መጽሐፍ ቅዱስ በሁለቱ ሰማያዊ ኪዳናት ማለትም በብለይ ኪዳንና በሐዲስ ኪዳን መንፈሳዊ ቃል በኩል ምድር ላይ የተገኘውን ሁሉ የሰው ልጆች ሕይወት በአንድም በሌላም መልኩ ይነካል፡፡ ይህም ታላቅ መጽሐፍ "ቅዱስ" የተባለበት ምክንያት፤ በእግዚአብሔር መንፈስ የተነገሩ ቃላትና ታሪኮች የተጻፉበት በመሆኑ ሲሆን፤ የሰማዩ ጌታ ደግሞ ለቀረቡት አባት፥ ለሚርቁት አምላክ ሲሆን፤ የእያንዳንዱ ግለሰብ የሕይወት ጊዜ ከእግዚአብሔር መጽሐፍ ቃል ጋር የተጋመደ ነው፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት የኑሮ መንገዳችን ጠርዝና ጠርዙ ሲሆኑ፤ በምንም ተዓምር ሕይወታችን ከዚህ መስመር አፈንግጦ ይወጣ ዘንድ አይቻለውም፡፡ ይህም ማለት፥ ሁላችንም መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ከተጻፉት ሰዎች፣ ታሪኮች፣ ቃላት፣ ትንቢቶችና ራእዮች ውጪ የተለየ ሆነን መኖር በፍጹም አንችልም፡፡ የምድር የአራቱም ማዕዘኗ ጉዞ በአራት ማዕዘኑ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጽፎ ያለቀ ጉዳይ ነው፡፡
ዓመታቶቻችን ተቀጽላቸውን ምሕረት ብለው እንዲጠሩ የዘመናችን ኪዳን የሆነው 'ሐዲስ ኪዳን' ዘመን ላይ ስንገኝ ታዲያ፤ ከላይ እንደተገለጸው ማናችንም ከመጽሐፍ ቅዱስ ቅርጽ ውጪ መቼውኑ ወልፈት አንልምና፤ የሐዲስ ኪዳን መነሻም መድረሻም ባለቤት ከሆነው ከተወዳጁ አባት ኢየሱስ ክርስቶስ የታሪክ ወንጌል ጋር ማንኛችንም በሆኑ ብዙ መንገዶች በየዕለቱ እንገኛለን፡፡
የዚህ ዘመነ ምሕረት የኪዳን ባለቤት ክርስቶስ ሲሆን፤ ከክርስቶስ ወደ መንበሩ መመለስ አስከትለው ያሉት ዘመናትም ምሕረትነታቸው እስካለቀረ ድረስ፤ ያንኑ የክርስቶስ እያንዳንዷ ሽርፍራፊ ሕይወት እንደ ዘመኑና ትውልዱ ራሳቸውን ነጽብራቅ እያደረጉ፤ የክርስቶስን ሕይወት በአንድም በሌላም እያሳዩ እስከ ዓለም ፍጻሜ ይጓዛሉ፡፡
የክርስቶስ ነጸብራቅ ሐዋሪያት ናቸው፡፡ የሐዋሪያት ነጸብራቅ ከነርሱ የተማሩ የተጠመቁት ደቀመዛሙርት ይሆናሉ፡፡ የነዚህ ደቀመዛሙርት ደሞ ተማሪዎች የእነርሱ ነጸብራቆቻቸው ይሆናል፡፡ ይህም ተዋረድ ልብ በሉ፤ እንደ ዘመኑና ትውልዱ እየተዋጀ የሚቀጥል ይሆናል፡፡ ስለዚህም የክርስቶስ ነጸብራቅነት መሰናሰል ነው ሐዋሪያው ለቆሮንቶስ ሰዎች በላከው መልእክቱ ምዕ. 11፥1 ላይ " እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እኔን ምሰሉ።" ያለው፡፡ አንደኛው እኔን ክርስቶስን እመስላለሁ አለና የክርስቶስ ነጸብራቅነቱን ገለጠ፡፡ በሁለተኛው እናንተ እኔን ምሰሉ አለና የርሱን ነጸብራቅነት ደሞ አስተላለፈ፡፡
ይሄ ሆኖ ሳለ፥ ነጽብራቅ ያለው ታዲያ ክርስቶስ ብቻ አይደለም፡፡ ፊሪሳውያኑ፣ ረበናቱ፣ ሰዱቃውያኑ እና አይሁዳውያኑ ሕዝቦች ጭምር ናቸው፡፡ እንግዲህ ይህ ከሆነ ዘንዳ፥ የዛን ዘመኖች ፈሪሳውያን መምህር፣ ረበናት አለቆችና አይሁዳውያን ሕዝቦች በዚህ የቴክሎኖጂና የሳይንስ ርዮተ ዓለም ዘመን ላይ ሲንጸባረቁ እነማን ሆኑ ?
የዘመኑ ፊሪሳውያን አገልጋዮች ጠባያት
" ኢየሱስም። ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠንቀቁና ተጠበቁ አላቸው።" (የማቴዎስ ወንጌል 16፥6)
ጠባይ አንድ ፦ የቤተክርስቲያን ሕግ የአንደበት ጠባቂነት
"ጻፎችና ፈሪሳውያን በሙሴ ወንበር ተቀምጠዋል፤ ስለዚህ ያዘዙአችሁን ሁሉ አድርጉ ጠብቁትም፥ ነገር ግን እየተናገሩ አያደርጉትምና እንደ ሥራቸው አታድርጉ።" (የማቴዎስ ወንጌል 23፥2-3)
ክርስቶስ በዘመነ አገልግሎቱ ጊዜ አብዝቶ የተቸገረበት ጉዳይ፤ የምኩራብ መምህራን የነበሩት በሕዝቡ ዘንድ የተፈሩት ፊሪሳውያን፤ ራሳቸውን የነ አብርሃምና የሙሴ ባላደራ አድርገው፤ ያልጣሰውን ይልቁንም የፈጸመውን ሕግ ጥሰሃል እያሉ ይበጠብጡት የነበረበት ጉዳይ ነው፡፡
የአሁኖቹም የነዚህ ሰዎች ነጸብራቅ አገልጋዮችም፤ የነፍስ መዳን ትምህርት ሰጪ አገልጋዮችን ከሚበጠብጡበት ትልቁ አካሄድ ውስጥ ራሳቸውን ለቤተክርስቲያን ሥርአት ተፋላሚ በማድረግ፤ በአባቶች የቅድስና ጀርባ ተከልለው አምልኮተ እግዚአብሔርን ያዳክማሉ፡፡ በዚህም ጠላትን ለመቃወም መቁጠሪያ ስንይዝ "መቁጠሪያ ለመነኮሳት ነው፥ መቁጠሪያ ለቆረበ ነው፥ መቁጠሪያ ለበቁ አባቶች ነው" እያሉ በየትኛውም የቅድስት ቤተክርስቲያን ሕግ ውስጥ ያልሰፈረ ሥርአት ቀርጸው ይታገላሉ፡፡ ልብ እንበል! እነዚህኞቹ አገልጋዮች የዛሬውን ዘመናዊ ዘመን ዋጅተው የተገኙ ሆኑ እንጂ፤ እሳቤያቸው ከክርስቶስ ዘመን ባለ ሕግ ነን ባይ አገልጋዮች ፈጽሞ አይለይም፡፡ ስለዚህም ዛሬ ላይ "ወጣት ቅዱስ ቁርባን ይቀስፈዋል፣ የየዕለት ስግደት ለበረቱ ሰዎች እንጂ ለልጆች አይፈቀድም፣ ቅባዕ ቅዱስ ከቤተክርስቲያን ውጪ መጠቀም አይቻልም" የሚሉ ካህናት፣ ንስሐ አባቶች፣ ዲያቆናትና በየዘርፉ ያሉ አገልጋዮች አሉ፡፡
እናስተውል! የቤተክርስቲያን ሕግና ሥርአት ይጠበቅ ዘንድ ግዴታ ነው፡፡ ምንም ጥያቄና መልስ የለውም በዚህ ጉዳይ፡፡ ታዲያ ሕጉ ሲጠበቅ አስቀድሞ ሰማያዊ ፍቅርን በማሰብ ነው፡፡ ምክንያቱም ፍቅር ማለት የሕግ መነሻውም መድረሻውም ነውና፡፡ "ፍቅር የሕግ ፍጻሜ ነው።" (ወደ ሮሜ ሰዎች 13፥10)
ፍቅር ያለው ሕግን በፍቅር ያከብራል፡፡ ፍቅር የሌለው ሕግን በታይታ ያከብራል፡፡ ሕጉን ያስጠብቃል እንጂ ራሱ በውል ከልቡ አያከብረውም፡፡ ፍቅር የሌለው ሕግ ስንከተል ፈሪሳዊ ያደርገናል፡፡ በነገራችን ላይ በዘመነ ክርስቶስ ጊዜ የነበሩት ፊሪሳውያን በሕግ መነጽር ብቻ በሥጋ እይታ ስናያቸው አልተሳሳቱም፡፡ ይጠበቅ ያሉትም የሙሴ ሕግጋትን ነው፡፡ ግን ያለ ፍቅር የተከተሉት ሕግ የዲያብሎስ መሣሪያ አድርጓቸው በሕግ ከለላነት የሙሴን አምላክ እስከ መስቀል ደረሱ፡፡ ሕግ ያለ ፍቅር ሞት ነው አየህ፡፡ ሕግ ግን ከፍቅሩ ሲከተል ሕይወት ይሆናል፡፡
በኛ ዘመን ደግሞ ያሉት ፊሪሳውያን፤ ከቀደሙት ዋነኞቹ ፊሪሳውያን ባስ ሳይሉም አይቀርም፡፡ ለምን፤ "ተጣሰ" የሚሉትም ቀድሞውኑ ያልነበረ፥ ያልተጻፈ እንደውም ቤተክርስቲያንን የሚጻረር ሕግን ነው፡፡ በየትኛውም የቅድስት ቤተክርስቲያናችን የቀኖና የዶግማ ሕግጋት ውስጥ "ከቆረቡ ምዕመናን ውጪ መቁጠሪያ መጠቀም አይፈቀድም፣ ወጣት ምዕመናን ለመሳሳት ቅርብ ናቸውና አይቆርቡም፣ ቅባዕ ሜሮንን እንጂ ቅባዕ ዘይትን ከቤተክርስቲያን ውጪ መጠቀም አይቻልም" የሚል አንዳችም በቃልም በጽሑፉም የተቀመጠ ሕግ የለም፡፡ ነገር ግን ዲያቢሎስ የሕዝብ ጆሮን በሚያገኙ አንደበቶች ላይ ተቀምጦ በእምነት ጦር ዕቃ እንዳንዋጋው ሕግን ከለላ አድርጎ በጣም እያጠፋ ይገኛል፡፡
ጠባይ ሁለት ፦ የሕዝብ ትኩረትን አብዝተው ይሻሉ
" ለሰውም እንዲታዩ ሥራቸውን ሁሉ ያደርጋሉ፤ ስለዚህ አሽንክታባቸውን ያሰፋሉ ዘርፉንም ያስረዝማሉ፥ በምሳም የከበሬታ ስፍራ፥ በምኵራብም የከበሬታ ወንበር፥ በገበያም ሰላምታና። መምህር ሆይ መምህር ሆይ ተብለው እንዲጠሩ ይወዳሉ።"
(የማቴዎስ ወንጌል 23፥5-7)
የእግዚአብሔርን ቃል የሚናገርና በቤቱም የሚኖር ሰው በተለምዶ በምዕመናኑ ይፈራል፡፡ ምክንያቱም ሰማያዊ ኃይልንና እውነትን የያዘ ግለሰብ ነው ተብሎ ስለሚታመን ስለ ክብር መፈራቱ መኖር ያለበትም ጉዳይ ነው፡፡ " ለሁሉ የሚገባውን አስረክቡ፤ ግብር ለሚገባው ግብርን፥ ቀረጥ ለሚገባው ቀረጥን፥ መፈራት ለሚገባው መፈራትን፥ ክብር ለሚገባው ክብርን ስጡ።" (ወደ ሮሜ ሰዎች 13፥7)
ፊሪሳውያንና ነጸብራቆቻቸው ታዲያ፤ በቤተእግዚአብሔር ታዛ ሥር በመሆናቸው በሕዝቡ ዘንድ የተፈሩ መሆናቸውን በስነልቦና ያውቃሉና፤ ይህን የበላይነት ስሜት በሁሉም ሰው ላይ በከፍታ ይቀዳጁት ዘንድ ይወድዳሉ፡፡ የዚህ ጠባይ ትልቁ ችግር ታዲያ ወደታች ያለውን፤ ሰይጣን፣ ሰው እና ዓለም የጣለውን ምዕመን ችግር እንደራስ ችግር እንዳይመለከቱ ከፍታው ወደ ማሕበረሰብ የመወረድ ዝቅታን የመጋረዱ ጠንቅ ነው፡፡
የእግዚአብሔር እውነተኛ የአገልግሎት መንገድ ወደጠፉት በጎች ወደታች መሄድ ነው፡፡ ለተቸገሩት ወደሚደረስ የክርስትና ጉዞ የማይመራ ጎዳና፤ የክርስቶስ በፍጹም አይደለም፡፡ ሌላውን በማትረፍ የማይገለጽ አኗኗር የክርስቲያን አይደለም፡፡ ለምን? የወደቁትን የማያነሣ እጅ ለመጣል ቅርብ ነውና፡፡ የተጨነቁትን የማያይ ዓይን፤ ሌላውን በምቀኝነት ለመመልከትና በተለወጠ እይታ ለመበከል አይቸገርምና፡፡ ለወገኑ የማይራራ ልብና ሕሊና፤ ለአመፃና የግፍ ሥራዎች እየፈጠነ ለመሄድ ኑሮውም አጋጣሚዎችም ያስገድዱታልና፡፡ ወደታመሙት የማይሄድ እግር፤ ሌላውን በማጥፋቱ በኩል ርቀትን በመጓዝ የበደልና የእርግማን ሥራዎች ላይ ለመሳተፍ የመንገዱ ምሪት ላይ ክፉዎች እየቀደሙ ወደ ግራው ይወስዱታልና፡፡
የክርስትና አገልግሎት ኃይሉ የሚገለጸው ወደ ሕዝቡ በመውረድ ነው፡፡ ወደ ወደቁት፡፡ ወደተጨነቁት፡፡ ወደታመሙት፡፡ ወደተቸገሩት፡፡ ግራ ወደገባቸው፡፡ መሄጃ ወዳጡት፡፡ ሰላም ወደሌላቸው፡፡ አገልጋይ ስትሆን፥ ላይ ወጥተህ ከቀረህ፤ የምታየው ሁሉ በምቾት የተሰቀለውን ይሆናል፡፡ ሰይጣን በአንድ ወቅት ክርስቶስን ወደ ተራራ አወጣውና የዓለምን ክብር አሳይቶ ስገድልኝ አለ፡፡ መድኅነዓለም ግን ወደታች መመለስንም ያውቃልና "ሂድ አንተ ሰይጣን" አለውና ዓለም ወደተወቻቸው ሊመለስ ከተራራው ወረደ፡፡ ፊሪሳውያን የሆኑት ሁሉ ግን ወደሕዝቡ አይወርዱም፡፡ ይልቅስ ከበሬታን፣ መደነቅን፣ አለሁ አለሁ ማለትን፣ እኔ አውቅላቹኋለሁ ማለትን፣ ከኔ በላይ ለሕዝቡና ለቤተክርስቲያን ላሣር የማለት ለራስ የመመስከር የዓለም ተራራ ላይ ወጥተው ይቀራሉ፡፡ ዛሬ በዚህ ዘመን ይህንን አይነት ጠባይ በግልጽ የሚገልጹ ስመ ጥር የሆኑ ጭምር አገልጋዮች የሉንም?
ጠባይ ሦስት ፦ የቀደሙ ቅዱሳንን ከፍታ ጠቅሶ ማሸማቀቅ
" እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ የነቢያትን መቃብር ስለምትሠሩ የጻድቃንንም መቃብር ስለምታስጌጡና። በአባቶቻችን ዘመን ኖረን በሆነስ በነቢያት ደም ባልተባበርናቸውም ነበር ስለምትሉ፥ ወዮላችሁ።" (የማቴዎስ ወንጌል 23፥29-30)
ከወንጌለ ክርስቶስ ታሪክ ውስጥ አስደናቂው ክፍል የአብርሃም ልጆች ነን የሚሉ ሰዎች የአብርሃምን አባት መስቀላቸው ነው፡፡ የሙሴ ሕግ ጠባቂዎች ነን የሚሉ መምህራን ለሙሴ ሕግ የሰጠውን ንጉሥ ሕግ ጣስክ ማለታቸው ነው፡፡ የዳዊት ዘሮች ነን የሚሉት ካህናት የዳዊት ልጅን ማሳደዳቸው ነው፡፡ በጣም የሚያስገርም ነው፡፡
የእነዚህኞቹ ነጸብራቅ የዘመናችን አገልጋዮች፤ በቤተእግዚአብሔር ስፍራ ላይ ምናልባትም ከልጅነት ጀምሮ የቆዩ ወገኖቻችን ሲሆኑ፤ ስለ ቤተክርስቲያን ትምህርት፣ ሥርአት፣ ትውፊት፣ ንግርትና ታሪክ በዕውቀት ደረጃ በልፋታቸው ልክ የቀሰሙ ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ስለ ቤተክርስቲያን በጣም ኃላፊነት እንዳለባቸው የሚሰማቸው፣ ትልቅ የአደራ ተቀባይነት ጫና እንዳለባቸው የሚሰማቸው፣ የአባቶቻችንን ታሪክና ገድል እንደ ንጽጽር ምሳሌነት በመጠቀም በአገልግሎት የበለጣቸውን የዘመኑን መልካም ባለጸጋ አገልጋይ የሚወርፉ ሰዎች ናቸው፡፡ ለምሳሌ፥ "አባ ተክለሃይማኖት እኮ እንዲህ ናቸው፥ አንተ እንዲህ ነህ" እያሉ የቅዱሳንን የጽድቅ ከፍታ በመጠቀም የዘመኑን በጎ ሰው ለማሸማቀቅ የሚጥሩ ናቸው፡፡ ልብ በሉ፡፡ የዛኔዎቹ አይሆዶች ለነቢያት አባት ክርስቶስ እንዲህ ብለው ሊያሸማቅቁት ሞክረው ነበረ፤ "በእውኑ አንተ ከሞተው ከአባታችን ከአብርሃም ትበልጣለህን? ነቢያትም ሞቱ፤ ራስህን ማንን ታደርጋለህ? አሉት።" (የዮሐንስ ወንጌል 8፥53)
እነዚህ ሰዎች የሚያፈሯቸውም ሰዎች በቅዱሳን አባቶች ገድል ጀርባ ነውራቸውን የሚከልሉ፣ ቀድሞውኑ ይተያይ ዘንድ የማይገባውን የገዳም አባቶች ኑሮ አንተርሰው የከተማ ኗሪ መልካም አገልጋዮችን ኑሮ "ሕይወታቸው ለምን አልተጎሳቆለም፣ ለምን አልተደበቁም፣ ለምን ሕዝቡ አወቃቸው" እያሉ የሚያሳድዱ፣ ስለ ጻድቃን ታሪክ ብዙ ስለተረኩ ብቻ ነባራዊ ጻድቅነታቸውን በውስጣቸው ያነገሡ፥ በመድረክ አንደበት የይስሙላ ትሑታን የሆኑ የክርስቶስ መንገድ ዘጊ የረበናት ፍሬዎች ናቸው፡፡ ግዴየላችሁም፥ ዘመን ዘመንን እንደየጊዜው እየዋጀ ራሱን ነጸብራቅ ያድርጋል እንጂ አዲስ ነገር በምድር ላይ አይመጣም፡፡
ጠባይ አራት ፦ ተደማጭነትን በመጠቀም ተቀናቃኞቻችቸውን ማሳደድ
" ስለዚህ፥ እነሆ፥ ነቢያትንና ጥበበኞችን ጻፎችንም ወደ እናንተ እልካለሁ፤ ከእነርሱም ትገድላላችሁ ትሰቅሉማላችሁ፥ ከእነርሱም በምኵራባችሁ ትገርፋላችሁ ከከተማም ወደ ከተማ ታሳድዳላችሁ፤" (የማቴዎስ ወንጌል 23፥34)
የፊሪሳውያን አገልጋዮች ትልቁ ትልቁ አደገኛነት ይህ ነው፡፡ እርሱም፤ በቤተእግዚአብሔር ውስጥ ሆነው የእግዚአብሔርን ሰዎች የማሳደዳቸው ጉዳይ ነው፡፡ እነርሱ ከሚያውቁት፣ እነርሱ ከሚወዱት፣ እነርሱ ከሚፈልጉት ሰው ውጪ በሰማያዊ ጸጋና ኃይል እየታገዘ ወደ ምዕመን ልብ የሚገባ አገልጋይ ፍጹም ጠላታቸው ነው፡፡ ሲደንቅ ደሞ፤ እነርሱ የሚያውቁት፣ እነርሱ የሚወዱት እና የሚፈልጉት አገልጋይ ጸጋና ኃይል ይኖረው ዘንድ በእግዚአብሔር የተመረጠ አይደለም፡፡
ይህንን ቃል በማጤን እንመልከት፡፡ እንዲህ ይላል፤ " የካህናት አለቆች ግን በርባንን በእርሱ ፈንታ ይፈታላቸው ዘንድ ሕዝቡን አወኩአቸው።" (የማርቆስ ወንጌል 15፥11)
ሕዝቡን ምን አሉአቸው ይላል? አወኩአቸው ይላል፡፡ በሕዝቡ የአንድነት ድምፅ ውስጥ የራሳቸውን የጥላቻ ጥማትና የእርግማን መንፈስ ለማሰታገስ፣ የምቀኝነትን አመልና የክህደት ጠባያትን ለማቆየት፣ የግል አመለካከትን ለማስፈንና ከኔ በላይ ሌላው አፈር ይብላ የሚል የመመጻደቅን የትዕቢት ኃይል ለማውጣት ከበስተኋላ ሆነው ወደፊት ይገፉ ነበረ፡፡ የተሾሙት ግን ሕዝብ ለማገልገል ነበረ፡፡ ወገኖችን ወደ በረቱ ሰማያዊ ርስት ለመስብሰብ እንዲሰሩ ወንበርን የተቀበሉ ነበሩ፡፡ ግን ለሕዝቡ የሚኖሩ አልነበሩም፡፡ በሕዝብ ላይ የሚኖሩ ናቸው፡፡ ወገንን የሚጠብቁ አይደሉም፡፡ በወገን የሚጠበቁ ናቸው፡፡ የከፍታቸውን ቦታና የማዕረግ ሥልጣናቸውን በእውነተኛ የእግዚአብሔር ሞገስና ጸጋ ያልመሠረቱ ስለሆኑ፤ ሲታገሉ ለሥርአቱ ብቻ ይሮጣሉ፡፡ ሰንበትን ያከብራሉ፡፡ ሰውን ግን አያከብሩም፡፡ መጽሐፉን በጥንቃቄ ይይዛሉ፡፡ ቃሉን ግን አይኖሩትም፡፡ ብዙ ሕዝብም ያስከትላሉ፡፡ እንኪያስ እነዚህ ብዙዎች ስለ ክህነታቸውና አገልጋይ መሳይ ማንነታቸው ሲሉ ስለሚሰሟቸው፤ በሸንጎው አደባባይ፤ የሚፈልጉት ውሳኔ ይተላለፍላቸው ዘንድ በሕዝቡ ድምፅ ውስጥ እውነትን የማሳደድ መድረሻ ቃላቸውን በየዘመኑ ያስደምጣሉ፡፡
ጠባይ አምስት ፦ የእግዚአብሔርን ሥራ እያዩ አለማየት
" ያም ቀን ሰንበት ነበረ። ስለዚህ አይሁድ የተፈወሰውን ሰው። ሰንበት ነው አልጋህንም ልትሸከም አልተፈቀደልህም አሉት።" (የዮሐንስ ወንጌል 5፥10)
ይደንቃል፡፡ መጻጉዕ ለ38 ተከታታይ ዓመታት በቤተሳይዳ መጠመቂያ በደዌ ሲሰቃይ አንድም የቤተክህነት መምህር፣ የመጽሐፍት ሊቅ፣ የምኩራብ ሰባኪ፣ ካህን አሊያ አገልጋይ ጠጋ ብሎ አንድ ብርጭቆ ውሃ እንኳን አልሰጠውም፡፡ ይሄንን ጽሑፍ የምታነቡ ዓይኖች ሆይ፥ የድውዪውን መከራ አስቡ፡፡ አጠገቡ መዳኛ መድሃኒት እያየ እጁ ስለማይደርስ ብቻ መድሃኒቱን መዋጥ አልቻለም፡፡ በዚያ የመጠመቂያ ስፍራ 38 ዓመታት ሲተኛ በብዙ የሚቆጠሩ ሰዎች መጥተው ድነው ሄደዋል፡፡ አንዳቸውም ግን መጻጉዕን ወደ መጠመቂያው ያወርዱት ዘንድ ከአልጋ ያስተኛውን በሽታ አልተመለከቱለትም፡፡ በኋላ የችግረኞች አባት ክርስቶስ መጥቶ አየው፡፡ ይሄ ድንቅ አምላክ ማንም ያላየውን ገና ሲያየው ለብዙ ዘመን በስቃይ እንዳሳለፈ ውስጡን አንብቦ አወቀለት፡፡ "በቃ ተነሥ አልጋህን ተሸክመህ ተመላለስ" ሲለው ታዲያ የዘመናት ቁስሉን ለሰኮንዶች ርዝመት በወጣ ቃል ሻረለት፡፡
ይሄንን ያዩ አይሁዳውያን ታዲያ አሁን መጻጉዕን አስታወሱት፡፡ ሲታመም ያልጠየቁት ሲፈወስ አፋጠጡት፡፡ "ሰንበት ነው አልጋህንም ልትሸከም አልተፈቀደልህም አሉት።"
በ38 ዓመታት ውስጥ ብዙ ሰንበቶችን በስቃይ ላሳለፈ ሰው፥ በሰንበት መዳን እንደምን ጉዳይ ይሆናል? የእግዚአብሔር ፈውስ ከሚስጠበት ቦታ ያላቀረቡት የእግዚአብሔር ሕግ አለቆች ስለየትኛው የእግዚአብሔር ሕግ ነው ፈረሰ የሚሉት? በደዌ የተሳሰረ ሰውነቱን አንስተው ወደ ጸበሉ ለማስገባት ፍቃደኛ መሆን ያቃታቸው አገልጋዮች በምን መስፈርት በሽተኛው የታሰርክበት ደዌ ተፈትቶ በሰንበት ትነሣ ዘንድ አልተፈቀድልህም ይላሉ?
እነዚህ ሰዎች ዛሬም በተገባ እጅግ በብዛት አሉ! ያሳዝናል፡፡ ራሳቸውን ያዩ ዘንድ እግዚአብሔር ይያቸው፡፡ መተት ያሠራቸው ሲፈቱ ሥርአተ ቤተክርስቲያን መጣስ አለመጣሷን ለማረጋገጥ ዶሴ የሚፈትሹ፣ ቡዳ የበላቸው ምስኪን ዜጎች ከሕመማቸው ሲላቀቁ የማጥመቅ ፍቃድን ለማስከልከል ፍትሐ ነገሥቱን የሚገልጡ፣ በሰላቢ መንፈስ ምክንያት በረከት በማጣት ለዘመናት በድህነት የሚማቅቁ ሰዎች ጠላታቸውን በመቁጠሪያ ሲዋጉ ዓይናቸው የሚቀላ መምህራን፣ ካህናት፣ ዲያቆናት፣ ዘማሪያን መሰል የቤተክርስቲያን አገልጋዮች የጌታን መስቀል በትከሻቸው አንጠልጠለው በልባቸው ትከሻ የግራውን ወንበዴ መስቀል ያነገቱ ብዙ ሺዎች አሉ፡፡ ልብ ይስጥልን፡፡
የየዘመኑ አገልጋዮች ፊሪሳውያን ይሆኑ ዘንድ ነጸብራቅነቱን የሚያስገድዱት መናፍስት እነማን ናቸው?
" እናንተ ከአባታችሁ ከዲያብሎስ ናችሁ የአባታችሁንም ምኞት ልታደርጉ ትወዳላችሁ። እርሱ ከመጀመሪያ ነፍሰ ገዳይ ነበረ፤ እውነትም በእርሱ ስለ ሌለ በእውነት አልቆመም። ሐሰትን ሲናገር ከራሱ ይናገራል፥ ሐሰተኛ የሐሰትም አባት ነውና።" (የዮሐንስ ወንጌል 8፥44)
በየዘመኑ ሁሉ የሚገኙ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉትን ወይ መልካም የእግዚአብሔር ሰዎች አሊያ በተቃራኒው የዲያብሎስ መሣሪያ ሰዎች ናቸው፡፡ ነጸብራቅነቱ ሳይቋረጥ እስከ ዕለተ ምጽዕት እንዲቀጥል የሆነው በነዚህ ሁለት የተለያዩ መናፍስት ምክንያት ነው፡፡ ቅዱስ መንፈስ ሰዎች ላይ ሲያድር ጊዜ፤ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱሶቹ ቅዱስ ሰዎች ይሆኑ ዘንድ የሕይወት ጉዞአቸውን ኃላፊነት እግዚአብሔር ይረከባል፡፡ ርኩስ መንፈስ ሰዎች ላይ ሲያድር ጊዜ፤ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱሶቹ ርኩስ ሰዎች እንዲሆኑ የዕድላቸው ምሪትና አቅጣጫ በአጥፊው መንፈስ መዳፍ ውስጥ ይገባል፡፡ በመሆኑም የፊሪሳዊነት ነጽብራቅን በየዘመኑ ሁሉ እያስጠበቁ የሚሄዱት መናፍስት
☞ ጠቋር
☞ የአረማዊ ደብተራ መተት፣ ድግምት፣ ሟርት
☞ የአውደ ነገሥት መናፍስት
☞ የአረማዊ መፍትሔ ሥራይ ተዋርሶ መናፍስት
☞ አብረው ከዘር ተወልደው አድገው አገልጋይ የሆኑ መናፍስት
☞ ስለ አገልግሎት ብልጽግና ተብለው በሚወሰዱ፣ በሚቀበሩ፣ በሚጠጡ ነገራት ላይ የተዋረሱ መናፍስት ናቸው፡፡
" እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ በውጭ አምረው የሚታዩ በውስጡ ግን የሙታን አጥንት ርኩሰትም ሁሉ የተሞሉ በኖራ የተለሰኑ መቃብሮችን ስለምትመስሉ፥ ወዮላችሁ።" (የማቴዎስ ወንጌል 23፥27)
በመጨረሻም፥
በቤተክህነት ቀሚስ ሥር ፊሪሳዊነትን ያጠለቁ ሰዎችን በሥጋ ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ ቃል በኩል ውስጣቸውን እንገነዘበው ዘንድ ሕይወታቸውን ዋቢ አድርገው የእውነት መስታዎት የሆኑንን የሐዋሪያት የዘመኑ ነጽብራቅ መልአከ መንክራት መምህር ግርማን እናመሰግናለን፡፡ ፊሪሳውያኑ እንደሚሉን እሳቸውን ሳይሆን እሳቸው ያሳዩንን ክርስቶስ ዕለት ዕለት እየተከተልን ገና ብዙ ሰው እናስከትልማለን፡፡

0 Comments