ሔርሜት - ዘመናዊ ሰዎችን የምታሳድደው ዘመናይቷ መንፈስ

 


✍ከመምህር ግርማ ተማሪ ናትናኤል


" አሕዛብ ሁሉ ከዝሙትዋ ቍጣ ወይን ጠጅ የተነሳ ወድቀዋልና፥ የምድርም ነገሥታት ከእርስዋ ጋር ሴሰኑ የምድርም ነጋዴዎች ከቅምጥልነትዋ ኃይል የተነሳ ባለ ጠጋዎች ሆኑ ብሎ ጮኸ።" (የዮሐንስ ራእይ 18፥3)
የሔርሜት መንፈስ መሠረታዊ የጥፋት ስምሪቷ የሰው ልጆች የጾታ ግንኙነት ውስጥ በሚካተቱ ተፈጥሮአዊ ጉዳዮች ውስጥ የሚጠቀለል ሲሆን፤ በዚህ በዘመናዊው የሳይንስና የቴክሎኖጂው ሥልጣኔ ትውልድ ውስጥ፤ ራሷን እንደዘመኑ የዋጀች፤ የዘመኑን የአኗኗር መልክና ሂደት ያጠናች፤ በተለይም በወጣት የማሕበረሰብ ክፍሎች ላይ የጽልመት ጥላዋን የምትዘረጋ፤ በዘመናዊነት የተጣመመ አምላክ-አስከጂ የሥልጣኔ ትርጎማ ውስጥ በመደበቅ፤ ድምፅ አልባ ጉዳቶችን እያስከተለች ያለች፤ በአብዛኛው ጊዜ በሴት ጾታ የምትገለጽ መንፈስ ናት፡፡
ክፉ መናፍስት በተፈጥሮ ግንባታቸው ጾታ የላቸውም፡፡ ነገር ግን፥ ያደርሱ ዘንድ እንደሚፈልጉት የጥፋት ስልት፣ በሰው ልጅ ተፈጥሮ ውስጥ ፍጹም የተጋቦት ባላጋራነትን ለመያዝ፣ ባሕሪይንና የአኗኗር አካሄድን በቀላሉ ተላምዶ ለመመሳሰል እንዲችሉ፤ የጾታ ክፍፍል እያደረጉ በአዳም ዘር ትውልዶች ላይ ድብቅ ክፋታቸውን ተሰውረው ይገልጣሉ፡፡ ምንም እንኳን ሁሉም ከሰማይ በታች የወደቁ የጨለማ መንፈሶች የመጨረሻ ግብና ተልዕኮአቸው የሰውን ልጅ ዘላለማዊ ነፍሱን ከእግዚአብሔር መንግሥት ለመለየት ቢሆንም፤ ይህንን የመድረሻ እቅዳቸውን ለማሳካት የሚመርጡትና የሚነሡበት የማጥፊያ መንገድ፤ በየስምሪታቸው ድርሻ፤ እንደ አገሩ ሁናቴ፣ እንደ ሕብረተሰቡ የባሕል እምነትና እሴት፣ እንደ ግለሰቦች የጋራ መግባባትና የኑሮ ዘይቤ፤ የሚወሰን የተለያየ ጥበባዊ መስመርን በመጠቀም ይጓዛሉ፡፡
ሔርሜት ሴት መንፈስ፤ በስፋት ሴት ልጆችን የምታሳድድና የምትፈልግ፤ እንደ ተፈጥሮ ጠባያቸውም የእንስትነት ገጽታቸውን የምትዋረስ የሰይጣን እና የአጋንንት ምድብ ስትሆን፤ ወንዶችንም በመዋረስ ለጥፋት አንድነት ሰዎችን የምታቀናጅ ቄንጠኛ ጠባያትን የምታንጸባርቅ ከትውልዱ እውቅና ራቅ ያለች መንፈስ ናት፡፡
ከአዳም ዘመነ ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን በምድር ላይ እየኖረ ያለው የሰው ልጆች ነገድ፤ ወደፊት በሚቆጥረው ጊዜ ውስጥ፤ የተለያየ የኑሮ ማቅለያ ፈጠራዎች፣ የእውቀትና የምርምር እድገቶች፣ የሕክምናና የሥነ ሕይወት ትምህርቶች፣ የጥበብና የርዮተ ዓለም ንድፎች፣ የሳይንስና የቴክሎኖጂ ዘርፍ ጥናቶች፣ የፖለቲካ ፖሊሲና የአገራዊ መስተዳደር መርሆች ላይ ዘመኑ በተሻገረ ቁጥር ለውጥና ከፍታ እያሳየ፤ አሁን ዓለም የምትገኝበት የክፍለ ዘመን ምስል ላይ መደረስ ተችሏል፡፡ ይህ የሰው ልጆች የሥጋ እንቅስቃሴና የአኗኗር መዘመን ሂደት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በሄደበት አንድ ጎን ታዲያ፤ በሌላው ጎን ደግሞ ሰዎች ከእግዚአብሔር አምላክ የተሰጣቸው የሕያውነት እስትንፋስ እንዳላቸው ፍጹም ዘንግተው፤ የነፍስ ማንነታቸውን በጊዜያዊው የምድር ቆይታ ለውጠው፤ መንፈሳዊ እውነታዎችንና ሰማያዊ ሕይወትን ከኑሮአቸው ጓዳና ላይ እያሸሹ እያሸሹ፤ ክቧ ዓለም በአንድ የሳንቲም መልኳ በሠለጠነች ቁጥር፤ በሌላኛው መልኳ እየሠየጠነች፤ መንፈሳዊ መዋቅሮች እየተናዱ፣ የእምነት እንድምታዎች እየተናቁ፣ የሃይማኖት እሴቶች ነጻነት አሳጪ እንደሆኑ እየተቆጠሩ፣ ሰማያዊ ቃላትና የእውነት ድምፆች ሰሚ እያጡ፤ ዓለም በማብቂያ ዘመኗ ላይ እንደተነገረላት አስጨናቂ ሆና ትገኝ ዘንድ በክፉ መንፈሶች ግፊት እየተነዳች ትገኛለች፡፡ " ነገር ግን በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን እንዲመጣ ይህን እወቅ።" (2ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 3፥1)
ከምዕራባውያኑ በሥጋ ከሰለጠኑ አገራት ተወራርሳ ወደ አገራችንም ከገባች የሰነበተቺው ሔርሜት፤ በግለሰቦች ባሕሪያት ውስጥ ከውጪው አገራት የአኗኗር መልክ ቀስማ ይዛ የመጣቺውን መነሻ ጠባያቶቿን በምትገልጽበት ጊዜ፤ የቀደሙ የእምነት ታሪኮችን የምትጠላ፣ በሃይማኖት የመሥዋዕትነት ተጋድሎ በኩል የእግዚአብሔር ሰዎች የከፈሉትን ዋጋ የምትተች ሲሆንም የምትከዳ፣ መንፈሳዊ እወቀቶችና ትምህርቶች የሚያንገፈግፏት አሊያም ለመረዳት የሚያስቸግሯት፣ የዘመናዊነት ውጤት ምርቶች የሆኑትን የፋሽን አለባበሶች፣ ጌጣጌጦችና መሣሪያዎች አብዝታ የምታፈቅር፣ ሕይወትን ያለ መጨናነቅ ለማሳለፍ በሚደረገው የሥጋ ትንንቅም ውስጥ ዘወትር ለመዝናናት የሚሆን ዘዴ፣ አቅምና ጉልበት የምታወጣ፣ አገር ውሰጥ በሥጋ ተቀምጣ በአሳብ፣ በንግግር፣ በአለባበስ፣ በኑሮ ዝንባሌ፣ በሕይወት መርህና በመንፈስ ፍቃድ ዘወትር የምትሰደድ ግለሰብ ሆና ትገለጻለች፡፡ "በክፋትሽ ታምነሻል፤ የሚያየኝ የለም ብለሻል፤ ጥበብሽና እውቀትሽ አታልለውሻል፥ በልብሽም። እኔ ነኝ ከእኔም በቀር ሌላ የለም ብለሻል። " (ትንቢተ ኢሳይያስ 47፥10)
የሔርሜት ሥልጡኗ መንፈስ የግብር ጭዳዎች
" ቅምጥሊቱ ግን በሕይወትዋ ሳለች የሞተች ናት።" (1ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 5፥6
➊• የማማሊያ(የመማረኪያ) ምልክቶች (flirting signs)
በሔርሜት መንፈስ የተዋርሶ አገዛዝ ሥር የወደቀች ሴት፤ ለውበት ገጽታዎቿ አብዝታ የምትጠበብ፣ ለሰውነት ተክለ ቁመናዋ ሌት ተቀን የምትጨነቅ፣ ራሷን ከሌሎች ሴት ጓደኞቿ ለማስበለጥ ካልሆነ ትከሻ ለትከሻ ለማስተካከል የምትታትር፣ ሥጋዊ እሳቦቶቿ ከፋሽን ዜናዎች ውጪ መሻገር የማይፈልጉ ተብለጭላጭ ሴት ትሆናለች፡፡
ርኩሳን መናፍስት፤ በጠቅላላ አንድነት አንዳች የግብር ጭዳ ይፈልጋሉ፡፡ የግብር ጭዳ ማለት፥ መንፈስ በሰው ሕይወት ውስጥ ሆኖ የሚጠይቀው የሥራ ደመወዝ እንደማለት ነው፡፡ ያንን የግብር ክፍያ ካገኘ በኋላ፤ አስከትሎ ግለሰቡ ውስጥ ሆኖ ፍላጎቱን በሰውየው የሥጋ ፍቃድ ልክ ሸፍኖ በመምራት፤ ባገኘው የግብር ጭዳ መሠረት የግቡን ራእይ ለማሳካት ይንቀሳቀሳል፡፡
የሔርሜት መንፈሶች ተቀዳሚ ግብራቸው የማማሊያ ምልክቶች ሲሆኑ፤ በመሠረታዊነት ሴቶች ላይ መናፍስቱ ሲዋረሱ፤ ለየት ያለ አነሁላይ ሳቅ ተቀዳሚ መገለጫቸው ይሆናል፡፡ መናፍስቱ ለምደውት ከመጡት የኑሮ ቅርጽና ፍላጎት አንጻር፤ መጨናነቅ፣ መደበት፣ ማልቀስ፣ ማዘን፣ መሸማቀቅ፣ መሸበርና መጎሳቆል አይወዱም፡፡ በዚህም ከሌሎች አጥቂ መንፈሶች ለየት በማለት፤ የያዙትን ግለሰብ በተለያየ መንስኤ ማሳዘን፣ ማስለቀስ፣ ማስጨነቅ፣ ማቆራመትና ማቆርፈድ እምብዛም አይፈልጉም፡፡ ከዚያ ይልቅ በፌሽታና በፌንጠዚያ ወከባ ውስጥ ዙሪያውን አጥረው ማስቀመጥ ይፈልጋሉ፡፡ ይህንንም ለማሳካት የሚሄዱበት ትልቁ ስልት፤ ለየት ያለ ሳቅን በማሳቅ የሰዎችን ቀልብ እንደ ቡዳ ሆኖ በመብላት ትኩረት መሳብ ይወዳሉ፡፡
ሳቃቸውና የሳቃቸው ድምፅ በተፈጥሮ የሚያስደስት ሴቶች ለዚህች መንፈስ የመጀመሪያ የጥቃት ሰለባነት ተመራጭ ሲሆኑ፤ የሴቶቹን የሳቅ ድምፅ በመጋራት መንፈሷ አብራ በምትስቅበት ጊዜ፤ አዚማዊ ኃይልን ዙሪያዋ ባሉ ሰዎች ልቦና ላይ በስውር በማሳደር፤ የሴቲቱ ሳቅ ደስታ አመላካች ከመሆኑ ጀርባ፤ በመናፍስቱ ተጽዕኖ አስራጺነት በመጀመሪያ ቀልብን በመማረክ፤ በመቀጠል የዝሙት አሳቦችን በመጫር፤ ለፍትወት ንዳድ የሚጋብዝ የተፈላጊነት ስሜት ሳቁን በሚሰሙት ሰዎች ላይ ሁሉ ይፈጥራል፡፡
የሔርሜት መንፈስ ያለባቸው ሴቶች፤ ቀልድ፣ ጨዋታ፣ ፌዝና ፍንደቃ ከሌሎች ሴቶች ባመዘነ ሁኔታ አብዝተው የሚወዱ ሲሆን፤ ዙሪያቸው ያሉትንም ሰዎች ሁሉ በዚህ ስሜታቸው በማሸነፍ ብዙ አድናቂዎችና ወዳጆችን በቶሎ ያፈራሉ፡፡ የሔርሜት ሴት መንፈሶች፤ በተለየ ሁኔታ ወንዶችን የማማለል ልዩ ፍላጎት ሲኖራቸው፤ በማቅበጥበጥ፣ አነሁላይ እንቅስቃሴዎችን በመፍጠር፣ በረባ ባልረባውም ረጅም ሳቅ በማሳቅ፣ የመዝናኛ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በመስጠት በመሳብ፤ እነዚህን ማማረኪያ ባሕሪያት አይቶ የተጠጋው ሰው፥ በስውራኖቹ አዚማዊ ስበት ውስጥ በመወድቅ፤ ሴቲቱን እንደወደዳትና እንደተመኛት መናፍስቱ ልቡ ውስጥ አልፈው በመደስኮር፤ ወደ ዝሙት ፈቃድ እንዲመጣ አጥብቀው ይወተውቱታል፡፡ የሔርሜት መናፍስት ተልዕኮ ይሄ ነው፤ " እኔ ግን እላችኋለሁ፥ ወደ ሴት ያየ ሁሉ የተመኛትም ያን ጊዜ በልቡ ከእርስዋ ጋር አመንዝሮአል።" (የማቴዎስ ወንጌል 5፥28)
ሌላው፤ በዚህ የግብር ጭዳ በኩል ሴቲቱ የተለየች፣ የተወደደች፣ ቶሎ ማራኪ እንደሆነች አድርጋ ራሷን እንድትመለከት መናፍስቱ የሚፈልጉ ሲሆን፤ በዙሪያዋ ያሉ ሰዎችን የፍትወት አጀንዳ ውስጥ የተሸጎረ የፍቅር ጣምራነት ጥያቄ እንዲያነሡ በመገፋፋት፤ ብዙ ወንዶችን ያለ ሰብአዊ ፍላጎቷ እንድትመለከት ሔርሜቶች ይጫናሉ፡፡ በዚህ ጉዞ ውስጥም ታዲያ፤ ሴቷ ወደ ተረጋጋ ሰላማዊ የትዳር ዓለም እንዳትገባ ብዙ አማራጮችን በማብዛት አሳይቶ ማነቆ በመፍጠር፤ ሳታስተውለው ዕድሜዋ እንዲሮጥ ይታገላሉ፡፡ እንደምንም ታግላ ወደ ጋብቻ ሕይወት መንገዷን ስታቀና ደግሞ፤ አሁንም ተጨማሪ አማራጮችን ከፊቷ በመዘርጋት የትዳሯን አስተማማኝነት ለማናጋት ዘዴ ይቀይሳሉ፡፡ ሌሎች የመንፈሱ ተጠቂ የሆኑ ሔርሜቶች የተዋረሷቸው ያላገቡ ጓደኞቿን የብቸኛነት ኑሮ፤ ደስታ የሰፈነበት፣ ፈንጠዚያ የሰፈነበት፣ ጭንቀትና ውጣ ውረድ የሌለበት፣ ክፍተቶች የሌለቡት እንደሆነ አድርገው ምናብን አጥብበው በመቅረጽ እያሳዩ፤ ያገቡት ሴቶች የትዳር ሕይወታቸውን እንዲያማርሩ፣ ልጆቻቸውን የእስረኝነታቸው ምንጭ አድርገው እንዲወስዱ፣ የዘመኑን ቶሎ ቶሎ የሚቀያየር ብልጭልጭ ገጽታ በማስናፈቅ ኑሮአቸውን እያዩ ኋላ ቀርነት እንዲሰማቸው ሕሊናንና ልቦናን በመጫን የመሰብሰብ ሕይወትን መበተን የእነዚህ መናፍስት ሥራ ነው፡፡
➋• ኮስሞቲክስ፣ ጌጣጌጦች እና አልባሳት
" እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው።" (ኦሪት ዘፍጥረት 1፥27)
እግዚአብሔር አምላክ በሥነ ፍጥረት ጥበቡ ውስጥ የሰውን ልጆች በራሱ አምሳያ ቀርጾ የፈጠረበትን ድንቅ መልክ፤ ዲያቢሎስ በቅናት በመመልከት ወደራሱ መልክና ገጽታ ለመለወጥ ብዙ አካሄዶችን በመጓዝ ፈጣሪ የሰጠውን ሰማያዊ ስጦታ ለመንጠቅ ይጥራል፡፡ በዚህም ሰዎች በማንነታቸው ተፈጥሮ የተቀዳጁትን ሰብአዊ መልክ "በሰው ሰራሽ የመልክ ማሻሺያ፣ የውበት ማድመቂያ፣ የገጽታ ማሳመሪያ" ተብለው በተዘጋጁ የኮስምቲክስ እና የሕክምና መሣሪያዎች እንዲሸፍኑ የሥልጣኔው ዘመን የማስገደድ ያህል ያልተጻፈ ሕግ በየግለሰቡ ልብ ውስጥ አጽድቆ ባልተፈጠረ የማንነት መልክ ሰዎች እንዲገለጹ ጊዜው ከድብቅ መናፍስቶች ጋር ተባብሮ እየሠራ ይገኛል፡፡
የሔርሜት መናፍስት፤ በአንጻራዊ ፍላጎት ከሌሎቹም መንፈሶች በተለየ መልኩ፤ ኮስሞቲክሱን በጣም ይፈልጉታል፡፡ ለምን ዙሪያቸው ላይ ሁሌ ፌሽታው፣ ደስታው፣ መዝናኛው፣ ሳቅ ጨዋታው እንዳይቀዘቅዝ ውበትን በመጠቀም ሰዎችን ለመሳብ ያስችላቸዋል፡፡ ስለዚህ ሴት ልጆች ከተሰጣቸው የእግዚአብሔር መልክ ርቀው ሄደው እንዲጓዙና ሰማያዊ ገጽታቸውን በምድሩ ቀለም እንዲለውጡ ሔርሜቶች የዘመናዊ ትውልድ የአብዝሃነት አመለካከት ጀርባ በመከለል የኃጢአት መንስኤ የሚሆኑ እይታዎችን በማብዛት፤ በሥጋ አስተሳሰብ ብቻ ኑሮ እንዲመሠረት መንፈሳዊውን ዓለም እንደ ፍቃደ-ባርነት አኮስሶ በማሳየት የነፍስን ሰማያዊ ጉዞ ያዳክማሉ፡፡ "እንዲሁም ደግሞ ሴቶች በሚገባ ልብስ ከእፍረትና ራሳቸውን ከመግዛት ጋር ሰውነታቸውን ይሸልሙ፤ እግዚአብሔርን እንፈራለን ለሚሉት ሴቶች እንደሚገባ፥ መልካም በማድረግ እንጂ በሽሩባና በወርቅ ወይም በዕንቍ ወይም ዋጋው እጅግ በከበረ ልብስ አይሸለሙ።" (1ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 2፥9-10)
የሔርሜት መንፈሶች ዓለም አቀፋዊ ሥራና ፍላጎት
"ደንዝዘውም በመመኘት ርኵሰትን ሁሉ ለማድረግ ራሳቸውን ወደ ሴሰኝነት አሳልፈው ሰጡ።" (ወደ ኤፌሶን ሰዎች 4:19)
ከመቼውም ጊዜ በላይ፤ በዚህ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ትውልድ ውስጥ፤ በየማሕበራዊ ሚዲያው፣ በየመገናኛ አውታሩ፣ በየሥነጥበብ መዝናኛው ለሕዝብ በገፍ የሚለቀቁትን ምስሎችና መረጃዎች በመቆጣጠር፤ የራቁትነት አለባበስን ጠባይ ያደረገ፥ ደረትና ሰውነት የሚገለብጡ ሽራፊ ፋሽኖችን በማምረት ወሲባዊ ቋንቋዎችን፣ ትርክቶችን፣ ምልክቶችንና እንቅስቃሴዎችን በተለያየ ገለጻ አማካኝነት ያንጸባረቀ፣ የሥጋ ነጻነትን ለማርቀቅ ሲባል የደስተኝነት ዕብደትን የሚያስመኙ የማደንዠዣ ሙዛቃዎችንና ፊልሞችን በመጠቀም የእምነት ሕግጋትን በፈቃድ ያስጣሰ ሥራ በስፋት የተከወነ ሲሆን፤ ከዚህ የሥልጣኔ መዘውር ውጪ የሆኑ ግለሰቦች በትውልዱ የተነቀፉ፣ የተጠሉ፣ ዘመናዊነትን የናቁ፣ ትምህርትና እውቀት የማይገባቸው፣ አመዛዛኝነት የጎደላቸው፣ ጓታች አመለካከት ያላቸው ተደርገው እንዲቆጠሩ የኢኮኖሚ ጫናና መጤ አመለካከቶችን ለዘመን መግለጫነት በቶሎ በማስፋፋት በዘርፈ ብዙ አቅጣጫ አሳልፎ ተጽዕኖ በመፍጠር፤ ልክ እንደ ኖህ ዘመን የመጥፊያ ጊዜው እስኪመጣ ድረስ ሰዎችን እያስጨፈሩ፣ እያዘፈኑ፣ እያሳሳቁ፣ እያጫጫሱ፣ እያስጨበሱ፣ እያዘናጉ፣ እያዘሞቱ ይዞ መጥፋት የሔርሜት መናፍስት አጠቃላይ እቅድ ነው፡፡
➌• የተለያዩ ሱሶች እና አደንዛዥ ዕፆች
" በቀን እንደምንሆን በአገባብ እንመላለስ፤ በዘፈንና በስካር አይሁን፥ በዝሙትና በመዳራት አይሁን፥ በክርክርና በቅናት አይሁን፤" (ወደ ሮሜ ሰዎች 13፥13)
ሦስተኛው የሔርሜት መናፍስት የግብር ጭዳ፤ ጫት፣ ሺሻ፣ ሲጃራ፣ አልኮል መጠጦች እና መሰል ዕፆች ናቸው፡፡ በነዚህ ጠላቶች ክንድ ውስጥ የወደቀ ግለሰብ፤ ለመዝናናት፣ ለመደሰት፣ ለመፈንጠዝ የሚሰጠው ትኩረት ከፍ ያለ በመሆኑ፤ ወደ ሱሶችና ጭሳጭሶች ለመሳብ የሚወስድበት ጊዜ አጭር ነው የሚሆነው፡፡ በመንፈሱ ተጽዕኖ ሥር የወደቀች ሴት ምናልባት ሱስን የምትሸሽና የምትጠየፍ ከሆነች፤ ቀድመው ሱስ በለመዱ ጓደኞቿ ውስጥ ባለ መንፈስ አዚም አስገዳጅነት ወዳላሰበቺው የሕይወት መስመር ገብታ ማንነቷን ታጣው ዘንድ ዕድሏ በክፉው ዘመንና ጠላት ይታሰራል፡፡
✝
ሔርሜት መናፍስት በወንዶች ላይ
✝
ሀ) ሔርሜት ሴትን የሚያስወድዱ ሔርሜት መንፈሶች
ከላይ እንደተገለጸው፤ የሔርሜት መናፍስት የዘመኑን ቅርጽ በጣም የተላበሱ ሆነው ሳቅ፣ ቀልድ፣ መዝናናት፣ ቅብጠት፣ ቅምጥልነት፣ ዝሙታዊ ገለጻዎችን አስውበው ለያዟት እንስት የሚያዋርሱ አሳስቆ አጥፊ መንፈሶች በመሆናቸው፤ ብዙ ሰው በሥጋ ዓይን ብቻ ሴቲቱን ተመልክቶ የእርሷ ተፈጥሮዋዊ ጠባይ ስለሚመስለው በቶሎ ይመኛት ዘንድ መንገዱ ክፍት ነው፡፡ እንኪያስ፥ እነዚህን የመማረኪያ ስልቶች ተከትሎ የሚመጣው ወንድ፤ ከሔርሜቶቹ መንፈስ ጋር በመዋረስ፤ የልጅቷን ሳቅ፣ ጨዋታና እንቅስቃሴዎች በምናቡ ምስል ላይ እያደጋገሙ በማምጣት፤ እንደወደዳት፣ እንደፈለጋት፣ እንዳሰባት አድርገው የአእምሮውን አሳብ በነርሱ ልክ በመንዳት፤ ጤናማ በሚመስል የሥጋ ፍላጎት ነፍሱን ለመንፈሶቹ እንዲያስገዛ ይገደዳል፡፡
ወንዶች አስቀድመው በሰላማዊ የትዳር ሕይወት ውስጥም ሆነው ሔርሜት ካለባቸው ሴቶች ጋር ሲገናኙ፤ በመንፈሷ ማራኪ ቅምጥልነትና ስሜት ሳቢነት ባለትዳሩ ተማርኮ ውስጡን አሳልፎ ሲሰጥ፤ እንደ ቀድሞው ሁኔታ ኑሮውን መቀጠልና መምራት ያዳግተዋል፡፡ ምክንያቱም ባለሔርሜቷ ሴት ከአሳቡ ውስጥ እንድትቀረጽ የተዋረሱት መንፈሶች ከውጥ ሕሊናው ላይ በግፊት ስለሚጫኑ፤ የትዳር አጋሩን ፍቃዱ ባልሆነ አካሄድ እየሸሸ፤ በአንጻሩ ወደ ሔርሜቷ ሴት እየቀረበ፤ በአመንዝራት ሕይወት ኃጢአት ላይ ለመውደቅ በር የተከፈተለት ሰው ይሆናል፡፡ ልብ እንበል፡፡ የመናፍስቱ መድረሻ ዓለማቸው የእግዚአብሔርን ቃል የሰው ልጆች እንዲጥሱት መንገድ መቀየስ ነው፡፡ "እኔ ግን እላችኋለሁ፥ ያለ ዝሙት ምክንያት ሚስቱን የሚፈታ ሁሉ አመንዝራ ያደርጋታል፥ የተፈታችውንም የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል።" (የማቴዎስ ወንጌል 5፥32)
ለ) የሴትን ገጸ ባሕሪይ ለወንድ የሚያዋርሱ ሔርሜቶች
በሁለተኛው፤ የሔርሜት መንፈስ በወንዶች ላይ በምትገለጽበት ጊዜ፤ ወንዱ ልጅ ከተፈጥሮአዊ ባሕሪያት በማፈንገጥ እንደ ኮረዳ ሴቶች አብዝቶ መሽቀርቀር የሚወድ፣ ጌጣጌጦችን የሚጠቀም፣ የንግግሩ ዘይቤና ይዘትም የሴቶችን የሚመስል፣ መቅለስለስና መዝናናት የሚወድ የወንድ ሴት ይሆናል፡፡
ሐ) ወንድ ሔርሜት መንፈሶች በወንዶች ላይ
እነዚህ የዘመናዊው ትውልድ ልክፍት የሆኑ መናፍስት፤ በወንድ ጾታ ተዋርሰው በወንዶች ላይ በሚገለጹበት ጊዜ፤ ከሴት ሔርሜቶች ጋር ተመሳሰይ የአሠራር ሂደትንና የስምሪት ጠባይን የሚገልጡ ሲሆን፤ ሆኖሞ እንደ ጾታው በወንድ ተፈጥሮአዊ ባሕሪይ በሚዳበሉበት ጊዜ፤ ሴቶቹ ላይ ሲታይ የነበረው መሳሳቅ፣ መቅበጥበጥ፣ መሽኮርመም፣ መቅለስለስ፣ መስለምለም ይቀርና፤ ይልቁን ወንዱ ባለው ሐብት፥ ባለው መልክ፥ ባለው እውቀት፥ ባለው ዝና የሚኮፈስ፣ የሚጀነን፣ ባለው ነገር ተጠቅሞ ሰዎችን ለመሳብ የሚሞክር በመሆን ጭዳዎችን በሥጋዊ መማረኪያ መንገዶች ለማነሁለል የሚጥር ይሆናል፡፡
ሔርሜቶች እንዴት ይዋረሳሉ?
1• በሌሎች መናፍስት ተስበው
አስቀድመው እንደ ጠቋር፣ ዛር፣ ዓይነጥላና መሰል መናፍስት ቀድመው በሚገኙበት ጊዜ፤ ሔርሜት ከአንድ ሰው ወደ ሌላ ሰው በቀላሉ በሌሎቹ መናፍስት ተጋብዘው ይዋረሳሉ፡፡ ብዙ ጊዜ በሥጋ ተለምዶ፤ ሰዎች በጓደኝነት የተጽዕኖ ግፊት(peer pressure) ይጠቃሉ የሚል ንግርት ሲቀርብ ይሰማል፡፡ ይሄ በመንፈሳዊው እውነታ በኩል ሲፈተሽ፤ የተረጋጋ ኑሮ ትመራ የነበረቺው፣ ሃይማኖቷንና ባሕሏን ትፈራ የነበረቺው፣ የመሽቀርቀርና የመዝናናት ልምዱ ያልነበራት ሴት፤ በሔርሜት መናፍስት ከተያዙ ሴቶች ጋር ቅርብ ስትሆን፤ ውስጧ ቀድሞ መሽጎ የነበረው መንፈስ ሠራዊት ለመጨመር፤ ፍንደቃና ሳቅ የሚወዱትን ዘመናዊ መንፈሶች ስቦ ያስገባቸዋል፡፡
2• በሱስ
በመኪና ጉዞ ከኬላ ኬላ የማለፊያ ፍቃድ በማሳየት እንቅስቃሴው እንደሚቀጥል ሁሉ፤ መንፈስም ከሰው ሰው እና ከአከባቢ ወደ ሰው ለመዋረስ የማለፊያ ፍቃድ ይኖረዋል፡፡ የሔርሜት መንፈሶች መወራረሻ አንዱ መንገድ አንደንዣዥ ዕፅ፣ ጫት፣ ሺሻ፣ ሲጃራ፣ መጠጥ እና መሰል ሱሶች ሆነው ይጠቀሳሉ፡፡
3• አብሮ በመወለድ
በሔርሜት መናፍስት የተጠቁ ወላጆች፤ ያለ አምልኮትና ቅዱስ ቁርባን ለሚወልዷቸው ልጆችም መንፈሱን ልክፍት አድርገው ከመወለድ ጀምረው ያዋርሷቸዋል፡፡ በዚህ ጊዜ ሕፃናቱ ገና ከልጅነት የመናፍስቱን ጠባይ በመጋራት ባሕሪያቸውን የተጣመረውን ጠላት ባሕሪይ በዕድሜ ዑደታቸው ልክ እያሳደጉ እያሳደጉ መግለጽ ይጀምራሉ፡፡
ሔርሜቶች ከሌሎች መናፍስት የሚለዩበት ጠባይ
የነዚህ ዘመናዊ መንፈሶች ልዩ ጠባይ፤ እንደ ሌሎች መናፍስት ማስጨነቅ፣ ማስለቀስ፣ ማሳዘን እና ማበሰጫጨት ብዙም አይፈልጉም፡፡ በአብዛኛው እነዚህን አሉታዊ ስሜቶችም ሊፈጥሩ የሚችሉት የግብር መጠየቃቸው ሳይሟላላቸው ሲቀር ነው፡፡ ከዚህ ይልቅ ሔርሜቶች ማዝናናት፣ ማሳሳቅ፣ ማስጨበስ እና መዳራት የሚወዱ የሰው ጠላቶች ናቸው፡፡
ሌላው ሔርሜቶች ከዓይነጥላ መናፍስት ጋር በጣም ተመሳሳይ ጠባያትን ቢጋሩም፤ የሚለዩበት ዋነኛ ድንበር፤ ዓይነጥላ መናፍስት የተዋረሱትን ግለሰብ በተቃራኒ ጾታ መልኩ ሲዋረሱት ትዳርን የሚከለክሉ፣ ብቸኝነት እንዲፈጠር የሚያደርጉ፣ ሰዎችን የሚያርቁ የሚገፉ ሲሆኑ፤ ሔርሜቶች በተቃራኒ በዘመናዊነት ድባብ ላይ ሰፊ ድርሻን በመውሰድ፤ ሰዎችን በመማረክ መሳብና ማቅረብ የሚወዱ መንፈሶች ናቸው፡፡ " ሴሰኝነታችሁንም በላያችሁ ላይ ይመልሳሉ፥ እናንተም የጣዖቶቻችሁን ኃጢአት ትሸከማላችሁ፤ እኔም ጌታ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።
" (ትንቢተ ሕዝቅኤል 23፥49)

Post a Comment

0 Comments