"በሕግ ልትጸድቁ የምትፈልጉ ከክርስቶስ ተለይታችሁ ከጸጋው ወድቃችኋል።" ገላ 5፥4


መምህር ታሪኩ አበራ

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ "በሕግ ልትጸድቁ የምትፈልጉ ከክርስቶስ ተለይታችሁ ከጸጋው ወድቃችኋል።" የሚለውን ቃል የጻፈው በገላትያ ለነበሩ ክርስቲያኖች ነው።ገላትያ ማለት የዛሬዋ ቱርክ አካባቢ የምትገኝ ጥንታዊ ከተማ ነች መልዕክቱን የጻፈውም በ56ዓ.ም አካባቢ እንደሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ሰነዶች ይጠቁማሉ።

በወቅቱ በዚህች የገላትያ ከተማ ባለች ቤተክርስቲያን ውስጥ ያሉ ክርስቲያኖች ከሁለት ወገን የመጡ ነበሩ አንደኛዎቹ ወገኖች ከይሁዲ እምነት( ከኦሪት ሥርዐት) በቅዱስ ጳውሎስ ስብከት ወደ ክርስትና አምነው የመጡ ክርስቲያኖች ሲሆኑ ሁለተኛው ወገኖች ደግሞ ከአሕዛብነት(ከጣዖት አምልኮ ) በቅዱስ ጳውሎስ ስብከት ወደ ክርስትና የመጡ ነበሩ።

ቅዱስ ጳውሎስ እነዚህን ሁለት ወገኖች በአንድ የክርስትና ጥላ ሥር እንዲኖሩ ሰብኮ ፣በሃይማኖት አጽንቶ ፣በአንድነት እንዲያመልኩ አድርጎ ወደ ሌላ ሃገር ለአገልግሎት ሲሄድ ከመካከላቸው ልዩነትነትን የሚዘሩ ሰዎች ተነሱ። እነዚህም ከአይሁድ ወገን የሆኑ ሲሆኑ ከአሕዛብ ወገን የመጡትን ክርስቲያኖች እንዲህ ይሏቸው ጀመር ወንጌል እንበለ ኦሪት፣ ጥምቀት እንበለ ግዝረት አትረባም አትጠቅምም ማለትም ወንጌል ያለ ኦሪት፣ጥምቀትም ያለ ግዝረት አትረባም አትጠቅምም ።በኦሪቱ ሕግ ሳታልፋ በወንጌል በማመን ብቻ መጽደቅ አትችሉም፤ በክርስቶስ ስም ብትጠመቁም ካልተገረዛችሁ አትጸድቁም እያሉ ከአሕዛብ የመጡትን ክርስቲያኖች ያስጨንቋቸው፣ቀንበር ይጭኑባቸው ነበር። ይህ ጉዳይ ቅዱስ ጳውሎስ ዘንድ ስለደረሰ ሐዋርያው ወደ ገላትያ ሰዎች ስድስት ምዕራፍ ያለውን መልዕክት ልኮላቸዋል።የመልዕክቱ አጠቃላይ ጭብጥ የሚያተኩረው በኦሪት የነበረው ሕግ፣ሥርዓት፣መስዋዕት ፣አገልግሎት ሁሉ ምንም ጽድቅ ስላላመጣ እግዚአብሔር የተሻለውን የጽድቅ መንገድ ለሰው ልጆች ራሱ አዘጋጅቶ መስጠቱን በስፋት የሚዘረዝር ነው። የኦሪቱ ሕግና ሥርዓት ሊመጣ ላለው የአዲስ ኪዳን ሥርዓት ምሳሌ፣ጥላ ፣ሞግዚት እንደነበረ በስፋት የገለጸበትና አካሉ ሲገለጥ ጥላ እንደማያስፈልግ፣እናት ስትመጣ ሞግዚት ልጅን ለእናት እንደምታስረክብ፣አማናዊው የጽድቅ መንገድ ሲገለጥ ምሳሌ የነበረው ነገር ሁሉ ቦታውን እንደሚለቅ በስፋትና በጥልቀት ያስተማረበት ነው።

ግዝረት በኦሪት ጊዜ እግዚአብሔርን የሚያመልኩ ሕዝቦች ጣዖትን ከሚያመልኩ አሕዛብ የሚለዩበት ምልክት ነበር።ይህ የግዝረት ሥርዐት ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰጠውን ለአብርሃም ነበር።በአዲስ ኪዳን ግዝረት በጥምቀት ተተክቷል ክርስቲያኖች ሁሉ ከአሕዛብ መለያቸው ጥምቀት ነው።

"በዚያው፡ቀን፡አብርሃም፡ተገረዘ፥ልጁ፡እስማኤልም።
በቤት፡የተወለዱትና፡በብር፡ከእንግዳዎች፡የተገዙት፡የቤቱ፡ሰዎች፡ዅሉ፡ከርሱ፡ጋራ፡ተገረዙ ።" ዘፍ 17፥ 26
ታዲያ ሐዋርያው በሕግ ጽድቅ የለም ያለው የትኛውን ሕግ ነው? ቅዱስ ጳውሎስ ዘመኑ በሚመለከት በክርስቶስ በማመን እንጂ በሕግ ጽድቅ እንደሌለ ያስተምር ነበር ገላ.2÷16 ሮሜ.4÷13-14 ይህ ሐዋርያ ወደ ሮሜ ሰዎች በላከው መልዕክቱ "ታስረንበት ከነበረው #ከኦሪት_ሕግ ነጻ ወጥተናል" (ሮሜ.7÷6) እንዳለ <<በሕግ ጽድቅ የለም>> ያለው #የኦሪትን ሕግ ነው ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስም ኦሪትን ሕግ ይላታል "ሕግ በሙሴ ተሰጥቶን ነበርና ጸጋና እውነት ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ሆነልን" እንዳለ ዮሐ.1÷17 ወንጌላዊው ሕግ ያላት ሙሴ የተሰጠችውን ኦሪትን ነው ጸጋና እውነት ያለው ደግሞ በኢየሱስ ክርስቶስ የተሰጠቺውን ወንጌልን ነው ይሁን እንጂ ሕግን ሁልጊዜ ለኦሪት ብቻ አንሰጥም ወንጌልም ሕግ ናት።

ቅዱስ ጳውሎስ <<በሕግ ጽድቅ የለም>> እያለ ያስተማረው ለኦሪታውያን ነበረ <<የኦሪት መሥዕዋት በአማናዊው በሐዲስ ኪዳን መሥዕዋት በክርስቶስ ሥጋና ደም ግዝረቱ በጥምቀቱ አልተተካም>> ብለው ለሞገቱት አፍቃርያነ መሥዋተ ኦሪት ነበር ሐዋርያው እነዚህን አይሁዳውያንን በሃይማኖታዊ ትምህርት ይቃወማቸው (ያወግዛቸው) እንደ ነበር በመልዕክቱ ገልጦታል ለምሳሌ:-

"የኦሪትን ሥራ በመሥራት የሚጸደቅ ከሆነ እንኪያስ ክርስቶስ በከንቱ ሞተ" (ገላ.2÷21) እያለ ለእነዚህ ሰዎች ምላሸ ይሰጣቸው ነበር:: "ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን እንጂ የኦሪትን ሥራ በመሥራት እንደማይጸደቅ እናውቃለን" (ገላ.2÷16) ያለውም <<ተግባራተ ኦሪትን አንለቅም>> ላሉት የተሰጠ ቃል እንደ ነበር በግልጽ የሚያሳይ ነው::

"ወንድሞች ሆይ! እኔ ግዝረትን ገና የምሰብክ ከሆነ እንግዲህ ለምን ያሳድዱኛል?" (ገላ.5÷11) ብሎ እንዳሰፈረልን በአካል ሲያሳድዱት እርሱም በትምህርት ወይም በወንጌል የሚያሳድዳቸው የግዝረት ዓላማ የዘነጉትን እንደነበሩ እንረዳለን
ይህ ሐዋርያ <<በሕግ ጽድቅ የለም>> ያለውን የኦሪትን ሕግ ሲሆን ነገር ግን ሌላ ሕግ የወንጌል ሕግ እንዳለም ይናገራል:: ሐዋርያው ወደ ሮሜ ሰዎች በላከው መልዕክቱ "በሕግ የምትመካ ሕግን በመተላለፍ እግዚአብሔርን ታሳፍራለህን?" (ሮሜ.2÷23) በማለት ያሰፈረው የወንጌል ሕግ እንዳለች የሚናገር ነው ቀጠለም አድርጎ "በእግዚአብሔር ፊት ሕግን የሚያደርጉ ይጸድቃሉ እንጂ ሕግን የሚሰሙ አይጸድቁምና" ሮሜ.2÷13 በማለት በሕገ ወንጌል መጽደቅ እንደሚቻል በግልፅ ጽፏል::

ማጠቃለያ

ዛሬም ቢሆን እግዚአብሔር በተለያየ መለኮታዊ ጥበብ ወደ ክርስትና የሚጠራቸውን ሰዎች አስጨናቂ ቀንበር እየጫንን ልናስጨንቃቸው አይገባም።እግዚአብሔር በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ደም ጽድቅን ያለዋጋ እንዲያው በጸጋ እንደሰጠን አውቀን ይህንን በእምነት ተቀብለን የጽድቅ ፍሬ እያፈራን ልንመላለስ ይገባል።
የእምነት ሥራ ና የሕግ ሥራ ልዩነት አላቸው የእምነት ሥራ ማለት በክርስቶስ አምኖ በደሙ የጸደቀ ሰው ሁሉ እምነቱን በመልካም ሥራ ሁልጊዜ ሊገልጥ ይገባል ምግባር የሌለው እምነት በራሱ የሞተ ነውና የሕግ ሥራ ግን ከላይ እንደዘረዘርነው ሰው በራሱ ድካም ሕግን በመጠናቀቅ እጸድቃለሁ ብሎ ለመፈጸም የሚደክምበት ነገር ግን አንዱን እፈጽማለው ሲል ሌላውን እየሳተ ዘመኑን ሙሉ በከንቱ ድካም የሚኖረው ሕይወት ነው።
አንድ ችግኝ ተተክሎ ጸደቀ የምንለው ለምለም ቅጠልና መልካም ፍሬ ሲያፈራ ነው እንጂ ስለተተከለ ብቻ ጸድቋል አንልም የተተከለ ሁሉ አይጸድቅም መጠውለግም አለ።

በክርስቶስ አምኖ የጸደቀ ክርስቲያን ክርስቶሳዊ መዓዛ በሕይወቱ ሊታይ ግድ ነው።የፍቅር ሕይወት፣ትሕትና፣ቸርነት፣በጎነት፣ራስን መግዛት፣ቅድስና፣ታማኝነት ፣ሰውን ሁሉ በፍቅር ማየት፣ምጽዋት ወዘተ የጽድቅ ፍሬዎች ናቸው።በጾም፣በጸሎት፣በስግደት ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን መንፈሳዊ ሕብረት ማጠንከር የጽድቅ ፍሬ ነው።እነዚህ ፍሬዎች ካልታዩብን ግን ጠውልገናል።
"ምግባር የተለየው እምነት በራሱ የሞተ ነው።" ተብሎ ተጽፏል ያዕቆብ 2፥14-20
ክርስቶስ ኢየሱስ ድካማችንን አውቆ ጽድቃችንን በደሙ በኩል በጸጋ ስላደረገልን ክብርና ምሥጋና ለስሙ ይሁን።

Post a Comment

0 Comments