ናትናኤል ሰሎሞን
የአምልኮት ሕይወት ወይንም በአምልኮተ እግዚአብሔር መሠረት ላይ የተገነባ ኑሮ ማለት፤ አንድ ክርስቲያን በየዕለቱ የአምልኮት ስግደት መስገድ፣ መጸለይ እና በቅዱስ ቁርባን በየጊዜው መቀደስ ሲችል የሚመራው ኑሮ የአምልኮት ሕይወት ነው እንላለን፡፡
ማንኛውም ምድር ላይ የተፈጠረ የሰው ልጅ፤ ከዚህ የአምልኮት ሕይወት በምንም አይነት ምክንያት በተለየ ጊዜ፤ ለመሞት የሚኖር ፍጡር ይሆናል፡፡ በአምልኮት ጥላ ውስጥ ለመገኘት የሚታገል ሰው ደግሞ ለመኖር የሚሞት ፍጡር ይሆናል፡፡
ዓለማችን ላይ እጅግ በጣም በበዛ ቁጥር የምንቆጠር የሰው ልጆች ለመሞት የምንኖር ሰዎች ሆነናል፡፡ የሰው ልጅ ለመሞት የሚኖር ፍጡር በሚሆንበት ጊዜ፤ በመጀመሪያው ላይ ሞት የሚባለው ቃል በራሱ እጅግ የሚያስፈራው ይሆናል፡፡ አሊያም በጭራሽ ደንታ የማይሰጠው፤ ከነአካቴውም ትዝ የማይለው ጉዳይ ይሆናል፡፡ በመቀጠል፤ ለመሞት በመኖር ውስጥ፥ የኑሮ አካሄድ መነሻው በሥጋዊ ፍቃድና ምኞት ላይ ብቻ የተመረኮዘ ሕይወት ይሆንና፤ እያንዳንዱ ቀን በዓለም ውጥረት መካከል ተሸፍኖ፤ ለሥራ የሚኖረው ሩጫ፣ ለትምህርት የሚኖረው ሩጫ፣ ለመዝናናት የሚኖረው ሩጫ፣ ለመብላት ለመጠጣት የሚኖረው ሩጫ፤ የነፍስን ጉዞ ቀድሞ በማለፍ መንገዷን እየጋረደ፤ የአዳም ዘር ስንሆን ከሥጋና ከመንፈስ ተገንብተን፤ እንደ ሥጋ መኖር አሸንፎ፥ መንፈሳዊ ማንነታችን ተሸንፎ፤ በጊዜ መዘውር ውስጥ በሚለዋውጥ የአዙሪት ኑሮ ተውጠን፤ የነፍስ ኑሮን ሳናውቀውና ሳይገባን እናልፋለን፡፡
የሰው ልጅ በተፈጥሮው ግንባታ፤ በአንደኛው አፈር ሲሆን በሌላኛው ደሞ የእግዚአብሔር እስትንፋስ ነው፡፡ ነገር ግን በተለይ በዚህ በመጨረሻው የዘመን ማገባደጃ ላይ በቢሊዮን በሚቆጠር ደረጃ ተሰፍረን የተገኘነው ሰዎች እንደ ጋራም ሆነ እንደ ተናጠል ስንፈተሽ፤ የእግዚአብሔር እስትንፋስ መሆናችንን ረስተን እንደ አፈር ብቻ ስንኖር፤ ሕይወታችንም ይሄንኑ ገጽታ ይዞ አፈር ሆነና ቁጭ አለ፡፡ አልሆነም? እስኪ እንዴት ነው ኑሮአችን? በአፈር የተገነባ ነገር በባሕሪይው ግጭት ሲያጋጥመው አይችልም፥ ይፈርሳል፡፡ እኛም እንደ አፈርነታችን ብቻ ስንመላለሰ፤ የምንነካው ሁሉ የሚፈርስ፤ ለመሥራት የምንጀምረው ሁሉ የሚናወጽ፣ የመኖር ጣዕምና ፋይዳ እስኪጠፋን ድረስ ዘርፈ ብዙ ችግር እንደ ውሃ የሚሸረሽረን በመሆን፤ አሁን ከስቃይ ጋር፣ ከጤና ማጣት ጋር፣ ከሰላም ማጣት ጋር፣ ከበረከት ማጣት ጋር፣ ከጸጋ ማጣት ጋር መኖርን ለምደነው፤ የእግዚአብሔር እስትንፋስ እንዳለው ሰው ሆነን ሳንኖር ቆይተን ቆይተን ደግሞ በአካልም አፈር የመሆኛችን ጊዜ ሲደርስ መቃብር እንወርዳለን፡፡ እግዚአብሔር ይማረን፡፡
ከላይ እንደተገለጸው፤ አንድ ሰው እንደ እግዚአብሔር እስትንፋስነቱ ይኖር ዘንድ ከፍቅር በሚነሣ በአምልኮተ እግዚአብሔር መንገድ ላይ አካሄዱን ማቅናት አለበት፡፡ ስለዚህ በተለይ አንድ በአካልና በአእምሮ ጤነኛ ነኝ የሚል አማኝ ሰው፤ በየቀኑ የአምልኮት ስግደትን በመስገድ፣ በመጸለይና በየጊዜው በመቀ'ደስ ሕይወቱን እንደ ነፍሱ ፍቃድ መኖር ሲጀምር፤ የሥጋ ክፍል የሆነው የአፈርነቱ ጠባይ ደግሞ ፈተና ይጀምራል፡፡ የተፈጠርንበት አፈር ከምድር ነውና የተገኘው፤ በምድር ላይ ዓለማዊ ሰው ሆነን ዓለምን እንድወድድ መግነጢሳዊ የሆነ የሕይወት ሰንሰለት በተለያየ ብዙ አቅጣጫ ወደ ምድራዊ አስተሳሰብና አቋም ይስበናል፡፡
ይህ የሥጋ ፈቃዳችን ታዲያ የነፍስ እውነታን እንዳንኖር መጋረጃ ሆኖ የሚከልልበት ምክንያት ለተሰወረው አጥፊው ጠላታችን ዲያቢሎስ ማደሪያ ቤት ሆኖ ስለሚያገለግል ነው፡፡ ዲያቢሎስ ሰማያዊነትን የተገፈፈ ምድራዊ ፍጡር ነውና፤ በእኛ ሕይወት ውስጥ ከሥጋ ግንዛቤ የተሰወረ ይዞታ ሲይዝ፤ ምድራዊ ሆነን ብቻ እንድንኖር ሰማይን ይጋርደናል፡፡ ልክ ሰብአ ሰገልን ለሁለት ዓመታት እየመራች ያመጣቻቸው ሰማያዊ ኮከብ፤ ሰብአ ሰገል ወደ ምድራዊው ንጉሥ ሄሮድስ ቤተመንግሥት ሲገቡ እንደተጋረደችባቸው፡፡
ልብ እንበል! እናስተውል ዘንድ እግዚአብሔር ይርዳን፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ሰውን በሚፈጥርበት ጥበብ ውስጥ፤ አስቀድሞ ከምድር አፈር አበጅቶን፤ እስትንፋሱን ለአፈሩ ሲለግሰው ነው "ሰው" የምንባለው ፍጡራን የተፈጠርነው፡፡ አፈሩ ለእስትንፋሱ ማደሪያ ሆነ እንጂ፤ እስትንፋሱ ለአፈሩ ማደሪያ አልሆነም፡፡ ይህ ማለት የሚታየው ግዙፈ አካል ሥጋ(አፈር) ለማይታየው ረቂቀ አካል ነፍስ(የእግዚአብሔር እስትንፋስ) ማኅደሩ ሆነ ማለት ነው፡፡
ይህ የሥነ ተፈጥሮአችን ግንባታ የሚያስረዳን፤ የሰው ልጅ የሚታይ ሥጋ፥ ለማይታየው ለመንፈስ ማደሪያ ይሆን ዘንድ እንዳለው ነው፡፡ ረቂቅ የሆነ መንፈስ ግዙፍ ነገር ላይ ያርፋል እንጂ፤ ግዙፍ ነገር ረቂቅ ነገሩ ውስጥ ሊገባ አይችልም፡፡ የሚዳሰሰው የማይዳሰሰውን ይይዛል እንጂ፤ የማይዳሰሰው ለሚዳሰሰው አካል ማኖሪያው አይሆንም፡፡ በግልጽ ምሳሌ፥ ነፋስ ጎማ ውስጥ ይሞላል እንጂ፤ ጎማ ነፋስ ውስጥ አይገባም፡፡
እነሆ የሰው ልጆች የሚታየው ሥጋ ውስጥ የማትታየው የእግዚአብሔር መንፈስ-ነፍስ እንዳለች ሁሉ፤ ተጨማሪ የማይታዩ ክፉ መናፍስትም ይኖሩበት ዘንድ ወደ ሕይወታችን ተሰውረው እንዲመጡ የጠላትነት ጠባያቸው ግድ ይላል፡፡ ስለሆነም ለማንኛውም፥ በየትኛውም ሥፍራና የኑሮ እርከን ላይ ለተገኘ ሰው ወሳኙ ጥያቄ፤ ይሄ በሥጋዬ ሆኖ፥ ሕልውናዬን ተቆጣጥሮ፤ ሕይወቴን ከውስጥ ወደ ውጪ የሚመራው መንፈስ፥ የእግዚአብሔር ቅዱስ መንፈስ ነው? ወይስ የዲያቢሎስ ርኩስ መንፈስ? የሚለው ሲሆን፤ አኗኗራችንን አተኩረን በማጤን መርምረን ጥያቄውን በሚገባ መመለስ የእያንዳንዳችንን የሕይወት ቅርጽ መልክ ያስይዛል፡፡
ለመመርመር ይቻለን ዘንድ ደግሞ፤ የምንመረምረውን ጉዳይ መለየት፣ ስለ እርሱ ማወቅ፣ እውነተኛ መረጃዎችን በሚገባ መያዝ እና የያዝነው መረጃ በሕይወት ገጽታችን ውስጥ ያለውን አንድነትና ተያያዥነት በእርጋታ ማገናዘብ ያስፈልገናል፡፡ ኑሮአችንና ዘመናችንን ለመመርመር የሚያስችል አስፈላጊው እውቀት(know how) ከሌለን ግን፤ የሕይወታችንን መሠረት በምናየው የዓይን ብርጭቆ ልክ ብቻ እየጀመርን፤ እንደምናውቀውና እንደለመድነው የሥጋ መረዳቶቻችን ብቻ ስንመላለስ የምንገኝ፤ የልቦና ዓይን የታወረብን የሥጋ ባለጉዳዮች እንሆናለን፡፡
ይህ ራስን የመመርመሩ ፈቃድ የሌላቸው፤ በሥጋ ጥረት ብቻ የተገነባ ሃይማኖት ቀመስ እውቀት ያላቸው፤ በተግባር የታነጸ የእምነት አካሄድ ያልገባቸው አንዳንድ አገልጋዮችና ከነዚህም አገልጋዮች የተቀበሉ ምዕመናን፤ የሚናገሩት የዘልማድ ንግግር አለ እንደዚህ የሚል፤ "እኔ ስለ ሰይጣን ማወቅ ምን ይጠቅመኛል? እግዚአብሔር፥ ስለ ሞተልኝ ጌታዬ እንጂ ስለ ርኩስ መንፈስ መማር ምን ያደርጋል? ስለ ጻድቃን፣ ስለ ሰማእታት እና ስለ ቅዱሳን እንጂ ስለ ዲያቢሎስ መስማት አያስፈልግም" የሚል ድምፅ የሚያሰሙ የበዙ ሰዎች ይገኛሉ፡፡
"ስለ ቅዱሳን እንጂ ስለ ርኩሳን ማወቅ አይጠቅመኝም" የሚለውን ንግግር እንዲሁ በሥጋ ሚዛን ስንፈትሸው፤ ስለ ቸሩ መሐሪ ጌታ አምላክ ብዙ ማወቅ እንጂ ስለ አጥፊው ክፉ መንፈስ መገንዘብ ጥቅም እንደሌለው የተነገረ ይመስል ይሆናል፡፡
ነገር ግን፤ ክፉ መናፍስት በሰው ልጆች ውስጥ በሚመሽጉበት ጊዜ፤ ሰዎች በሚናገሩት ሰውኛ አንደበት ውስጥ ተከልለው ነው የነርሱን ሚስጢራዊ ፍቃድ የሚያስተላልፉት፡፡ ለምሳሌ ከላይ በተጠቀሰው ንግግር ላይ እንደተመለከተው "እኔ ጌታዬን ከያዝኩ ከዲያቢሎስ ጋር ምን አታገለኝ?" አይነት አዎንታ-ለበስ ቋንቋ የሚያሰሙ ሰዎች ውስጥ፤ ሁለት ድንበር አለ፡፡ አንደኛ የሰውየው ድንበር ሲሆን፤ ሰውየው የክፉ መናፍስትን ውጊያ በማወቅ እና በጦርነቱም መካከል ስለሚከሰተው የጸጋ ማደግ፣ የእምነት ግንዛቤ መስፋት፣ የበረከት ዕድል መምጣት፣ በጠላት የተዘጋው በእግዚአብሔር መከፈት የሚባሉ፤ የዲያቢሎስ ውጊያ ውጤቶችን፥ በዘመኑ አኗኗር ውስጥ በአምልኮት ምግባር ተርጉሞ ባለማወቁ የተናገረው ንግግር ነው፡፡ ክፉ መናፍስት እንዴት ባለ ድብቅ ስልትና የየዕለት ፈተና እንደሚያጠቁ አስርጾ የራሱን ሕይወት ፈትሾ ባለመገንዘቡ የተናገረው ንግግር ነው፡፡ ይሄ የሰብአዊው ፍጡር የሰውየው ድንበር ነው፡፡ ሁለተኛው ሰውየውን የተጋራው የመንፈሱ ድንበር ሲሆን፤ ግለሰቡ ባለማወቁ ምክንያት ባልያዘው ሰማያዊ መረጃና እውቀት በኩል ጠላት ምሽግ ሠርቶ በመደበቅ፤ የርሱን ዲያቢሎሳዊ ፍላጎት በሰውየው አለማወቅ ውስጥ ተከልሎ ያስፈጽማል፡፡ ሰውየው "ስለ ሰይጣን መስማቴ ምን ያድርግልኛል? ስለ አምላኬ እንጂ" በሚለው ለአምላክ ቀናዒ መስሎ በተናገረው ንግግር ውስጥ፤ መናፍስትን በአምልኮት መቃወም ያለውን ሁለገብ ጥቅም እየኖረበት ስላልተረዳ፤ በዚህ አለመረዳቱ ቦታ ላይ ሥፍራ የያዘው ክፉ መንፈስ፤ ሰውየው ወደ ራሱ ውድቀት፣ ወደ ራሱ አለመከናወን፣ ወደ ራሱ የሕይወት መሰናከል እና ወደ ራሱ ውስጣዊና ውጫያዊ መከራ አስተውሎ እንዳይገነዘብ ማስተዋሉን በማጨለም፤ በአምልኮት የእምነት ጦር ዕቃ እንዳይዋጋው አለማወቁን ተጠቅሞ የሰውየውን ልቦና አጥብቦ ይገዛዋል፡፡ በመቀጠል ሌሎች ሰዎች ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር እንዳይመጡ፤ በንግግሩ ውስጥ የአሳብ ቃል ይሆንና አጥፍቶ እንዲጠፋ ዕድሉን ከፊት እየቀደመ ይመራል፡፡
አንድ ከልቡ "እግዚአብሔርን እፈልጋለሁ፤ ከእርሱ ጋር መኖር እፈልጋለሁ፤ የእርሱን መለኮታዊ ኃይልና እውነት በሕይወቴ ውስጥ በተግባር መመልከት እፈልጋለሁ" የሚል #ማንኛውም_ግለሰብ ዲያቢሎስን ይዋጋ ዘንድ የግዴታ ግዴታው ነው፡፡ ይሄንን እውነት ደግሞ ማንም ሳይሆን ያስተማረን ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ስለዚህም የጌታ በምድር ከወንድማችን እንደ አንዱ ሆኖ የመምጣቱን መሠረት ነገር መጽሐፍ ቅዱስ ሲናገር "የዲያብሎስን ሥራ እንዲያፈርስ የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ።" ይላል 1ኛ.ዮሐንስ 3÷9 ላይ፡፡
በዚህም መሠረት፤ ቅዱሱን ጌታ መስለው ምድር ላይ የተገኙ ቅዱሳን የተባሉ ሁሉ ታሪካቸው "ገድል" ሆኖ ሲጻፍ፤ የመዋደቃቸው ጉዞ የሚያሳየው ከክፉ መንፈሶች ጋር ያደረጉትን ጦርነት ነው፡፡
እኛ ታዲያ፤ ሰው የሚያደርገንን የመናፍስትን ጦርነት ለመገንዘብ እምቢ ስንል፥ የአባቶቻችን ገድል የማይዘለል "ገደል" ሆኖብን፥ የታሪካቸውን ፈልግ ሳንከተል በአንደበት ስንዘክራቸው ብቻ እንገኛለን፡፡
"እኔ ቅዱስ እንደሆንኩ እናንተም ቅዱሳን ሁኑ" በሚለው የጽድቅ ጥሪ ውስጥ፤ እንደ ቅዱሳን የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር ለመረዳት የዲያብሎስን የዕለት ተዕለት ፈተና ማወቅና መዋጋት አስፈላጊ ነው፡፡ የመልካሙን መንገድ መስመር ለመያዝ እንችል ዘንድ፤ ክፉው መንገዳችን ላይ እንዳይገባ፣ ከፊት እየቀደመ መንገዱን እንዳይዘጋ፣ ከኋላ እየተከተለ እንዳያዘገየን፤ አሠራሩን ለየተን በማወቅ የጥፋት ጥበቡ ላይ በመንቃት፤ በምግባር የአምልኮት ኃይል ልንዋጋው ውዴታችን ሳይሆን ግዴታችን ነው፡፡ ክፉውን ሳልዋጋ መልካሙን አገኛለው የሚል ሰው፤ በሃያ አራት ሰዓት ጊዜ ውስጥ ሳይመሽ ይንጋ እያለ ነው፡፡ ጨለማውን እየገፈፍን ነው ብርሃኑን የምንገልጠው እንጂ፤ ጨለማውን ባለበት ትተነው አይደለም ብርሃን እናይ ዘንድ የምንችለው፡፡
ብዙ ሰዎች በእርግጠኝነት፤ በሕይወታቸው ውስጥ ተሰውረው ስለተደበቁ መናፍስት መረዳትና እነርሱን ለመዋጋት አምልኮት ከጀመሩባት ቅጽበት አንስቶ፤ እግዚአብሔርን ከዚህ በፊት ባላወቁት መንገድ ሊያውቁት ጀምረዋል፡፡ ይሄ ለምንድነው፤ ክፉው ጠላት የዘጋውን ቦታ በእግዚአብሔር ጦር ዕቃ እየታገሉ ለማስከፈት ሲጓዙ እግዚአብሔርን በቅርባቸው ያዩታልና ነው፡፡ አንድ ወቅት ላይ፥ ሚስኪኑ የመንገድ ዳር ሰው ዕውሩ በርጤሜዎስ፤ በመንገዱ ላይ ጌታ ሲያልፍ በሰማ ጊዜ "የዳዊት ልጅ ማረኝ" ብሎ ወደ ሰማዩ አባት ጸለየ (የማርቆስ ወንጌል 10፥47)፡፡ ጌታም ከወደ አጠገቡ አስጠርቶት "ምን ላደርግልህ ትወዳለህ?" ቢለው በርጤሜዎስ "አይ ዘንድ" አለ፡፡ "እይ!" ብሎ የተዘጋውን ዓይን ሲዳብሰው፤ በርጤሜዎስም በመጀመሪያ ሲያይ ጊዜ ከሁሉ አስቀድሞ አጠገቡ ያለውን ጌታን ማየት፡፡ እግዚአብሔር ይመስገን፡፡
በኛም ሕይወት ውስጥ፤ በስውር ጠላቶቻችን በኩል ለዘመናት የተዘጋው፤ በአምልኮት ውጊያ በኩል ሲከፈት፥ አጥፊውን መንፈስ በማድከም ፍልሚያ በዲያቢሎስ የታሰረው ሁሉ ነጻ መውጣት ሲጀምር፤ የማስተዋል ልቦናው ይኑረን እንጂ እግዚአብሔርን ከአጠገባችን በብዙ መንገድ እናየዋለን፡፡
የተዘጋውን ለማስከፈት የሚያስፈለግው የዕለት ዕለት ትንንቅ ላይ ድርሻ ሳይወስዱ፤ እግዚአብሔርን አያለሁ የሚሉ ሁሉ በተዘጋ በር የሚገባውን የብርሃን ጸዳል እንጂ ብርሃኑን እያዩ አይደለም፡፡ ክፉውን እየታገልክ ሳታሸሽ ደጉ ቸር ነውና ዘወትር እየመጣ ቢቀርብህም፤ ባንተ ኑሮ ውስጥ ከክፉው ጋር እየተደባለቀ፥ የደግ ነገሩ ጣዕምና ኃይል ንጹሕ ሆኖ ተተርጉሞ ሊገባህ አይችልም፡፡ አሁን እኮ ክፉውን ለይተን ስለማንታገል ነው አረማዊ ክርስቲያን ሆነን እንድንኖር፤ መልካሙን ከመጥፎው ጋር ቀይጠን፤ ለሰይጣንም ለእግዚአብሔርም አልመች ብለን የተቸገርነው፡፡
ማንኛውም ሰው ማረጋገጥ እንደሚችለው፤ አንድ ግለሰብ በእውነተኛ እምነት ላይ መነሻውን በመጀመር፤ በአምልኮት የዘወትር እንቅስቃሴ፥ መስገድና መጸለይ ሲጀምር በሥጋው ውስጥ ከእርሱ እውቅና ውጪ ሆኖ የተደበቀውን ጠላት መለየትና ማወቅ ይጀምራል፡፡ ምክንያቱም፤ ከውስጥ ተመሳስሎ የተቀመጠው አጥፊ መንፈስ የማይሰግድ የማይጸልይ አመፀኛ ፍጡር ስለሆነ፤ ግለሰቡ ለአምላክ መንበርከክ ከጀመረበት ሰዓት አንስቶ መቃወም ይጀምራል፡፡ ይሄ፤ የአምልኮት ስግደት ሰግደው፣ ከልብ ጸልየው፣ በመቁጠሪያ ጠላትን ተቃውመው ለማያውቁ ሰዎች 'የማይመስል' ወሬ ነው፡፡ እግዚአብሔር በምሕረት ያወቀው፥ መንበረከክ የጀመረው፤ ብቻ ነው የክፉ መንፈስ የተዳብሎ ማድፈጥ ምልክቶችን ሰውነት ውስጥ በሚፈጥራቸው የመቃወሚያ መንገዶች በኩል መገነዘብ እንደምን ያለ ጥቅም እንደሆነ ሊገነዘብ የሚታደለው፡፡ ይኸውም ሰው፤ ለእግዚአብሔር በመሰግድ ጠላቱን ያውቅ ዘንድ ሰማያዊ ጥሪን ለማድመጥ የታደለ ልበ ንጹሕ የሆነው ነው፡፡ "ልበ ንጹሖች ብፁዓን ናቸው፥ እግዚአብሔርን ያዩታልና።" (የማቴዎስ ወንጌል 5፥8)
( ከላይ እንደተገለጸው፤ ስለ አምልኮትና የመናፍስት ውጊያ ማወቅ ዕድል ጭምር ነውና፤ በማለዳ ንቁ ቻናል ውስጥ ስለ አምልኮት ስግደት፣ ስለ ቅዱስ ቁርባን፣ ስለ መናፍስትና መደበቅና ሌሎችም አስፈላጊ ትምህርቶችን በpdf ተሰናድተው ታገኛላችሁ፡፡ ተርፋችሁ አትርፉባቸው፡፡ )

0 Comments