ዲጅታል መታወቂያ ለምን እንቃወማለን?

አንዳንድ ሰዎች ባለማስተዋል እና ባለማወቅ የዲጂታል አይዲን መቃወማችንን እንደ ከፋት አይተውታል። ተቃውሞአችንንም፣ ሃገርን የሚለውጥ አዲስ ቴክኖሎጂን እንደመቃወም፣ እንደ ኋላ ቀርነት አይተውታል። ይህ ስህተት እና አለማስተዋል፣ የኛን አንግልም ካለመረዳት የመጣ ነው። ስለዚህ ተገቢውን መልስ እንስጥበት።

የዚህ ሰው ስህተት የሚመነጨው፣ አዲስ ነገር ስለመጣ ብቻ በራሱ ጥሩ ነገር ነው ብሎ ከማሰብ፣ ቴክኖሎጂንም እንዲሁ እንደወረደ ከመቀበል ነው። እንዲሁም ሃገራችን ያለችበትን የቴክኖሎጂ እድገት ደረጃ ካለመረዳት ነው።

ስለ ሃገር እናስብ ከተባለማ፣ ሀገር የሚለውጥ አዲስ ሃሳብ እንቀበል ከተባለማ ስለሱ ብዙ ነገር ማለት ይቻላል እኮ። ስለ ቴክኖሎጂ እናንሳ? እንግዲያውስ ኢትዮጵያ ምን አይነት የቴክኖሎጂ ደረጃ ላይ ነች? ለሃገር የሚጠቅም፣ እድገትና ሃብት የሚያመጣ፣ የሰዎችን ህይወት የሚያሻሽል፣ የዜጎችን የኑሮ ደረጃ ከፍ የሚያደርግ ቴክኖሎጂን እናስብ? ስለርሱ እናውራ? እሺ።

እንግዲያውስ ኢትዮጵያ ምን አላት? ምን አላት ከሚለው ይልው ምን የላትም? የሚለውን መመለስ ይቀላል።

ከውጭ የምናስመጣቸውን ነገሮች ለመቀነስ እዚሁ እንዲገኙ ለማድረግ የሚያስችሉ ኢንዱስትሪዎች የሏትም። ኢንዱስትሪዎቹ ያመረቱትን፣ ከእርሻም የሚመረተውን ከአንዱ የሃገር ክፍል ወደ ሌላው በብዛትና በፍጥነት ለማጓጓዝ የሚያስችል የተዘረጋ የባቡር ስረአት የላትም። (ባቡር ያለው በአዲስ አበባ ያለው 2 መስመር እና ወደ ጅቡቲ/ድሬደዋ የሚወስደው ብቻ ናቸው። እርሱም ግን ከሚያስፈልገን ውስጥ 5 ወይም 10 በመቶው ቢሆን ነው።)

ሰዎች በዘመናዊ መልኩ እቃ እንዲላላኩ የሚረዳ የፖስታ ስርአት የለንም። በስም ደረጃ አለን ግን ተጠቃሚ የለንም። ሰው እስካሁን በባህላዊ መንገድ በሰው ነው እቃ የሚላላከው። ፖስታ ስረአቱ እንዲሰራ የሚረዳ ዘመናዊ የአድራሻ ስረአትም የለንም። ዛሬም ድረስ "ከእከሌ ህንጻ ጀርባ ወረድ ብሎ ባለው መንገድ" እየተባለ ነው ቦታ የሚነገረው። የዓለም ዲፕሎማቶች መጥተው ስብሰባ በሚያደርጉበት ከተማ፣ አድራሻ የሚነገረው "በዚህ ወርደህ እንትኑ ጋ ስትደርስ እንትኑ አለ" እየተባለ ነው።

ከተማው ውስጥ ዝናብ ሲዘንብ ጎርፉን ከመንገድ አስወጥቶ ወደ ወንዞች የሚወስድ፣ ፍሳሽን ከየሰዉ ቤት ወስዶ ወደ አንድ ማጣርያ ጣብያ የሚመራ የተደራጀ ደህና የፍሳሽ ስረአት የለንም። ዛሬም ዝናብ ሲዘንብ ጎርፉ እና ከሰው ሽንት ቤት የሚፈሰው አብሮ መንገዱ ላይ ይጎርፋል። አዲስ አበባን ጨምሮ በመላው ሃገሪቱ ሰዎች እስካሁን የጭቃ ቤቶች ውስጥ፣ በ1980ዎቹ የነበረውን አኗኗር ይዘው ነው የሚኖሩት ። እስካሁን የመብራት ሃይል ያልገባላቸው ከተሞች እና የገጠር መንደሮች አሉ።

መኪና እና ላፕቶፕ በሃገራችን እጅግ ውድ ከሆኑ ነገሮች ውስጥ ናቸው። የላፕቶፕ እጥረት ከመኖሩ እና ከመወደዱ የተነሳ እጀግ የሚበዛው የሃገሪቱ ወጣት ኮምፒውተር ተጠቅሞ አያውቅም። ከ40ዎቹ እድሜ በላይ ያለው እንዲያውም፣ አብዛኛው ሰው ስማርት ፎን እንኳ በቅጡ መጠቀም አይችልም። ዲጂታል አይዲው ቢመጣ እንኳን በመላው ሃገሪቱ ቀበሌዎች እና ከተማ አስተዳደሮች ያሉት ሰራተኞች እጅግ የሚበዙቱ መሰረታዊ የኮምፒውተር አጠቃቀምን የማይችሉ ናቸው። ስራው ሁሉ የሚሰራው በወረቀት ነው። መረጃ የሚቀመጠው በወረቀት ነው። የኮምፒውተርና ሶፍትዌር ሰረአት ልክ እንደ ህንጻና ድልድዩ ሁሉ እርሱም የራሱ መሰረተ ልማት ይፈልጋል። ኢትዮጵያ ደግሞ የሶፍትዌር መሰረተ ልማቷ ገና አልተጀመረም። ገና ምኑም አልተነካም አልተነካም። አንዳንዱ ሊሰራም ገና አልታሰበም። ይሰራ ቢባል እንኳ የመስራቱን ጥረት ቢሮክራሲው አንቆ ይዞ እንዲቋረጥ ያደርገዋል።

ታድያ እንዲህ አይነት ኋላ ቀር የሆነ፣ ገና መሰረታዊ ቴክኖሎጂ ያልገባው ሃገር እና ህዝብ ይዘን፣ በቴክኖሎጂ ዙርያ የተገነባ ባህል የሌለው ማህበረሰብ ይዘን፣ አሁን አዲሱ ብልጭልጭ ነገር ለምን እኛም ቤት አልመጣም ብሎ መናደድ የራስንም ሃገር፣ የቴክኖሎጂንም አሰራር፣ የማህበረስብንም አሰራር አለመረዳት አለማስተዋል፣ አለማወቅም ጭምር ነው። ሌላው ዓለም እነዚህን ነገሮች ጨርሶ ነው ወደ ዲጂታል አይዲ ያመራው። ዘመናዊ ስረአቶችን ዘርግቶ ጨርሶ፣ ህዝቦቹ በዚያ ስረአቶች ውስጥ መኖርን እንዲለምዱ አድርጎ፣ በአሰርት ዓመታት ሂደት ቴክኖሎጂ መር የሆነ ባህል ከገነባ በኋላ ነው አሁን ድጂታል አይዲን ያመጣው። ህዝቡም ከአንዱ የቴክኖሎጂ ሰረአት ወደ ሌላው ቴክኖሎጂ ማምራትን በደምብ ስለተለማማደ አዲስ ቴክኖሎጂ ሲመጣም ለመቀበል አይቸገርም።

እኛ ያ ሳይኖረን፣ ባቡርና ፖስታ ሳይኖረን፣ ሽንት ቤቶቻችን ከደህና የፍሳሽ ስረአት ጋር ሳይገናኙ፣ አራት እና አምስት እስቴፕ ዘለን፣ ዲጂታል ሰረአት ጋር ካልመጣን፣ ቴክኖሎጂ መር እስማርት ከተማ ካልገነባን ማለታችን በሌላው ዓለም እንኳ እንዲሳቅብን የሚያደርግ ነገር ነው። ትክክለኛውን የእድገት እና የሽግግር እስቴፕ ሳንከተል መጥተን ይህኛውን ግን አሁኑኑ ካላገኘን፣ ይህኛውን ካልተገበርን ማለታችን ራሱ አለማስተዋላችንን ብቻ ሳይሆን ችኩልነታችንን ነው የሚያሳየው። ይህ ሁሉ ታዲያ ዲጂታል አይዲ፣ ክፋት ባይኖረው ብለን አስበን ነው። እንደው መልካም ቴክኖሎጂ፣ ጠቃሚ ስረአት ነው ብለን ብናስብ እንኳ ማለት ነው። በዚያ ሁኔታ ውስጥ እንኳ አጉል መቸኮል ነው። አንዳንዶች፣ ዲጂታል አይዲው ይፈታዋል ብለው የሚያስቧቸው ችግሮች፣ በሌላው ዓለም የዛሬ 20 እና 30 ዓመት ያልነበሩ ወይም የተፈቱ ናቸው። እኛ ዛሬ ላይ የወረቀት አሰራራችን እንኳ በቅጡ ሳይተገበር፣ የቀበሌ ሰራተኞቻችን የተሻለ እንዲማሩ በማድረግ እና ፈረንጆች የዛሬ 30 ዓመት የተጠቀሙትን የወረቀት አሰራር ሰራቶች በመጠቀም ብቻ መፍታት የምንችላቸውን ችግሮች፣ ዲጂታል አይዲ ካልመጣ መፍታት አንችልም ማለት የኛን አለማወቅና አለማስተዋል፣ ቴክኖሎጂ ነክ እውቀታችንና አረዳዳችንም ትንሽ እንደሚቀረው ብቻ ነው የሚያመላክተው። ስለዚህ እባካችሁን እናስብ፣ እናስተውል። ዓለም ምን ደረጃ ላይ ነው፣ ከየት መጥቶስ ነው እዚህ የደረሰው፣ እኛ ምን ያህል ወደኋላ ቀርተናል የሚለውን እናስብ። እዛስ ለመደረስ እነሱ ያለፉትን 30 ደረጃዎች እኛም ማለፍ አለብን ወይስ በአንዴ ዘለን እነሱ አሁን ያሉበት ጋር መቆም አለብን የሚለውንም ጊዜ ሰጥተን እናስተውል። እግዚአብሔር ማስተዋሉን ያድለን።

Post a Comment

0 Comments