“በሽታ X መከሰቱ የጊዜ ጉዳይ እንጂ አይቀሬ ነው“ - ዶ/ር ቴዎድሮስ


ቀጣዩ ወረርሽኝ መከሰቱ እንደማይቀር ተገለጸ

“በሽታ X መከሰቱ የጊዜ ጉዳይ እንጂ አይቀሬ ነው“ - ዶ/ር ቴዎድሮስ

በዓለማችን ላይ የቀጣዩ ወረርሽኝ መከሰት የጊዜ ጉዳይ እንጂ አይቀሬ መሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም አስጠነቀቁ፡፡
የሆነ ጊዜ ላይ “ወረርሽኝ X” የመከሰት ዕድሉ ከፍተኛ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ሰሞኑን መናገራቸው ተዘግቧል፡፡

ባለፈው ሳምንት በተካሄደው የዓለም ጤና ድርጅት ጉባኤ ላይ ለታደሙ ተሳታፊዎች ንግግር ያደረጉት ዶ/ር ቴዎድሮስ፤ “በቀጣዩ ወረርሽኝ ዝግጁነት ላይ አጣዳፊ ዓለማቀፍ ስምምነት ያስፈልጋል” ብለዋል፡፡
”በሽታ X እያልን የምንጠራው ወረርሽኝ በኢንፍሉዌንዛ ቫይረስ ወይም በአዲስ ኮሮናቫይረስ አሊያም በአዲስ በሽታ አምጪ ተህዋስያን ሊከሰት ይችላል፤ ስለመንስኤው ገና አላወቅንም” ብለዋል፤ የጤና ድርጅቱ ሃላፊ፡፡

ሳይንቲስቶች፣ ቀጣዩ “በሽታ X“  ከኮቪድ ወረርሽኝ ሃያ እጥፍ ገዳይ እንደሚሆንና አደገኛ ዓለማቀፍ ወረርሽኝ ያስከትላል ብለው እንደሚያስቡ የዓለም ጤና ድርጅት ሰነድ ይጠቁማል፡፡

”አሁን ባለው ሁኔታ ዓለም ለቀጣዩ በሽታ X እና ለቀጣዩ ወረርሽኝ አልተዘጋጀም” ሲሉ ዶ/ር ቴዎድሮስ ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

በሽታ X የሚለውን ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀምነው በ2018 በተመሳሳይ መድረክና ጉባኤ ላይ ነው ያሉት የጤና ድርጅት ሃላፊው፤ አጠቃቀማችንም ገና ላላወቅነው ነገር ግን ዝግጁ ልንሆን ለምንችልበት በሽታ ነው ብለዋል፡፡

“ኮቪድ- 19 በሽታ X ነበር፤ አዲስ በሽታ የሚያመጣ አዲስ ተህዋስያን፡፡ ነገር ግን ሌላ በሽታ X ወይም በሽታ Y ወይም በሽታ Z  ይኖራል” ብለዋል፤ የተቋሙ ሃላፊ፡፡
የዶ/ር ቴዎድሮስ ተቋምና ዓለማቀፍ መንግሥታት በዓለማቀፍ የወረርሽኝ ዝግጁነት ስምምነት ላይ ሲሰሩ መቆየታቸው የተጠቆመ ሲሆን፤ የስምምነቱ ቀነ- ገደብ በመጪው ግንቦት ወር ላይ እንደሆነና በፍጥነት እየተቃረበ መሆኑ ተነግሯል፡፡

ለዚህ ዓለማቀፍ የወረርሽኝ ዝግጁነት ስምምነት አንዱ እንቅፋት፣ በዘፈቀደ የሚነዛው ውሸትና የሴራ ንድፈ ሃሳብ መሆኑን ዶ/ር ቴዎድሮስ ይናገራሉ፡፡

”--ስምምነቱ የአገር ሉአላዊነትን ለዓለም አቀፍ ጤና ድርጅት አሳልፎ የሚሰጥ ነው -- ዓለማቀፍ የጤና ድርጅት በአገራት ላይ የእንቅስቃሴ ገደብና የክትባት ግዴታ እንዲጥል ሥልጣን ይሰጠዋል --- ተቋሙ የሰዎችን የግል ህይወት ለመቆጣጠር ይፈልጋል--” የሚሉት እየተሰራጩ ከሚገኙት ውሸቶች ጥቂቶቹ መሆናቸውን ሃላፊው ጠቁመዋል፡፡

“እነዚህ ነገሮች ሙሉ በሙሉ ሃሰት ናቸው --- እንደዚህ የሚል ሰው አንድም መረጃው የለውም አሊያም እየዋሸ ነው” ብለዋል፤ ዶ/ር ቴዎድሮስ፡፡

የስምምነቱ ረቂቅ ቅጂ በተቋማቸው ድረገጽ ላይ እንደሚገኝና ሁሉም ሰው ለራሱ እንዲያነበውም ሃላፊው ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

“አንድ ነገር ግልጽ ማድረግ እፈልጋለሁ፡- ዓለማቀፍ የጤና ድርጅት በኮቪድ- 19 ወቅት በማንም ላይ ምንም ዓይነት ግዴታ አልጣለም፡፡ የእንቅስቃሴ ገደብም ሆነ የማስክና የክትባት ግዴታ አልጣለም” ብለዋል፤ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም፡፡

“ያንን የማድረግ ሥልጣን የለንም፤ አንፈልገውምም፡፡” ሲሉም አክለዋል፡፡

ምንጭ፦ አዲስ አድማስ 

Post a Comment

0 Comments