የወሲብ ፊልምና ጠንቆቻቸው (ክፍል - 6)


በስመ አብ፥ ወወልድ፥ ወመንፈስ ቅዱስ፥ አሐዱ አምላክ፥ አሜን፡፡

የወሲብ ፊልም ለአስገድዶ መድፈር ያለው ተጽዕኖ

በተደጋጋሚ እንደገለጽሁት የወሲብ ፊልም በተለይ በዚህ ክፍለ ዘመን ትውልድ ላይ ያሳረፉት ስውርም ሆነ ግልጽ መናፍስታዊ ጫና በሚገባ ባለመመርመሩና ባለመጠናቱ እንጂ፤ ያስከተሉት አይነተ ብዙ ቀላልና ውስብስብ ጥልቅ ችግሮች የተለያዩ መከራዎች እንዲከሰቱ መነሻ ምክንያቶች ሆነው፤ የትውልዱን ገሚስ የሕልውና፣ የስነልቦና፣ የሃይማኖት እና የሞራል ሥነ ምግባረ ሕይወት በእጅጉ ፈትነው አደጋም ላይ ጥለውት ሲገኙ፤ በጥገኝነት የቁራኛ አዚም ውስጥ ጠፍንገው በማሰር በስሜት ግፊት በኩል እያንደረደሩ ለሰፋፊ ማሕበረሰባዊ ውደመቶች እንዲሁም ዘግናኝ የወንጀል ድርጊቶች ውጤት እየሆኑ በገሐድ ቢስተዋሉም፤ አብዛኞቻችን ዛሬም ጥሬዋን በምትታየን የዓለም ውዥንብር ውስጥ ገና ሳንነቃ በሰመመን መካከል የተዋጠ እንቅልፍ ጭልጥ ብለን በቁም ተኝተን፥ ራሳችን፣ ቤተሰቦቻችን፣ ልጆቻችንና ወዳጆቻችንን ጨምሮ አንድ በአንድ በዲያቢሎሳዊ ወጥመድ ተይዘን ስንማቅቅ የቆየን በመሆናችን፤ የመናፍስት አገዛዝንና ፈተናን እንደ አንድ የኑሮ ክፍል በአኗኗሪነት ለምደነው፤ የጋራ ፍዳችንም በመናፍስቱ አጥፊነትና መጠነ ሰፊ የጀርባ አጥቂነት በፍጥነት ተስፋፍቶ እንደ አገርም ብዙ ታሪካዊ ቁስለቶችን አሻራ እያደረገ ለሚመጣው ትውልድ እያስቀረ እንደሆነ ልናጤን ያስፈልገን ነበረ፡፡

ከወሲብ ፊልሞች የአፈዝ አደንግዝ ዲያቢሎሳዊ የዓላማ ግቦች መካከል በሚስጢር ማኅበራቱ እቅድ ተካተው እንዲጠፉ የተፈለጉት የሥነ ምግባር መሠረቶች፣ የሃይማኖት የጽድቅ ምግባሮችና የቅዱስ መንፈስ ፍሬዎች በዋናነት ሲሆኑ በተጓዳኙ ደሞ እንዲበራከቱ የተፈለጉት የዝሙተኝነት ገጽታዎች፣ የወንጀል ክንውኖች፣ የርኩሰትና የእርግማን ሥራዎች፥ ዛሬ ላይ የትውልዳችን የየዕለት ዜና 'ሪፖሮቶች' መሆናቸውን ስንመለከት፤ ሕይወታችን ከኋላው የአተላ ታሪክ እንዲይዝ ለዘመናት በህቡዕም በግልጽም ሲፋለም የቆየው ጠላት ዕድላችንን ብዙ ቦታ ላይ ሞክሮት ሲያጨነግፈው፥ በድሉም ደስ ተሰኝቶ፥ የራሱን ልጆችም ወልዶ፥ ለተጨማሪ ጥፋቶች አሁንም የሰውንና የዘመን አሰላለፍን ዋጅቶ፤ እየሠራ መሆኑንን ብዙዎቻችን በጣሞ ዘንግተናል፡፡ ችግር ካልደረሰብን፣ አደጋ ካልገጠመን፣ መከራ ካላየን የምንል ስለሆንን ተራ በተራ የችግርና የእፎይታ አልባ ስቃዮችን ገፈት ቀማሽ እስከምንሆን ድረስ መዘንጋታችን ይቀጥላል፡፡ እግዚአብሔር ይማረን፡፡

የወሲብ ፊልሞች ከመነሻው መጀመር፣ ማደግንና በከፍተኛ ፍጥነት በሁሉም የዓለም አገራት አቅጣጫ መንሰራፋትን ተከትሎ በአደገኛና ዘመናትን በቆየ የመናፍስቶች የተዋርሶ ግፊት ምክንያት በዓለማችን ብሎም በአገራችን እየጨመረና የርኩሰት አሠራሩም እየጋሸበ፤ ግፈኝነቱን፣ አሰቃቂነቱን፣ ጨካኝነቱንና ሕሊና ቢስነቱን እያሳደገ ከመጣው ተጠቃሽ የወንጀል ድርጊቶች ውስጥ አንደኛው ክፍል የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ድርጊት ነው፡፡

የወሲብ ፊልም ለአስገድዶ መድፈር ያለው ተጽዕኖ

ይሄን በርዕሱ የተገለጸውን አሳብ ለማስረዳት ምንም አይነት ሰፊ ትንተና አሊያ የማሳመኛ ቃላት አያስፈለግውም፡፡ ርኅራኄን በሕይወትህ ካስገባህ ሩኅሩኅ ትሆናለህ፤ የሰላምና የደስታ ቆይታዎችን ለማግኘት በጣርከው ልክ ሰላማዊና ደስተኛ ትሆናለህ፤ ለጨካኝነትና ለሰቆቃ ድርጊቶች የምትሰጠው ጊዜ ከበዛ ያው አረመኔ ሆነህ የሰው አውሬ ትሆናለህ፤ እንዲሁ የወሲብ ፊልሞችን በጊዜህም፣ በሕሊናህም፣ በምትሰጠው ቦታ መካከልም ወድደህ ካቆየኸው በተመሳሳይ የዝሙት ቀበኛ ሆነህ በወሲብ ጤናማ ያልሆነ ስሜቶች መሪነት እየተነዳህ የወንጀል ሰው ለመሆን ያለው ዕድልህ በእጅጉ ይገዝፋል፡፡

" ዓይኖችህም ከሚያዩት የተነሣ ዕብድ ትሆናለህ።" የሚለው ቃል በኦሪት ዘዳግም 2834 ላይ የተገኘው ቃል ነው፡፡ እነሆ ዛሬም በወሲብ ፊልም ዲያቢሎሳዊ አደንዛዥነት የተነሣ ሕሊና እና ማስተዋል በመናፍስት የደባ ጉም ምክንያት ፈዝዘው የሰው ልጆች በአማዊ ስሜት ሲያብዱ ብዙ የአስገድዶ መድፈር ወንጀሎች የተፈጸሙባቸው ጊዜያት በተጨማሪ እንዲከሰቱና እንዲበራከቱ ግድ ሆኗል፡፡ እንግዲያው ታዲያ ምን እንጠብቃለን? የእግዚአብሔር መለኮታዊ ፍቅርና ኃይል በባሕሪያችን ውስጥ አልገኝ ሲል፤ ከኃጢአት የግፍ ሥራዎችና የአመፃ ክፉ ቀናት ለመጠበቅ የምናሳየው ፈቃድ ግልጽ ለመሆን አቅም ሲያጥረው፤ ለቡራኬና መንፈሳዊ የሃይማኖት እውነታዎች ልባችንንና ሕይወታችንን ለማስገዛት እምቢ ስንል፤ ፍላጎታችን የክፉ መንፈስ ፍቃድ ሆኖ ለጥፋት አድራሽነት መሣሪያ መሆናችን የሚጠበቅ ዕጣ ፋንታ ነው፡፡

ገና ሰይጣን አለ የለም እያለ የሚደናበር ትውልድ ውስጥ መናፍስት ጥልቅ የመደበቂያና ጥፋትን የማበልጸጊያ ሽፋን አግኝተው ብዙ አቅጣጫዎች ላይ እንደ አገርም ጭምር በነዚህ እንደ ዝሙት ፊልሞችና መሰል የአመፃ መዝናኛዎች በሚያመርቱት የርኩሰት አፍዝ አደንግዝ ማሰሪያዎች ምክንያት የሥልጣኔ ወቅት ያልነው ዘመናችን የሰይጣን ዘመን ሲሆን፤ አንዳንዶቻችን ገና የዕለት እንጀራ ውጣ ውረድ ላይ ነን፡፡ አንዳንዶቻችን ሳይንሱና ቴክሎኖጂውን ለመያዝ ሩጫ ላይ ነን፡፡ አንዳንዶቻችን የዓለምን ሁከት አንሰማም ብለን በራሳችን የድበታ ዓለም ውስጥ የምናዋዥቅ ነን፡፡ አንዳንዶቻችን ደግሞ ባጣነው ነገር ላይ ሙሉ የሆነ ነገር ለመፈለግ ስንደክም ስንደክም መንፈሳዊ ጥቅሞችና ጉዳቶች ተሰውረውብን በጥሬዋ ዓለም ብቻ ዝም ብለን እንመላለሳለን፡፡

በወሲብ ፊልም ሱስ የናወዘ ልቦና በዝሙት መናፍስት እስራት ውስጥ ውስጣዊ የማስተዋሉ ኃይሉ ስለሚደክም፤ ለቅጽበት የሕሊና ከሳሽነትን ረግጦ በመናፍስቱ ግፊት በመነዳት የማመዛዘኛ ቀልቡን ስለሚያጣው የአስገድዶ መድፈር ተሳታፊ ወንጀለኛ ለመሆን አስቀድሞ ጭንቅላቱና የአኗኗር ስልቱ በቀላሉ በር የከፈተ ነው፡፡ ስለሆነም ግለሰቡ ቁጭ ብሎ በሚያያቸው የምናብ ሰይጣናዊ ስዕሎች መንፈሱ የነፍሱን መንፈሳዊ ክፍል ስለሚያፍነው፤ ያንን ሲያየው የቆየውን በሕሊና የተሳለ የዝሙት ጠባይና ተነሳሽነት በክፉ ቀን በክፉ መናፍስት በኩል ወደውጪ ይገልጠዋል፡፡ አንድ ቀላል ምሳሌ ስናንሳ፥ በአንድ ሸራ ላይ ተጸንባርቆ የሚታይ ምስል(projected image) ቢኖር፤ ሸራው እንዲያሳይ የሚገደደው ያንኑ ምስል ብቻ ነው፡፡ በዚሁ አይነት አሠራር የዝሙት መናፍስትም ውስጣዊ ሕይወትን የመቆጣጠር ተጋቦታቸው ፈጣን በመሆኑ ግለሰቡ እንደ ሱስ በየጊዜው ሲያየው የቆየውን ምስል በሕሊናው ሸራ ላይ በምናባዊ መልኩ ስለሚያንጸባርቁት፤ ሰውየው በምንም አይነት ሥጋዊ ጥበብና ዘዴ ከዚህ የውስጥ ፈተና ለማምለጥ እንዳይችል የጥፋት መንፈሶቹ የእምነት ሂደቶቹን ጥንካሬ ይሸረሽሩትና ገፍተው የሚፈልጉት ነጥብ ላይ ሲደርስ ይተዉታል፡፡ ስለዚህ ነው እጅግ የበዙ ሰዎች በሥነልቦናዊ ዘዴ ማለትም ለምሳሌ በማረሳሳት፣ ጊዜን በመጽሐፍትና ከሰዎች ጋር በመሆን በማሳለፍ፣ ስፖርታዊ እንቅስቃሴን በማድረግ መነቃቃትን ለመፍጠር ጥረት አድርገው ምናልባት የተወሰነ ጊዜ ከሩካቤ ፊልሞች ሱስኝነት ቢላቀቁም መልሰው ግን የሚወድቁት፡፡ የክፉ መናፍስት አሠራርና የጥፋት አገዛዝ የሚመከተው በመንፈሳዊ ጥበብና በመንፈስ ቅዱስ ስምና ኃይል እንጂ በሥጋዌ መፍትሔዎች በፍጹም አይደለም፡፡


ከነባራዊ ክስተቶችና እውነታዎች ላይ በመነሣት በእርግጠኝነት አስርጾ መናገር የሚቻለው(ሰሚ ካለ) የወሲብ ፊልም ኢንደስትሪዎችና አቅርቦቶች በእጅጉ ጨምሮ በዓለም አገራት ውስጥ መስፋፋት በጀመረበት ልክ እንዲሁ ጎን ለጎን የአስገድዶ ደፈራ ወንጀሎችና ጾታዊ ትንኮሳዎች በተመሳሳይ ጨምረዋል፡፡ በተለይም ከተማ ቀመስ በሆኑ የቴክሎኖጂ ምርቶች በተሰራጩባቸው ቦታዎች ላይ ይህ የበደል ፍሬ በተገለጠ መልኩ ተስተውሎ ለማንኛውም ለማጤን ፈቃደኛ ለሆነ ሰው ሁሉ የርኩሰቱ ገጽ ይታያል፡፡

መንግሥታት ስለዚህ የወሲብ ኢንደስትሪ እጅ ጠምዛዥ ትውልድ አጨንጋፊነት አያውቁም ብላችሁ ምስኪን እንዳትሆኑ፡፡ የሲጋራና ትምባሆ ውጤቶች ሲመረቱ ማሸጊያቸው ላይ "ጤናን የሚጎዳ" የሚል ማስፈራሪያ በመንግሥታቱ ደንብ መሠረት እንዲጽፉ ለአምራቾቹ ከመደነገግ ባለፈ ምርቱን ለመቆጣጠር የሚችሉበትን ሥልጣን በተገባ መሬት አውርደው ምርቶቹን አለመከልከላቸው << ሰው የፈለገውን የመከተል መብት አለው >> ከሚለው የሚስጢር ማኅበራቱ ዲሞክራሲ መሰል የአስገዳጅነት የጀርባ ተጽዕኖ ውስጥ መንግሥታቱ የተጨፈለቁ ስለመሆናቸው ማረጋገጫ ነው፡፡

በአብዛኛው ጊዜ ከብዙ የግፍ ወንጀሎችና የአመፃ ሁከቶች በስተጀርባ የርኩሳን መናፍስት በመሪነት የታገዘ የሕሊና ተምዣኝነት የድርጊቶቹ መነሻ ሲሆን፤ በውስጣዊውም ሆነ በውጫያዊ ኃይል አሳብ አመንጪነት፣ አቀናጅነትና አስፈጻሚነት በኩል የሚከናወኑ በሚሆኑበት ጊዜ፤ በመናፍስቱ ወጥመድ ሥር የገባው ግለሰብ በወንጀል ድርጊቱ የተግባር ሂደት መነሻና መድረሻ ጊዜ መካከል በግማሽ ልቦናው ሰው፥ በግማሽ ልቦናው ደግሞ ርኩስ መንፈስ፥ የሚሆን ሲሆን፤ አንዳንዴም መንፈሱ በሙሉ ኃይሉ ልቡን ስለሚይዘው ራሱን ሳያውቅ ወንጀሉን እንዲፈጽም ያደርገዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ብዙ ወንጀል ፈጻሚ ግለሰቦች፤ በደም የተነከረ ስለታማ መሳሪያዎችን ከያዙ በኋላ፣ ሰው ከከፍታ ላይ ወርውረው ከጣሉ በኋላ፣ በዱላ አሊያም በብረታማ ነገሮች ቀጥቅጠው ከገደሉ በኋላ፣ በጦር መሳሪያ ተኩሰው ካቆሰሉ ወይ ሕይወት ካሳለፉ በኋላ፣ እሳትና ተቀጣጣይ ፈንጂዎችን አስነስተው ንብረት ካወደሙ በኋላ፤ መንፈሱ ከልቦናቸው ባወቀ ለቀቅ ስለሚል ከሕሊናቸው ማገናዘብ ጋር የተመለሱት ግለሰቦች በጥልቅ ድንጋጤ፣ በከፍተኛ ፍርሃት፣ በማያባራ መርበትበት ውስጥ የሚገኙ ሲሆን፤ ከሕሊናና ሕግ ፍርድ አስከትሎ በዘወትር ጸጸት ሥር ስለሚወድቁ ከራሳቸው ጋር በመጣላት ነፍሳቸውን ሊያጠፉ ይችላሉ፡፡ እንዲሁ አስገድዶ የመድፈር ወንጀሎችም በተመሳሳይ በመናፍስቱ ግፊትና የልብ መሰወር በኩል የሚፈጸሙ የዲያቢሎስ የከሳሽነት ውጤቶች ናቸው፡፡


የአስገድዶ መድፈር አስገዳጅ ስሜቶችን ለመፍጠር የወሲብ ኢንደስትሪዎች የሚያመርቱት ፊልምና ምስሎች መነሻ ምክንያቶች የሚሆኑበት አጋጣሚ እጅግ ሰፊና የበዛ ነው፡፡ በዝሙት ቁራኛነት የተለከፉ ሰዎች ከቁጥጥራቸው በራቀ የግንፍልተኛ ስሜት መሪነት ተገድደው ፊልሞቹን ለማየት በመናፍስቶቹ የሚገደዱትን ያህል፤ በተመሳሳይ ለአስገድዶ መድፈር ድርጊት የሚጋበዙ ወገኖችም ለተያዙበት መንፈስ መሣሪያ ሆነው በጠላት ፍቃድ ሥር የሥጋ ፍላጎትን ለማሟላት በሚሰጡት ትንሽ ክፍተት ውስጥ ብዙ ስህተት ይሠራሉ፡፡

ከዚህ አልፎ ተርፎ የዝሙት ፊልም ኢንደስትሪዎቹ በራሳቸው የፊልም ድርሰትና ዝግጅት ውስጥ የአስገድዶ መድፈር ትዕይንቶችን እንደመዝናኛ ክፍል አድርገው በማቅረብ፤ የሰዎች አእምሮ ነውርን እንዲለምደው፣ ወንጀልን እንደ እርካታ እንዲቆጥረው፣ ጥፋትን እንዲንቀው የሚያሰለጥኑ በጣም አደገኛና አጥፊ የዘመናችን ትውልድ መርዞች ናቸው፡፡ በተጨማሪም የዲያቢሎስ ጉዳይ አስፈጻሚዎቹ በሚሠሩት ፊልሞች ላይ በተዋናይነት ገጸ ባሕሪይ ይጫወቱት እንጂ፤ በፊልማቸው ይዘት ላይ ግን የአስገድዶ መድፈሩን አረማዊ ርቀት እጅግ ሰይጣናዊ ከፍታ ላይ ለማድረስ ከሄዱበት አሠራሮች መካከል የደም ትስስር ያላቸው ቤተሰቦችና ዘመዶች የወንጀል ክንውኖችን በነጻነት እየፈጸሙ የሚያሳዩ ድርሰቶችን በማዘጋጀት አባት ልጁን በመድፈር ሲቀጣ፣ እናት በልጇ ስትደፈር፣ እህት በወንድሞቿ ጥቃት ሲደርስባት እያሉ በማቅረብ፤ እንስሳዊ ስሜትን በዘመናዊው ትውልድ ላይ ፈጥረው፤ የሰው ልጅ የማገናዘቢያ አቅሉን ስቶ ለመናፍስቶች የግብር ጭዳ ሆኖ እንዲኖር ያደረጉትም ጥረት ብዙ ቦታ ላይ ተሳክቶ ይኸው ዛሬ እንኳን በውጪው ዓለም ቀርቶ እዚሁ እኛም አገር ሕፃናት ሲደፈሩ፣ ልጆች በገዛ የቤተሰብ አባላት ሲጠቁ፣ ወንድ ልጆችም ሳይቀር አረማኔያዊ ተግባር ሲፈጸምባቸው እየሰማን ነው፡፡

ስለዚህ ምንድነው የምንጠብቀው ጎበዝ? ምን እስኪመጣ ነው እንዲሁ ዝም ብለን የምንቀመጠው? ለምንድነው የማታስተውሉት? እንደ ጋራ ዳፍንት ሆኖብን ዝም ብለን በአዙሪት ኑሮ እንድንኖር ያስገደደን የዲያቢሎስ ሠራዊት ላይ መቼ ነው የምንነቃው? "አባት ልጁን ደፈረ" ከሚል ሰይጣናዊ ዜና የተሻለ ኑሮአችን በመናፍስት የተከበበ ስለመሆኑ ምን አይነት ማረጋገጫ ነው የምንፈልገው? "ሕፃናት ወንዶች በወንዶች ተደፈሩ" ከሚል ኢትዮጰያዊ (ኢትዮጵያዊ እኮ ነው ወገን) ድምፅ የበረታ የረከሰ የአጋንንት ዘመን ላይ ስለመገኘታችን የሚያረጋግጥ ምን አይነት ቃል ቢመጣ ነው የምንበረግገው? እውነት ምን ቢመጣ ነው ማሕበረሰቡ ውስጥ ማሕበረሰብ ሆኖ ያለን የጥፋት ሠራዊት ለይተን የምናውቀው? ለምንድነው እንደዚህ አይነት የአራዊታን ሰቅጣጭ ዜናዎች ከልብ ውስጣችን ቆይተው የማይጠዘጥዙን? ለምንድነው እንደነዚህ አይነት ዘግናኝ ድምፆች እስከ አጥንታችን ቅዝቃዜ ድረስ የማያሳምሙን? ለምንድነው የተቀደሰች አገር ላይ እንኖራለን የምንል ሕዝቦች ውስጥ እንደዚህ አይነት መርዶ ሲወጣ ያላፈርነው? ለምንድነው የሌላው ችግር አልታይ ብሎን እንደ ሕብረተሰብ አንድ ጊዜ በጅምላ የፈዘዝነው? ከማሕበራዊ ድረገጾች የወረት ቀናት ውጪ እነዚህ የዲያቢሎስ ውጤቶች ሰርገው ለብዙ የእውነት ቀናት ያላስጨነቁን ለምንድነው? ካስጨነቁንስ ለምንድነው ወዲያው ከሕይወታችን በቶሎ የሚርቁት? እስኪ ለምንድነው? ለነገሩ በማብቂያው ዘመን ለክፉው ዕድል የተገኘ ትውልድ በየግል በየግል ቤቱ ችግር እየመጣ ከአቅሙ በላይ ካላሰቃየው ቶሎ አይገባውም፡፡ እነሆ ተጨማሪ የሰቆቃ፣ የምሬት፣ የጭካኔ ዜናዎችን እያስተናገድን በየመንደራችን መጮህ ስንጀምር ገና ያኔ ለመንቃት እንጀምራለን፡፡

የመጨረሻው ክፍል ይቀጥላል..

 


Post a Comment

0 Comments