ለቅዱስ ሲኖዶስ


መ/ር ታሪኩ አበራ

« ሁሉ በአገባብና በሥርዓት ይሁን »1ኛ ቆር 14፥40

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሦስት ሺህ ዘመናት ታሪክና ጠንካራ ተቋማዊ የአስተዳደር መዋቅሯን ጠብቃ በክብር ዘመናትን የተሻገረች ታላቅ የእግዚአብሔር ተቋም ነች። ቤተክርስቲያኒቱ ቀኖናዊና አስተዳደራዊ ውሳኔዎችን በምታስተላልፍበት ጊዜ ሁሉ መሠረቷ የእግዚአብሔር ቃል በመሆኑ ድንጋጌዎቿ ቤተክርስቲያንን ወደ ሰላም ወደብ እያሻገረ ከዘመናችን አድርሷታል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በመንጋ ፍርድና  በማኅበራዊ ሚዲያ በሚፈጠሩ መርሕ አልባ ጩኽቶች የብፁዓን አባቶች ስም ሲሰደብና ሲዋረድ በተደጋጋሚ እየተመለከትን ነው። ይህ የቅዱስ ሲኖዶስን ክብርና ልዕልና የሚያንኳስስ የግለሰብና የጥቂት ቡድኖች ጫጫታ የብዙ ምዕመናንን ልቡና እያዋከ የሚገኝ ሲሆን እንደ ተቋም ደግሞ  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሌሎች ቤተ እምነቶች መቀለጃና መሳለቂያ እንድትሆን እየደረጋት ይገኛል።ለዚህ ሁሉ ችግር መከሰት ምክንያት ደግሞ የጠቅላይ ቤተክህነት የሕግ ክፍልና የሚዲያ ዲፓርትመንት የጋራ ጥምረት በመፍጠር  የቤተክርስቲያኒቱን ክብርና ሉዓላዊነት የሚያዋርድ ተግባራት የሚፈጽሙ ግለሰቦችንና ቡድኖችን እየተከታተሉ በየትኛው የማኅበራዊ ሚዲያ ፕላት ፎርሞች ላይ ለሚመለከተው አካል ሪፓርት እያደረጉ ባለማዘጋታቸውና  በቸልተኝነት ነገሮችን አቅልለው  በመመልከታቸው የሚፈጠር ችግር ነው።

በቅርቡ አባ ዮሐንስ የተባሉ መናኝ በሰሜን አሜሪካ ቤተክርስቲያን ሊከፍቱ ነው በሚል ምክንያት ብዙ ውዝግብና እሰጣገባ በየሚዲያው እየተመለከትን ነው።ጉዳዩ ከልክ በላይ እየተለጠጠ ሄዶ የቤተክርስቲያኒቱ ታላላቅ አረጋውያን ሊቃነ ጳጳሳት ሳይቀሩ ማንም እየተነሳ ሲሰድባቸው፣ሲያንጓጥጣቸውና ሲዋርዳቸው እየተመለከትን ውስጣችን በጣም እያዘነ ነው።እነዚህ አረጋውያን ብፁዓን አባቶች ዕድሜያቸውን ሙሉ ቤተክርስቲያንን ሲያገለግሉ የኖሩ፣ በቤተክርስቲያን ትምህርት በቂ ሙያና ልምድ ያካበቱ፣በፈተና ሰዓት ለቤተክርስቲያን የግንባር ሥጋ ሆነው መከራን የታገሉ፣ ሌሊትና ቀን የክርስቶስን ቤተመቅደስ በክህነት የሚያገለግሉ ለቤተክርስቲያን ዕድገትና ከፍታ ከማናችንም በላይ ግድ የሚላቸው ዋኖቻችን ናቸው።

አለመታደል ሆኖ ግን  ማንነታቸውና ምንነታቸው የማይታወቁ የፌስቡክ አርበኞች ከብፁዓን አባቶች በላይ ለቤተክርስቲያን አሳቢና ተቆርቋሪ መስለው ከጀርባቸው የተለያየ የፓለቲካና የጥቅም ድብቅ አጀንዳ ተሸክመው እግረ መንገዳቸውንም  የዩ-ቲዩብና የቲክቶክ ምጽዋት ሳንቲሞችን ተስፋ አድርገው ነገሮችን በሚዛናዊነት መመልከት ያልቻሉ ምዕመናን ግራሲያጋቡ እየተመለከትን በመሆኑ ቅዱስ ሲኖዶስ አስፈላጊውን ውሳኔና ሕጋዊ እርምጃዎችን በመውሰድ የቤተክርስቲያንን ክብር ያስጠብቅ ዘንድ በአጽንዖት ማሳሰብ እወዳለሁ።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ታሪክ ውስጥ መናኝ ባሕታውያን የከበረ ሥፍራና የላቀ ጥቅም አላቸው በጸሎታቸው ሃገርን ከጥፋት ሕዝብን ከስደት ይጠብቃሉ፣ከእግዚአብሔር በሚሰጣቸው መልዕክት ኃላፍያትንና መጻዕያትን በመናገር ቀናውን መንገድ ለሕዝብና ለካህናት  ያመላክታሉ፣ምዕመናን በፈሪሃ መለኮት፣በቅድስና፣በጾም፣በጸሎት፣በስግደት እንዲኖሩ መልካም አርአያ በመሆን ትውልድን ለትሩፋት ሥራ ያነቃሉ።

በኢትዮጵያ ውስጥ እንደዛሬው የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ከመሥፋፋቱና መንፈሳዊ ኮሌጆች ከመበራከታቸው በፊት በመላ ሃገሪቱ በመዘዋወር የወንጌል ብርሃንን ያዳረሱ ሕዝቡን ከአምልኮተ ጣዖት ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር የመለሱ ፣ከአባይ ጠንቋይ፣ከባዕድ አምልኮ እስራት አላቀው ወደ ክርስቶስ ፍቅር የሰበሰቡ ሰባኪ ባሕታውያን ናቸው።ከአጼ ኃይለ ሥላሴ እስከ ደርግ ዘመነ መንግሥት ከዚያም በኋላ ከኢኃዴግ አሁን  እስካለሁ ሥርዓት ድረስ ለቤተክርስቲያን ጠበቃ በመሆን አምባገነን ፓለቲከኞችን ፊትለፊት በመጋፈጥ የቤተክርስቲያንን ክብርና ልዕልና ያስከበሩ በዚህም ብዙ እስርና እንግልት የተቀበሉ እነዚሁ መናኝ ባሕታውያን ናቸው።ከአጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመንግሥት በፊትም ምንም እንኳ ብዙ የከፋ የፓለቲከኞች ጫና ቤተክርስቲያንን ባይፈትናትም ባሕታውያን በተለያየ ጊዜ ብቅ እያሉ መንፈሳዊ መልዕክታቸውን ያስተላልፉ ነበር። ጸረ ኦርቶዶክስ ሥርዐት በኢትዮጵያ ከመጣበት ከደርግ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ በመላ ኢትዮጵያ በመዘዋወር አዳዲስ አብያተ ክርስቲያናት እንዲተከል ሕዝብ ያስተባበሩ፣ገዳማትን በሚያስፈልጋቸው ነገር ሁሉ በመርዳት ያጠናከሩ፣ሃይማኖት እንዲሰፋ ምዕመናን በእምነት እንዲበረቱ ትልቅ አስተዋጽዖ ያደረጉ  እነዚሁ መናኝ ባሕታውያን ናቸው።

ከቅርብ ጊዜ ትዝታዎቻችን በዋነኝነት የምናስታውሳቸው።

* ባሕታዊ አባ ገበሬው

*ባሕታዊ አባ ገ/እግዚአብሔር

* ባሕታዊ አባ መሸ በከንቱ 

*ባሕታዊ ቀለመወርቅ

*ባሕታዊ ገ/መስቀል

* ባሕታዊ አምሐ ኢየሱስና ሌሎችም በስፋት ይገለጻሉ።

እነዚህ ባሕታውያን በወቅቱ ቤተክርስቲያንን በዘመናቸው ብዙ ቢጠቅሟትም አንዳንድ ክፉ ልብ ያላቸው ሰዎች በቅንዓት መንፈስ ሌሊትና ቀን ያለ እረፍት ስማቸውን በማጥፋትና በማሳደድ ከአገልግሎት ውጪ ሲያደርጓቸው እነዚህ መናንያን  የሞት ሽረት ትግል አድርገው በቤተክርስቲያን ውስጥ አንገታቸውን ሰብረው እንዲኖሩ ተደርገዋል። እነዚህ መናንያንን ቤተክርስቲያን በአግባቡ ብትጠቀምባቸውና ሲያጠፉ እየገሰጸች፣ሲያለሙ እያመሰገነች በመዋቅር ውስጥ ተይዘው በሕግና በሥርዓት አገልግሎታቸውን እንዲቀጥሉ ብታደርግ ቤተክርስቲያኒቱ ብዙ ታተርፍ ነበር።አለመታደል ሆኖ ግን እጃቸውን  አለስልሰው ምላሳቸውን  አርዝመው የሰው ስም እያጠለሹ በብዕርና በምላስ መርዝ ብዙዎችን እየገደሉ  የሚውሉ ለቤተክርስቲያን አንዳች ነገር ሳይሰሩ ሆድና ጀርባቸውን እያሳበጡ ተቀምጠው በአገልግሎት የሚደክሙና የሚሰሩ ሰዎችን ሲያኮላሹ የሚኖሩ ርጉማን ሰዎች በየቤተክርስቲያኑ ተሰግስገው  ቤተክርስቲያንን በጣም ጎድተዋታል ።

ይህ ብልሹ ያለፈ  ታሪክ ዛሬም ሲደገም  እያየን በጣም እያዘንን ነው።ባሕታዊ አባ ዮሐንስ ከ 10 በላይ አብያተ ክርስቲያናትን አሳንጸዋል፣ገዳማትን አልምተዋል፣ጥርጊያ መንገድ አሰርተዋል፣የአቅማቸውን ያህል ሕዝብን እያስተማሩ ወደ መንፈሳዊ ሕይወት እንዲመጣ ሲጥሩ ይታያል  ይህ ሁሉ ለኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቀሪ ሐብትና ቅርስ ነው።የእሳቸውን ሩብ ያህል እንኳን መሬት ላይ ወርደው  ያልሰሩ ሰዎች በየሚዲያው ሲሳደቡ፣ሲራገሙ፣አቃቄር ሲያወጡ እየተመለከትን በንግግራቸው እጅግ እያፈርን ነው።ሰውየው ያጠፉት፣የተሳሳቱት ነገር ካለ የቤተክርስቲያኒቱ የበላይ አካል ቅዱስ ሲኖዶስና የሚመለከተው የጠቅላይ ቤተክህነት መምርያ ተከታትሎ እርምት በሚያስፈልገው ጉዳይ እርምት እየሰጠ፣የዕውቀት ክፍተት ካለ በትምህርት የሚያድጉበትን መንገድ እያመቻቸ፣ውይይት በሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ላይ ጥልቅ ውይይት እያደረገ የቤተክርስቲያንን ጥቅም እያስቀደመ እንዲህ ዓይነት ሰዎችን በመዋቅር ውስጥ በሕጋዊ መንገድ በመያዝ ሊጠቀምባቸው ይገባል እንጂ በየፌስቡኩ ሲንጫጩ በሚውሉ አውርቶ አደር ሥራ ፈቶች ወሬ ሕዝብ ሲታወክ ዝም ብሎ መመልከት አግባብ አይደለም።

ለመሆኑ በየፌስቡኩና በዩቲዩብ በቲክቶክ ሲሳደቡ ሲነቅፉ የሚውሉ እነርሱ ለቤተክርስቲያን ምን ሠርተዋል? አንድ ቤተክርስቲያን አሰርተዋል ? ገዳማትን አቋቁመዋል?ጧሪ ቀባሪ ያጡ አረጋውያንን ሰብስበው ይረዳሉ፣ወላጅ አልባ ሕጻናትን ያሳድጋሉ? ለቤተክርስቲያን ተገቢውን አሥራት ያወጣሉ ? ወይስ እየተሳደቡ ሳንቲም ይለቃቅማሉ ?

አንዳንዶችማ አንድም ቀን ቤተመቅደስ ገብተው ቀድሰው፣አወድሰው፣ማኅሌት ቆመው ፣ሰዓታት አድርሰው የማያውቁ ወገበ ነጮች በቤተክርስቲያን ትምህርት የደከሙ ሊቃውንትንና ብፁዓን አባቶችን ሲሳደቡ ሲያዋርዱ እያየን አዕምሯቸው የቀነጨረ ምናምንቴ መሆናቸውን እየታዘብን ነው።

ትናንት የፕሮቴስታንት ፓስተር ሆኖ ድንግል ማርያምንና ቅዱሳንን ሲሳደብ የኖረ ብንያም ሽታዬ የተባለ አንድ ተራ ግለሰብ ዘመናቸውን ሙሉ ቅዱሳንን ሲያከብሩ ለድንግል ማርያም ክብር ሲሰጡ የኖሩ አባቶችን በየሚዲያው ሲያበሻቅጥ ማየት እጅግ ያሳፍራል ከእርሱ ጋር ሆነው ሆያ ሆዬ የሚሉ ሰዎችም ከእርሱ የማይሻሉ ምናምንቴዎች ናቸው።

ስለዚህ ቅዱስ ሲኖዶስ የቤተክርስቲያንን ክብር፣ ጥቅምና ሉዓላዊነትን ማዕከል በማድረግ በሕዝብ መካከል እየተነሳ ላለው ውዝግብ አስፈላጊውን መፍትሔ ይሰጥ ዘንድ በእክብሮት እንጠይቃለን።



#

Post a Comment

0 Comments