ከመምህር ግርማ ተማሪ ናትናኤል
መጽሐፈ ሰይፈ ሥላሴ እንደሚነግረን፤ እግዚአብሔር አምላክ መቶ ነገደ መላእክትን ፈጥሮ ከፊታቸው ተሰወረ፡፡ ማስገደድ ሲችል ፍቅር የባሕሪው መግለጫ ነውና፤ የነጻነት አምላክ ነውና፤ ወደውት ይከተሉት ዘንድ ከፊታቸው ተሰወረ፡፡ በመላእክቱም ላይ አስቀድሞ በአለቅነት ተሹሞ የነበረው ሳጥናኤል፤ ወደላይ ቢመለከት ጊዜ ከእርሱ በላይ ያለ የለም፡፡ ወደታች ቢያማትር ደግሞ ወገኖቹ መላእክትን አሰበ፡፡ ይህም የከፍታው ቦታ ወደ ዝቅታ መርቶት ከሥሩ ያሉትን ጓደኞቹ መላእክትን ከግራ መጋባትና መሪ ከማጣት ውስጥ ያውጣቸው ዘንድ ሲገባ፤ ይልቁኑ የበለጠ ከፍ ማለት ተመኝቶ "ሁላችሁም ከአሁን ቅጽበት ጀምሮ ለኔ ስገዱ፤ አምላካችሁ ነኝና" ሲል ያልተሰጠው ዙፋን ላይ ለመቀመጥ ተንጠራራ፡፡
በኛም በሰው ልጆች ሕይወት ውስጥ ብዙ ጊዜ በባሕሪያችን ወደ ከፍታ በወጣን ቁጥር፤ መመጻደቅ፣ መኮፈስ፣ መናቅ፣ መኩራራትና ማጥላላት አይነት ጠባያትን እንገልጣለን፡፡ ይሄንን በዘልማድ የሥጋዊ ቅኝት ውስጥ እንዲሁ ለምደነው የመጣነው ጉዳይ ሲሆን፤ ነገር ግን በመንፈሳዊ እንድምታው በኩል ስናስተውለው፤ አብሮን በባሕሪይ አንድነት ውስጥ እኛን ሆኖ የተቀመጠው ክፉ መንፈስ፤ ጠባዩን በሰውኛ በጠባያችን ውስጥ የሚገልጥበት መናፍስታዊ አሠራር መሆኑን እንገነዘባለን፡፡
ሳጥናኤል ወደ ዓለም "ብርሃን ይሁን" የሚለው የእግዚአብሔር ቃል ሳይገለጥ በፊት፤ በጨለማው ጊዜ ላይ ራሱን ወደ ከፍታ ማማ አውጥቶ "ለኔ ስገዱልኝ" አለ፡፡ እነሆም ከዛች ቅጽበት ጀምሮ፤ ዲያቢሎስ እንደ አምላክ ለመሆን በእጅጉ በመሻቱ፤ ይህ የልቡ ፈቃድ የተፈጥሮው መግለጫ እስኪሆን ድረስ ጠባዩ ሆነ፡፡ ስለዚህ ነገር መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? ስለ እዚህ ጉዳይ ትንቢተ ኢሳይያስ ምዕራፍ 14'ኝ ሙሉውን ብናነብ "የንጋት #ኮከብ" በሚል ገለጻ የተቀመጠው፤ ቀድሞ የብርሃን መልአክ ስለነበረው ዲያቢሎስ መታበይ፤ በሚገባ የተብራራ መረጃ እናገኝበታለን፡፡ አሁን ለዚህ አንቀጽ መደገፊያ የሚሆነውን ቃል ከቁጥር 13 እና 14 ላይ ነጥለን ስንመለከት እንዲህ ይላል፤
(ትንቢተ ኢሳይያስ ምዕ. 14)
----
13፤ አንተን በልብህ። ወደ ሰምይ ዐርጋለሁ፥ ዙፋኔንም ከእግዚአብሔር #ከዋክብት በላይ ከፍ ከፍ አደርጋለሁ፥ በሰሜንም ዳርቻ በመሰብሰቢያ ተራራ ላይ እቀመጣለሁ፤
14፤ ከዳመናዎች ከፍታ በላይ ዐርጋለሁ፥ በልዑልም እመሰላለሁ አልህ።
እንግዲህ አምላክነትን በአመፃ ውስጥ የፈለገው መልአክ፤ ርኩስ መንፈስ ይሆን ዘንድ ሰማያዊ ክብሩ ተነጥቆ ጨለማን ተከናንቦ ወደ ሲዖል፣ ወደ ምድርና ወደ ባሕር እርሱን ከተከተሉት ከሠራዊቱ ጋር ተጣለ፡፡ "ነገር ግን ወደ #ሲኦል ወደ ጕድጓዱም ጥልቅ ትወርዳለህ።" (ትንቢተ ኢሳይያስ 14፥15) ፤ "ስለዚህ፥ ሰማይና በውስጡ የምታድሩ ሆይ፥ ደስ ይበላችሁ፤ #ለምድርና_ለባሕር ወዮላቸው፥ ዲያብሎስ ጥቂት ዘመን እንዳለው አውቆ በታላቅ ቍጣ ወደ እናንተ ወርዶአልና።"
(የዮሐንስ ራእይ 12፥12)
በጣም የሚደንቀው ግን ይህ ዲያቢሎስ የተባለው ርኩስ መንፈስ፤ ወደ ሲዖል፣ ወደ ምድርና ወደ ባሕር ከተጣለም በኋላ፤ እንደ አምላክ የመሆን ፍላጎቱ ይበልጡኑ ጨመረ እንጂ አልበረደም፡፡ በነብዩ ኢሳይያስ ትንቢትም ላይ " ከዳመናዎች ከፍታ በላይ ዐርጋለሁ፥ በልዑልም እመሰላለሁ አልህ።" በማለት ወደላይ ወደ አርያም በመውጣት የሥላሴን ዙፋን መቀዳጀት እንደሚፈልግና፤ በልዑል እግዚአብሔርም መመሰልን እንደሚመኝ በጉልህ ቃል አስቀምጦልናል፡፡
እንግዲህ ይህ እብሪተኛ መልአክ ይልቅና እንደ እግዚአብሔር መሆኑ ቀርቶ በመንፈቀ ደይን እንዲታሰር ተፈርዶበት፤ ሰማያዊ ኃይልን ተነጥቆ በጨለማ ውስጥ ሰልጥኖ ይኖር ዘንድ ወደ ጥልቁና ወደ ምድር ተጥሎ ባለበት ወቅት ላይ፤ እግዚአብሔር አምላክ በዚህ ትዕቢተኛ ፍጡር ምትክ የእርሱ አርአያነት የሚላበሱ ፍጡራንን በሕያውነት እስትንፋሱ በኩል ቀርጾ "የሰው ልጅ" ብሎ ፍጹም አፍቅሮ፤ በተፈጥሮም ላይ ሹሞ፤ ጸጋና ክብሩን አውርሶ ፈጠረ፡፡ ታዲያ እንደ አምላክ ይሆን ዘንድ በእያንዳንዷ ቅጽበት የሚታገለው የወደቀው የክፋት ሠራዊት፤ እርሱ ያጣውን አምሳለ ሥላሴነት ከምድር አፈር የተበጁ አዲሶቹ ፍጡራን እንደተቀበሉ ሲመለከት ጊዜ፤ በሰው ልጆች ነገድ ላይ የማያባራ ጥላቻ፣ ቁጣ፣ ንዴት፣ ጥልቅ ምቀኝነት እና በቀል አደረበት፡፡ ይሄ ስሜቱም እኛን አጥብቆ ይፋለመን ዘንድ አስገድዶት ዛሬም ድረስ እያንዳንዳችንን ሊወጋ ወደ ሕይወታችን መጣ፡፡ "መጋደላችን ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለምና፥ ከአለቆችና ከሥልጣናት ጋር ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዦች ጋር በሰማያዊም ስፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት ጋር ነው እንጂ።" (ወደ ኤፌሶን ሰዎች 6፥12)
እናስተውል! የዲያቢሎስና የሠራዊቱ ልዩ መታወቂያ ባሕሪያቸው ዘወትር እንደ አምላክ መሆንን አጥብቀው መመኘታቸው ነው፡፡ ስለዚህ የሰይጣንና የአጋንንት መላ የክፋት ባሕሪያቸው ከዚህ ምኞታቸው ላይ የሚነሣ ነው፡፡ አምላክነትን፤ ከፍታን አብዝቶ ተመኝቶ ያጣው መሆኑ በየጊዜው ያበሳጨዋልና፤ ይሄንን የውስጥ ሽንፈቱን በአመፃኛነት፣ በትምክህተኝነት፣ በአልሞት ባይ ተጋዳይነት፣ በተንኮለኝነት፣ በጨካኝነት፣ በስግብግብነትና ወዘተ ለመከለል ይጥራል፡፡ ለምን ሁልጊዜ ለራሱ የሚነግረው አምላክ እንደሆነ ነውና፤ በነዚህ ግራ ዘመም ባሕሪያት ውስጥ በመደበቅ ሽንፈቱን በማስመሰል ከፍታ ውስጥ ለመደበቅ ይሞክራል፡፡
እስኪ በአንክሮ ሕሊናችንን ከነፍሳችን፤ ልቦናችንን ከአእሞሮአችን አስማምተን ራሳችንን እናጢን፡፡ እኛም ብዙ ጊዜ ሽንፈትን እንጠላለን፡፡ ዝቅ ማለት የቋጥኝ ያህል ትከሻችንን ይጫነዋል፡፡ በተለይ ከኛ እኩል ነው አሊያ ያንሳል ብለን ለምንገምተው ወገናችን የምናሳየው የተገለጠም ይሁን ያልተገለጠ ንቀት አሊያ መገዳደር ሁላችን ውስጥ አለብን፡፡ ለምንድነው?
ምክንያቱም 1ኛ ጴጥ. 5፥8 ላይ በተገባ እንደሚነግረን ዲያቢሎስ ለኛ ለሰው ልጆች ባላጋራ ነውና፤ ባላጋራ ሲሆን በአንደኛው የኛን ባሕሪይ፣ ጠባይ፣ ልማድ፣ ዕውቀት፣ እቅድ፣ ጸጋ፣ ጊዜና የኑሮ መስመር ይጋራል፡፡ አስከትሎ አኛን ከተጋራ በኋላ በሁለተኛው የርሱን ባሕሪይ፣ ፍላጎት፣ ዕውቀት፣ መርህ፣ አሠራርና እይታ ለኛ ደግሞ ያጋራናል፡፡ ስለዚህ በኛ ልብና ሰውነት ውስጥ አድሮ ባሕሪይውን በሚያጋራን ጊዜ፤ አስቀድሞ ጓደኞቹ መላእክትን የተገዳደረበትን ብሎም የናቀበትን ጠባይ ለኛም ሲያዋርሰን፤ እኛም ወገኖቻችን የሆኑትን የሰው ልጆች እንገዳደራለን፥ እንንቃለን፡፡
"ኸረ ሁሉም ሰው ሽንፈትን አይወድም" እንላለን ባሕሪያችን በተለያየ አጋጣሚ ለትሕትና እና ለፍቅር አስቸጋሪ እየሆነ አልመች ሲል፡፡ ይሄ ማለት "ሁሉም ሰው" ውስጥ ሽንፈትን አምርሮ የሚጠላው የተሰወረው አጥፊ መንፈስ ስለመመሸጉ ማረጋገጫው ነው፡፡
ዲያቢሎስ ወደ ምድር ተዋርዶ ተጥሎም ቢሆን እንደ አምላክ የመሆንን እሳቤው ከልቦናው ይብልጡኑ ተቀጣጠለ እንጂ "በይቅርታ ልመለስ" አላለም፡፡ ዛሬ ብዙዎቻችን ከልብ የሆነ ይቅርታን መጠየቅ ይከብደናል፡፡ ሰው ይቅርታ ሲለን እንጂ ይቅርታ ስንል አንወድም፡፡ ምክንያቱም ከተሰወረው ጠላት ጋር ጠባይ ተሻምተን ነዋ በቃ የምንገኘው፡፡ ለዚህ ነው ዛሬ የተነገረው የትንቢቱ ቃል ይፈጰም ዘንድ "ቅድስና የሌላቸው፥ ፍቅር የሌላቸው፥ ዕርቅን የማይሰሙ፥ ሐሜተኞች፥ ራሳቸውን የማይገዙ፥ ጨካኞች፥ መልካም የሆነውን የማይወዱ፥" (2ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 3:3) ሰዎች በዝተን በዝተን፤ እንደኖህ ዘመን የጥፋት ውሃው ጠራርጎ ሊያጠፋን በየቀኑ እየቀረበ፤ እኛ ምንም ሳይመስለን የሥጋ ኑሮአችንን የቀጠልነው፡፡
ክፉ መናፍስት ከይቅርታ ይልቅ መጨረሻው የተረጋገጠ ትግልን መታገል ምርጫቸው አድርገው፤ እንደ አምላክ ለመሆን በእጅጉ ይጥራሉ፡፡ እንኪያስ፥ እንደ አምላክ ይሆን ዘንድ፤ የአምላክን አካሄድ መከተል አለበት፡፡ እርሱ የሚሠራውን መሥራት አለበት፡፡ በመሆኑም የእግዚአብሔርን መለኮታዊ አሠራር ከሥር ከሥሩ እየተከታተሉ በቀጥታ መገንዘብ እንዳይችሉ የክፉት ሠራዊት " ከዚያም ወዲያ በሰማይ ስፍራ አልተገኘላቸውም።" (የዮሐንስ ራእይ 12፥8)፤ ስለሆነም በምድር ርስታቸው ላይ አብረው በሚኖሩት የሰው ልጆች ሕይወት ውስጥ የሰማያዊውን አምላክ አካሄድ እየተከተሉ በመገንዘብ ሰማያዊ መረጃን ለማግኘት ይጥራሉ፡፡ ዲያቢሎስ በዚህ በሰው ልጆች ውስጥ በሰበሰበው ሰማያዊ መረጃ ላይም በመቆም፤ እንደ አምላክ ይሆንባቸው ዘንድ መመጻደቅ የወለደው የምኞት ኃይሉን ማሳየት የሚችለው፤ ከአምላክ ክንድ ተለይተው በሚኖሩ ሁሉ የሰው ልጆች ላይ ነውና፤ ከኛ ኑሮና ሕይወት ላይ ጥብቅ ብሎ እያንዳንዷን ቀን ፈተና የሚሆነው በዚህ ምክንያት ነው፡፡ "ዲያቢሎስ በጭራሽ ወደኔ አይደርስም!" የምትሉ በአንደበት ሰማያዊ ሆናችሁ በተግባር ከእግዚአብሔር የተለያችሁ ሰዎች ጊዜው ሳይረፍድ ቀስ በሉና ወደ ውስጣችሁ አድምጡ፡፡
ዲያቢሎስ እንደ እግዚአብሔር ከሥር ከሥሩ የሚከተለው የለም፡፡ እርሱን መሆን አብዝቶ ይሻልና ስለርሱ አሠራርና አገዛዝ ለመረዳት የማይፈነቅለው ድንጋይ፣ የማይገባበት ጉድጓድ፣ የማይቧጠው ተራራ የለም፡፡ ታዲያ ግን ሲከተለው የርሱን አካሄድ ወደ ራሱ #በመገልበጥ ነው፡፡ እግዚአብሔር ደግ ነገር ለማድረግ ድንቅ ነገርን ሲያከናወን፤ ዲያቢሎስ ጥፋትን በዛ ደግ ነገር ልክ ለመፈጸም አቅሙን ይጨርሳል፡፡ እግዚአብሔር ለማዳን ሲሠራ፤ ዲያቢሎስ ለማጥፋት ይሮጣል፡፡ እግዚአብሔር ለአዳም "ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለው" ሲለው፤ ሰይጣን ደግሞ "ከልጅ ልጅህ እየተወለድኩ አጠፋሃለው" የሚለውን ለመፈጸም ከቃየን ጀምሮ ከማኅፀን አብሮ በመወለድ የአዳም ዘርን ያመክነው ጀመር፡፡ እግዚአብሔር ልቤ ባለው ንጉሥ ዳዊት በኩል "የሚጠብቀኝ አይተኛም" የሚለውን ቃል በተስፋ አረጋግጦ የሰጠው፤ "የሚያጠቃኝ አይተኛም" የሚለው የአጋንንት የማጥፋት እረፍት አልባነት አብሮ ስላለ ነው፡፡
"ቃል ተናገር ብላቴናዬ ይፈወሳል" የሚለው የፈውስ ቃል ሲገኝ፤ "ቃል ተናገር ብላቴናዬ ይታወካል" የሚለው የዲያቢሎስ የመተት፣ የአውደ ነገሥት፣ የሟርት፣ የእርግማን፣ የስልብና፣ የማፍዘዝ የቃል መናፍስታዊ አሠራር እንዳለ መገንዘብ አለብን፡፡ በትርጓሜው 'ተከፈት' ማለት የሆነው "ኤፍታህ" የሚለው የክርስቶስ ቃለ ትእዛዝ ሲኖር፤ "ይዘጋ" የሚል የርኩስ መንፈስ ሚስጢራዊ አሊያም ሕቡዕ ቃላት በሕይወታችን ውስጥ እንዳለ ማስተዋል ያስፈልገናል፡፡ "የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው" የሚለው የምሕረት ድምፅ ካለ፤ "አውቆ ነው ስለዚህ እንዳትራራለት" የሚለው ውስጣዊ የመናፍስት ቋንቋ በየሰዉ ሕሊና ውስጥ ለጥፋት የሚጋብዝ ሹክሹክታ እየሆነ፤ አሊያ በሌላ ሰው ጥፋት ላይ ለማስፈረድ በየሰው አንደበት ላይ ቃል ሆኖ ይደመጥ ዘንድ ይጠበቃል፡፡ በሐዲስ ኪዳን ውስጥም ከዕርገት በፊት በሐዋሪያቱ በኩል ለሁላችን የተሰጠው፤ የክርስቶስ "እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ከእናንተ ጋር ነኝ" የሚለው የማቴዎስ 28፥20 የአብሮነት ማረጋገጫ ቃል ካለ፤ ዲያቢሎስም "እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ከእኛ ጋር" በአብሮነት ሲፋለም እንደሚኖር ማስታወስ ይጠበቅብናል፡፡ ምክንያቱም ዲያቢሎስ የእግዚአብሔርን በምድራዊ የሰው ልጆች ውስጥ ያለውን ነገርና አሠራሩን ሁሌ እየተከተለ በራሱ የሚገለብጥ ፍጡር ነውና፡፡ አሁን እኮ ለዚህ ነው አብዛኞቻችን 'የአምልኮት ስግደት፣ የዘወትር ጸሎት፣ የምግባር ሃይማኖት፣ የእምነት ባሕሪያት' ከኑሮአችን ውስጥ ቆይተው አልለመድ ብለው፤ ዘወትር ጸጉረ ልውጥ እየሆኑ የሚፋለሙን፡፡ ምክንያቱም ውስጣችን ሆኖ እንደ አምላክ ለመሆን አብዝቶ የሚፈልገው አመፀኛው ጠላት፤ ለአምላክ እንዳንገዛ በየቀኑ አቅሙ የቻለውን ያህል ለመታገል ስለሚታደስ፤ አምልኮተ እግዚአብሔርን ለማከናወን በየቀኑ ባሕሪያችንና ኑሮአችን መሰናክል እየሆነ አብዝቶ ይታገለናል፡፡

0 Comments