አንድ ወቅት ላይ አንድ እህት እንዲህ አለች
"...የቤተሰቤ ምኞት ትልቅ ነበር፡፡ ተምሬ ጥሩ ውጤት አምጥቼ እንዳኮራቸው ሁልጊዜ ይነግሩኝና ይመክሩኝ ነበር፡፡ እኔ ግን ምክራቸውን ጠብ እንደመፈለግ ቆጥሬ፤ እልኽ ያዘኝ፡፡ በዚህም የተነሣ አጥኚ ሲሉኝ፤ በር ዘግቼ እተኛ ነበር፡፡ ገና ከ7 ዓመቴ ጀምሮ፤ የወሲብ ፊልም ተደብቄ ስለማዘወትር፤ ከትምህርቴ ይልቅ የበለጠውን ጊዜ የምጨርሰው ፊልሙን በመመልከት ነበር፡፡
ይህ ፊልም ሱስ ከሆነብኝ በኋላ ግን፤ ከቤተሰብ ራቅሁ፡፡ እንደውም ትምህርት አልገባ አለኝ፤ ጭራሽም ፊደል እንኳ እየጠፋብኝ መጣ፡፡ በዚህም ማንበብና መጻፍ የማልችል መሃይም ሰው ሆንኩኝ፡፡ አእምሮዬ ተሰርቆ የማስበው ሁሉ፤ ያየሁትን ፊልም በመሆን፤ ፍላጎቴ ከአቅሜ በላይ ስለሆነ፤ ከቤተሰቤ ተለይቼ በመጥፋት፤ ሆቴል ቤት ተቀጥሬ አዲስ ሕይወት ጀመርኩ፡፡ በዚም ሥራዬ፤ ያየሁትን የፊልሙን ዓይነት ሰው ሆንኩ፡፡ ስለዚህ ወንዶቹም ሴቶቹም ሱስ ሆኑብኝ፡፡ በዚህም ምክንያት 9 ጊዜ ጽንስን አስወረድሁ፡፡
ይህ አሁን አድጎ የሚታየው ልጄ 10ኛዬ ነው፡፡ እርሱም ቢሆን ለእኔ፤ ሌላ መከራ ነው የሆነብኝ፡፡ እንደባሌ ይቀጣኛል፤ እየደበደበ እጄን ሰብሮታል፡፡ አባቱን ስለማላውቀው በመከራ አሳደኩት፡፡ ከዘጠኙ መካከል አንድ እርሱ ቢተርፍ፤ እርሱም ደግሞ ዱላው ሰለቸኝ፡፡ ወይ አይማር፣ አይታዘዝ፣ አይሰማ፣ ሥራ አይወድ፣ በዱላ እያስፈራራ ገንዘብ ይቀማኛል፡፡ በዚህ ላይ ሱሰኛ ነው፡፡ የማያጨሰውና የማይጠጣው ነገር የለም፡፡ ሲሰክር የሚያደርገውን አያውቅም፡፡ 9ኙ ያስወረድኳቸው ልጆቼ ቢኖሩ ኖሮ፤ ቢያንስ ሦስት እንኳን ዕድለኛ ሆነው ያግዙኝ ነበር፡፡ አይ ዕድሌ! ምነው? ሞቼ ባረፍኩት"እንግዲህ የወሲብ ፊልሞች እስራትና የመናፍስት የአጥፊነት ወጥመድ ትሩፋታቸው እንዲህ አይነት ሰቆቃ ነው፡፡ በዲያቢሎሳዊ ፊልሞች ኢንደስትሪ ዓለማቀፋዊ ጫናም ውስጥ እምነትን ለማደብዘዝና ከሰው ልጆች የልቦና ፍቃድ ለመራቅ ከሄዱባቸው ስልቶች መካከል የፊልሞቹን ትዕይንቶች በጣም ዘግናኝ፣ የሰብአዊነት ክብር የሚረግጡ፣ አረማዊ ብሎም እንስሳዊ አካኋን የሚገለጥባቸው፣ የፈቃደኝነት እብደት የሚነበብባቸው፣ ከቤተሰብ አሊያ ከዘመድ አዝማድ ጭምር ጋርም ሩካቤ የመፈጸም ድርሰቶችን እየዘጋጁ ስለሚለቁ፤ አፍሪካውያን በዚህ አዚማዊ ሱስ በመጠለፍ ከሕይወታቸው እንዲሰናከሉ፣ የሥነምግባር ሞራልን እንዲጥሱ፣ ጤነኛ የትዳርና የቤተሰብ ኑሮ እንዳይመሠርቱ በቴክሎኖጂ ገመድ አርዝሞ በማሰር ብዙ ኪሣራዎች እንዲከሰቱ ሆኗል፡፡ ዘመናዊ የሚመስለው ትውልዳችን ከመቼውም ጊዜ በላይ የውስጥ ሕይወትም የውጪ ገጽታም በሽተኛና መከራ ቆጣሪ ሆኖ፤ በሠለጠነ ጊዜ መካከል የምዕራባውያንን በብልጭልጭ መናፍስታዊ ሽፋን የተለወሱ የቴክሎኖጂ፣ የርዮተ ዓለም የኢኮኖሚና የሳይንሰ ጫናዎችን ለመቋቋም ሲል የቤተሰብንና የአከባቢን ትርምስምሶች አፍኖ ይዞ በግድ እየተማረ እየተማረ ከርሞ፤ እንጀራ ፍለጋ ለሥጋ ኑሮ ብቻ ሲዳክር ሲዳክር ቆይቶ፤ አሁን የረቀቀውን የአጥፊዎችን ጥቃት ለመረዳት እንኳን አጋጣሚውን እስኪያጣ ርቆ ጠፍቶ ሄደ፡፡
የማብቂያው ዘመን ላይ ለመገኘታችን ነባራዊ ምስክሩ፤ መናፍስታዊ አሻጥሮችን ለመገንዘብና ለመረዳት ምንም አይነት የውስጥ ፍቃዱ ስለሌለን፤ አዳምና ሔዋንን በእባብ ተሰውሮ ወደ ሞት ጎዳና የወሰዳቸው ጠላት፤ ዛሬም እኛም ጋር በቴክሎኖጂ አውታሮች፣ በየዕለት ኑሮ ክስተቶች፣ በማሕበረሰባዊ መዋቅሮች፣ ሕይወትን ለማቅናት በምናደርገው ትግሎች ውስጥ ተሰውሮ ወደ ዘላለም ሞት ጎዳና እየወሰደን ሲገኝ፤ ከመጤፍም ቆጥረን በዚህ ጉዳይ ላይ ትኩረት ልንሰጠው ስላልቻልን፤ በየቤቱ ሁሉም ሲሰቃይ፣ በየግሉ ሁሉም ሲንከራተት፣ እንደጋራም ምንም ነገር አልሳካ ሲለን እንመን ብንል አስቸጋሪ ነው፡፡
የምናሳልፈው ሁሉ የዓመፃ ጠባያትና የትውልድ መጋሸብ፤ ከፖሊቲካዊና ማሕበራዊ አውታሮች ጋር ብቻ የሚያያዙ ከመሰለን ተሞኝተናል፡፡ የሕዝባችን መተረማመስና በግራው መዝመም፤ በመንግሥታዊ መዋቅሮችና ተያያዥ ፖሊሲዎች የሚፈታ ከመሰለን ደንግዘናል ማለት ነው፡፡ ይኸው ስንት ዓመት አልነው አልነው አይደለም እንዴ?
ከ60ዎቹ ዘመን አንስተን ፖለቲካዊ ንድፈ አሳቦችን እየቀያየርንና የርዮተ ዓለም ትንተናዎችን እየሞከርን መጣን፡፡ አሁን ይሻላል ስንለው፤ ወደ የሚብሰው እየሄደ፥ አዋጣን ስንል፤ ኪሣራ እያመጣብን፤ አለፈልን ስንል፣ ጭራሽ እየቆረቆዝን ቁጭ አልን፡፡ በመሳካትና በመጣመም መካከል እንዲሁ እየዋተትን የፍልስፍናና የፖሊሲ ቤተሙከራ ሆነን ዘመናትን አቆራረጠን መጣን፡፡ ወደባሰው ሁኔታ በጣም በፍጥነት የማንዘበላችን ምክንያቶች በብዙ ልሂቃኖችና ምሁራን አስተንትኖ ቢገለጽም ከዘላቂ መፍትሔ ግን የሚያስቀምጠንን የሰላምና የእፎይታ ጊዜያቶቻችንን ግን ማምጣት አልተቻለም፡፡
ምክንያቱም የእግዚአብሔርን ረሳን በቃ፡፡ እምነት የኋላ ቀሮች ነው አልን፡፡ በባህልና በሃይማኖት መካከል ያለውን ድንበር አጠፋነውና ቀላቅለነው በልማድ ብቻ ክርስትናን ተቀብለን ቁጭ አልን፡፡ ዓለማዊና መንፈሳዊ አኗኗር ብለን በአንዱ የእግዚአብሔር መንግሥት ሥር እንኖር ዘንድ የሚያስፈልግበትን የሕይወታችንን መንገድ ወደ ሁለት ዓለማት አወቃቀር ከፍለነው፤ ለሥጋዊ ፍቃድና ፍላጎቶች ብቻ የሚሮጠውን ዓለማዊ፤ የሃይማኖትን ኃይልና የቃልኪዳን እውነት የሚይዘውን መንፈሳዊ፤ ብለን ሁለት አኗኗሮችንና አካሄዶችን ፈጥረን በዓለማዊነት ፍቺም ውስጥ ዓለማዊ ማለት ከሰማይና ከምድር ገዢ እግዚአብሔር ነገራት የራቀ ነው አልንና ተርጉመነው የዓመፃ ዘመናትን በሰጠነው የፍቺ ትንተና በኩል እየመነጨ ሲወጣ መልሶ ደሞ ግራ ይገባናል፡፡ ዓለማዊ ማለት ዓለም ውስጥ የሚኖር ማለት ብቻ ነበረ፡፡ ነገር ግን በተጣመመ ርኩስ መናፍስቶችን በሚያግዝ አተረጓገም ውስጥ መንፈሳዊነት በዓለማዊ ሕይወታችን ውስጥ ሊከሰት የሚያስፈልግበትን የነፍስ መስመር ዘግተነው፤ ዘመናትን አስቀድሞ ወደ ምድር የወደቀው ጠላት ወደ ዕድሜያችና ወደ ዕድላችን ገብቶ አጣመን የያዝነው ዓለማዊነታችንን ተጋርቶን ሲቆይ አሁን አሁን ላይ ይኸው ርኩሰትን፣ አመፃን፣ ግፍን፣ መሰደድን፣ መዘበራረቅን በብዛት ተለማምደን ስናበቃ ቅድስና የተራራ ያህል ሸክም ሆነብን፡፡ እግዚአብሔር ይማረን፡፡
0 Comments