በቁጥር የበዛን ሰዎች፤ በመንፈሳዊ ዓለም ውስጥ ኑሮአችንን ጠቅልለን በመግባት ሕይወታችንን ሰማያዊ አድርገን ለመምራት እንዳንችል ከምንቸገርባቸው አያሌ ምክንያቶች መካከል አንደኛው፤ ሁለት ፍጹም የተለያዩ የተራራቁ ነገራትን በግድ አቀራርበን ያለ ውላቸው በአንድነት ለማቆየት በምንታገለው ትግል ውስጥ የሚፈጠረው ራሱን የቻለ ችግር ምክንያት ነው፡፡
አንድ ጤናማ እምነት ያለው ሰው ወደ እግዚአብሔር ይሄድ ዘንድ መሻቱ የሚጠበቅ የሰውነት ሕልውናው ነው፡፡ ምክንያቱም ከላይ የሚታየውን ሥጋችንን ሕያው አድርጋ የምታቆየው ነፍሳችን፤ ከእግዚአብሔር መለኮታዊ ኃይል የወጣች ክፍሉ ነችና፤ ዘወትር እርሱን ትፈልግ ዘንድ ሰማያዊ ስበት አላት፡፡ በዚህ የነፍስ ፍቃድ ውስጥም ብዙዎቻችን ተጎብኝተን፤ ወደ ሰማዩ አባታችን ለመሄድ በምናደርገው ጉዞ ውስጥ ታዲያ፤ አንድ እግራችን ወደ ፊት ወደ እግዚአብሔር መንገድ፥ አንድ እግራችን ደግሞ ወደ ኋላ ወደ ዓለም ጓዳና እየረገጠብን፤ መለስ ቀለስ የሃይማኖት መስመር ላይ ቆመን የምንዋትት ሰዎች በትንሽ ቁጥር የተገኘን አይደለንም፡፡
ብዙዎቻችን፤ እግዚአብሔርን በልባችን፣ በአሳባችንና በእቅዳችን ላይ አስቀድመን ስንፈልገው፤ በምግባራችን ደግሞ ዓለምን እና ጉዳዯን እናስቀድማለን፡፡ በዚህ መንታ መንገድ ላይ ቦታ እየቀያየርን የምንኖር ሰዎች፤ ጠባያችንና ልምዳችንም እንደ ውሎአችን ራሱን እየቀያየረ፤ ከመንፈሳዊ ወደ ዓለማዊ፥ ደግሞ ከዓለማዊ ወደ መንፈሳዊ እየተገለባበጥን በሁለት ቢላ እንበላለን፡፡ ብዙ ክርስቲያኖች፤ ሰንበተ ክርስቲያን እና የነፍስ ጊዜ ሲሆን ጊዜ፤ ቤተክርስቲያን እንሄዳለን፡፡ ቀዳሚት ሰንበት እና የሥጋ ጊዜ ሲሆን ጊዜ፤ ኃጢአት መሸመቻ ቤቶች እንሄዳለን፡፡ የእግዚአብሔርን ቃልና ስብከት እንሰማለን፤ እርሱን ሰምተን በልቦናችን እንኳን ይዋሐድ ዘንድ አንዳንዴ ጊዜም ሳንሰጥ ሐሜትና ክፉ ወሬ ወዲያው ሰምተን እናሰማለን፡፡ ሙዚቃና መዝሙር በአንድ ስልክ የምናጫውት ሲሆን፤ ንግሥ ሲሆን፣ ክብረ በዓል ሲሆን፣ ሲከፋንና ሲያሰኘን መዝሙሩን እንሰማና፥ መዝናናት ሲያምረን ደግሞ ወደ ዘፈኑ ስንዞር፤ እንደው ተሳስቶ ስልኩ በተከታታይ የማጫወቻው ቅደም ተከተል(playlist) መካከል መዝሙር ካጫወተ፤ ተሸቀዳድመን ስናሳልፈው ሌላ ጊዜ ዳግም መዝሙር የማንሰማ እንመስላለን፡፡ እንዲሁ በአለባበስ፣ በዘይቤ፣ በንግግር፣ በፍላጎት፣ በኑሮ አካሄድ ላይ፤ እንደ ጊዜው አንዴ መንፈሳዊ ደግሞ ዓለማዊ በመሆን ውስጥ፤ ለዘመናት ይዘነው የመጣነው ዓለማዊ ፍቃድን በመንፈሳዊው አካሄድ ላይ ደባልቀን መገኘት፤ ክርስትናን ከአንገት አሳልፈን ልብ ላይ ላለማሰራችን አንዱ መገለጫ ነው፡፡
ሲሆንም፤ ከዘልማድ ክርስትና የመላለቀቂያ መንገዱንም አውቀው፤ የዲያብሎስ ሚስጢራዊ አሠራርና ተንኮል ላይ ነቅተው፤ መስገድና መጸለይ የጀመሩ ሰዎችም፤ ከሚገጥማቸው ወሳኝ የፈተና ምዕራፍ ውስጥ ይኸው በዓለምና በመንፈሳዊ ሕይወት መካከል መዘበራረቅን የተመለከተው ጉዳይ ነው፡፡ ወደፊት እየሄድን፣ ጠላትን እየተዋጋን፣ የተዘጉ በሮችንም እያስከፈትን፣ በበረከትና በሞገስ ለመኖር ልንጀምር ስንል፤ ወደኋላ ለማየት የሚዳዳን ብዙ ጊዜ አለ፡፡ አንድ ወቅት ላይ ሎጥና ቤተሰቡ ከቁጣ ዘመንና ትውልድ በስተፊት በሚሸሹበት ጊዜ፤ ወደፊት በሚደረገው ጉዞ መካከል የሎጥ ሚስት ወደኋላ ዘወር ብላ ብትመለከት፤ የጨው ሐውልት ሆነች፡፡ እንግዲህ ዓለምን ለመሸሽ ወደፊት ወደ መንፈሳዊ ቦታ ለመድረስ በምታደርገው የትንንቅ ጉዞ መካከል፤ ዓለምን እየናፈቅህ ስትጓዝ የሚገጥምህ ዕጣ እንዲህ አይነት ይሆናል፡፡
ምናልባት ኑሮአችንን አስተውለን አልተመለከትነው ይሆናል እንጂ፤ የእግዚአብሔርን መንገድ ይዘን ወደፊት ወደ ቅድስና፣ ወደ ጽድቅ፣ ወደ በረከት፣ ወደ ጸጋና ሞገስ የሚወስደውን ጓዳና ተከትለን እየሄድን፤ ወደኋላ ትተን ወደመጣነው ሱስ፣ አመል፣ ጠባይ፣ ፍላጎትና ልማድ በተመለከትን ቁጥር እንደሎጥ ሚስት የጨው ሐውልት የሆንንበት አጋጣሚ ብዙ ነው፡፡
ሐውልት አይንቀሳቀስም፡፡ እኛም፤ ሄድ መለስ በሚለው የክርስትናችን ምሪት ላይ ስንቆም፤ ወደፊት እንዳንሄድ ትተን የመጣነው የዓለም ጉዳይ ሥጋችንን እያዘገየው፥ ወደ ኋላ እንዳንመለስ የዓለም ከንቱነትን በነፍስ በኩል አስተውልን ስንነቃ፤ ወደ መነሻም፥ ወደ መድረሻም ሳንጓዝ፤ መካከል ላይ ረጅም ጊዜ እያጠፋን፤ ሳናጣና ሳናገኝ ቀናቶቻችንን በአንድ የአዙሪት ተመሳሳይ ቅርጽ ልክ ሰፍተናቸው፤ መንፈሳዊ አቅማችንን ሳናሳድገው ዘመናችንን እያሳለፍን እንገኛለን፡፡
በአንዱ ለመንቀሳቀስ አንዱን ከእውነት መምረጥ
መጽሐፍ ቅዱስን በምናነብበት ጊዜ፤ በዚህ በማቴዎስ ወንጌል 27፥21 ላይ አገረ ገዢው ጲላጦስ ለሕዝቡ አንድ ጥያቄ ሲያቀርብ እንገኘዋለን፡፡ በአንድ ጎን ያለ በደሉ በሸንጎ አደባባይ የቆመውን ክርስቶስን፤ በሌላ ጎን በበደሉ እንዲፈረድበት የቆመውን በርባንን በተመለከተ፤ መርጠው እንዲፈርዱባቸው የሚዛኑን ውሳኔ በሕዝቡ ድምፅ ላይ ለማስቀመጥ ጥያቄ ጠየቃቸው፡፡ እንዲህ ብሎ ነበረ የጠየቃቸው፤ "ከሁለቱ ማንኛውን ልፈታላችሁ ትወዳላችሁ?"
ይሄ ጥያቄ ዛሬም በኛ ሕይወት ውስጥ ዘወትር ያንቃጭላል፡፡ እኛስ ማንን መርጠናል? ክርስቶስን ነው በርባንን? ሥጋችንን ነው ነፍሳችንን? ዓለማዊነታችንን ነው መንፈሳዊነታችንን? ጥያቄው ዛሬም ድረስ አለ፡፡ ስለዚህ የቱን መርጠናል? አንዳንዶቻችን ጥያቄውን ባለማወቅ መልሰነዋል፡፡ አንዳንዶቻችን ወደንና ፈቅደን መልሰነዋል፡፡ ገሚሶቻችን ተገደን መልሰነዋል፡፡ ብዙዎቻችን ግን ሁለቱንም ለመምረጥ ስንታገል፤ ምርጫዎቹ ተራርቀው ቆመዋልና፤ ሁለቱንም በአንድ እጅ ለመያዝ በመጣር ውስጥ መሰብሰብ አቅቶን፥ ሁልግዜ አሳባችን፣ ቋንቋችን፣ እንጀራችን፣ እውቀታችን፣ ገንዘባችን፣ ራእያችን መንታ መንታ መንገድ ላይ እየወደቀ ሲበተን ጊዜ ተደበላልቀን ቁጭ አልን፡፡ እንኪያስ፥ ዛሬ ስቀን ተጫውተን፥ ነገ ስንበሳጭ ትናንት ትንሽ እንኳ የተደሰትን አንመስልም፡፡ ትናንት በፍቅር ውለንና ሰላማዊ ሆነን፤ ዛሬ ስንራገምና እየተረበሽን ስንውል በቶሎ መለዋወጣችን አይገባንም፡፡ አንዳንዴ የባሕሪያችን መገለባበጥና መተራመስ፤ የቀናትን መፈራረቅንም ሳይጠብቅ እዛው ተደስተን እዛው በቅጽበት ስንከፋ፥ የቆምንበትን ለማስተዋል የተራመድንበትን መንገድ መለስ ብለን የመመርመር ጎዳና ላይ የተደረገ ጉዞ ስሌለን ወይንም የመጓዝ አቅሙ ስላጠረን፤ የተገኘንበትን የምናመዛዝንበት ጊዜና ጉልበቱ ሸሽቶናል፡፡
በዚህ ዘመንና ትውልድ 'የባቢሎን ጊዜ' በእጅጉ በረታ፡፡ የባቢሎን ጊዜ በሰናዖር ሜዳ የሰዎች ቋንቋ የተደበላለቀበትና አንዱ አንዱን ማገዝ እንዳይችል መግባባት የማያስችል ወቅትና ሰዓት ነው፡፡ የዛሬው የባቢሎን ጊዜ በልባችን ውስጥ ነው፡፡ ምግባራችን ላይ ይታያል፡፡ ድምፃችን ላይ ይሰማል፡፡ አካሄዳችን ላይ ይነበባል፡፡ አንዴ መንፈሳዊ፥ አንዴ ዓለማዊ እየሆነ በሥጋና በነፍሳችን ፍቃድ መካከል ከውስጥ ያልተግባባው ማንነታችን ወደ ውጪም በተገለጠ ጊዜ፤ የተግባባ የአንድ ምዕራፍ መስመር ላይ አቅጣጫውን ጠብቆ ለመሄድ ሲከብደው፤ ትናንት መንፈሳዊ ሆነንበት ያሳለፍነው ሰዓትና ደቂቃን ዛሬ ከርብተነው አረማዊ ለመሆን ፍቃዳችንን አሳልፈን ስንሰጥ "ምንድነው ነገሩ?" ብለን ራሳችንን ለመፈተሽ ወደ ውስጣችን አላየንም፡፡
ይልቅ፥ ዛሬ ዛሬ መንፈሳዊነትን ከአረማዊነት አግባብቶ ለመያዝ በሚደረገው ትግል ውስጥ የተጠመቀ አህዛባዊነት በሕይወታችን ዙፋን ላይ ነግሦ፤ ቢነግሩት የማይሰማ፣ ቢመክሩት የማይገሰጽ፣ ቢቀሰቅሱት የማይነቃ፣ ቢለምኑት የማይቀበል ሞገደኛ ጠባያትንና የባሕሪይ አመልን አበልጽገን ስንይዝ፤ መንፈሳዊነትን መርጠው በሚታገሉ ሰዎች በጎ ሲደረግ አይስማማንም፡፡ ቢስማማንም አንሳተፍም፡፡ ለምን፤ ባቢሎን ከውስጥ ነዋ ምን አደከመህ በቃ፡፡ የውስጥ ቋንቋችን ስለተደበላለቀ፤ በውጪ በምናወራው አንድ ቋንቋ ተግባብተን ለመልካሙ ነገር አንደጋገፍም፡፡ በመሆኑም ብዙው በጎ ነገር ላይ በጋራ ተስማምቶ ለመገኘት እየተሳነን በየተናጠል ራቅ ብለን እናያለን፡፡ ከሩቅ በመመልከታችን ክፍተት ውስጥ ታዛቢ ስንሆን፤ ለማፍረስ የሚቸኩል ስብእና፣ ለመተቸት የሚሮጥ አሳብ፣ ለመጣል የሚሮጡ እግሮች፣ ለመገፍተር የሚፋጠኑ እጆች የመያዝ አዝማሚያዎችን ተቀብለን፤ እንደ ጊዜው፤ ጊዜውን መስለን ስንኖር፥ ቀኝም ግራም ነክተን መምጣትም መሄድም አቅቶን የተምታታ የኑሮ መስመርን እንከተላለን፡፡ ታዲያ እንዴት ነው ነገሩ? ለምንድነው በየዕለቱ የምንደበላለቀው? ለምንድነው ረግቶ መቆየት የተሣነን?
ምክንያቱም መሠረታዊውን የሕይወት ጥያቄ አስረግጠን አለመለስንምና ነው፡፡ በመሆኑም ገና ሮጠንባቸው ከዳር ያላደረስናቸው ጉዳዮች በይደር እየተላለፉ ጥያቄውን እንዳንመልስ ወጥረውን ይዘዋል፡፡ አሊያም ነገ የሚጎድለው ነገር ላይ ዛሬ ሙሉ ነገርን ለማከማቸት እያደረግነው ያለነው ከፍተኛ ትግል የጊዜያችንን ገሚሱን ክፍል ፈትኖት እረፍት አልባ አድርጎናል፡፡ ስለዚህ ወሳኙ የጲላጦስ ጥያቄ ሳይመለሰ እየባተተ፤ ስንዋዥቅ እንድኖር ተገደን ቁጭ ብለናል፡፡
እስኪ እናስበው ጥያቄውን፡፡ "ከክርስቶስና ከበርባን ከሁለቱ ማንን ልፈታላችሁ ትወደላችሁ?" ይለናል ጲላጦስ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ክርስቶስም በርባንም በኛ ውስጥ ታስረዋልና ነው፡፡
ከውስጣችን ክርስቶስ ሲታሰር፤ መንፈሳዊ ሕይወታችን ብዙው ሂደቱ ላይ ማነቆ የሆነ መልክን እየገለጸ፤ በጎነታችን ታስሮ፣ ፍቅር መስጠታችን ታስሮ፣ ትሑት የመሆናችን ዝቅታ ታስሮ፣ ለሌላው ደግ ማሰባችን ታስሮ፣ ሰማያዊ እውቀትና ማስተዋላችን ታስሮ፣ መንፈሳዊ ፍላጎታችንና እቅዳችን ታስሮ፤ የነፍስ ፍቃዳችን በእንጀራውና ወጡ፣ በሥራ ድካሙ፣ በትምህርት ሥልጠናው፣ በፌሽታ ሁካታው፣ በትዳርና በልጆች ውጥረቱ ተሸብቦ፤ የመለኮት ምሪት በኑሮአችን ውስጥ ሕይወታችንን ሊመራ የሚችልበትን ክፍተት አሳልፎ መስጠት ከብዶን፤ ነፍሳችንን አስረን ሥጋችንን ፈትተን እየኖርን አለን፡፡
ደግሞ በግራ ጽንፍ የቆመው በርባን ከኛ ውስጥ ሲታሰር፤ ድንገቴ ቅዱስ እየሆንን፣ የትንሽ ቀን ብዙ ጻድቅ እየሆንን፣ ዞረን የምንመለስባትን ዓለም "ዓይንሽን ላፈር" እያልን፣ ከደቂቃዎች በኋላ ለመከተል የማንፈልገውን ሰማያዊ ቃል በደስታ እየተቀበልን፣ ለጊዜያት ያልጎበኘናት ቤተክርስቲያችን ትዝ እያለችን፤ እንደ ሥጋ ብቻ የምንመላለስበትን ቀን በመርገም በሰግደት ያልጸደቀ 'ልብ ስጠን' የሚል ተማጽኖን በማሰማት፤ ነፍሳችንን ለተወሰኑ ጊዜያት ትንፋሽ እንሰጣታለን፡፡
አንዳንዶቻችን ደግሞ ክርስቶስንም፥ በርባንንም ከውስጣችን አስረን፤ ገልለተኛ በሚመስለን ነገር ግን የበርባን ቁመተ ክፍል በሆነ ደንባራ ፍልስፍና፣ መላ ቅጡ ያልተለየ አመለካከት፣ ብቸኝነትን በሚፈልግ ውጥንቅጥቅ ጠባይ ተይዘን፤ ከብርሃን አሊያ ከጨለማው የተለየ ሦስተኛ አማራጭ በሌላት ዓለም፤ ብርሃንንም ጨለማንንም አንፈልግም ብለን በግራ ገብ እይታ ውስጥ የምንዳክርም ሰዎች ጥቂት በማይባል ቁጥር እንገኛለን፡፡
ዲያቢሎስ ዓለምን እንድንመርጥ ይታገላል
በክፉው መንፈስ የጥፋት አሠራር ውስጥ በአንድ ወጥነት ሳይለወጥ ሁላችን ጋር የሚመጣው ፈተና፤ በመንፈሳዊነት በኩል ያለውን እውነታና ሰማያዊ ኃይል ከዓይናችን ፊት በመጋረድ ዓለምን ብቻ የማሳየት አካሄዱ ነው፡፡
ዓለም የዲያቢሎስ ናትና፤ ዲያቢሎስ ሁሌ ዓለምን ያሳያል፡፡ ክርስቶስ በገዳመ ቆሮንቶስ ውስጥ ባደረገው የመንፈሳዊነት ትግል ውስጥ፤ ፈታኝም ወደርሱ ቀርቦ የዓለምን መንግሥታትና ክብራቸውን ሁሉ አሳየው፡፡ (የማቴዎስ ወንጌል 4፥8)
የዛኔ ወደ ክርስቶስ ከውጪ ቀርቦ የነበረው፤ ዛሬ ከውስጣችን ያለው ፈታኝ፤ እንደ ጌታችን ከውጪ ወደ ውስጥ ሳይሆን፤ ከውስጥ ወደ ውጪ ዓለምን እያሳየን፤ በሥጋ ትሩፋቶች በኩል የሚመጡትን ውጤቶች፣ ምቾቶች፣ ጥቅሞች፣ ደስታዎች፣ እረፍቶች፣ ድካሞች፣ ጎዶሎዎች፣ ግማሽ ነገሮች ላይ ትኩረት እንድናደርግ፤ የምድራዊ አኗኗር ጥገኝትን ከኑሮአችን ድጋፍ ሥር ሲያኖር ጊዜ፤ ከነጠላ በታች የተከለለ ቅብ ጸጉርን አሲይዞ፤ ከዕድለኝነት ጀርባ ያልተነገረ ሙሰኝነት ውስጥ ከትቶ፤ ጠበል ጻዲቅም አስካሪ መጠጥም የሚጠጣ ጊዜን እንዳናሳልፍ አድርጎ፤ በመንፈሳዊውና በዓለማዊው ዓለም መካከል እያገለባበጠን፥ ዓለምን ባሳየን አቅም ልክ ለገንዘብ፣ ለርዮተ ዓለም እውቀት፣ ለጥበብና ለዝና በተግባር እንድንሰግድ አሰገደደን፡፡
ምርጫው ላይ እንወስን
በርባንና ክርስቶስ ዛሬም ግራና ቀኝ ቆመዋል፡፡ እናስተውለው ዘንድ የሚያስፈልገው ነገር፤ ይሄ ምርጫ ዘወትር በየቀኑ እንደየሕይወታችን አጋጣሚ መቅረቡን ይቀጥላል፡፡ ሰላም ሰጪነትን እና ሰላም ነጣቂነትን የሚወስኑ ሁነቶች በየቀኑ ምርጫ ሆነው አሉ፡፡ መታገስ እና አለመታገስን የሚፈትኑ ነገራት ዘወትር አሉ፡፡ ቁርጠኝነትን አሊያ ግዴየለሽነትን የሚያስመርጥ አጋጣሚ በየዕለቱ ወደኛ ይመጣል፡፡ ይቅርታ ማድረግ እና በደልን መመዝገብ አሁንም ምርጫችን ነው፡፡ ቸርነትና ንፉግነት በየኑሮአችን መስመር ላይ ተራርቀው ቆመው መልሳችንን ይጠብቃሉ፡፡ ስለዚህ እንወስን፡፡ ማንን መርጠናል? በርባንን ነው ክርስቶስን?
ልብ እንበል! ዓለም፤ የምርጫ ኮሮጆዋን ለበርባን ከሰጠች ቆይታለች፡፡ ያኔ በዘመነ ክርስቶስ፤ የበዙት ሰዎች ስለ በርባን እንደጮኹ ሁሉ፤ ዛሬም ይኸው ጊዜ ራሱን ሲደግም ብዙ ሰዎች ወደ ተገለጠው በርባን ይጮኹ ዘንድ ውስጣቸው ያለው ያልተገለጠው በርባንን ጥፋትን፣ ግፍን፣ አመፃን፣ ስግብግብነትን፣ ትምክህትን፣ ግንፍልተኝነትን፣ ቸልተኝነትን፤ እየመራ፥ የብዙሃን ድምፅ የአንድነት ፍላጎት ሆኗል፡፡ እንኪያስ፥ ምርጫችን ክርስቶስ ከሆነ ዘንዳ፤ ከውስጥ ካለው በርባን ጋር በየሰኮንዱ ልንታገል ግድ እንደሚያስፈልገን እናስተውል፡፡ 'የዓለም መናኝ' ሆኖ ለመኖር በመጀመሪያ ከውስጥ ያለው በርባን በየቀኑ መታሰሩን ማረጋገጥ ግድ ነው፡፡ አለበዚያ ሁለት ዛፍ በአንዴ እንወጣ ስንል፤ መድረሻ ማረፊያችን የሚሆነው ሁለቱንም ዛፍ አለመውጣት ነው፡፡ ሁለቱንም አለመውጣት ሆነ የግራው ዛፍ ላይ መገኘት ደግሞ የውስጠኛው በርባን ፍላጎት ነው፡፡

0 Comments