አነቃቂ ተናጋሪዎች . . .


በዘላለም መንግሥቱ

የአነቃቂ ተናጋሪዎች ንግግር ባሕርያት ምን መሆኑን ስናውቅ ነው የሚናገሩት ነገር፥ ስብከት ወይም ንግግር መሆኑን የምናስተውለው። ግባቸው ጥቅማቸው መሆኑን መናገር አያስፈልግም።

የንግግራቸው ይዘት ስሜት ኮርኳሪና ቀስቃሽ ነው። ቢርቅ ቢርቅ፥ ነፍሳዊ እንጂ መንፈሳዊ አይደለም። ጉዳያቸው በራሳቸው ቋንቋ የpositive mindset ጉዳይ ነው። ንግግራቸው ግብ ተኮር ተጽዕኖ ማሳደር ነው። ስሜት መቀስቀሱ ከድምጽ፥ ከአለባበስ፥ ከመድረክ መሰናዶ፥ ወዘተ ይነሣል፤ እዚያ ግን አያበቃም።

ንግግራቸውን ከተለያዩ ምንጮች ቃርመው፥ ሸምድደው፥ በጣም ተለማምደው ነው የሚያቀርቡት። ልምምዳቸው ንግግራቸውን ወደ ድራማነት ይቀይረዋል። ለምሳሌ፥ ልብሳቸውን በጭቃ ሊለውሱ፥ ደም ሊቀቡ፥ ወለል ላይ ሊንደባለሉ፥ ሊያለቅሱ ይችላሉ። የሚናገሩ ሌሎች ሰዎችን ከትዋኔያዊ ማዕዘን አንጻር እንዲታዩና እንዲናገሩ ያደርጋሉ።

ከክርስትና አንጻር ስንፈትሸው፥ ዘላለማዊው እና መንፈሳዊው ነገር የለበትም፤ ወንጌል የለበትም፤ ኃጢአት፥ መስቀል፥ ደም፥ ሲዖል፥ ዘላለማዊ ሞት፥ ዘላለማዊ ሕይወት የሉበትም። ክርስቶስ የለበትም። ክርስቶስን ከጠሩ፥ 'ክርስቶስ ምስክሬ ነው!' ብሎ ለመማል ብቻ ነው። እነዚህ ጉዳዮች ለክርስቲያናዊ አገልግሎትና መልእክት ዋና ሲሆኑ፥ የአነቃቂ ተናጋሪዎች ትኩረት ግን እነዚህ ሳይሆኑ ምድራዊ ስኬት፥ ሥጋዊ ጥቅም፥ አእምሯዊ መዳረሻ፥ ስሜታዊ ደስታ ናቸው። በጊዜያዊ ሞቅታ ወደ 35ሺህ ጫማ ከፍታ ከፍ ማድረግ ነው። ይህንን ለማወቅ የአንድ አነቃቂ ተናጋሪ አንድ ንግግር ብቻ ወስዶ መመርመር በቂ ነው።

ልብ እንበል፤ ምድራዊ ስኬት፥ ሥጋዊ ጥቅም፥ አእምሯዊ መዳረሻና ስሜታዊ ደስታ በራሳቸው ጠቃሚ ናቸው። ይሁን እንጂ፥ እነዚህን ነገሮች ማንም ክርስቲያን ያልሆነ ተናጋሪ ሰውም አሳምሮ ሊናገራቸው የሚችላቸው ናቸው። የክርስቲያናዊ መልእክት ልዩነቱ ዘላለማዊ ልዩነት መፍጠሩ ላይ ነው። ዘላለማዊ ልዩነት።

አነቃቂ ንግግሮችንና ወንጌልን እየለየን።


Post a Comment

0 Comments