ክፍል አንድ
አሁን ላይ እየመጡ ያሉ ክሪፕቶዎች የሚገርሙ ናቸው። ተጠቃሚዎች ሞባይላቸውን ታፕ በማድረግና የሆኑ ጌሞችን በመጫወት፣ እንዲሁም አዲስ ሰው በመጋበዝ ponzi scheme የሚመስል ተግባር በመስራት ብቻ ተጠቃሚዎቻቸው ብዙ ሺ ዶላሮችን ሊያገኙ እንደሚችሉ ቃል ይገባሉ። ነገር ግን እነዚህ ክሪፕቶዎች ከፍተኛ ጉዳት ያላቸው የትውልዱ ወጥመዶች ናቸው።
ስለዚህ የሚያስከትሉትን ጉዳት እንመልከት። ይህንን ጉዳይ ከሶስት ነጥቦች አንፃር እንመለከታለን፦
1. ስለ ጥረት እና እሴት (labour and value)"
2. የአውሬው ገንዘብ እና cashless society አጀንዳ
3. ይህኛው አዲስና ለየት ያለ ሀሳብ ነው። ለጊዜው "energy" ብዬዋለሁ።
አሁን ነጥቦቹን እናብራራ።
ነጥቦቹ በየራሳቸው ሰፋፊ ስለሆኑ ሁሉንም በአንድ በአንድ ክፍል እንመለከታለን።
1. ጥረት እና እሴት።
አንድ ሁላችንም ማወቅ ያለብን ጉዳይ፣ በዚህ ዓለም ላይ ነፃ የሚባል ነገር እንደሌለ ነው። ሁሉም ነገር ተለፍቶበት የሚመጣ ነው። ማንም ሰው ሳይጥርና ላቡን ሳያፈስስ ገንዘብን ወይም ሀብትን ሊያገኝ አይችልም። ጥረቱ የጉልበት ሊሆን ይችላል፣ የጭንቅላት ስራ ሊሆን ይችላል። ወይም ደግሞ ሁለቱንም አንድ ላይ ሊሆን ይችላል። ብቻ ግን በማንኛውም መንገድ መጣር አለበት።
ታዲያ ሰው ሲጥር ዝምብሎ አይደለም፣ ይልቅስ ወደ ዓለም አዲስ እሴትን በመጨመር እንጂ። እሴትን መጨመር ነው ዋናው ነጥብ። ሰው በጥረቱ እሴትን ሲጨምር፣ የዚያ ክፍያ ደግሞ ደሞዙ ይሆናል። ያ ሰው ገንዘብ እንዲከፈለው የሚያደርገው የጨመረው እሴት ነው። እሴቱ ደግሞ የመጣው በጥረቱ ነው።
ይህ መሠረታዊ ህግ ነው። በኢኮኖሚክስ ውስጥ እንኳ የራሱ ቦታ አለው።
እሴት ስንል ምን ማለታችን ነው? እሴት ሁለት አይነት ሊሆን ይችላል። ምርትን ማምረት (product) ወይም አገልግሎት መስጠት (service) ናቸው። ምርት የምንለው ለምሳሌ የገበሬው ስንዴና ቡና፣ የእንጨት ሰሪው መቀመጫና ሶፋ፣ የኢንጂነሩ ማሽን ወይም ሶፍትዌር ወዘተ ናቸው። እነዚህ ሰዎች ይህንን ሲያመርቱ ቀድሞ የነበረውን ጥሬ እቃና ሀብት (resource)፣ በሱ ላይ አዲስ ነገር ጨምረዋል። ስለዚህም አዲስ እሴት ጨመሩ ማለት ነው፣ በጥረታቸው። ቀድሞ ያልነበረ ነገር፣ አሁን ግን እነሱ ያመጡት፣ ለሰዎች ጠቃሚ የሆነ፣ ሰዎች ለተለያዩ ምክንያቶች (ለመጠቀም በሉት፣ ህይወት ለማቅለል፣ ለመደሰት ወዘተ) የሚፈልጓቸው አዲስ ነገሮች ፈጠሩላቸው።
ስለዚህ ሰዎችም እነዚህን ጠቃሚ ነገሮች ለመውሰድ ሲሉ ዋጋ ይከፍላሉ ማለት ነው። ያ የሚከፍሉት ዋጋ ምንን ነው የሚወክለው? አምራቾቹ የፈጠሩትን እሴት (value) ነው። አምራቾቹ ደግሞ እሴት ለመፍጠር ምን አደረጉ? ጣሩ። ለፉ ደከሙ።
ይህ እጅግ ትልቅና ጠቃሚ ጽንሰ ሀሳብ ነው። እንዲያውም የራሱ ቲዮሪ አለው፣ "labour theory of value" የሚባል።
በተመሳሳይ ደግሞ አገልግሎት በመስጠትም እሴትን መጨመር ይቻላል። ሹፌሩ ከቦታ ቦታ ሲያጓጉዘን፣ ሆቴሉ ምግብና መኝታ ሲያቀርብልን፣ የቱሪስት አስጎብኚው ፓርኩን ወይም ሙዚየሙን ሲያስጎበኘን፣ መምህሩም ሲያስተምረን ወዘተ እነዚህ ነገሮች ለኛ አዲስ እሴትን እየጨመሩ ናቸው። ያንን እሴት ለመጨመር ደግሞ ጊዜያቸውን፣ ገንዘባውን፣ ጉልበታቸውን፣ እውቀታቸውን ወዘተ ለዚህ ሰውተው ነው።
እኛም ደግሞ ያንን አገልግሎት ለመጠቀም ስንል ዋጋ እንከፍላለን። ዋጋ የምንከፍለው ለምንድነው? ያንን እሴት ለማግኘት። የምንከፍለው ዋጋ ሰውየው ከፈጠረው ወይም ከጨመረው እሴት እኩል እንደሆነ ስለምናምን ነው።
እናም ያንን እሴት በምን እንለካው? የሚለው ነው ወሳኙ ጥያቄ።
ለዚህ የተለያዩ መፍትሄዎች አሉ። አንደኛው፣ ሌላ ተመጣጣኝ እሴትን በመመለስ ነው። ማለትም ለሰውየው ሌላ አገልግሎት ወይም ምርትን በማቅረብ ነው። ለምሳሌ ድሮ ሰዎች አንድን እቃ ለመግዛት ለሻጩ ሌላ እቃ ይሰጡት እንደነበረው። ከዚያም ደግሞ እቃን በእቃ መቀያየር ቀርቶ በአሞሌ መግዛት፣ ከዚያም በማርትሬዛ ሳንቲም የቻሉም ደግሞ በወርቅ፣ ከዚያ ደግሞ በብር እያልን መጣን። እነዚህ ሁሉ ነገሮች የሚወክሉት ሰዎች በጥረታቸውና በልፋታቸው የጨመሩትን እሴት ነው። ክፍያ በምንከፍላቸው ጊዜ የጨመሩልንን አዲስ እሴት በዚህ ያህል ብር ወይም አሞሌ ወይም ወርቅ እንለካዋለን ብለን እያሰብን ነው። ያንን ነው የምንሰጣቸው።
ስንሰጣቸው ለምን ይቀበሉናል? ምክንያቱም እነሱም ሌላ የሚፈልጉት ምርት ወይም አገልግሎት ስላለ። ከኛ የተቀበሉትን ገንዘብ ተቀብለው የሚሹትን እሴት ያለው ምርትና አገልግሎትን ስለሚገዙበት።
ይህንን ርዕስ በጣም ልናሰፋው እንችላለን። ለጊዜው ግን እናሳጥረውና ከተነሳንበት ርዕስ ጋር እናያይዘው።
ስልኩን ታፕ ታፕ ያረገ ሰው ምን ልፋት ለፋ? ምን ጥረት ጣረ? በጥረቱስ ምን አዲስ እሴት ጨመረ? ለማን ምን አገልግሎት ሰጠ ወይም ምን ምርት አቀረበ? ላቀረበው ምርትና አገልግሎት የሚገባው ዋጋስ አለ ወይ?
በሞባይል እስክሪን ላይ ያሉ ቁጥሮችስ የሰውን ጥረትና ልፋት ይወክላሉ ወይ? የሚጥርና የሚለፋ ሰው እስክሪኑ ላይ የሆኑ ቁጥሮች ስለተቀመጡ ብቻ አምኖ ይቀበላል ወይ? የልፋትህ ዋጋ ይህ ነው ቢባል ያምናል? ለምንስ ያምናል?
ከየት እንደመጣ የማናውቀው፣ የኛ ይሁን አይሁን እርግጠኛ ያልሆንበት ዶላርስ ዝምብሎ የሚቀበል ሰው አለ? ብር እንዴት ተለፍቶበት እንደሚመጣ የሚያውቅ ሰው፣ ከመሬት ተንስቶ 40ሺ ብር አለህ ሲባል እሺ ብሎ ይቀበላል? ይሄ ብር የማነው? በትክክል ማነው ባለቤቱ፣ እንዴት አመጣ ይህንን ገንዘብ? ሰርቶ ነው ወይም በሌላ መንገድ በግፍ የመጣ ነው? ለኔስ ለምን ይሰጠኛል? ብሎ አይጠይቅም? ካልጠየቀ ሰውየው ወይ ማገናዘብ አይችልም? ወይም ዝምብሎ መንጋውን የሚከተል ነው? አልያም ደግሞ ሞራላዊነት የጎደለው ስስታም ነው።
ችግሩ አብዛኛው የኢትዮጵያ ወጣት ስራ የለውም። ቢዝነስ ኖሮት አያውቅም። ክፉዎቹ ገዢዎቻችንም ወጣቱ የራሱን ቢዝነስ ከፍቶ፣ ሰርቶና ለፍቶ እንዳያልፍለት መንገዱን ሁሉ ዘጋግተዋል። አንዳንድ ሰዎች መሪዎቹ መሃይም ስለሆኑ ለወጣቱ ስራ መፍጠር አልቻሉም ይላሉ። እንደኔ ግን ከመሃይሞቹ መሪዎች በላይ እውቀት ያላቸው ክፉዎች አሉ። የሀገሪቱ የማህበራዊ ስርአት፣ የሚዲያና ደህንነት መዋቅር በእጃቸው ያለ ጥቂት ክፉዎች አሉ። የክፋታቸው ጥግ እንዲህ ነው ተብሎ የማይነገር። በነዚህ ክፉዎችና ከነሱ ስር ባሉት መሃይሞች ምክንያት ትውልዱ መስራት እየቻለ ግን መንገድ ሁሉ ተዘጋግቶበት ስራ አጥቶ፣ በለጋ እድሜ ያለውም የወደፊት እድሉ ተጠረቃቅሞ ቁጭ ያለ ነው። በዚህም ምክንያት አብዛኛው ወጣት ስራ ሰርቶ ስለማያውቅ ከላይ የተገለጠው ጽንሰ ሀሳብ ለሱ ግልጽ አደለም። ሰርቶ ለፍቶ የሚያውቅ ግን በጥቂቱም ሆነ በሰፊው ይረዳዋል። ነገር ግን በሚሊዮን የሚቆጠር ኢትዮጵያዊ የመስራትና የመልፋት እድሉን እንኳ ስለተነጠቀ ያንን ጽንሰ ሀሳብ የመረዳት እድል የለውም።
በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለ ታዲያ ድንገት የሆነ እድል ሲፈጠር፣ ለአንድ ወር ስልክህን መታ መታ አርገህ ሺ አስር ሺ ዶላር ታገኛለህ ሲባል፣ እሺ የማይል ማን አለ? የማይቀበል ማን አለ? ያ ነው ችግሩ።
ይቀጥላል
0 Comments