በስመ አብ፥ ወወልድ፥ ወመንፈስ ቅዱስ፥ አሐዱ አምላክ፥ አሜን፡፡
ከወሲብ ፊልም ጥገኝነት እንዴት እንላቀቅ?
በወሲብ ፊልም የሱሰኝነት እስራት ውስጥ መውደቅ መንፈሳዊ እስራት ነው፡፡ በሚታይ ሰንሰለት፣ በሚዳሰስ እጀ ሙቅ፣ በሚንቀሳቀስ ብረት የሚከናወን እስራት አይደለም፡፡ የክፉ መናፍስት አዚማዊ እስራት ነው፡፡ ይሄን በተገባ አስርጸን ከመገንዘብ ስንጀምር የመፍትሔ አቅጣጫውንም ከመነሻው ለመረዳት መንገድ እናገኛለን፡፡
ብዙ በዚህ ዲያቢሎሳዊ ፈተና ውስጥ የወደቁ ወገኖች ታዲያ የማይገነዘቡት ጉዳይ ይህንኑ ነው፡፡ የወሲብ ፊልም ቀበኝነት ከአጥፊ መናፍስት ጋር ሳይሆን፤ ከፈቃደኝነት የሥጋ ፍላጎት ላይ የተነሣ የሥጋ ሱስ ጋር ብቻ አያይዘውት፤ ከመፍትሔውም ለመላቀቅ የሚሄዱባቸውም መንገዶች በአብዛኛው የሚከተሉት የሥጋ መፍትሔዎች ናቸው፡፡
☞ ስነልቦናን የማረሳሳት ዘዴን ለመጠቀም ጊዜን በተለያዩ ተጨማሪ ሥራዎች፣ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችና መዝናኛዎች ማጣበብ
☞ መጽሐፍትን፣ ሙዚቃዎችንና ሌሎች ጊዜ ማሳለፊያ ነገሮች ላይ ትኩረት በመስጠት አእምሮን ፋታ ለማሳጣት መሞከር
☞ ከጓደኞች፣ ከቤተሰቦችና የቅርብ ሰዎች ጋር በመሆን የብቸኝነት ጊዜ እንዳይመጣና የሱሱ ጥያቄ ተያይዞ እንዳይከሰት ቀድሞ መንገድ መዝጋት
☞ ባስ ያለ ደረጃ ላይም ደርሶ የሱሱ እርከን ወደ ጭንቀት መለወጥ ሲጀምር የሥነልቦና ባለሙያ ማማከር
እንግዲህ እነዚህንና ሌሎች ያልተጠቀሱ ሥጋዊ መፍትሔዎችን በመከተል ብዙ ሰዎች ከሩካቤ ፊልሞች ሱሰኝነት ለመላቀቅ ይጥራሉ፡፡ በእርግጥ ለተወሰኑ ሳምንታት ወይንም ቆይታዎች ከአዚማዊ የውስጥ ጥያቄው ሸሸት ቢሉም፤ ዘላቂና እስከወዲያኛው የሚገላግሉ መፍትሔዎች ግን አይደሉም፡፡ በዚህ ምክንያት በሌላ ጊዜ ላይ ደግሞ ችግረኞቹ መልሰው በፊልሞቹ ሱሰኝነት ሲቸገሩ፤ ከጥገኝነቱ መላቀቅ እንደማይችሉ ስለሚሰማቸው የበለጠ ተስፋ መቁረጥና ጭንቀት የሚጀምርበት አጋጣሚ ሰፊ ነው፡፡
አስተውሉ! መንፈሳዊ ጥቃቶች በመንፈሳዊ ክንድና አቅም በኩል ነው የሚመከቱት፡፡ በክፉ መናፍስት ጥበብና አሠራር የመጣ አበሳ፤ በመንፈስ ቅዱስ ኃይልና ጥበብ ብቻ ነው የሚመለሰው፡፡ በአጥፊ ጠላቶች ቀጥተኛም ይሁን ተዘዋዋሪ ምክንያት የተፈጠረ ማንኛውም አይነት ችግር፤ በሰማያዊ የአምልኮት ልምምድና ብርታት በኩል ነው የሚቀረፈው፡፡ ከዚህ ውጪ ያሉት ሥጋዊ ጥበቦችና አካሄዶች ተጨማሪ የመፍትሔ መንገዶች እንጂ በምንም መልኩ ቀዳሚ የችግር መፍቻ ቁልፍ ሆነው የዲያቢሎስን ኃይል አይቋቋሙም፡፡
ስለዚህ ምን እናደርግ ?
➊• የአምልኮት ስግደት
እነዚህ በዓለም አቀፍ የሴራ ደባና የጥፋት መናፍስቶች በኩል እየተመረቱ የሚወጡት የዝሙት ፊልሞችና ተያያዥ ምርቶች ሁሉ ከሕይወታችን ውስጥ አዚም ሆነው ገብተው በጥገኝነት ቁራኛ አስረውን ከሆነ፤ እስራቱን የመበጠሻ አንዱ መጋዝ የዘወትር የአምልኮት ስግደት ነው፡፡
ከስሙ እንደምንረዳው የአምልኮት ስግደት የማምለኪያ ቅጽ ማስገቢያ ስግደት ነው፡፡ የአምልኮት ስግደት ከነፍስ ውስጥ በየጊዜው ያድግ ዘንድ የሚገባውን የመለኮት ኃይል እየጨመረ የሚመጣ ስግደት ነው፡፡ ይሄ የሚገባው በመስገድ የሚጠቀምበት ሰው ብቻ ነው፡፡ እነሆ ታዲያ ከእውነት የፍቅር መሠረት ካለው የእምነት መነሻ ላይ አስጀምራችሁ መስገድ በመናፍስቱ በኩል ተጠፍንጎ የተጠመጠመውን ሰንሰለት የሚገዘግዝ መቁረጫ ነው፡፡ እንግዲህ ልብ በሉ፡፡ እየተገዘገዘ የሚቆረጥ ሰንሰለት ሙሉ በሙሉ እስራቱን ለመበጠስ ሁለት ነገር ይፈልጋል፡፡ አንደኛው እየገዘገዙ መቆየት፥ በሁለተኛው የግዝገዛውን ጉልበት እየጨመሩ መሄድ ያስፈልጋል፡፡ አሁን ወዲያው መስገድ እንደጀመራችሁ ወዲያውኑ ትልቅ ለውጥ ማየት የምትፈልጉ አላችሁ፡፡ እንደዚህ አይሆንም፡፡ አስታውሱ፡፡ ክፉ መንፈሱም እስራቱን እያጠበቀ እያጠበቀ ነው የሚመጣው፡፡ በአንዴ ግጥም አድርጎ አያስርም፡፡ የመታሰር ሂደት ቁልቁል የመውረድ ገጽታ ምሳሌ ስለሆነ መቼ ተንሸራተን ታች ሸለቆ ጋር መቼ እንደደረስን ባለማስተዋል ስለምናሳልፍ እንጂ፤ አጥፊዎችም የጊዜ ኡደትን ጠብቀው ነው የሚሠሩት፡፡ ስለዚህ ቀስ በቀስ የታሰረ ገመድ፤ ቀስ በቀስ ነው የሚፈታው፡፡ ችግርን የመቅረፊያ መንገድ ገና ሲጀመር በዕውቀት ይታገዛል፡፡ መንገዱ ላይ ደሞ የጊዜ እገዛን ይፈልጋል፡፡ የመፍቻ አቅጣጫውን አንዴ ከተገነዘብን በኋላ የመፍታቱን ሂደት ሳያቋርጡ በተገኘው አቅጣጫ በኩል በመዞር ከጊዜ ጋር ጨርሰን የምንፈታው ጉዳይ ይሆናል፡፡ የወሲብ ፊልሞች እስራት መፍቻ መነሻ መፍትሔው አንዱ የአምልኮት ስግደት እንደሆነ አወቃችሁ፡፡ ስለዚህ ቀጣዩ ከጊዜ ጋር ሳያቋርጡ በየዕለቱ እየጨመሩ በመስገድ መበርታት አንድ በአንድ የአዚሙን የቋጠሮ ክሮች እየበጠሰ የሚሄድ ይሆናል፡፡
➋• ጸሎት
ጸሎት የሰማዩን አባት የምናነጋግርበት ቋንቋ ነው፡፡ እዚህ ጋር በጣም ትልቁ ችግራችን ሰውን መፍትሔ ፍለጋ የምናማክረው ያህል እግዚአብሔርን በጸሎት አናማክረው፡፡ ምክንያቱም የእግዚአብሔር መንፈስ ከሥጋ የተሰወረ ረቂቅ ስለሆነ የሚሰማንና መልስ የሚሰጠን አይመስለንም፡፡ ብዙዎቻችን በጣም ችኩሎች ነን፡፡ ከእግዚአብሔር ይልቅ ሰውን የምናማክርበት ሌላኛው አመንክዮም ይሄው ችኩልነታችን ነው፡፡ ሰው ወዲያውኑ በሰውኛ ቋንቋ መፍትሔ ነው የሚለውን ድምፅ ስለሚያሰማን፤ ስንሮጥ የምንገኘው ሰው ፍለጋ ነው፡፡ በአጽንዖት ግን ያዙ፡፡ የትኛውም የምድር ሰው በአብዛኛው የሚያማክራችሁ ከእውቀቱ፣ ከልምዱና ካለበት የጊዜና የሁኔታ አንጻር ነው፡፡ የሚነግራችሁ መፍትሔ ፍጹም ትክክል እንኳን ቢሆን፤ እያንዳንዱ ውስጣዊ ስሜታችሁን እንደናንተ ሆኖ ማንም አይገነዘብላችሁም፡፡ ይሄ ተፈጥሮአዊ ግዴታ ነው፡፡ ሰለዚህ አትሞኙ፡፡ በየቀኑ አስቀድማችሁ ለሰማዩ አምላክ በጸሎት አማክሩ፡፡ ግጥም አድርጋችሁ አምናችሁ አማክሩ፡፡ አይምሰላችሁ በእውነት፡፡ በጣም የሚሰማ ገር አባት ነው፡፡ መለኮታዊ መዳፎቹ እርዳኝ እያሉ የሚጮኹ እጆችን ለመያዝ ለአንዲት ሰከንድ ታጥፈው አያውቁም፡፡ ስለዚህ በዚህ የመናፍስት ወጥመድ ውስጥ ገብታችሁ የምትሰቃዩ ወገኖች፤ ዘወትር ከወጥመድ አውጣኝ እያላችሁ ጸሎት ቤት በገባችሁ ልክ አሳስቡ፡፡ መቼ መቼ አሳስቡ? ዘወትር፡፡ እዚህም ጋር ጥልቅ የሆነ የመንፈስ ቅዱስ ሃይማኖታዊ አሠራርን ስለማንገነዘብ "በቃ እግዚአብሔር ሁሉን አዋቂ ነውና አንዴ ከነገርነው ይበቃል" ብለን የተሳሳተ ግንዛቤ እንይዛለን፡፡ በእርግጥ ለእግዚአብሔር አንዴ መንገር አይደለም ሳንነገግረውም ችግራችንን ለማስተካከል የዋህ ልቡናው ሁሌ ወደኛ ነው፡፡ የነገሩ መጠላለፍ ግን ያለው እኛ ውስጥ ካለው ርኩስ ጠላት አንጻር ነው፡፡ መንፈስ ጸሎት ባደረግን ቁጥር በመጀመሪያ ለማስቆሞ ይታገል ይታገልና፤ ስንጸናበት እርሱ እየደከመ እየደከመ ይመጣል፡፡ ስለሆነ ውስጣችን አዚም ሆኖ ያለው ጠላት አጠብቆ የእስራት ሰንሰለቱን የያዘበት ክንዱን ለማዛል ጸሎቱ በየቀኑ በእውነተኛ የአቅም ልክ ድረስ ነው መደረግ ያለበት፡፡ በጣም የሚያሳዝነው ግን ብዙዎቻችን፥ በመናፍስት የተጨነቅነውን ያህል መናፍስቱን በየዕለት ጸሎት ለማስጨነቅ ጠንካራ የውስጥ ሞራልና ፍላጎት የለንም፡፡ ፍላጎቱ ግማሽ የሆነበት ወይንም ትንሽም ብትሆን ክፍተት ያለበት ሰው ደሞ ላለማከናወን፤ በፍላጎቱ ክፍተት ልክ ሰበብ ይፈልጋል፡፡ ስለዚሁ ችግሩን እየዘከረ የሚቀመጥ ሰው ይሆናል ማለት ነው፡፡ ግን አስታውሱ #ፍጹም_የታመነ_ቃሉ እንዲህ ይላል፡፡ " አምናችሁም በጸሎት የምትለምኑትን ሁሉ ትቀበላላችሁ።"
(ማቴ. 20፥21)
➌• መቁጠሪያ
ሌላው በሩካቤ ፊልም ሱሰኝነት ውስጥ ጠፍንገው የከረቸሙንን ጠላቶች የምናደክመው በመቁጠሪያ ነው፡፡ እዚህ ጋር መሠረታዊ መረጃ የምሰጣችሁ፤ በመቁጠሪያ መናፍስትን በምትቃወሙበት ሰዓት ላይ ርዕስ እየሰጣችሁ አቃጥሏቸው፡፡ ምን ማለት ነው፥ ለምሳሌ አሁን የዚህ ክፍል ትምህርታችን 'እንዴት ከወሲብ ፊልም ሱሰኝነት እንላቀቅ' የሚል ነው፡፡ የዝርዝር ጉዳዩ መምሪያ አድራሻ በርዕሱ ውስጥ የተጠቀለለ ነው፡፡ እንዲሁ መናፍስቱንም ስትቀጠቅጡ የችግራችሁን ዝርዝር ጠቅልሎ የሚይዝ ርዕስን በመስጠት ማድከም ያስፈልጋል፡፡ "በዚህ ጥገኝነት ውስጥ ያሰራችሁኝ ጠላቶች" ብለን ለብቻ ጠርተን ነው መቀጥቀጥ ያለብን፡፡ ለምንድን ነው ይሄ፥ አንደኛ ያንን የእስራት ሥራ እየከወነብን ያለው መንፈስ በቀጥታ ባለጉዳይ አድርገን እንድንቀውረው የመንፈስ ቅዱስ ኃይልን እናነጣጥርበታለን፡፡ ሁለተኛ፥ መንፈሱን እንደነቃንበት ማገናዘቢያ ስለሆነ፤ የተሰወረው ጠላት ግልጽ መምጣት ይጀምራል፡፡ ይሄ ደግሞ የፍልሚያውን ጉልበት እንድናሳድግ አቅምና ብርታት ይሰጠናል፡፡ ሦስተኛ መናፍስት ግብራቸው ስለሚለያይ፤ ዝም ብለን በደፈናው ከምንቀጠቅጥ የባሰ ችግር እያመጣብን ያለውን መንፈስ ቅድሚያ ለማስቆምና እርሱም ያንን ችግር እያከናወኑ ባልሆኑ መናፍስት ተደብቆ፤ ደካማ መናፍስትን እያጋለጠ ግብሩን ቀጥሎ የአምልኮታችንን ሞራል "እየቀጠቀጥኩም ሥራውን አያቆምም እንዴ?" ብለን የምንጎዳበት አሳብን አበልጽጎ እንዳያጠቃን እየለየን ነው ማድክም ያለብን፡፡ ስለዚህ ሁሌ መቁጠሪያውን ሰትጠቀሙ የየዕለቱ አልከናወን ያሉ ችግሮችን እያያችሁ "ይሄን ይሄን የምታደርግ መንፈስ አንተ ለብቻህ ታስረሃል" ብላችሁ ቀጥቅጡት፡፡ ትልቁ ነባራዊ እከል እየፈጸመ ያለውን ጠላት በእንዲህ መልኩ ለብቻው ከቀጠቀጣችሁ በኋላ ደግሞ "አጠቃላይ በሕይወቴ ውስጥ ያደፈጣችሁ ታስራችኋል!" ብላችሁ ደግሞ ከሌሎቹ ጠላቶች ጋር አንድ ላይ ማድከም ብዙ ሥራውን በጊዜ ሂደት እንድታከሽፉት ያደርግላችኋል፡፡ አይመስላችሁ በርቱ፡፡
" በእግዚአብሔር የምታምኑ ሁላችሁ፥ በርቱ ልባችሁም ይጥና።"
(መዝሙረ ዳዊት 31፥24)
➍• ፊልሞቹን አለማየት
ይሄን ገና ርዕሱን ስታዩ ልትደናገሩ ትችላላችሁ፡፡ ከጅምሩ ላለማየት አይደለም ወይ መፍትሔ የምንፈልገው እንዴት ነው አትዩ የሚለው ጉዳይ ጥያቄ ይሆናል፡፡
አንድ ግን በጣም ግልጽ መሆን ያለበት ጉዳይ አለ፡፡ አንድ ወቀት ላይ ቅዱስ ጌታ ለደቀመዛሙርቱ የእምነትን ኃይልን ባስረዳቸው ጊዜ "የሰናፍጭ ቅንጣት ያህል እምነት ቢኖራችሁ የሚሳናችሁ የለም" ብሎ ነበረ፡፡ ርኩስ መንፈስ ሁሌ ታዲያ አምላክን በተቃራኒው አቅጣጫ አበክሮ የሚከተለው ፍጡር ነውና በእርሱ የአሠራር ስልት በኩል ደግሞ ይሄን ያስፈጽማል፡፡ "የሰናፍጭ ያህል ስህተት ስትሠሩ የማይሳናችሁ የለም" ብሎ ገልብጦ ዙሪያችንን በስህተት አማራጮች አጭቆ የምጣድ ብልጭልጭታ ያህል ጥፋት እንድንሠራ አድብቶና ጸንቶ ይጠብቀናል፡፡
በጣም በእርግጠኝነት የምነግራችሁ፤ በዚህ የወሲብ ፊልም ጥገኝት እስራት ውስጥ ብትሆኑም፤ የሆነች ያህል ድርሻ ደግሞ እኛ በራሳችን ፍላጎት ወደን እንሳብበታለንም፡፡ ለዚህ እኮ ነው አስቀድሜ በ6 ክፍሎች ትምህርት በኩል የወሲብ ፊልምን እውነተኛ የመናፍስት ገጽታና ጠንቅ ላሳያችሁ የሞከርኩት፡፡ በሙሉ ሰብአዊ ልብ እንድትጸየፉት ነው መረጃው የተሰጣችሁ፡፡ በውስጥህ በሰናፍጭ ቅንጣትም ያህል ሳትጸየፈው ከተገኘህ፤ መንፈሱ የርሱን ፈቃድ የሚወክል ያንተን ፍቃድ አግኝቷልና ትንሿን ፍም ፍላጎት አረገብግቦ በወጥመድ እሳት መጣድ ቀላል ይሆንለታል፡፡ ከውስጥህ ግን ምንም መሻት ከሌለ፤ መንፈሱ አዚማዊ ጥያቄዎችን ገና ከውስጥህ ሲፈጥራቸው ትለየዋለህ፡፡ ምክንያት? ያንተ አይደለማ፡፡ ባንተ ውስጥ የሚመላሰውን ያንተ መሰል የመንፈስ አሳብን ሰንጥቆ ለመለየት፤ በፍጹም መሻት የዝሙት ሕይወቱን መጥላትህ አቅም ይሆንሃል፡፡ ትንሽም ብትሆን የራስህ ፍላጎት ከተገኘ፤ ይሄንን አውጥተህ እስክትጥል ድረስ እግዚአብሔርም ዝም ይላል፡፡ በፈቃድህ በኩል የሚያድን አባት ነውና፡፡ የመናፍስትን ውጊያ ለማስቆም የኛ የውስጥ ፍላጎትና የእምልኮት ልምምድ አንድ ቦታ ላይ መገናኘት አለባቸው፡፡ ብዙዎቻችን አንድ እግራችን ወደ እግዚአብሔር መመለስ ላይ፤ አንዱ ደሞ አለመመለስ ላይ ረግጦ ነው ወደፊትም ወደኋላም እየሄድን የምንቸገረው፡፡ ስለዚህ መጠየቅ አለባችሁ፡፡ ዘመናትን የበጠበጣችሁን ይሄ ጨካኝና ክፉ ጠላት ለማስቆሞ ምን ያህል ትፈልጋላችሁ? ይሄ የፍላጎታችሁ መጠን ልክ ከፍ ሲል የአምልኮት ልምምዱ በራሱ ይጣፍጣችኋል፡፡ የውስጥ ፍላጎቱ ነው በሥጋችን የውጪ ገጽታ በኩል አምልኮታችን ላይ የሚተረጎመው፡፡ ክፋትን የመሸሽ ፍላጎትህ ላይ ጥያቄ ኖርብህ ክፋትን ስትቀጠቅጠው ብትውል እርሱን የሚወክል ምሽግ አግኝቶብሃልና ተዳክሞም እንኳን ቢሆን ይፋለማል፡፡ ስለዚህ ውጊያው የኛን ባሕሪይ ጭምር ከማረም ጋር የተያያዘ ሂደት አለው፡፡
➎• መቆጠብ
ይሄኛው ደግሞ መንፈስ የሚመጣበትን መንገድ አስቀድሞ የመዝጊያ መፍትሔ ነው፡፡ አንድ ግልጽ አስተንትኖት የማይሻ ጉዳይ አለ፡፡ ርኩሰት የሚሰተናገድበት ቦታና ጊዜ ላይ ቆመህ ርኩሰት አይምጣብኝ አይሠራም፡፡ ክፉ የሚመላለስበት ሥፍራ ላይ ተገኝተህ ክፉ አይንካኝ አይሆንም፡፡ ስለዚህ የወሲብ ፊልሞች የሚመላለሱባቸው መንገዶች ላይ ቆማችሁ፤ መልሶ ደግሞ በእስራቱ ተቸገርኩኝ አይሠራም፡፡ ከምታየው ነገር የተነሣ ዕብድ ትሆናለህ" የሚለው ቃል ከተገኘ፤ ከውጪ ወደ ውስጥ የምታስገባቸውን ማንኛውንም አይነት መረጃዎችን መቆጠብ ግዴታ ይሆናል፡፡ ምን ማለት ነው ሲባል፥ እነዚህን የእርግማን ትዕይንቶች ወደ ሕይወታችን የመሳቢያ መንገዶች ማለትም ሙዚቃዎች፣ ፊልሞች፣ ጽሑፎችና ሌሎች መዝናኛዎችን እየተከታተሉ በዚህ ጋር ደግሞ ነጥሎ የዝሙት ፊልሞቹን ማስቆም አይቻልም፡፡ ለዚህ ነው በክፍል 3 እና 4 ትምህርታችን እነዚህን ለዝሙት ኢንደስትሪዎች ማገዣ ድልድዮችን እንድታፈርሱ መረጃ የተሰጠው፡፡ በቀላሉ የፍትወት ስሜቶችን የሚጠሩ መዝናኛዎችን፣ ቋንቋዎችንና ደባል ሱሶችን ይዞ፤ ከመናፍስቱ አዚማዊ ፊልሞች መላቀቅ አይቻልም፡፡ አልሸሸም ዘወር አሉ መዝናኛዎችን እያስተናገዱ፤ በሌላ በኩል ችግሩ አልተወኝም አብሮ አይስማማም፡፡ ከላይ ለዚህ ነው ሙሉ ፍላጎት ሲኖረን ነው መናፍስቱን ማስቆሞ የሚቻለው የምለው፡፡ ከተያያዥ መዝናኛዎችና ድርጊቶች ለመቆጠብ፤ ከእጅ ሥልካችንና ኮምፒውተራችን ላይ ደምስሰን ስናጠፋቸው፤ መናፍስቱ እንደ ግብር ይጠይቁ ዘንድ ወደኛ የቅጽበትም ትሁን የሚያገኙት ምክንያት ስለሚዘጋባቸው የውስጥ ግፊቱን በቀላሉ ማሸሽ እንችላለን፡፡
➏• ዙሪያውን በእግዚአብሔር ነገራት መሙላት
በመፍትሔ አምስት ላይ የተጠቀሰውን የመቆጠብ መንገድ ስንጓዝበት፤ ጎን ለጎን በተቆጠብንባቸው ቦታዎች ላይ ምትክ አድርገን የእግዚአብሔርን ነገራት መሙላት ነው፡፡ ሙዚቃውን ስትከለክል በምትኩ ዝማሬዎችን መፍቀድ ነው፡፡ አመፃ ፊልሞችንና መዝናኛዎችን ስትከለክል በምትኩ መንፈሳዊ ትምህርቶችን መፍቀድ ነው፡፡ አጠር ባለ ቋንቋ ጊዜያችን ሁሉ በሰማያዊ ገጽታዎች እየተወረሰ ሲመጣ፤ ምድራዊያኑ ማታለያዎች የኛን የሥጋ ፍቃድ የሚገዙበት መንገድ ያጣሉ፡፡ ስለዚህ መንፈሳዊነትን በዘርፈ ብዙ አቅጣጫዎች ማሳደግ ነው፡፡
አስጀምሮ ያስፈጸመን ልዑል እግዚአብሔር ስሙ ለዘላለም የተመሰገነ ይሁን፡፡

0 Comments