አዲሱ ዓውደ ዓመት ከተጀመረ እነሆ 30 ቀናት አለፉ፡፡ እንግዲህ ከሰማይ በታች ለውጥ እንጂ አንዳች አዲስ ነገር በሌለባት ዓለም ውስጥ፤ ዘመኑ ስለተለወጠ አዲስ የሆነ መስሎን፤ በዘልማድ መኖርና መናገር የብዙዎቻችን ባሕሪያቶቻችን ናቸውና በየሚዲያው፣ በየመገናኛ አውታሩ፣ በየንግግር ማሳረጊያው ላይ አዲሱ ዓመት "የሰላም፣ የጤና፣ የብልጽግና፣ የአንድነት፣ የፍቅርና.. ይሁንልን" ብለን መልካም ነገራትን ለአገራችን ብዙዎቻችን ተመኝተን ነበረ፡፡
+++
ምኞት ከእውነት ጋር ስትጣመር እቅድ ትሆናለች፡፡ ከዚህ ውጪ ከሆነች ደሞ ቅዥት ትሆናለች፡፡ አሁን ብዙዎቻችን ለ2013 ቃዠን እንጂ አላቀድንለትም ነበረ፡፡ ምክንያቱም እውነት የሕያው እግዚአብሔር መለኮታዊ ክፍል ናት፡፡ ስለዚህ ያለ እግዚአብሔር መልካም ምኞት መመኘት ወጉ እንዳይቀር ለዘልማድ ግብር ማስከፊያ ከመሆን በዘለለ፤ ምኞቱ የሚጸድቅ አይሆንም፡፡ እንደማይሆን ደግሞ ይኸውላችሁ የ2013 ቀናቱ እንኳን በቅጡ ሳይጓዙ፤ ምን ምን እየተከሰተ እንዳለ በማየት ማረጋገጥ ነው፡፡
+++
በ2013 ዓውደ ዓመት፤ በመካከሉ ሂደት ላይ እግዚአብሔር ፍጹም የመንፈስ ቅዱስን ጣልቃ ገብነት አከናውኖ ብዙዎቻችንን ወደ ልቦናችን እስካልመለሰን ድረስ፤ ከቀደመው ዓመት የሚብሰው እንጂ የሚለመልመው ዓመት አይሆንም፡፡ ይህ አራት ነጥብ እውነታው ነው፡፡
+++
በዮሐንስ ወንጌል 5፥14 ላይ የተመለከተውን ቃል የተናገረው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፥ 38 ዓመት በቤተሳይዳ መጠመቂያ በአልጋ ደዌ ለተገኘው መጻጉዕ ነበረ፡፡ ክርስቶስ ወደ ሕይወቱ መጥቶ፣ ችግሩን አይቶ፣ ከአልጋ አስነሥቶ፣ ከደዌው ከፈወሰው ከጊዜያት በኋላ፤ ድውዩም መሄድን ለምዶት በመቅደስ ሲጸልይ ጌታ ዳግም አገኘው እና እንዲህ የሚል ኃይለኛ ቃል አስተላለፈለት፡፡ "የሚብስ እንዳይደርስብህ ወደ ፊት ኃጢአት አትሥራ"፡፡
የሚብስ እንዳይደርስብህ ነው ያለው፡፡ የሚብስ፡፡ በክፋት የሚብስ፡፡ በአመፃ የሚብስ፡፡ በግፍ የሚብስ፡፡ በችግር የሚብስ፡፡ በመከራ የሚብስ፡፡ በስቃይ የሚብስ፡፡ በመለያየት የሚብስ፡፡ የሚብሰው እንዳያገኝህ ወደ ፊት ምን አታድርግ አለው? "ኃጢአት አትሥራ" አለው፡፡ የሚብሰው እንዳይመጣበት መከላኪያ መስፈርቱን አስቀመጠለት ማለት ነው፡፡ "ከ38 ዓመት በሽታህ የባሰው እንዳይመጣብህ ወደ ፊት ኃጢአት አትሥራ" አለው፡፡ እኛ እንደ አገር ለዘመናት ከያዘን በሽታችን እንዳንላቀቅ፤ በትናንታችንም፣ በአሁናችንም፣ በሚመጣውም ኃጢአትን ከመሥራት ስላላቆመን ወደ ሚብሰው እንሄድ ዘንድ ግዴታ ነው፡፡
+++
ሁላችን እንደየግል ኃጢአት ስንሠራ ስንሠራ ስንሠራ፤ የሚብሰው ከዘመን ዘመንም እየባሰ እየባሰ እየባሰ መጣ፡፡ ስለሆነ ክፉው ነገር፥ የእርግማኑ ነገር፥ ግራ ዘመሙ ነገር ከጊዜ ጊዜ እየጨመረ ወደፊት ይቀጥላል፡፡ ኃጢአትን መሥራትና የሚብሰው ነገር ኩታ ገጠም ናቸውና፥ ኃጢአትን መለማመድ እስከቀጠልን ድረስ የሚብሰውም እየባሰ ይቀጥላል፡፡ እንኪያስ፥ 'የ2012 ክፉ ነገራት አንገሽግሾናል' ብለን ለአገራችን መልካሙን ዘመን የተመኘንላት ሁላችን ታዲያ ዘንድሮስ ኃጢአታችንን አጠብን ወይ? ንስሐ ገባን ወይ? ንስሐ ለመግባትስ ወስንናል ወይ? የየዕለቱን የአምልኮት ስግደት መስገድ ጀምረናል? ጸሎት ጀመርን? ወደሥጋወ ደሙ ለመሄድ ቆርጠናል? አይ አልቆረጥንም፡፡ ከእውነት ጋር ያልተገናኘ የአፍ ምኞት እንዲሁ ተመኘን እንጂ፤ ዓለም ላይ እንደዘመኑ፥ ዘመኑ የሚጠይቀውን አሟልተን ለመገኘት ዓመታትን በሥጋ ኑሮ ተሳስረን የመጣን ስለሆንን፤ ገሐዱን የዓለም ከንቱነት ምንም ቢሆን ቆም ብለን አካሄዱን የምንመረምረው አይደለንም፡፡ ለምንድነው ይሄ፤ ከውስጥ በኩል ባለው ሳናውቀው ለዘመናት እኛን ሆኖ በተዳበለው ክፉ ጠላት ምክንያት ሰብአዊ የነፍስ ማስተዋላችንን ጥለነዋልና ነው፡፡ ስለዚህ እውነት እውነት እላችዋለሁ፤ ስለ ዘራነው ያልተቋረጠ የኃጢአት ዘር ፍሬውንም እንለቅም ዘንድ ግድ ነው፡፡ "ዛፍ ሁሉ ከፍሬው ይታወቃልና፤ ከእሾህ በለስ አይለቅሙም፥ ከአጣጥ ቍጥቋጦም ወይን አይቈርጡም።" (የሉቃስ ወንጌል 6፥44)
+++
አሁን ያለነው ትውልድ በአብዛኛው ተወራራሽ አማኞችም ሆነን፤ በዐርባና በሰማንያ ቀን ተጠምቀን፤ የሃይማኖት አገር አለን ብለን፤ ግን በምግባር አኗኗር ውስጥ እግዚአብሔርን ጥርግርግ አድረገን ከሕይወታችን ውስጥ አውጥተነዋል፡፡ ስለዚህ አየህ እግዚአብሔር በወጣበት ቦታ ላይ ደግሞ ክፉው መንፈስ ይኖር ዘንድ ያለ አማራጭ ግድ ነው፡፡ መብራቱን አጥፍተን ለምን ጨለማ ሆነ አይሠራም፡፡ የእግዚአብሔር ብርሃን በኑሮአችን ውስጥ ሥፍራ ይዞ እንዳይገለጥ የነፍስን ጩኸት አፍነን ስናበቃ፤ የጽልመቱ አበጋዝ ዲያቢሎስና ሠራዊቱ ሁላችንንም በተናጠል በተናጠል ተሰውረው ቢይዙን አንዳች አይገርምም፡፡ የምለው እውነት ስለመሆኑና ስላለመሆኑ ደግሞ ከዚህ ዓለም ተለይተን በሥጋ ፈርሰን በነፍስ ማየት ስንጀምር ራሳችን እውነትን እናረጋግጠዋለን፡፡ ግን ምን ዋጋ አለው? ያኔ ወደኋላ ተመልሰን ያበላሸነውን ልናስተካክል አንችልም፡፡ "እንግዲህ እንክርዳድ ተለቅሞ በእሳት እንደሚቃጠል፥ በዓለም መጨረሻ እንዲሁ ይሆናል።" (የማቴዎስ ወንጌል 13፥40)
+++
አሁንም ፍጹም እርግጠኛ ሆኜ በማስረጽ እናገራለው፡፡ እናስተውል! ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን የአገር መሪ ስለተቀያየረላቸው፣ በቀለም ትምህርት ከፍታ ጫፍ ስለነኩ፣ በጥበብና በቴክሎኖጂ ምጥቀት ምዕራባውያን ላይ ስለደረሱ፣ የሳይንሱንና የርዮተ ዓለሙን ድንጋጌ በሚገባ ስለተከተሉ፣ ፖለቲካዊ አጀንዳዎች ስለተለዋወጡና የአገር ፖሊሲ ስለ ሁለንተናዊ የእድገት ራእይ ስለተቀረጸ፣ ዜጎች በኢኮኖሚና በማሕበራዊ የአኗኗር ደረጃ ስለተለወጡ ብቻ፤ ኢትዮጵያና ዜጎቿ ብሩህ እና ሉዓላዊ ዘመንን ያገኛሉ ማለት አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ፤ ሕዝቦቿ ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር በፍጹም ልባቸው እስካልተመለሱላት ድረስ የሚገባትን ቦታ ከቶውኑ በዚህ ትውልድ አታገኘውም፡፡ ለምን? ለምን አታገኘውም? ምክንያቱም በዮሐንስ ወንጌል 15፥5 ላይ "ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉምና በእኔ የሚኖር እኔም በእርሱ፥ እርሱ ብዙ ፍሬ ያፈራል።" ይላል፡፡ #ያለ_እኔ_ምንም_ልታደርጉ_አትችሉም ነው፡፡ ይሄ ቃል መሬት በመውረድ ሕይወታችን ውስጥ በመገለጽ ኑሮአችን ላይ ታትሞ የተረጋገጠ ቃል ነው፡፡
ያለ እኔ ምን አትችሉም? ምንም ማድረግ አትችሉም፡፡ ማን እንደዚህ አለ? ኢየሱስ ክርስቶስ፡፡ ኢየሱስ ማለት ከዕብራይስጡ ወደ አማርኛ አተረጓጎም ሲመለስ መድሃኒት ማለት ነው፡፡ ዛሬ የሕይወትን መድሃኒትን አጥተን በሮጥንባቸው መስኮች በሙሉ ከዳር መድረስ ያቃተን በሽተኞች ሆነን እንገኛለን፡፡ ያለ እግዚአብሔር የያዝነው ክርስትናችን ነጠላችን ላይ ተንጠልጥሎ ከቤተክርስቲያን ስንወጣ የሃይማኖት ገጽታችንም በዛው ከልባችን ይወጣል፡፡ ቅዳሴ አስቀዳሽ እንጂ በቅዱስ ቁርባን ተቀዳሽ መሆንን አናውቅበትም፡፡ ስለዚህ ምንም ልናደርግ አልቻልንም፡፡ ያለ እኔ ምንም አታደርጉም ነው በቃ፡፡ ይኸው አየነው ታዲያ፡፡ የአምልኮት ጊዜያቶቻችንን ቆርጠን ስለጣልን በየጊዜው የሚገነፍል ክፉ ነገር በተደጋጋሚ እያወከን፤ ስለማንበረከክ እንደዜጋ ተሳስቦና ተከባብሮ አብሮ መኖር እያቃተን፤ ስለማንጸልይ የግፍ ሥራዎችና ሰቅጣጭ ዜናዎች ከዕለታዊ የቀን ውሎዋችን የማይጠፉ ወሬዎቻችን እየሆኑ፤ ስለማንቆርብ የትዕቢትና 'ለኔ ብቻ' የሚል የኑሮ ባህልን ጠባያችን አድርገን እርስ በእርስ እየተሳደድን፤ ደሞ ከአገርም ተሰደን እንኳ ችግሮቻችን ተከትለውን የሚሰደዱ ሲሆን፤ ሰውም አገር ሆነን እንቅልፍ አጣን፡፡ ውስጠኛ ሰላም አጣን፡፡ እውነተኛ ደስታ አጣን፡፡ ስለዚህ ከ18 ሰዓታት በላይ እየሠራንም የእጆቻችን ፍሬዎች እየደረቁ፤ በረከትና ረድኤት ሸሽቶን፤ ለፍተን ለፍተን የምናገኘው ኢሚንት መና እየሆነ፤ ብዙ ነገር ላይ በብዙ መልኩ ድሃ ሆነን ቁጭ አልን፡፡ እዛ'ጋ ሰማዩ ቃል ምን ነበረ ያለው? "ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉም" ነው ያለው፡፡ እንዳለውም ምንም ልናደርግ ሳንችል እንገኛለን፡፡
+++
አሁንም በ2013፤ እንደ ጋራ እንተወው፥ ቃሉ እስኪፈጸም ድረስ አይሆንምና፤ እንደው እንደ ግል ግን፥ እየባሰ እየባሰ በሚሄደው ዘመን መካከል ሕይወታችሁ ትርጉም በማጣቱ፣ ጤና በማጣቱ፣ ሰላም በመጥፋቱ፣ በረከት በመነፈጉ፣ ጸጋና ሞገስ በመገፈፉ እና በሁሉ ክፉው ጎኑ በኩል እንዳይብስ የምትፈልጉ፤ በዚህ ጽሑፍ ውስጥ በሰማያዊው አባት ለነፍስ የተጠራችሁ ሁሉ ይሄንን ቃል ልባችሁ ላይ በእውነት አድምቃችሁ ጻፉት፡፡ "ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉምና #በእኔ_የሚኖር_እኔም_በእርሱ፥ #እርሱ_ብዙ_ፍሬ_ያፈራል።"

0 Comments