የወሲብ ፊልምና ጠንቆቻቸው (ክፍል - 4)

 

ክፍል- 4

በስመ አብ፥ ወወልድ፥ ወመንፈስ ቅዱስ፥ አሐዱ አምላክ፥ አሜን፡፡

የወሲብ ፊልምና የመዝናኛው ኢንደስትሪ ተያያዥነት 

በክፍል ሦስት ትምህርታችን ለማንሣት እንደተሞከረው "የወሲብ ፊልሞችና የፋሽን ኢንደስትሪ በጣምራ እንዲጓዙ" የአያያዥነቱን ሚና መሣሪያ ሆኖ የተጫወተው የመዝናኛው ኢንደስትሪው ነው፡፡ አሁን እንዴት ማለት ነው፥ አንድ በሦስት ፈረሶች የሚጎተት ጋሪ ላይ ተቀምጦ የሚንቀሳቀሰን ሰው አስቡ፡ ግለሰቡ ፈረሶቹን ወደሚፈልግበት አቅጣጫ መንገድ በማስያዝ መሪ እየሆነ ወዳሻው ቦታ ይጓዛል፡፡ እንዲሁ ደግሞ ሦስቱን ኢንደስትሪዎች ማለትም የወሲብ ፊልሞችን ኢንደስትሪ፣ የፋሽን ኢንደስትሪ እና የመዝናኛ ኢንደስትሪን በጋራ አያይዞ በመጠቀም የመናፍስት ማኅበራቱ ትውልዱን ወደሚፈልጉበት አኗኗር፣ ሁኔታና የዘመን ገጽታ ለመምራት ችለውበታል፡፡ በዚህ አካሄድ ላይ ዲያቢሎሳዊ ቅኝቶችን እንደ ዓለም ትውልድ በሚገባ አስርጾ ለማስፈን እና የሚፈልጉት የዘመን ትውልድና የሕይወት ዘይቤ እንዲከሰት የሚከተሉትን ስልቶች ተጠቅመዋል፡፡

☞ የሥልጣኔ ዘውጎችን ጤናማ የውስጥ ትርጉማቸውን በማፋለስ፤ የሰው ልጅ ከተፈጠረበት መነሻ ዓላማ ኪሎ ሜትሮችን ርቆ አፍታ ቆም ብሎ ሳያገናዝብ እንዲጎዝ የዓለም ሩጫዎችን መድረሻ ግብ የሥጋ መሠረታዊ ፍላጎቶችን ማሟላት እንደሆነ ብቻ ስለማሳመን ሲሉ፥ በዘርፈ ብዙ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ታሪካዊና ነባራዊ ስዕሎች ውስጥ የሚፈልጉትን አድምቀው በተደጋጋሚ እያሳዩ በመሳብ፤ ተረጋግቶ የዓለም ነገራትን የመፈተሻ ጊዜን እያሳጡ የነፍስ ጥያቄዎችና የሃይማኖት እንድምታዎች የሚጨፈለቁበት ስርዓት መዘርጋት

☞ የሰው ልጆች ሰብአዊ ማንነታቸውን እስኪዘነጉ ድረስ ሌት ተቀን ለሥጋዊ ፍቃዶች ብቻ እንዲሮጡ ዓለምን እንደ ውድድር መድረክ አድርጎ በመቅረጽ፤ መሠረታዊ የእምነት መደንግጎች የሆኑት ፍቅርን፣ እምነትንና ተስፋን በተለያየ ዘዴ በመጉዳት፤ በምትኩ ጉልበት፣ ውበት፣ ገንዘብ፣ ዝና እና ሥልጣን የመኖር  መጀመሪያም መጨረሻም ማረፊያ ተልዕኮዎች እንደሆኑ አስመስሎ የሕይወትን ቅርጽ በሥጋዊ አተረጓጎም  ውስጥ ብቻ ለክቶ፤ የእምነትንና የባሕልን እሴቶች በየዘመኑ መድምሰስ

☞ የሕሊና፣ የልቦና እና የነፍስ ሰማያዊ ፍቃዶች በተፈጥሮም በሥጋ ስሜቶች የተከለሉ በመሆናቸው፤ እነዚህ መንፈሳዊ ፍቃዶች ወደ ውጪ እንዳይገለጡና ሥጋን እንዳይገዙ ለመቆጣጠር፤ የሥጋ ምቾቶችን የሚያገዝፉ እንዲሁም የሚያስጠብቁ የተብለጨለጩ ስብከቶችን እና ሽልማቶችን ከፊት እያስቀደሙ በማስቀመጥ፤ ፍላጎቶች ሁሉ ተመሳሳይ የሥጋ ዝንባሌ እንዲንጸባረቅባቸው መናፍስታዊ አዚሞችን በመጠቀም የትውልድን የጊዜ መስመር ከመነሻው፣ ከመካከሉ እና ከመድረሻውም ላይ እየሆኑ መቆጣጠር

☞ የሃይማኖትን ኃይልና መንገድ እንደ ጭቆና ቆጥሮ በማስቆጠር፤ የእምነት አካሄዶች የነጻነት ብዝበዛ ተጽዕኖ አሳዳሪዎች እንደሆኑ በተለያዩ ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ ገለጻዎች ለዓለም በማድረስ፤ ለታሪካዊ ብሎም ለነባራዊ የሕብረተሰብ ችግሮች መንስኤ ናቸው በማለት ተጠያቂነትን ከፈጠሩ በኋላ፤ የሃይማኖት ፋይዳዎችና ጉዞዎችን ማቃለል፣ ማሳደድና ማጥፋት

☞ የፋሽን አልባሳትንና የአካል ተክለ ቁመና ውበትን በፉክክር መልኩ በማቅረብ፤ መገላለጥና መራቆት እንዲሁም የተዛነፈ አለባበስንና ገጽታን መጠቀም እንደ ልዩ የዘመናዊነት መታያ አድርጎ፤ እርቃንን እንደ ትልቅ ጀብዱና ዝና በመቁጠር፤ ለኃጢአት ማደግና ለመቅሰፍት መብዛት ምክንያት መሆኑን ሰው እንዳይረዳ አድርጎ ትውልዱን የፋሽን ምርኮኛ ማድረግ

☞ የማኅበራዊ ድረገጾችን፣ የመገናኛ አውታሮችን፣ የፊልም እና የሙዚቃ ኢንደስትሪዎችን ከሥር ከመሠረቱ በመቆጣጠር፤ በሰዎች ውስጥ ያሉትን መናፍስት ለክፋት አንድነት እንዲተባበሩ የማቀናጂያ ትስስሮሾችን በማመቻቸት፤ ርኩሰት እንዲያይል፣ አመፃ እንዲስፋፋ፣ እርግማን እንዲጸና፣ ሐሰት እንዲበራከት፣ እምነት እንዲሰናከል የማዳከሚያ ዕድሎችን በመጨመር ዘመኑን ከነፍስ ወከፍ አንስቶ በሰይጣናዊ አገዛዝ ሥር መጣል

☞ የሰው ልጆች በአእምሮ አመዛዛኝነትና በሕሊና ፍረደኛነት ነገሮችን እንዳያስተውሉ ስሜታዊነትን እንደ ደስታ መሸመቻ እንዲሁም ማንጸባረቂያነት በማድረግ፤ አስፈላጊ የኑሮ ግንኙነቶችንና ግንባታዎችን በአጥፊ መናፍስት መሪነት ሥር የወደቁ አጋጣሚ የሚመስሉ ሁነቶች ላይ እንዲጀምራቸው የተለያዩ የፌዝ፣ የቲዎሪና የፍልስፍና ጽንሰ ሐሳቦችን በመዝናኛ ማዕከላት በኩል በገፍ በማሰራጨት፤ አጢኖ የማስተዋልንና የሚመጣውን አሻግሮ የመመርመርን መንፈሳዊ ኃይል በማድከም፤ ስለቅርብ ቅርቡ ክስተቶች ብቻ እንዲኖሩ በውጪያዊ ግፊት ውስጥን ማጨለም

ዓለምን በአንድ ማዕከላዊነት ለመጠቅለል ከሚያገለግሉ ታላላቅ መሣሪያዎች መካከል አንደኛው የሆነው የመዝናኛው ኢንደስትሪ፥ በተለይም ዛሬ ዛሬ ተጽዕኖው እጅግ ሥር የሰደደና የአጥፊዎቹን የርኩሰት ኃይሎች ለጥፋት የሚውልን ድካም  ያቀለለ፤ በአያያዥ ሰፊ አድማስነቱ በኩልም ብዙ የኃጢአት ሥራዎችን እንዲያከናውኑ መንገድ የሆነ ተቋም መሆንን ችሏል፡፡

በዛሬይቱ ዘመን ላይ ደግሞ የመዝናኛ ኢንደስትሪዎች ጫናና ስርጭት በብዙ የአኗኗር አቅጣጫዎች ላይ ተገኝቶ የአሁኑን ትውልድ ጉዞ መሪ መሆን የቻለ፤ በአቋሙ ግንባታ ውስጥም ሰርጎ ገብቶ ወደ ውጪያዊ ገጽታ ሊያውም እንደሚያኮራ ሆኖ እየተገለጠ ያለ፤ በቋንቋና ማንነት ላይም የራሱን አሻራ ያለ ብዙ አድካሚ ውጣ ውረድ ማኖር የቻለ በመሆኑ፤ ይህንን ተከትሎ የዘመኑ ወጣቶች ኑሮና ሕይወት ምን መልክ ያዘ ስንል የሚከተሉትን እናገኛለን፡፡

❖ በሚታየው የመዝናኛ ኢንደስትሪ ውስጥ ባሉት የፊት ገጽ አርቲስቶችና ፊት አውራሪዎች አማካኝነት የሚሰጠውን የንግግር፣ የአለባበስና የአኗኗር ልማዶችን ሳይጨምር ሳይቀንስ ወደራሱ ማንነት ያንጸባረቀ ሲሆን ታዲያ፤ አሁን  አርቲስቶቹ ሲንጨባረሩ ትውልዳችንም ይንጨባረራል፣ ጠምዛዦቹ ሲራቁቱ ትውልዳችንም ይራቆታል፣ ፊት አውራሪዎቹ ሰላምታቸው ስድብ አዘል ሲሆን እዚህም እኛም ጋር ጸያፍ ቃላት "ደህና አደርክ?"ን ተክተዋል፡፡

❖ አብዛኛዎቹ በመዝናኛው ማዕከላት የሚንጸባረቁት የታይታ ገጽታዎች ሥጋዊ ምቾቶችን የሚያሳዩና ነጻነት መሰል መረን የለቀቁ አንዳንዴም ግልጽ እብደቶችን የሚወክሉ ናቸውና፤ ትውልዳችንም ይህንን የሥጋ ምቾት ለመቀዳጀትና በእንጀራ ብቻ የተመሠረተ ኑሮን ለመገንባት ሲል እርስ በእርሱ በዘመናዊነት ልኬት የሚወዳደር፣ በኢኮኖሚ ደረጃዎች ለመበላለጥ የሚውተረተር፣ ከፊት ፊት ቀድሞ ለመታየት በሚደረገው ጥረት ውስጥ እርስ በእርሱ ከውስጥ የተገፋፋ፤ አንድነትና መተባበር የራቀው ዜጋ ሆነና ቁጭ አለ፡፡

❖ በተጨማሪ ሃይማኖታዊ እውነታዎችን፣ አገረሰባዊ ባሕሎችንና ቤተሰባዊ መስተጋብሮችን የሚንቅ፤ በሥልጡንነት ጓዳና ላይ ለመጓዝ የእምነት ጫናዎችን እንደ ጎታች ተጽዕኖ የሚቆጥር፤ ወደፊት መሄድ ማለት የኋላውን መናድና በእርሱ ቦታ አዲሱን ተክቶ መራመድ የሚመስለው፤ ነገራትን ሁሉ ከሥጋ ፍቃድና ዓይን ብቻ የሚለካ፥ ግራ ግብት ያለው፥ መንፈሳዊ ሞገሱን የማያውቅ፣ ጸጋና ራእዩን ያጣ፣ የአባቶቹን የታሪክ ፈለግ ማግኘት የተሣነው፣ ለውሳኔ የሚቸገርና ሁልጊዜ የድካም ስሜት ያልተለየው ትውልድ ሆነን፤ እንዳደረጉን የምንሆን መሞከሪያ አሻንጉሊቶች በመሆን ሰማያዊ ኃይል ርቆን እንባትታለን፡፡

✞ የመዝናኘው ኢንደስትሪና የወሲባዊ ፊልሞች ኢንደስትሪ ተደጋጋፊነት ✞

የእነዚህ ሁለቱ ኢንደስትሪዎች የመጀመሪያው የመጣመሪያ አሪቡናቸው፥ ሁለቱም የመዝናኛ አውታር ተቋማት ተደርገው እንዲታሰቡ በተደረጉበት መተሳሰሪያው ላይ ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ለምድር ፍጥረታት ባርኮና ቀድሶ የሰጠው የጾታ ግንኙነት፤ ዛሬ በተገኘንበት ዘመን ራሱን የቻለ የርኩሰት መዝናኛ ሊሆን ችሏል፡፡ በአዳምና ሔዋን በኩል የተሰጠው የቡራኬ ኃይል፥ በአጥፉ መናፍስቶች አማካኝነት በአመንዝራነት ጎኑ የተተረጎመ በመሆኑ፤ ከብዙ ሰዎች ጋር ግንኙነት መፈጸም እንደ ብዙ መዝናናት የታየ ሆኖ ለክፋት ሠራዊት የእርግማን መግለጫ የሚሆን የዝሙት ድሪቶን ዘመኑ ተከናንቦ ቁጭ ብሏል፡፡ 

የወሲብ ፊልሞች ጥገኝነት እንዲጨምር የፋሽን ኢንደስትሪዎች የማርገብገቢያውን የውጪ ገጽታ የቡዳ መናፍስትን እያዋረሱ ምርቶችን ሲያቀርቡ፤ ጎትቶ የማምጫውን ሥራ ደግሞ የስብከቱን ክፍል የሚያከናውነው የመዝናኛው ማዕከል ነው፡፡

ካለፉት 100 ዓመታት ወዲህ የይዘታቸው ቅርጽና ሁኔታ ወሲባዊ ቃናዎችን የሚይይዝ የፊልም፣ የሙዚቃና የተለያዩ የመድረክ ዝግጅቶች ተስፋፍተው መጥተዋል፡፡ ግለሰቦች በዝሙት ፊልሞች ማዕበል ሰምጠው ባይገኙ እንኳን፤ በነዚህ የመዝናኛ ዘርፎች በኩል "አልሸሹም ዘወር አሉ" የሚያሰኙ ሩካቤያዊ ገጽታዎች፣ ራቁት መልኮች፣ ወሲባዊ ትዕይንቶችና ቃላቶች፣ የስሜት ንዳድን የሚፈጥሩ ታሪኮችና ምልክቶች እየተዘጋጁ ስለሚተላለፉ፤ የወጣቱና የጎልማሳው ክፍለ ዘመን ትውልድ የሆነው የዛሬ ዘመን፥ በሚለቀቁት የመዝናኛ መልዕክቶች አቅሉን ስቶ ሲገኝ፥ አሁን አሁን በቃ ወሲባዊ ጉዳዮች የማይነሡበት የኑሮ ዘርፍ እየቀነሰ መጣ፡፡

የኛም አገር የጋሸበው ትውልድ በዘመናዊነት ካባ ተጀቡኖ አድርግ የተባለው የሥልጡንነት ፍቃዶች በውዴታ ግዴታ ከገባበት በኋላ አሁን ግዴታው ውዴታ ሆኖበት ይሰቃያል፡፡ እዚህም በኛም አገር የሚለቀቁ የመዝናኛ መልዕክቶች ከጊዜያት በኋላ ልክ እንደፈረንጆቹ ለመሆን በብዙ የደከመ ሲሆን፤ አንዳች ዝሙታዊ ምልክት አሊያ ገጽታ መጠቀም ልክ ወጥ ውስጥ እንደሚቀላቀል ማጣፈጫ ጨው የግዴታ አስፈላጊ መስሎ እስከተቀረጸበት ጥጉ ድረስ ግራ ዘመም ሆነን ስንገኝ ያው ቢቸግር ነንና አይገባንም፡፡ 

ወጣቶች በልጅነት ጊዜያቸው በዐርባና በሰማንያ የተጠመቋት የጥምቀት የሙሽራነት ልብስ ለዕድሜ ዘመን ተከትሎ የሚቆይ በመሆኑ፤ ከነፍስ ፈቃዳቸው የተጣረሱ የእነዚህ ኢንደስትሪዎች መግለጫ ሲሆኑ በውስጣዊ ማንነታቸው ይረበሻሉ፡፡ ነገር ግን ብዙሃኑ እንደሆነው መሆን ነው የሚለውን የዲያቢሎስ አገዛዙን የሚያበልጽግ አስተሳሰብ ስላለ፤ ተያይዞ መጥፋት አማራጭ ተደርጎ ለብዙ ዘመናት ሐሰት በእውነት ቦታ ተሰይማ ስትመራ ስለቆየች፤ ከመከራ ጋር መኖር ፋንታችን ነው፡፡

ኢሉሚናቲ እና መሰል የመናፍስቱ ማኅበራት በተቀዳሚ ራእይና ተልዕኮ ሃይማኖትን ለይቶ ማጥቃት የሚል አጀንዳ ስላላቸው፤ በመዝናኛ ማዕከሎቻቸው በኩል የሚያሰራጩት መልዕክቶች የዲያቢሎስን ፍላጎት የሚያስፈጽሙ፣ የሥጋ ፍቃድን አግዝፈው የነፍስ ጩኸትን የሚያፍኑ፣ ሰማያዊ አኗኗርን ከሕይወት መስመር ላይ አሽሽተው በሚታይ ነገር ላይ ብቻ ጊዜን የሚያስመረኩዙ መልዕክቶች በመሆናቸው፤ እውነትም ታዲያ ትውልዳችን ከእምነት እሴቶች ተለይቶ በዝሙት መናፍስት ታስሮ ለየግል ለየግሉ የሚያለቅስ ቢሆን የሚያስገርም አይሆንም፡፡ 

ቡዳ የሚሆኑ መናፍስት ግዴታ ከሰው ላይ ብቻ ተነስተው አይመጡም፡፡ እንደነዚህ የርኩሰት መዝናኛ መንገዶችን ድልድይ በማድረግ በቀላሉ በማየት ብቻ ይዋረሳሉ፡፡ ለዚህ ነው ተዋናዮቹ ሲራቆቱ እዚህም ትውልዳችን የሚራቆተው፡፡ የሚያየውን ነገር ከውስጥ ያለው አጥፊ መንፈስ ወደ ውጪም እንዲገልጠው ዘመኑን፣ ሥልጣኔውንና የኢኮኖሚ አቅም አንጸባራቂነቱን እየነጠለ አስውቦ ስለሚያሳየው፤ ሰውየው ባየው ነገር ላይ ራሱን ለማግኘት ዕድል ብቻ የሚጠብቅ ይሆናል፡፡

ይሄ የመናፍስቱ ውስጣዊ ጫና ሁለቱን ኢንደስትሪዎች ተመጋጋቢ ያደረጋቸው በመሆኑ፤ የሩካቤ ትዕይንቶች የበዙበትን ፊልሞችና ሙዚቃዎች የተከተለው ወጣት፤ መድረሻው የወሲብ ፊልም ጥገኝነት ላይ ነው፡፡ ፊልሙ አሊያ ሙዚቃው ላይ በጨረፍታ የሚያሳዩት የዝሙት እንቅስቃሴዎች፤ ከውስጥ ላለው ዓይነጥላ የወሲብ ስሜትን በጫና ለመፍጠር ጥሩ ጉልበት ስለሚሆነው፤ በጨረፍታ አሊያም በከፊል ያየውን የሩካቤ እይታ በሙሉ አድማስ እንዲመለከተው ገፋፍቶ ገፋፍቶ የወሲብ ፊልሙን እንዲያይ የልቦናውን ኃይል እያስጨነቀ ይመራዋል፡፡ እንኪያስ ብዙ የተበላሹ የመዝናኛ መልዕክቶችን ወደ ውስጥህ ባስገባህ ቁጥር፤ ከውጪ ቡዳ ሆነው የሚዋረሱትና ከውስጥ የእስራት አዚም ለመሆን የሚጠባበቁት መናፍስት፤ በምታየው ልክ መጥፊያውን አበጅተው የግል ዝሙት ቁራኛ አድርገው ያሰቃዩሃል፡፡

ስለዚህ ምን ይሻላል? ክርስቲያንም ሆነን አረማዊም ሆነን እንኖር ዘንድ እንደምን ይቻለናል? አሁን አንደኛው ፈተና የሆነብን ጉዳይ እኮ ዛሬ ዛሬ መንፈሳዊነትን ከአረማዊነት አግባብቶ ለመያዝ በሚደረገው ትግል ውስጥ ቢነግሩት የማይሰማ፣ ቢመክሩት የማይገሰጽ፣ ቢቀሰቅሱት የማይነቃ፣ ቢለምኑት የማይቀበል ሞገደኛ ጠባያትንና የውስጥ አመልን አበልጽገን ይዘን፤ በጎ ሲነገረን፣ ስናይ እና ሲደረግ አይስማማንም፡፡ ቢስማማንም አንሳተፍም፡፡ ራቅ ብለን እናያለን፡፡ ከሩቅ በመመልከታችን ክፍተት ውስጥ ታዛቢ ስንሆን፤ ለማፍረስ የሚቸኩል ስብዕና፣ ለመተቸት የሚሮጥ ቋንቋ፣ ለመጣል የሚሮጡ እግሮች፣ ለመገፍተር የሚፋጠኑ እጆች የመያዝ አዝማሚያዎችን እንደ ጋራ ጠባይ ስናስተናግድ ለምን ብለን አንጠይቅም፡፡ ታዲያ እንዴት ነው ነገሩ? ለምንድነው የምንደበላለቀው? ለምንድነው ረግቶ መቆየት የተሣነን?

ብዙ ቦታዎች ላይ መንፈሳዊ አቋማችን እየሄደ የሚቋረጥበት ምክንያት ይሄ ነው፡፡ መንፈሳዊነትን ከአረማዊነትን ጋር አንድ ላይ ተሸክመን ለማቆየት ስለምንጥር፡፡ መዝሙርንና ሙዚቃን ለማግባባት ስለምንጥር፡፡ የተቀደደ ጅንስንና ነጠላን ለማጣመር ስለምንሞክር፡፡ ፍቅረ ንዋይን ከፍቅረ መለኮት ጋር ለማቻቻል ስለምንዳክር፡፡ ውስጣዊ መረጋጋትን ለምቾት መቸኮል ጋር ደባልቀን ስለያዝን፡፡ ታዲያ እንዴት ይሁን? በአገራችን የሚነገር አባባል አለ፡፡ "ሁለት እግር አለኝ ተብሎ ሁለት ዛፍ አይወጣም" የሚል፡፡ እኛም ሁለት ገጽ አለን አንዱ መንፈሳዊ አንዱ አረማዊ ብለን እንኖር ዘንድ አንችልም፡፡

ነጭ አርጎ የሰጠን ላይ ጥቁር እየለወስንበት፣ በጎ ቃልን እንድንናገር የከፈተልንን አንደበት ነገርና ክፋትን ጨምረን አሰልጥነን ይዘን፣ ፍቅራችን ውስጥ ጥላቻ፣ እውቀታችን ውስጥ ምቀኝነት፣ ገንዘባችን ውስጥ ግፈኝነት፣ ምገሳችን ውስጥ አመፀኝነት፣ ችሎታችን ውስጥ ጨቋኝነት፣ ጸጋችን ውስጥ ተንኮለኝነት፣ ጥበባችን ውስጥ አጥፊነት #አቀላቅለን ይዘን ለሌላውም ስናቀርበው ይህንኑ የተደባለቀ ባቢሎንነትን ከትውልድ ትውልድ፤ ከዘመን ዘመን እያሸጋገርን አምጥተን የምንጓዝበት ጓዳና ሁሉ ወደ መከነው እያደረሰን፤ አንዱን ስንለው አንዱ፣ ተስተካከለም ስንለው እየተደመሰሰ፣ ጠራ ስንል እየደፈረሰ፣ አማረበት ሰንል እየጠወለገ ግልብጥብጡ የወጣ ዘመንና አኗኗር ላይ መቆማችንን ስንመለከት በእርግጥም ሳንጠራጠር 'መካን በዘመኑ ሁሉ የማይከናወንለት ሰው ብለህ ጻፍ' የሚለው የነብዩ ኤርሚያስ ትንቢት የኛ ገጽታ እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡ 

ስለዚህ ምን ይሻለናል? እንዴት ነው ነገሩ? ምን እንወስን? 


ይቀጥላል..


Post a Comment

0 Comments