድሞ አጭር ቀሚስና ደረት የሚገለብጥ ልብስ መልብስ በተለይ በኛ ማኅበረሰብ እሴትና እይታ መሠረት ነውር የተባለ ሲሆን፤ ዛሬ ነውሩ ረጃጅም ቀሚስ መልበስ እንደሆነ ሁሉ ከተማና ፈረንጅ ቀመስ የኑሮ ዘልማዶቻችን ውስጥ የአእምሮ መፍዘዝን በመናፍስቱ አስገዳጅነት አስቀምጠውብን ራቁትነትን እንደ ባሕል ለውጥ አጸደቅነው፤ 'እሴትን' የዘመን ያለፈ ታሪክ 'ነውርን' የዘመን ነባራዊ እውነት ለማድረግ ተገድደናል፡፡ በዚህ ጊዜ የሚመረቱትም ልብሶች በብዛት ሆነ ብለው ሙታንታ ላለመሆን ሩብ የቀራቸው ቀሚሶችና አልባሳት ላይ በጣም ያተኮሩ ስለሆኑ፤ ይህንን እንቃወማለን አሊያም አንለብስም የሚሉ ሴቶች እስኪቸገሩ ድረስ ዘመኑ እንደጠቅላላ አጋድሎ ራሱ አስገዳጅ ራሱ ፈራጅ የሆነ ትውልድን ሲያፈራ ከጀርባ ያሉት የመናፍስት ማኅበራት በእጅጉ ረክተውና በግባቸው መሳካትም ተደስተው፤ ዝሙት ዝሙት የሚሸት ኑሮን ከተለያየ አቅጣጫ ለጊዜው ሲያሠለጥኑ እኛ ቢቸገር ነንና ተራ በተራ እስከምንጨነቅ ድረስ፤ ተራ በተራ እስከምንሰቃይ ድረስ ቶሎ አይገባንም፡፡ ቢገባንም ዘመኑንና ትውልዱ እንደሆነው ለመሆን እንጂ የእምነትንና የማኅበረሰብን የእውነት ኃይል ለማስጠበቅ ሰብረን የምናልፍበት እውነቱም፣ ድፍረቱም፣ ፍላጎቱም የለንም፡፡
በመናፍስታዊ ቁራኝነት ተለውሰው የሚለቀቁት የዝሙት ፊልሞችና ምስሎች በብዛት ሴቶችን እንደ ፍትወት ስሜት ማስታገሻ የቆጠሩና ተፈጥሮ ሁነታቸውንም ያከበሩ ስላይደሉ፤ ይህንኑ የመርዝ ዲያቢሎሳዊ ፕሮፖ-ጋንዳ በአልባስና በጌጣጌጥ በኩል እየለወሱት ለትውልዱ ልቦና መጋሸብና መጥፋት መንስኤ ሆነው፤ ሴት ልጆች በአጭር ቀሚስና ቁምጣ፣ ደረት በሚገለብጥ ልብስና ተክለ ሰውነትን በጉልህ በሚያሳይ ፋሽን እንዲያጌጡ የማስገደድ ያህል በስውር እየተጫኑ፤ በዚህኛው በኩል ደግሞ ይመጡና የውበት መለኪያና ደረጃ ራሳቸው ሆነው፤ ያልተራቆተች፣ ዘመኑን ያልመሰለችና ያልተጋጌጠች እንስት ከውበት መለኪያው በታች እንደሆነች፣ በተቃራኒ ጾታ ተመራጭነት ደረጃ ውስጥ ያልተካተተች፣ ኋላ ቀር እንደሆነች፣ ዘመኑን መዋጀት የተሣናትና የኢኮኖሚ ጥገኛ የሆነች እንደሆነች አድርገው በሙዚቃው፣ በፊልሙ፣ በመጽሐፍቱና በመዝናኛ ሚዲያው በኩል ይደሰኩራሉ፡፡
ገንዘብንና የሚዲያ አውታሮችን በመቆጣጠሩ ረገድ ከፍተኛ ሚና እና ኃይል ያላቸው እነዚህ የዲያቢሎስ እጆች የሆኑት ህቡዕ ድርጅቶች፤ የተራቆተ ልብስና ዘመኑን የሚመስል ልብስ ለመልበስ የሚፈልጉ ቆነጃጅት እንስቶችን እየመረጡ በየፊልምና መዙቃው ኢንደስትሪው የፊት ገጽነትን ሽፋን እየሰጡ፤ የዜናዎችንና የመገናኛ ሚዲያ አትኩሮት አቅጣጫዎችን ቀድመው እየቀየሱ፤ በኢኮኖሚና የዝና ደረጃ እየደገፉ ወደላይ ወደ አርአያነት ደረጃ እንዲወጡ ከተደረገ በኋላ፤ ትውልዱን በነዚህ አርቲስቶችና የሚዲያ ሰዎች በኩል ስቦ መምራት ብዙም የማይቸግር ሆኖላቸዋል፡፡ ካለፉት መቶ ዓመታት ወዲህ በሚያስደነግጥ በከፍተኛ ፍጥነትና ተደራሽነት ወደ ዓለም የተሰራጩት የወሲብ ፊልሞችም የዓለሙን ዘመናዊ ትውልድ የሰብዓዊነት ቅርጽ ከነሥነ ምግባር ገጽታው ከውስጥ በመናፍስት ዳፍንታዊ አገዛዝ ስልት በኩል ስለተቆጣጠሩ፤ በእውነት ያለበሱትን የሚለብስ ትውልድ መገኘቱ ምንም የሚያስገርም አይሆንም፡፡
" ሴቲቱም በቀይና በሐምራዊ ልብስ ተጐናጽፋ በወርቅና በከበሩ ድንጋዮች በዕንቈችም ተሸልማ ነበር፥ በእጅዋም የሚያስጸይፍ ነገር የዝሙትዋም ርኵሰት የሞላባትን የወርቅ ጽዋ ያዘች፤"
(የዮሐንስ ራእይ 17፥4)
የወሲብ ፊልሞችና የዘመኑ የፋሽን ገጽታዎች አይገናኙም ብሎ ማሰብ የበዛ የዋህነት ነው፡፡ ምክንያቱም የዝሙት ኢንደስትሪዎች ከዘመን ዘመን አቅማቸውና ብዛታቸው እየጨመረ በመጣበት ልክ፤ በተመሳሳይ የፋሽን ኢንደስትሪውም የሚያንጸባርቃቸው የምርት ውጤቶችና ገጽታዎች እጅግ በብዛት ወሲብ ነክ መሆኑ ግልጽ ምርምር የማያሻ ማስረጃው ነው፡፡ የወሲብ ፊልም ኢንደስትሪውና የፋሽን ኢንደስትሪው በጣምራ ሂደት በስኬት ሲጓዙና እንዲጓዙም በጎን የዝሙትን ትኩሳት የሚወክል እንቅስቃሴና ትርክት በቀልድ እያዋዙ በመዝናኛ ሚዲያዎች በኩል የሰዎችን ቀልብ በማነሣሣት፤ ትውልዱ በዝሙት ምኞት በእጅጉ እንዲጠመድ የተቀናበረ ሴራ በመሆኑ፤ በመናፍስት የደነዘዘ ትውልድ፤ ራቁት ሲለበስ ደስ ይለዋል እንጂ አይከፋውም፡፡ ስለዚህ ከዘመን ዘመን የምትመጣው የቀሚሷና የቁምጣዋ ዲዛይን የቱን ያህል ገላን ብትገልጥ ተቃውሞ እንደማይገጥማት ዘመኑን በማጤን ብቻ መገነዘብ ይቻላል፡፡
" ያየሃትም ሴት በምድር ነገሥታት ላይ የምትነግሥ ታላቂቱ ከተማ ናት።"
(የዮሐንስ ራእይ 17፥18)
ወደኛም አገር ስንመጣ፤ የፋሽን የዘመን ልብሶችና የማጌጫ መንገዶችን ከነአተላው ከምዕራባዊያን የተቀበለው ትውልዳችን፤ አሁን ላይ ረጅም ርቀትን ተጉዞ መረን አልባነትን በፋሽን ዘመናዊነት ማዕቀፍ ሥር በጥምዘዛ ተቀብሎት በጊዜያትም ውስጥ እንደራሱ አንፃራዊ ገጽታ አስተናግዶት ለምዶት መጥቶ፤ አሁን ብዙ ሐሰቶች መካከል አንድ እውነት ዋጋ እንደሌላት በምትቆጠርበት የመስማማት ሂደት ላይ ደርሰን "ኸረ ተዉ እንደርሱ አይደለም!" ለማለትም አስቸጋሪ ሆነ፡፡ በመሆኑም ዘመናት በጨመሩ ቁጥር እህቶቻችንን ልብስ እየቀነሱ ተቸግረው አስቸገሩ፡፡ ወንድሞቻችንም እንደው ዘመኑን መስላ የምትታይ ሴትን ለማድነቅ እጅ ስልካቸው ላይ የተሰገሰገው የዝሙት መዝናኛ አዚም እና ጫና ስላለባቸው አራድነት በመሰላቸው እይታ ገለጥለጥ ላለቺው እያጨበጨቡ፤ ሸፍነፍን ያለቺውን እየፎገሩ የዝሙትዋን ንግሥት መንፈስ እያገዙ ስንት ዘመን መጡ?
የፋሽን ኢንደስትሪዎቹን በተመሳሳይ መልኩ ከዝሙት መናፍስት ጋራ በማቆራኘት፤ እርቃን እይታን በመፍጠር የስሜትን ገጽ መንዳት የሚችሉ ቡዳዎችን ልክፍት በማድረግ፤ የአስተሳሰብ ጠለልን ወደ ሥጋዊ ፍቃድ ብቻ እንዲያዘነብል በመቀየስ፤ የውበት አድናቂነት የሚመስል የሩካቤ ምኞትን በማንገሥ፤ የዝሙት ተነሣሽነትን እንደ ልዩ ደስታ በመቁጠር፤ የመንፈስ መሳሳብን እንደ ጤናማ ግንኙነት በማስመሰል የሚፈጸመው የአጥማጅነት መረብ በብዙ መንገድ ላይ ተሳክቶለት የተራቆተ ዘመን፣ የተራቆተ ትውልድ፣ የተራቆተ ሕሊናና የእምነት ኃይል እንዲኖር ጊዜው ተፈርዶበታል፡፡
የሚስጢር ማኅበራቱ በዚሁ በፋሽንና በጌጣጌጡ ኢንደስትሪ በኩል ትውልዱን በአሻጥር መናፍስታዊ የእጅ አዙር ቀኝ ግዛት መንገድ ላይ ለማቆም የቻሉበት መርሃቸው 'ሰው የፈለገውን የመከተል መብት አለው!' የሚል ነፃነትንና አማራጭን የሚከፍት የሚመስል ነገር ግን የውዴታ ግዴታ ተገዢ የሚያደርግ አሠራር ያለበት ወጥመድ በመዘርጋታቸው ነው፡፡ ስለሆነም ትውልዱ 'ሰው የፈለገውን የመልበስ መብት አለው፣ ካሻው ራቁቱንም ይሂድ፣ እኩልነት ሰው የፈለገውን እንዲያደርግ መተው ነው' የሚል አመለካከቶችን እንዲይዝ በታቀደለት መርብ ውስጥ ገብቶ ሲያበቃ ልምከርህ፤ ቆይ ላርምህ ብትለው ነፃነቱን እየነጠቀውና ከሥልጣኔ ዘመንም እያወጣኸው ይመስለዋል፡፡
<< ሰው የፈለገውን የመከተል መብት አለው! >> የሚለው የመመሪያ መፈክር(Slogan) ጀርባ ያለው የሚስጢር ማኅበራቱ አሳብ ምንድነው?
☞ እግዚአብሔር አምላክ በግድ የሚገዛና የሰው ልጆችን ነፃነት የሚያፍን አምባገንን አድርጎ ትውልዱን በፍልስፍናና ቲዎሪዎች በኩል ማሳመን
☞ የሰው ልጅ ከፈለገ ከሰይጣንም ጋር መግባባትና ለጋራ ሕልውና መሥራት ይችላል የሚል መናፍስታዊ እገዛዎችን ማሰልጠን
☞ የፈለከውን ተከተል በሚል የምርጫዎች ክፍተት ውስጥ ዲያቢሎሳዊ አማራጮችን በመሰግሰግና በማብዛት የአስተሳስብን አድማስ ወደግራ ግራው እንዲያዘንብል አቅጣጫ መቀየስ
☞ በሃይማኖትና በእውነታ መስመሮች በኩል ያሉትን የሰው ልጆችን መርሆች ከሰብአዊነት የተፈጥሮ ሕገ ልቦና ጋራ መሻርና መጣስ ደስታ የሚሰጥ ብሎም ነፃነትን የሚያጎናጽፍ እንደሆነ አድርጎ በተለያዩ መንገዶች በማሳየት የአዋቂነትና የመዘመን መግለጫ ሚዛን ውስጥ ደረጃ አሊያም ልኬት ማስቀመጥ
☞ ትውልዱን "አንተ ለራስህ አዋቂ ነህ" በሚል የማፍዠዣ ፖሮፖ ጋንዳ በማጥመቅ፤ ደጉንና ክፉውን በአእምሮና ልቦና ውስጥ ብቻ እንዲያውቃቸው የይስሙላ ትምህርት በመስጠት መሬት ላይ የሚወርደውና የሚተገበረው የርዮተ ዓለም ትምህርት፣ ጽንሰ ሐሳብ፣ ፍልስፍና እና የግኝቶች አስተንትኖት ክፋትን በተሸፋፈነ ሴራ የሚያስፈጽሙ እየሆኑና ገሚስ ደግነትን ለታይታ እንዲያሳዩ እየተደረጉ፤ መልካምና ደግ ነገራት ከአእምሮና ልቦና ውስጥ የማይወለዱና የቀሩ ሐሳቦች እያደረጉ ማጨንገፍ
ወገኖቼ የክርስቲያን ልብስ ምንድነው? " ነገር ግን ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን ልበሱት፤ ምኞቱንም እንዲፈጽም ለሥጋ አታስቡ።
" ነው የሚለው ወደ ሮሜ ሰዎች 13፥14 ላይ፡፡ ክርስቶስ የጸድቅ ልብሳችን ነው፡፡ ሥጋና ደሙን በምድር ትቶልን የሄደው እንደ ልብስ እናጠልቃቸው ዘንድ ነው፡፡ በውስጣችን እርሱ ይኖር ዘንድ ነው፡፡ አኛ በእርሱ እንኖር ዘንድ ነው፡፡
ዛሬ ክርስቲያኑ ምን ይለብሳል? አንገቱ ላይ መስቀል ያነገተው እንዴት ነው ገጽታው? በዚህ በዚህ ሙሲልም እህቶቻችን በንጽጽር የተሻሉ ጎበዞች ናቸው፡፡ በአብዛኛው ሃይማኖታቸውን ከሚወክል ታይታ ውጪ አይገለጹም፡፡ እንደው ዘመናዊ እንሁን ቢሉ እንኳ አጠማጠሟን እንደሚያደርጉ ያደርጓታል እንጂ የወጣ ነገር አይታይባቸውም፡፡ መስቀል ያደረገነውስ?
እንግዲህ ፋሽንና አለባበስ ላይ ርዕስ ስናነሣ ዋናው ተዋናዮች እህቶቻችን ናቸው፡፡
እስኪ እንዴት ነው ወጣት ሴቶች ምን ታስባላችሁ? አሁን ይሄን የአለባበስ ጉዳይ ከሕግ አንፃር ሲነገረን ማምለጫው እንጂ ማመኛው ላይ መንገድ አንፈልግም፡፡ ለዚህ ነው ደጋግሜ የሃይማኖት ጉዞ መነሻ የእግዚአብሔር ፍቅር መሆን አለበት የምለው፡፡ እስኪ ስለ ሁኔታው ከነፍሳችሁ ጋር አውሩበት፡፡ በአለባበስ ሁኔታችን አባት የሆነን እግዚአብሔር አምላክ ምን ይሰማዋል? ብለን ነፍሳችንን ስናወራ ምን ይሰማናል? ነገሩ ከውስጥ ካልቆረቆረን ከላይ ተደጋግሞ ብንሰበክም፣ ብንመከርም፣ ብንዘከርም አስቸጋሪ ነው፡፡ ስለዚህ እህቶቻችን እስኪ ትንፋሽ ውሰዱና አስቡበት፡፡ እውነቴን ነው የምላችሁ ውበት ሃይማኖት ነው፡፡ በዘመናዊነት ጫና መካከል የወደቃችሁ ወጣቶች ሁሉ በደንብ ልታስቡበት ይገባል፡፡ እናንተ የግዜዎች አይደላችሁም፡፡ ግዜ ሲበርደው የሚበርዳችሁ፣ ግዜ ሲሞቀው የሚሞቃችሁ፣ ግዜ ሲራቆት የምትራቆቱ፣ ግዜ ሲከናነብ የምትከናነቡ፣ ግዜ ሲደነግጥ የምትደነግጡ፣ ግዜ ሲረጋጋ የምትረጋጉ መሆን የለባችሁም፡፡ ዘላለማዊነት ከውስጣችሁ እንዳይወጣ ዕለት ተዕለት ጊዜያችሁን በአምልኮተ እግዚአብሔር እየባረካችሁ እና በቅዱስ ቁርባን ውስጥ ዘመናችሁን አሳርፉት እንጂ እንደ ዘመኑ አትሁኑ፡፡
(ወደ ኤፌሶን ሰዎች ምዕ. 5)
15፤ እንግዲህ እንደ ጥበበኞች እንጂ ጥበብ እንደሌላቸው ሳይሆን እንዴት እንድትመላለሱ በጥንቃቄ ተጠበቁ፤
16፤ ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁ።
17፤ ስለዚህ የጌታ ፈቃድ ምን እንደ ሆነ አስተውሉ እንጂ ሞኞች አትሁኑ።
ይቀጥላል..

0 Comments