ክፍል - 5
በስመ አብ፥ ወወልድ፥ ወመንፈስ ቅዱስ፥ አሐዱ አምላክ፥ አሜን
የወሲብ ፊልምና ከእምነት መሸሽ
ወደ ሕይወታችን ውስጥ በተለያየ መንገድ የሚገቡ መረጃዎች፣ መርሆች እና አሳቦች ውስጣችን በመከማቸት የኑሮአችንን አቅጣጫና ሂደት የሚወስኑበት አጋጣሚ ሰፊ ነው፡፡ በዚህም መሠረት የምናየው እይታ፣ የምንሰማው ድምፅ፣ የምናስበው አሳብ፣ የምንውልበት ቦታ፣ የለመድነው ልማድ የሕይወታችንን ቀጣይ ጊዜ ዕድሉ ላይ የመወሰን ድርሻ ሲኖር፤ ወደ ውስጥ የሚገባው ጉዳይ ወደ ውጪም በተገለጠ ጊዜ ያንኑ የገባውን ነገር በሁኔታውና በጊዜው ክስተት ልክ የሚያንጸባርቅ ይሆናል፡፡
እንግዲያው፥ ወደ ውስጣችን ርኩሰት ሲገባ ወደ ውጪም የረከሰው ነገር ይገለጣል፡፡ ወደ ውስጣችን ክፋት ሲያድር ወደ ውጪም ያው ክፋት እየተገለጠ ይወጣል፡፡ ወደ ውስጣችን መርገም በዘለቀ ጊዜ ወደ ውጪኛው ክፍልም እርግማን የመቆየት ኃይሉ የጸና ይሆናል፡፡ ይህንን የሕይወት ጉዞ አሠራር ጠንቅቀው የሚያውቁት መናፍስት፤ የሚታገሉንም ቦታ እዚህኛው እውነት ላይ ይሆናል፡፡ ወደ ውስጣችን አመፃን ለማኖር፣ ርኩሰትን ለማንገስ፣ ጥፋትን ለማኖር፣ እኩይነትን ለመጀመር፣ ጋጠወጥነትን ለማሰልጠን፣ ቂምና ግፍን ለማስተማር በተለያየ መልኩና መስመር ከውጪ ወደ ውስጣችን ኃጢአትን ለማስገባት ይጥራሉ፡፡ ከነዚህ ከውጪ ወደ ውስጥ ከሚገቡት የመናፍስት መሣሪያዎች መካከል ዋና ዋናዎቹ ፊልሞች፣ ሙዚቃዎች፣ ጽሑፎችና ሥልጠናዎች ናቸው፡፡
የወሲብ ፊልሞችም ከመነሻው ሲመሠረቱ ተቀዳሚ ዓላማቸው ርኩሰትን ከፍ ለማድረግና የዝሙት ኃይልን በትውልድ አኗኗር መካከል ለማስፈን ሲሆን፤ በዚህም ተልዕኮዋቸው በጋሸበው ትውልድ አለማወቅና ለማወቅም አለመፈለግ ምክንያት በተገባ ተሳክቶላቸው ሲገኙ፤ ዘመኑ ወደ ማብቂያው መድረሻ ላይ የሚደርስበትን መግለጫዎች ገጽታው አድርጎ፤ የእምነት እውነታና ታሪክ እየተናቀ፣ እየተገፋ፣ እየተጨቆነ፣ አማራጭ እየተደረገ፣ በሌላ እየተተካ ስለቆየ፤ ዛሬ ላይ በቃ ከ"አቤቱ አድነኝ" ጸሎት ውጪም ሌላ ጩኸት ማሰማት መፍትሔ እስከማይሆንበት ድረስ ዓለምና ዜጓቿ በአንድነት የመጥፋት ዕጣ ውስጥ ውደቀን አስጨናቂ ጊዜ፣ አስጨናቂ ኑሮ፣ አስጨናቂ ዘመን ላይ ተገኝተን በብዙ የሕይወት መንገዶች ላይ ፈራ ተባ እያልን እንድንመላለስ ይኸውና ተገደን ቁጭ ብለናል፡፡ እግዚአብሔር ይማረን፡፡
በዝሙት መናፍስት የእስራት ኃይል ልብና ጊዜያችን የታሰረ ሲሆን፤ ወደ እምነት አምባዎች ለመጠጋት የምናደርገው የተሰካ ለመሆን እንዳይችል ገና ከመነሻው ላይ ፍላጎት በማጣት እና በመረበሽ ምክንያት ከባድ ይሆናል፡፡ የወሲብ ገጽታዎች፣ ቋንቋዎች፣ ድምፆችና ንባቦች ወደ ውስጣችን ገብተው፤ የመናፍስቱ አዚማዊ የሩካቤ ይዘት ያለው ቅርጽ ከሕሊናችን ላይ ስለሚታተሙ፤ ከውጪ ወደ ውስጥ የምናስተናግደው የእምነት አካሄድና መንፈሳዊ ምግባራትን ለመሸሽ እንገደዳለን፡፡ በቃ ይሄ ግልጽ ጉዳይ ነው፡፡ የወሲብ ፊልሞችን አይተህ ስለጸሎት ስታስብ ራስን በመውቀስ የአጥፊዎቹ ስልት አማካኝነት ከሃይማኖት መሸሸ የሚጠበቀው ውጤት ነው፡፡ የወሲብ ጽሑፎችን አንብበህ ስለ ስግደት ስታስብ ራስን እንደ ኃጢአተኛ በመቁጠር የቁጭት ስሜት ምክንያት ከሰማያዊ የቅድስና ልምምድ መራቅ መፈለግ ሊከሰት የሚችል ግዴታ ነው፡፡
ከመነሻው የክፉዎቹ ባለህቡዕ ማኅበራትም ፍላጎትና እቅድ ይኸው ነው፡፡ መዝናኛ በሚመስሉ የአእምሮና የነፍስ ማስከሪያዎችን በመጠቀም፤ ከእምነት ኃይል የመሸሽ ነገር ከእያንዳንዱ ሰው ላይ በነፍስ ወከፍ ለቀማ ሽሽቱ የበለጸገ አቅም እንዲያገኝ አድርገው፤ ማሕበራዊ እሴትን መደምሰስ፣ የአባቶችን የሃይማኖት ታሪክና ቃልኪዳን ማዛነፍ ከዛ ማስካድ፣ የሕሊና ዝቅጠትን መጨመር፣ የሥነ ምግባር ክስረትን በማጽደቅ ዓለምአቀፋዊ አጀንዳዎችን ማስፈጸም ሌት ተቀን ለማሳካት የሚጥሩለት ጥልቅ ግባቸው ነው፡፡
በዚህ ዘመን አጥፊው መንፈስ ግብረ-ገብነትን አጥፍቶ፤ የጾታ ነፃነትን ለዘመናዊው ትውልድ መብትህና ነፃነትህ ነው በማለት፤ በወሲብ ፍላጎት ትምህርት፤ የወንድ ለወንድ፣ የሴት ለሴት ጋብቻን መልክ እንዲኖረው በማገዝና በማበረታታት የስሜት ሥነ ልቦናን በሚያነቀቁና ጋጠወጥነትን በሚያደራጁ ሰዎች በመታገዝ፤ የክርስትናን የሥነ ምግባር ሥርዓት በማፋለስና በማርከስ ፈጣን የትውልድ ርኩሰትን አስፋፍቷል፡፡
የእምነትን መንገድ ለማሰናከልና የሰው ልጆችን ከሃይማኖት ለማራቅ ዲያቢሎስ ከሚጠቀምባቸው የስምሪት መንገዶች ውስጥ አንደኛውና ርኩሰቱን ከሚገለጥበት ግብሮች ውስጥ በዛሬ ዘመን ሰፊውን አድማስ የያዘው፤ የሰዎች ልጆች በአዳምና ሔዋን በኩል ከሕያው እግዚአብሔር የታደላቸው የሩካቤ-ሥጋን የተቀደሰ የአንድነት ትዳር የቡራኬ ሕይወት በመጠቀም ወደራሱ የግራ ዘመምነት መሣሪያ አድርጎ የመለወጥ የክፋት አሠራሩ ነው፡፡ ይህንን ተባርኮ የተሰጠውን የእግዚአብሔር ስጦታ ዲያቢሎስ በመለወጥ ወደ "ዝሙት አመፃ" ይቀይረዋል፡፡
ከዲያቢሎስ አሠራር ውስጥ ዋነኛና መሠረታዊ አካሄዱ ነገሮችን #የመለወጥ ስልቱ ነው፡፡ ከቅድስና ወደ ርኩሰት፣ ከሰላም ወደ ብጥብጥ፣ ከፍቅር ወደ ጥላቻ፣ ከመተባበር ወደ መለያየት፣ ከመሰማማት ወደ መደናቆር፡፡ የዲያቢሎስ ዓላማ ይህ ነው፡፡ በመጀመሪያ ማጥመም፥ በሁለተኛው መለወጥ፡፡ ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ ተወልዶ ሲዛመደን፤ ጠላት ደሞ ከማኅፀን ጀምሮ በመቆራኘት አብሮ በመወለድ ዛር እየሆነ ከሚጠብቀን የበረከትና የቅድስና ሕይወት ለማስወጣት ይሞክራል፡፡ አባቶቻችን መቁጠሪያን ይዘው የቆዩበትን ዘመንና አኗኗር ለውጦ ጨሌ ያሲይዛል፡፡ ቀደምት ሌላውን ለማንሳት የሚሯሯጡበትን የታሪክ እውነታ ደምስሶ እርስ በእርሳችን የመተባተብ፣ የመገፋፋትና የመነቃቀል ታሪክ እንዲኖረን ይለውጠናል፡፡ በቁርባንና በስግደት ውስጥ የቆዩ አገልጋዮችን ለውጦ የአሉባልታ ወሬና ዘረኝነትን በተሞሉ፣ ቃሉ እንደዚህ ይላል ብለው በሚቀመጡ፣ የቤተክርስቲያንን ክብርና ልዕልና ከልባቸው ባራቁ አጋልጋዮች ይተካቸዋል፡፡ ዲያቢሎስ አንዴ ልብህና ቤትህ ውስጥ ከገባ በኃላ እንደቀደመው መኖር አይታሰብም፡፡ አሁን አንዳንዶቻችን ድሮ'ኮ አስቀዳሽ ነበርኩ አሁን ምን እንደነካኝ እንጃ ቤተክርስቲያንም ከሄድኩ ዓመት ሞላኝ እንላለን፡፡ በፊት ሰንበት እንኳን እሳለማለሁ አሁን በደጁም ማለፍ ትቻለሁ እንላለን፡፡ እምነቴ ላይ ጎበዝ ነበርኩ፣ ትምህርቴ ላይ ጎበዝ ነበርኩ፣ በሥራዬ ታታሪ ነበርኩ፣ ቤተሰቤ ጋር ፍቅር ነበረኝ ሰላም ነበረኝ፣ ትዳሬ ሰላምና ጸጋ የሞላው ነበረ፣ ገንዘቤ በረከት ያለውና የሚተርፍም ነበረ፣ ፈጣንና ተደማጭ ነበርኩ፣ ብዙ ደስታና ጓደኞች ነበሩኝ እንላለን፡፡ ዛሬ ምን እንደነካኝ በቃ እንደበፊቱ የሆነልኝ የለም፡፡ ጊዜው ሲሄድ እየተበላሸሁ መጣሁ፡፡ ሕይወት ከበደኝ እንላለን፡፡ የብዙዎቻችን አሳቦችና ድምፆች እንደዚህ ሆነዋል፡፡ ለምን? ዲያቢሎስ ወድቋላ፡፡ ዘሬ ብሎ ዛር ሆኖ ቁጭ ብሏል፡፡ አብሮ ተወልዶ አብሮ አድጓል፡፡ ወደ መጥፎው የመለወጥ ጉዞ ውስጥ የክፉ መናፍስት ወጥመድ የቱን ያህል በተወሳሰበና በተሰወረ መልኩ እንደተዘረጋ ብዙዎቻችን አንረዳም፡፡
በዚህም የመለወጥ የጥፋት አሠራር ሂደት ላይም በመቆም፤ የወሲብ ፊልሞችን ኢንደስትሪዎች በመጠቀም፤ ክፉ መንፈስ የእምነት ምሪትና ሰማያዊ ጉዞ ከወየበበት ለሥጋ ስሜት ብቻ ከምንኖርበት ሕይወት ውስጥ ለመዝፈቅ መረቡን በሰፊው የኢንተርኔትና የመዝናኛው ምኅዋር ላይ ጥሎ ተጠማጆችን በየጊዜው እየጨመረ ይገኛል፡፡

0 Comments