ናትናኤል ሰሎሞን
በአብዛኛው በሚባል የገለጻ ደረጃ፤ ሰዎች ውስጥ አስቀድመው በመዋረስ ጠባይን፣ ልምድን፣ ባሕሪይን፣ የኑሮ አካሄድንና የሕይወት አቋምን በመጋራት ተመሳስለው አድፈጠው የሚገኙት መናፍስት የዛር መናፍስት ናቸው፡፡
የዛር መንፈሶች ረዘም ባለ በትውልድ የዘር ሐረግ ተከታታይነት ውስጥ ሰርገው በመግባት፤ ከማኅፀን ጀምሮ አብረው ልክፍት ሆነው በመወለድ፤ አዲሱን ትውልድ ገና ከመነሻው አንስቶ በመቆራኘት፤ የቤተሰቡን የዘር መዋቅር በመጋራት የተሰወረ ባላንጣ ሆነው አብረው ያድጋሉ፡፡ "አባቱንም። ይህ ከያዘው ስንት ዘመን ነው? ብሎ ጠየቀው። እርሱም። ከሕፃንነቱ ጀምሮ ነው፤" (የማርቆስ ወንጌል 9፥21)
በተጨማሪም እንደ ዛር መናፍስት ረጅም የትውልድ ሐረግን አቆራርጠው ባይዋረሱም፤ ሌሎች መናፍስትም ከማኅፀን ጀምሮ አብረው ተወልደው ተመሳስለው ያድጋሉ፡፡
እንደተገለጸው፤ ብዙ ጊዜ፥ በመጀመሪያ አንድ ግለሰብ ውስጥ አስቀድመው ሊኖሩ የሚችሉት መናፍስት በደም ሐረግ ውስጥ አብረው በመዋረስ የሚመጡት የዛር መንፈሶች ናቸው፡፡ እናትና አባት የአምልኮተ እግዚአብሔር አኗኗርን ባልመሠረቱበትና ያለ ቅዱስ ቁርባን መቀ'ደስ የሚወልዱት ልጅ፤ የዛር መንፈሱ ተጠቂ ሆኖ ከአጥፊ ጠላት ጋር አብሮ ያድጋል፡፡ ይኸው ልጅም፥ እያደገና እየጎለመሰ በሚመጣበት የተፈጥሮ ዑደት ውስጥም፤ ከእውቅናው ውጪ አብሮት በመፀነስ፥ አብሮ የተወለደው የእናትና የአባት የዛር መንፈስ፥ ሌሎች የክፉ መንፈስ ዓይነት የሆኑትን መተት፣ ዓይነጥላ፣ ቡዳ፣ ቁራኛ፣ ድግምት፣ መስተፋቅር አና ወዘተ.. መንፈሶችን ከውጪ ወደ ውስጥ እየሳበ በማስገባት ሠራዊት ይጨምራል፡፡
በተለይ በዚህ በመተቱ፣ በድግምቱ፣ በሟርቱ፣ በመስተፋቅሩ፣ በመስተባርሩ ወይንም በሌላ ክፉ መንፈሶችን በማዋረሻ ዘዴን በመጠቀም፤ በመተተኞች በአስማተኞች፣ በጠንቋዮች፣ በአረማዊ ደብተራዎች፣ በሟርተኞችና የመሳሰሉት የጥፋት ጥበብ ፈጻሚዎች በኩል ሰዎች ሌላ ሰዎች ላይ አጥቂ መናፍስቱን ሲልኩ መስማት አሊያ ማወቅ ትንሽ ለማይባሉ ሰዎች አግራሞትን የሚፈጥር ጉዳይ ሲሆን እናገኘዋለን፡፡ በዚህም ምክንያት ስለዚህ ነገር ሰዎች "እንዴት አንድ ሰው ሌላው ላይ ሰይጣንን ይልክበታል? እንዴት ሰው ጨካኝ ቢሆን ነው የዘላለም ሕይወትን የሚያሳጡ መርዛማ መንፈሶችን ወደ ሌላ ሰው ሕይወት ለጥፋት የሚሰድደው? ምን አይነት ሕሊና ማጣት ቢከሰት ነው አጋንንትን ወደ ሌሎች ኑሮ ሰዎች የሚያዋርሱት?" ሲሉ ይሰማሉ፡፡
እዚህ ጋር ታዲያ በጣም አጽንዖት ሰጥተን እንድናስተውል የሚያስፈልገው ጉዳይ፤ ሰዎች ራሳቸውን ለክፉ ፈቃድ አሳልፈው የመስጠት ወጥመድ ውስጥ በመውደቃቸው የሚሠሩት ስህተት እንጂ፤ መተት የሚልኩት፣ በጠንቋይ የሚያስጠነቁሉት፣ በአስማተኛ የሚያስተበትቡት ሰዎች በሙሉ ክፉዎች ሆነው አይደለም፡፡ ይልቁኑ፥ መተት ለላኩብን ሰዎች "ጌታ ሆይ፥ አያውቁምና ይቅር በላቸው" እያልን አባታችን ክርስቶስን ብንመስል፤ አንደኛ የላኩት መንፈስ በእጅጉ ይደክማል፥ በቶሎም ይጋለጣል፡፡ ሁለተኛ ታላቅ ጸጋና በረከትን እናገኛለን፡፡
ሰዎች ወደው ሌሎችን በክፉ መንፈስ እንደማያጠቁ የተጠቀሰው አሳብ ማሳያ የሚሆነን መረጃ ከላይ የተገኘው የመናፍስት ሠራዊትን የመሳብ አሠራራቸው ውስጥ ያለው የማጥፋት ስልታቸውን ለመጨመርና የቁጥጥር አድማሳቸውን ለማስፋት ሲሉ የሚያደርጉት ግብራቸው ነው፡፡
መናፍስት ሠራዊትን የሚስቡበት መንገዶች
ሀ] መተት እንዲሠራብን በማጋለጥ
አዲስ በመተት በኩል ተልኮ ከሚመጣው መንፈስ አስቀድመው እኛ ውስጥ ያሉት መናፍስት፤ ሰዎች እኛን ሲያዩ እንዲቀኑ፣ እንዲጠሉን፣ እንዲበሳጩብን፣ ባላጋራቸው እንደሆንን፣ የእነርሱን ነገር የቀማን መስሎ እንዲሰማቸው፣ እኛን ካላጠፉ ሰላም የማያገኙ እንደሆነ አድርገው በአዙሪት ሹክሹክታ ከውስጥ በመደስኮርና ሰዎቹ ውስጥ ካሉት ሌሎች አጥቂ መናፍስት ጋር በመቀናጀት ምናብን ወደ ክፉው በማስለወጥ፤ የሰዎቹንም የዕውቀትና የልምድ ክፋት በማበልጸግ፤ መተት እንዲልኩብን ገፋፍተው ሠራዊት ከውጪ ወደ ውስጥ ይጨምራሉ፡፡
ለ] ቡዳ እንዲበላን በማጋለጥ
ሌላው ደግሞ ወደ መናፍስት ቡዳነት የተለወጡ ሰዎች እንዲመለከቱን፤ ከውስጥ ያሉት ጠላቶች የሁኔታና የጊዜ አጋጣሚዎችን በማመቻቸት፤ የቡዳ መንፈስ ያለባቸው ሰዎች አንዳች ነገራችንን ወደውት ከመንፈሱ ዓይን ጋር አብረው እንዲያዩን ያደርጋሉ፡፡ በዚህ ጊዜ የቡዳው መንፈስ፤ ወደኛ ሠራዊቶችን በመላክ ተጨማሪ መንፈሶች እንዲመሽጉብን ይሆናል፡፡
ሐ] በኃጢአት ግብር ጊዜ መናፍስቱ እርስ በእርስ በመናበብ
በየቀኑ ከተለያዩ ሰዎች ጋር የምንገኛንበት ዕድልና አጋጣሚ በሰፋ ቁጥር ከብዙ መናፍስት ጋርም የምንጋፈጥበት ሁኔታ በዛው ልክ ይጨምራል፡፡ " #ዓለምም_በሞላው በክፉው እንደ ተያዘ እናውቃለን።" (1ኛ የዮሐንስ መልእክት 5፥19) በመሆኑም እኛ ውስጥ ያሉት ክፉ መንፈሶችና ሌሎች ሰዎች ውስጥ ያሉ ጠላቶች ሲገናኙ፤ የሠራዊት ሽግግር ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ በተለይ ደግሞ ከምናገኛቸው ሰዎች ጋር የምንጫጫስ፣ የምንጠጣ፣ የምንዘሙት፣ ክፉ ነገርን የምናደርግ ሲሆን፤ መናፍስቱ እየተሳሳቡ ሠራዊት ለመጨመር ድልድይ የሚሆንላቸውን የኃጢአት ግብር ያገኛሉ፡፡ በቀላል ምሳሌ፥ እኛ ውስጥ ቀድሞ የነበረ የጠቋር መንፈስ፤ ሌላ የሔርሜት መንፈስ ካለበት ሰው ጋር ሆነን ስንቅም፣ ስናጨስ፣ ስንጨብስና ወዘተ... ጠቋሩ ሔርሜት መንፈሷን አብራው እንድትሠራ ይጋብዛል፡፡
መ] ለኃጢአት የሚመቹና የመናፍስት መግቢያ በሆኑ ነገሮች
ኃጢአት በምንሠራበት ልክ፤ የመናፍስትም በሠራዊት ብዛት የመጨመር ልክ እያደገ ይመጣል፡፡ በሌላውም ለኃጢአት የሚጋብዙ የመናፍስት መሣሪያ የሆኑ ነገራትንም ስንፈጽም እንዲሁ መናፍስት ሠራዊት ለመጨመር እንዲችሉ በር ይከፍትላቸዋል፡፡ ለምሳሌ የወሲብ ፊልሞችን የምንመለከት ሲሆን፤ ከውስጥ ያሉት ጠላቶች በአየር ለሚያዣብቡ የዝሙት መናፍስት ጥሪ ያደርጉላቸዋል፡፡ አንዴ እንዲህ አይነት ፊልሞችን ለማየት ከጀመርን በኋላ ለማቆም የሚከብደን ለዚህ ነው፡፡ በሌላውም ደግሞ ለመናፍስት የሚመቹ ሙዚቃዎችንና የአመፃ ፊልሞችን በምንመለከትበት ጊዜ፤ እንዲሁ አይነት መጽሐፍትን በምናነብበት ጊዜ፤ ባየነው አሊያ ባነበብነው ጉዳይ ላይ የሚመለከታቸው መንፈሶች፤ አስቀድመው በመሸጉ መናፍስት ጋባዥነት ከያሉበት ተጠርተው ይመጣሉ፡፡ ለምሳሌ ሃይማኖት አስከጂ እንደ ዶ/ር ራምፓ እና ኦሾ መጽሐፍት ሲነበቡ፤ ይህንን ግብር የሚከተሉ የ'ሳይኮሎጂ' ፍልስፍና መናፍስት በሌሎች መንፈሶች ተስበው ይመጣሉ፡፡ የባሕሩ መንፈስ መናፍቁ ደግሞ የርሱን መዝሙሮች፣ ስብከቶች እና ፕሮግራሞች በመከታተል መካከል ተስቦ ይመጣል፡፡
ሠ] መናፍስቱን የሚወክል ምልክት፣ ጌጥ እና አልባስ ሲኖር
እንደ ከልከልዮስ(የመቃብሩ መንፈስ) ያሉት አጥፊ የሞት አበጋዞች፤ የመዋረሻ ምልክታቸው በራስ ቅል አፅምና በ ( X ) ምልክት የተቆላለፉ አጥንቶች ናቸው፡፡ ይህም በአብዛኛው በአደገኛ አጥር ምልክት ላይ፣ በማስጠንቀቂያ አዘል መልእክቶች ላይ፣ በአልባሳት ላይ፣ በቆዳ ውጤት የሆኑ ምርቶች ላይ፣ በጌጣጌጦችና ወዘተ... ላይ የሚቀመጥ ሲሆን፤ ይሄ የመናፍስቱ ምልክት ያለባቸውን መገልገያዎች በሕይወታችን ውስጥ የምንጠቀም ሲሆን፤ ያንን ምልክት ተከትለው የሚዋረሱ መንፈሶች ተስበው ይመጣሉ፡፡ ለምሳሌ የከልከልዮስ ምልክት ያለበትን ቀበቶ ታጥቀን የምንዞር ከሆነ፤ በጠቋር አሊያ በሌሎች መንፈሶች ከልከልዮስ ከመቃብር ሥፍራው ተጠርቶ ይመጣል፡፡
በሌላውም ደግሞ በተለይ የቡዳ መናፍስትን የሚስቡ አለባበስ ማለትም ደረት ገልብጦ መሄድ፣ ሰውነትን አራቁቶ መሄድ፣ ሰውነትን በልብስ አጣብቆ የለበሰ ራቁት ገላን እያሳዩ መሄድ፣ የበዛ የተሽቀረቀረና ያፈነገጠ አልባስ ለብሶ መሄድ፣ አርቴፊሻል ነገሮችን በመጠቀም መልክ ያልሆነ መልክን መገለጫ አድርጎ መሄድ፣ የተበጫጨቁና የተቀዳዱ ትኩረት ሳቢ ፋሽኖችን ለብሶ መሄድ፤ የሚያንዣብቡና በሰዎችም ውስጥ ያሉ መንፈሶች እንዲሳቡ መንገድ ይሰጣል፡፡
ረ] መናፍስት ያሉባቸው ነገራት ጋር ንክኪ በመፍጠር
ሱሉስ የዝውውር መናፍስት የተደፉ፣ የተጣሉ፣ የተረጩ፣ የተቀበሩ የምግብ ተረፎችን፣ የእንስሳት ቅሪቶችን፣ ብስባሾችንና ወዘተ.. ደንቃራ ነገራትን በመንካት ቁራኛ የሚሆኑ መንፈሶች ናቸው፡፡ በመሆኑም ሳንጸልይና ሳንሰግድ በምንውልበት ቀን ሁሉ፤ ከውስጥ ያሉት መንፈሶች እነዚህ የመናፍስት ቁራኛ ማስደረጊያ ደንቃራዎችን ሳናስተውልም ሆነ በውል እያወቅን እንድንነካቸው በማድረግ ተጨማሪ ሠራዊቶችን ከደንቃራው ቦታ ላይ ያነሣሉ፡፡
በተጨማሪ ሳንጸልይበትና ሳንባርክ በምንጠቀማቸው የምግብ ምርቶች፣ የአልባሳት አይነቶችና ሌሎች የኑሮ መሣሪያዎች ጋር ንክኪ እንድፈጥር በስልት ሳንጸልይ እንድንነካቸው በነባራዊ ባለንበት ጉዳይ በመወጠር፣ በማወዛገብና ቸል እንድንል ልቦናን በመስረቅ አሊያ ቀድመውኑ ነገራትን ሳንባርክ የምንጠቀምበትን የዘልማድ አኗኗር በማበልጸግ፤ ተጨማሪ መንፈሶች እንዲዋረሱ አስቀድመው የመሸጉት መናፍስት ሠራዊት ይስባሉ፡፡
መናፍስት ሠራዊት እንዳይስቡ ምን እናድርግ?
☞ ጠዋትና ማታ ግንባር ላይ በማሰር ሠራዊት እንዳይስቡ በሰማያዊ ስሞች ማዘዝ
☞ አቅማቸው እንዲዳከም ዘወትር የአምልኮት ስግደት መስገድና መቀጠሪያ መጠቀም
☞ ከኛ ውጪ ያሉ መናፍስት ወደ ሕይወት መስመራችን እንዳይመጡ አስቀድመን ከቤት ከመውጣታችን በፊት መጸለይ (መዝሙር 90)
☞ ቀን በሥራና በትምህርት፥ በሌሎችም ቦታዎች ላይ ውለን ከመጣን በኋላ፤ አዳዲስ ተስባችሁ የመጣችሁ መናፍስት ካላችሁ እያሉ ለብቻ በመቁጠሪያ መቀጥቀጥ - አዳዲሶቹ የአምልኮት ሕይወታችን ጠንካራ ከሆነ በፍጹም መቀመጥ አይፈልጉም፡፡ ሳይላመዱን በነው ይሄዳሉ
☞ እንደ ቡዳ ያሉ መናፍስት ከውጪ ወደ ውስጥ እንዳያዩን በቅዱስ ቁርባን በየጊዜው መቀ'ደስ
ልብ እንበል! በየሰኮንዱ፥ ዓይናችን፣ አሳባችን፣ እጃችን፣ እግራችን፣ ምግባራችን፣ እቅዳችን ሁሉ ንቁ መሆን አለበት፡፡ እናስታውስ! ምድር የኛ አይደለችም፡፡ የምድር ርስትነት ለክፉ መናፍስት እንጂ ለሰው ልጆች ከቶ አይደለም፡፡ ሳይንሱ፣ ርዮተ ዓለም ንድፉ፣ ፍልስፍናው፣ ቴክሎኖጂው በጠቅላላ ዓለም የኛ እንደሆነች አድርጎ በመቅረጽ ምድራዊነታችንን እያጠናከሩ ነፍሳችንን በማይገባን አቅጣጫ በኩል ይፋለሟታል፡፡ ለዚህ ነው ብዙ ጊዜ በአስኳላ ትምህርት ከፍ ያሉ ሰዎች የእምነት ነገር ብዙ ጊዜ አልዋጥ የሚል ሞኝነት የሚመስላቸው፡፡ " ጥበበኞች ነን ሲሉ ደንቆሮ ሆኑ፥" (ወደ ሮሜ ሰዎች 1፥22) ምድር ላይ የሰው ልጆች በተቀዳሚነት የዓለም ባለቤቶች የሆኑ ክፉ መንፈሶችን በሃይማኖት ኃይል በኩል ተዋግተን አሸንፈን ወደ ሰማይ ቤታችን ለመሄድ ነው በመሬት ዘመናችን የምንኖረው፡፡ ከዚህ በተሻገረ መሬት ላይ የምንሠራው ነገር ሁሉ ከንቱ፥ የከንቱ ከንቱ፤ ባዶ፥ የባዶ ባዶ ነው፡፡ ስለዚህ፤ ለምድራዊ ነገር አስቀድመን መጨነቅ ሰማያዊነታችንን ይነጥቃል፡፡ የምድር ነገር ደሞ ጉዳይዋ ብዙ ነው፡፡ ለእንጀራው፣ ለዳቦው፣ ለአስቤዛው፣ ለክፍያው፣ ለደመወዙ፣ ለትምህርቱ፣ ለሥራው፣ ለአልባሱ፣ ለልጆች ወጪው ብቻ እንድናስብ የምድር ጉዳዮች ዘወትር ያስገድዳሉ፡፡ አንሸወድ! የሰማይ ጉዳይ ይቀድማል፡፡ ምድር ላይ ጥለነው የማንሄደው አንዳችም፥ አንዳችም ነገር የለም፡፡ እንኪያስ፥ ጥለነው ለምንሄደው ከንቱ ነገር፥ ጥሎን የማይሄደውን ድንቅ ነገር እንዳናጣው ሁሉ ነገራችን በየሽርፍራፊ ሰኮንዱ ንቁ ይሁን፡፡ ከሰማይ በታች የወደቁ መናፍስት በሙሉ ትግላቸው እዚህኛው ቦታ ላይ ነው፡፡ ጥለናቸው በምንሄደው ነገራት መካከል ሸብበው ሊጥሉን ይታገላሉና ንቁ! " ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል።" (የማቴዎስ ወንጌል 6፥33)

0 Comments