"በዚህ ዘመን ደግሞ ምን የሚታመን ሰው አለና? ሰው ሁሉ አስመሳይ ሆንዋል፣ ሰው ሲባል ቀን ጠብቆ የሚከዳ ፍጡር ነው፣ ማንም በአቋሙ የሚጸና የለም እና ወዘተ..." አይነት ስለ ሰው ልጅ ጠባያት በአስገራሚ ፍጥነትና ይዘት የመለዋወጥ አባዜ የሚያወሱ አባባሎች፤ በተለያየ ገለጻ እየተነገሩ፣ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይም የብዙ ሰው መግለጫ እየሆኑ፣ ሰዎችን ለሐሜት የሚጋብዝ የንግግር አጀንዳ ሲሆኑ ይስተዋላል፡፡
በእርግጥም፤ እጅግ በጣም ብዙ ለማለት በሚያስደፍር ሁኔታ በቁጥር የበዛን ሰዎች አንዳንዴም ለራሳችን ባሕሪያችን ውሉ አልለይ እስከሚለን ድረስ የሚለዋወጥ ጠባይ ይዘን የምንገኝበት አጋጣሚ ቀላል አይደለም፡፡ በዚህ ስለዚህ፤ አንዳንዶቻችን የአመላችን በተደጋጋሚ መቀያየርና አንዳች የጸና አቋም አለመያዝ ገርሞን እንዲሁ ራሳችንን እየታዘብን ተቀምጠናል፡፡ አንዳንዶቻችን የሰውነት ባሕሪያችን የመገለጫ አንድ ክፍል እንደሆነ አድርገን ተቀብለነው ከጊዜያዊ ሁነቶች ጋር ተሳስረን ከቅጽበት ጋር እንደ ቅጽበት የምንመላለስ ሰዎች ሆነናል፡፡ አንዳንዶቻችን ከራሳችን ጠባያትና አልጨበጥ የሚሉ ባሕሪያት ጋር የግብግብ እልህ ተያይዘን፤ የጸና አንድ መልክ ለመያዝ የምናደርገው ጥረት በተደጋጋሚ እየከሸፈ ግራ ሲያጋባን፤ ተስፋ ባለመቁረጥና በመቁረጥ መካከል ስንዋትት እንገኛለን፡፡ አንዳንዶቻችን ደግሞ፤ ከላይ የተገለጹትን አይነት ሰዎች ሁሉ በመሆን፤ አንዳንድ ቀን ራሳችንን የምንታዘብ፣ አንዳንድ ቀን እንደ ማንነታችን አንድ ክፍል አድርገን የምንቀበል፣ በሌላ ቀን ከራሳችን ጋር የምንጣላና የምንፋለም ቀለም አልባ ሰዎች በመሆን እየተዘበራረቅን ዕድሜያችንን ቀጥለናል፡፡
በጣም ብዙዎቻችን ግን፤ የሰው ልጅ የጠባይና የአመል መተረማመረስና አልጨበጥ ማለት ከክፉ መልአክቶች መናፍስታዊ አሠራር ጋር በቀጥታ እንደሚያያዝ ገና ሊገባንም አልጀመረም፡፡ ምክንያቱም ርኩስ መንፈሶች ዓላማቸውን ለማስፈጸም የሚሄዱበትን ሚስጢራዊ አካሄድ፣ ከሰው ልጆች ጋር ያላቸው ጥብቅ ትስስር፣ የማጥፋት አሠራር ጥበባቸውን እና ወደ ግባቸው ለመድረስ የሚጓዙበት ሂደታቸውን፤ በሚገባ ለመገንዘብ የምናሳየው ፍቃድ በጣም አነስተኛ በመሆኑ፤ ስውራኑ አጥቂዎቻችን በቸልተኝነታችን በኩል የተቀዳጁትን ኃይል የበለጠ ከዘመን ዘመን እያጠነከሩ፤ የእስራት ገመዳቸውን በማጥበቅ ሰብአዊ ማንነትና ሕልውና ከምድረ ገጽ እንዲጠፋ በብርቱ እየሠሩ ይገኛሉ፡፡
በአንድ ሰው ውስጥ ብዙ የተለያዩ ማንነቶች፣ ባሕሪያት፣ አመሎችና አስተሳሰቦች ሊከሰቱ የሚችሉት ከዚህ በታች በተገለጹት የአጥፊ መንፈሶች የውጊያ አካሄድ ጋር በተገናኘ ጉዳይ ነው፡፡
ሀ ] ሰውየውና መንፈሱ ሲጋጩ
" አቤቱ፥ የሰው መንገድ ከራሱ እንዳይደለ አውቃለሁ፥ አካሄዱንም ለማቅናት ከሚራመድ ሰው አይደለም። " (ትንቢተ ኤርምያስ 10፥23)
ይሄ የአብዛኞቻችን የተለመደ ችግር ነው፡፡ ከውስጥ የሚመራን፣ አሳብ ሆኖ የሚነግረን፣ ምሪት ሆኖ የሚቀድመን ኃይል ሲቆጣጠረን ብዙ ጊዜ ይገኛል፡፡ የኛ የሰብአዊ ማንነት ክፍል እና የመናፍስቱ የማንነት ክፍል አንድ ጉዳይ ላይ የተለያየ አቋም፣ የተለያየ አመለካከት፣ የተለያየ አካሄድና የተለያየ እቅድ ሲኖረን፤ መናፍስቱ ከውስጥ እኛን መስለው እኛን ይጣሉ ዘንድ ስልት ይቀንሳሉ፡፡
ቀላል ምሳሌ እንመልከት፡፡ የሰላቢ መንፈሶች፤ ሰዎች ዐሥራት በኩራት ሲያወጡ አይወዱም፡፡ ስለዚህ ሠርተው የሚያገኙት ገንዘብ ወደ ቤተክርስቲያን ዐሥራት ሆኖ እንዳይደርስ፤ የውስጥ ግፊት በመሆን አሳብን በመምራት፤ ዐሥራቱ እንዳይወጣ በራሳችን አሳብ ልክ አሳብ ሆነው ይጣሉናል፡፡ "ኸረ ብዙ ቀዳዳዎች ያሉብህ ሰው ነህ ቀጣዩን ወር ታወጣለህ፤ አሁን ለዚህ ጉዳይ አውለውና በቶሎ ተክተህ ትሰጣለህ፤ ምንም በረከት ላታገኚ ዝም ብለሽ ነው ተይው ባክሽ፤ እግዚአብሔርን ያንቺን ችግር ያውቃል ሲመችሽ ታወጪያለሽ" እና ወዘተ... የአሳብ ግፊቶችን በኛ ውስጠኛ ሕሊና ውስጥ በማመላለስ ዐሥራት ማውጣት የፈለገውን ሰብአዊ ማንነታችንን ይዋጉታል፡፡
እጅግ በቁጥር የበዙ ሰዎች ስሜታቸው ከመለዋወጡ በፊት፤ ስሜታቸው እንዲለወጥ ከውስጥ የሚገፋ ኃይል እንዳለባቸው ልብ አይሉትም፡፡ ምክንያቱም፤ መናፍስቱ ከውስጥ ሆነው በኛ አሳብ ልክ ሲጣሉን፤ ራሳችንን በራሳችን የምናወራ እንጂ ከሌላ ባዕድ ፍጡር ጋር እየተዋጋን እንደሆነ አናስተውልም፡፡
ርኩስ መናፍስት የጥፋት አሳባቸውን ወደ ጥፋት ግብር ከመቀየራቸው በፊት ሁልጊዜ መቼት የሚባለውን "መቼ" እና "የት" የሚለውን የሥነ ጥበብ ሕግ ይጠቀሙታል፡፡ ይኸውም፤ መቼ የጥፋት አሳብ ማመንጨት፣ መቼ የጥፋት ግፊት መጨመር፣ መቼ የጥፋት ግብርን ማጽደቅ የሚል፤ ጊዜን ከውስጥ ወደ ውጪና ከውጪ ወደ ውስጥ የመጠበቅ ሂደት ይጓዙበታል፡፡ የት ብለው በሚጠብቁት የቦታ መምረጥ አሠራር ውስጥ፤ የት ሥፍራ ላይ ጥፋቱን እንደሚመሩ፣ የውስጥ ጫናውን እንደሚፈጥሩ፣ የግብር ሂደቱን እንደሚያስፈጽሙ እኛ ውስጥ ሆነው ያቅዳሉ፡፡ ምሳሌ ስንመለከት፤ በመንፈሳዊ ጥንካሬና መረዳት ውስጥ ባለንበት ሰዓትና ቦታ ላይ መናፍስት ዝም ይላሉ፡፡ ከጊዜያት ቆይታ በኋላም ወደ ሥጋዊ አኗኗርና ድክመት የምናዘነብልበት ጊዜና ቦታ ሲመጣ፤ ከውስጥ ሆነው የመጣላት እቅዳቸውን ከውጪ በመጣው አጋጣሚ አስታከው ለመፈጸም ይታገላሉ፡፡
አሁን አንዳንድ ሰዎች ትናንት ሰላም ብለናቸው ዛሬ ሰናገኛቸው ኩርፍ ብለውን ያልፋሉ፡፡ ትናንት ተሳስቀን፣ ተደስተን፣ ብዙ ቁም ነገር አውርተን፣ ለዛሬው ጊዜ እቅድ አውጥተን ሳለ፤ ዛሬ ስናገኛቸው ፍጹም ከትናንት ተቃራኒ ሆነው የሚያስደነግጡን ሰዎች አሉ፡፡ ይሄ ግለሰቦቹ ውስጥ ያሉት መናፍስት ሰውየውን ከውስጥ ወደ ውጪ ሲጣሉት፤ ይሄ የውስጥ ፍጭት ወደ ውጪ በተገለጠ ጊዜ፤ ግለሰቡ ለራሱ መለዋወጡ ሳያውቀው በሚተረማመስ አሳብ መካከል ዝብርቅርቅ ያለ ጠባይን ይገልጣል፡፡
በሌላውም ደግሞ፤ ከጊዜያት በኋላ ወደ ሕይወታችን የሚገቡ መናፍስት የጠባይ መዘባረቅ እንዲፈጠርብን ያደርጋሉ፡፡ አንድ ግለሰብ በቡዳ መንፈስ ቢያዝ፤ መንፈሱ የተዋረሰውን ግለሰብ የተነሣበትን ሰው(አዋራሹን) ጠባይ ሊያሲዘው ይችላል፡፡ ችኩል የነበረ ሰው በቡዳ ሲበላን፤ እኛም ካለተፈጥሮአችን ችኩል ለመሆን እንገደዳለን፡፡ ጠበኛና ደመኛ የሆነ ሰው የቡዳ መንፈስ ወደ ሕይወታችን ሲመጣ፤ ጥል የምንፈራና የምንሸሽ የነበርነው ሰዎች ተለውጠን አምቧ ጓሮ የምንፈጥርና ለጠብ የምንጋበዝ ሆነን ቁጭ እንላለን፡፡ የመተት መናፍስትም በተመሳሳይ፤ የመታቹንና የአስመታቹን ጠባይና ባሕሪይ ለተመታቹ ግለሰብ ስለሚያዋርሱት፤ መናፍስቱ የኛ የተፈጥሮ ጠባይ ባልሆነ ሁናቴ እንድንግለጽ ሊያስገድዱን ይችላሉ፡፡
ለ ] ሰውየው ውስጥ መናፍስቱ እርስ በእርስ ሲጋጩ
" መልካም ሰው ከልቡ መልካም መዝገብ መልካም ነገርን ያወጣል፥ ክፉ ሰውም ከክፉ መዝገብ ክፉ ነገርን ያወጣል።"
(የማቴዎስ ወንጌል 12፥35)
መናፍስት በተፈጥሮና በዓላማ ሁሉም አንድ ቢሆኑም፤ በጥፋት አሠራር፣ በስምሪት አሰላለፍ፣ በጥቃት አቅጣጫ፣ በእቅድ አፈጻጸም፣ በአከባቢ ልማድና በውጊያ ስልት እርስ በእርስ ይለያያሉ፡፡
በቀላል ምሳሌ፤ በስምሪት አሰላለፍ አንድ ሆነው በጥፋት አቅጣጫና በእቅድ አፈጻጸም ስለሚለያዩት የሔርሜት መናፍስትና የዓይነጥላ መናፍስት እንመልከት፡፡
የሔርሜት መንፈሶች መዝናናት የሚወዱ፣ ፍንደቃና ሳቅ የሚያበዙ፣ በሰው መከበብና መጫወት የሚወዱ፣ ከተቃራኒ ጾታ ጋር መሳሳብን ትኩረት የሚሰጡ የፈንጠዚያ መንፈሶች ናቸው፡፡ በተቃራኒው ዕድል ዘጊ ዓይነጥላዎች፤ ማስለቀስና ማስጨነቅ የሚወዱ፣ ብቸኛ ማድረግና ማስደበት የሚፈልጉ፣ ተቃራኒ ጾታ እንዳይመጣ የትዳር ዕድል የሚዘጉ፣ ሰውን የሚገፉና የሚያርቁ መንፈሶች ናቸው፡፡ እነዚህ ሁለት መንፈሶች አንዲት ልጅ ውስጥ በሚያደፍጡበት ጊዜ፤ የአሠራር አካሄዳቸው የተለያየ ነውና ሁለቱም መናፍስት የራሳቸውን እቅድ ለማሳካት ሲሉ አንዱ መንፈስ ሌላውን ይጫናል፡፡ በዚህም መናፍስቱ እርስ በእርስ ሲጋጩ፤ ልጅቱ ከውስጧ ፍጹም የማትረዳው ነገር ግን መላ ቅጡ ያልተያዘ ዝብርቅርቅ ስሜት ይሰማታል፡፡ በመሆኑም፤ አንዴ መሳቅ መጫወት፥ አንዴ ደግሞ ማልቀስ፣ አንዴ መዝናናትና ሰው መፈለግ፥ አንዴ ደግሞ ብቸኛ ሆኖ በር ዘግቶ መቀመጥ፣ አንዴ ደስተኛና ጭንቀት አልባ ሆኖ መታየት አንዴ ደግሞ በአሳብ መወጠርና መቆዘም የሚፈራረቁበት የልዩነት ስሜቶችና ጠባያት ማንጸባረቂያ ትሆናለች ማለት ነው፡፡
ይሄ ሲሆን ታዲያ፤ መናፍስቱ የተፈጥሮ ዑደትን፣ የተፈጥሮ ጊዜንና የተፈጥሮ መሥፈርትን ጠብቀው ነው የሚሠሩት፡፡ ለምሳሌ የሔርሜት መናፍስት የጥፋት ግብራቸውን ለመፈጸም መጫን የሚጀምሩት፤ መንፈሶቹ የተዋረሱት ግለሰብ ዕድሜው ለአቅመ አዳም በደረሰበት ጊዜ ይሆናል፡፡ ለምንድነው፤ በዛ የወጣትነት የዕድሜ ክልል ውስጥ ከተፈጥሮ ዑደት አንጻር ሰውየውን ለማጥመድ ምቹ የሆነ አጋጣሚዎችና ጊዜዎችን መናፍስቱ ያገኛሉ፡፡ በተለምዶ አንድ ታዳጊ ሰው ከማሕበረሰቡ እሴትና ባሕል ያፈነገጠ ነገራትን መፈጸም ሲጀምር፤ ባሕሪይው መቀያየርና አስቸጋሪ መሆን ሲጀምር፤ የአስተሳሰብ መድረሻው ወደ መዝናናቱና ፌሽታው ማዘንበል ሲጀምር "አይ በቃ እርሱ ፈነዳ" እንላለን፡፡ ነገር ግን፤ የማይታዩ ስውራን አጥቂ ጠላቶች የታዳጊውን ፈቃድ በመጋራት ማንነቱ ባልሆነ ፍላጎት ውስጥ አጥብበው መርተው ጠባያቱን እንደሚለዋውጡ፣ አስተሳሰቡን በመቆጣጠር የነርሱ እቅድ ማስፈጸሚያ እንደሚያደርጉትና ከቤተሰብና ከቤተክርስቲያን ትእዛዝ ውጪ ሆኖ መኖር ደስታ እንዲሰጠው በተለያየ ስልት እንደሚሠሩበት የውስጡን ሕመም አንረዳለትም፡፡
ሐ ] የተለያዩ መናፍስት እርስ በእርስና ከሰውየው ጋር ሲጋጩ
" በላዬ በመተባበር ጠላቶቼ ሁሉ ይሾካሾኩብኛል፥ በእኔ ላይም ክፋትን ያስባሉ።" (መዝሙረ ዳዊት 41፥7)
አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ወደ ሕሊናቸው አትኩረው በሚያዳምጡበት ጊዜ፤ ከውስጥ በኩል ግራ የሚያጋባ ብዙ ሰው ጭንቅላታቸው ውስጥ እንደሚያወራ አይነት ሹክሹክታ ይሰማሉ፡፡ በተለያየ የስምሪት አሰላለፍና የጥፋት አሠራር የተሰየሙ አጥፊ መንፈሶች አንድ ላይ በመሆን ከውስጥ በኩል የሚያሰሙት የሕሊና ትርምስ ድምፅ የአዙሪት ሹክሹክታ ይበላል፡፡
የአዙሪት ሹክሹክታ፤ የራስ የአእምሮ ድምፅ የሚመስል ከውስጥ በኩል ከእኛ ወደ እኛ የሚደርስ መልእክት ሲሆን፤ ልንሄድበት ካሰብነው መንገድ ወይም መድረሻ ላይ መሰናክል በመሆን አሳብን አዙሮ በማስለወጥ፤ ወዳላሰብነው አቅጣጫ በዝግታ አሊያም በፍጥነት የአካሄድ ጉዞን የማስለወጥ የመናፍስት አሠራር ነው፡፡
በዚህም የተለያየ መንገድና የጉዞ መስመርን የጀመሩ የተለያዩ መንፈሶች፤ እርስ በእርስና ከተዋረሱት ግለሰብም ጋር በሚጋጩበት ጊዜ፤ ሰውየው በአንድ ጊዜ የብዙ ስሜቶች መግለጫ የሆነ የግጭት ማዕበል ከውስጡ የሚያናውጠው ሰው በመሆን፤ በአመልም፣ በጠባይም፣ በአስተሳሰብም፣ በምግባርም፣ በእቅድም ቶሎ ቶሎ የሚለዋወጥ ይሆንና ወጥ የሆነ የአኗኗር ጎዳና የሌለው፤ ሁሉንም ቦታ በአንዴ የሚረግጥ ነገር ግን በአንዱም ሥፍራ ላይ የማይረጋ ተቅበዥባዥ ፍጡር ይሆናል፡፡
መናፍስት እርስ በእርስ ሲጋጩ እና እርስ በእርስ የሚጣሉ መናፍስት ከዳፈጡበት ግለሰብ ጋር ሲጋጩ፤ ትልቁ ልዩነት ምንድነው፤ እርስ በእርስ የሚቃረኑ መንፈሶች ከሰውየው ጋር ሲፋለሙ፤ ሰውየው በልቦናው የሚያውቀው በውስጡ የሚፈጠር የተለያዩ አሳቦች፣ ስሜቶችና ባሕሪያት ግጭት ይስተናገዳል፡፡ መናፍስቱ ብቻ እርስ በእርስ የሚጋጩ ከሆነ፤ ሰውየው በልቦናው የውስጡን መዘበራረቅ ሳያውቀው እንዲሁ ከውጪ ባለው ገጽታ ላይ ብቻ የባሕሪይ መነዋወጥ፣ የአመል መለዋወጥ፣ የስሜት መተራመስ፣ የአስተሳሰብ መዋዠቅ፣ የእቅድ መዛባትና መነሻ መሠረቱ ያልተለየ ጭንቀት ይስተናገድበታል፡፡
ከውስጥ በኩል ባለ የመናፍስት ግጭት ምክንያት ወደ ሰዎች የሚደርሰው የአዙሪት ሹክሹክታ፤ ሰዎች ወደ ማንነታቸው፣ ወደ ተሰጥዖአቸው፣ ወደ ብቃታቸው፣ ወደ ችሎታቸውና ወደ ጸጋቸው እንዳይደርሱ የሚታገል ኃይል ሲሆን፤ ያለ ፍላጎትና ያለ እቅድ ሰዎች ባለመረጡት የሕይወት መስክ ላይ እንዲሰማሩ የሚያስገድድ ግፊት ነው፡፡

0 Comments