"ኢትዮጵያ ብዙ የሌላት ቴክኖሎጂ አለ" የሚል ጽሁፍ ካነበባችሁ በኋላ እንዴት ነው "ቴክኖሎጂን ከሰይጣን ስራ ጋ አንድ አድርጋችሁ ታያላችሁ" የሚል መልስ የምትሰጡት? ያነበባችሁትን አልተረዳችሁም እንዴ? እስቲ ምናልባት ደግማችሁ አንብቡት እንደትረዱት። ተቃዋሚ ሁላ እንደ ሚኒሊክ ዘመን ተቃዋሚ ይመስላችኋል እንዴ? አንዱን ቴክኖሎጂ መቃወም እኮ ሁሉንም እንደ ክፋት ማየት አይደለም።
አዎ ሰይጣናዊ ቴክኖሎጂ አለ። እና ምን ይሁን? ያ ማለት ስልክ ሰይጣን ነው ማለት አይደለም። ያ ማለት መኪና ሰይጣን ነው ማለት አይደለም።
በሚኒሊክ ዘመን የነበሩ ሰዎች ባለማወቃቸው ነው ያንን ያሉት። የድንቁርና ጭለማ ዘመን ውስጥ ስለነበርን ነው ያንን ያሉት። ኢትዮጵያ ከነበራት የስልጣኔ ከፍታ ተፈጥፍጣ ወድቃ የድህነት እና የድንቁርና እመቀ እመቃት ወርዳ ነበር። በዚያም ጊዜ ባለ ራዕዩ አጼ ቴዎድሮስ ያንን ለመለወጥ ስልጣኔን፣ የእጅ ስራን፣ ቴክኖሎጂን ለማምጣት ደከመ።
በልጅነቱ መቅደላ ላይ በቴዎድሮስ ስር ያደገው ምኒልክም ብዙዎች ያልተረዱትን ቴዎድሮስን ተረዳው። ዘመናዊነትንም ለማምጣት ብዙ ስራ ሰራ። እርሱ ውጪ ሃገር ልኮ ያስተማረው ኃይለ ስላሴም፣ ብዙ ነገር ቢያጠፋም እርሱም ምኒልክ የጀመረውን ቴክኖሎጂ ጨምሮበት ብዙ ነገር ሰራ።
ታድያ ምንሊክ አዲስ ቴክኖሎጂ ሲያመጣ፣ ቴዎድሮስን እንደ እብድ የቆጠረው በድንቁርና ዘመን ውስጥ የነበረው ኢትዮጵያዊ፣ ምኒሊክን ደግሞ የሰይጣን ስራ አመጣህብን ብሎ ወቀሰው። ምኒሊክ ግን ያንን ወደጎን ትቶ ትኩረት ሳይሰጠው ብዙ ነገር ሰርቶ አለፈ። ቴሌኮምን፣ ባቡርን፣ ትምህርት ቤትን ሰጥቶን አለፈ።
እና እሁን፣ ቴክኖሎጂ እና እድገት መምጣቱ ክፉ አይደለም። ሃብት መምጣቱ ክፉ አይደለም። እንደ ሃገራችን ትልቅነት ብዙ ስልጣኔ፣ ብዙ ሃብት፣ ብዙ ቴክኖሎጂ፣ ብዙ ብልጽግና ይገባናል።
ያ ማለት ግን ፈረንጅ ያመጣውን አሰስ ገሰስ ሁሉ መቀበል አለብን ማለት አይደለም። እነሱ የራሳቸውን ዜጎች ለመሰለል የሰሩትን እኛም ለኛ ካልሆነ ማለት የለብንም። በቃ ብልጭልጭ ነው። ጎጂ ሲያዩት የሚያምር ብልጭልጭ። አዲስ ብልጭልጭ ነገር ለምን እኛም አልኖረንም ማለት የለብንም። ይህንን ተረዱ።
እዚህ ጋር ሌላም ማብራርያ። አንዳንዶች ደግሞ ኢትዮጵያ በድንቁርና ዘመን ውስጥ ነበረች ሲባል ሁሉ ነገሯ እንደዛ ነው ብሎ ያስባል። ባህሉ ሁሉ እምነቱ ሁሉ የኋላ ቀርነት እና የድንቁርና አድርጎ ያስባል። ትንሽ ዘመናዊ ትምርት ቤት ገብቶ የፈረንጅ ፊደል እንደቆጠረ፣ ወድያው ኢትዮጵያ ያላት ሁሉ ኋላ ቀርነት ይመስለዋል። ሃይማኖት ሞኝነት፣ ማህበራዊ ኑሮ ሞኝነት፣ ባህል ኋላ ቀርነት ነው ብሎ ያስባል።
አውሮፓውያን እምነታቸውን አሽቀንጥረው ጥለው ባዶነት ሲሰማቸው የፈጠሩትን ፍልስፍና ያነብና ከዚያ ያም ሁሉ እንደ ወረደ ይቀበለዋል። ኒቼ ብቻ ትክክል፣ አልበርት ካሙስ ብቻ ትክክል፣ እስቴፈን ሆውኪንግ ብቻ ትክክል፣ ሌላው ደንቆሮ ነው ብሎ ያስባል። እነ አባ ጊዮርጊስን እንደ ደንቆሮ፣ እነ ቅዱስ ዮሓንስ አፈወርቅን እነ ቅዱስ ቄርሎስን እንደ መሃይም መቁጠር ይዳዳዋል።
በዚህ ሁኔታ ሁላችንም ጽንፍ ይዘን ነው ያለነው። አንደኛው፣ እውቀትና ቴክኖሎጂ ከመጣ ባህል እና ሃይማኖት ሙሉ በሙሉ መጣል አለበት፣ አያስፈልግም ይላል። ከዚያም ሌላ መጥቶ ቴክኖሎጂን ሲቃወም፣ አሃ! አንተማ ከዚያ ኋላ ቀር ባህል እና እምነት የመጣህ አደለህ? በቃ ሁሉም ነገር ላንተ የሰይጣን ስራ ነዋ??!! ብሎ አፉን ሊያዘጋ ይሞክራል። በቃ ከሳይንስ ወይም ከቴክኖሎጂ አንዱን ነገር ከተቃወምክ ፍጹም መሃይም ኋላ ቀር ወግ አጥባቂ መሆን አለብህ። እንጂ "የተወሰነው ትክክል ነው፣ ግን እዚህ ጋ ስህተት አለ" ማለት አትችልም። እንዴት ሲሆን? ለምን ሲባል ሚዛናዊ የሆነ እይታን ትይዛለህ? እንደኛ ጽንፍ ርገጥ እንጂ!!! አዋቂ ስልጡን የምትሆነው ፈረንጅ እና አይሁድ ነው ያለህን ነው አይደለም ያለህን ሁሉ አይደለም ካልክ ብቻ ነው። አሰስ ገሰሱን ሁሉ እንደወረደ ከተቀበልክ ብቻ ነው። ያ ነው እርድና እና ስልጣኔ በቃ።
አንዱ ደግሞ እምነቱና ባህሉ ላይ ችክ ብሎ ስልጣኔን ላለመቀበል ያስቸግራል። አድዋን ያሸነፍነው እግዚአብሔር ስለረዳን ብቻ አይድለም፣ የጦር መሳርያም ስለነበረን፣ የጦር እስትራቴጂን ስለተጠቀምን፣ ከሱዳኖች ጋር አውርተን ጦርነቱ ቀጣናዊ እንዳይሆን ስላደረግን፣ የስለላ ስራን ሰርተን የጠላትን መረጃ ስለያዝን አይደለም ይልሃል። እነዚህን ነጥቦች ካነሳህ አንተ ማለት እዛኛው ጽንፍ ላይ ያለኸው ነህ። በቃ ሁሉም ነገር ሎጂካል ማብራርያ አለውና የእግዚአብሔር እርዳታ አልታከለበትም ብለህ ነው ምታስበው። እንጂ እኛም ለፍተን ብልጥ ሆነን፣ እግዚአብሔርም ረድቶን ነው ብለህ ማሰብ የለበህም። እንዴት ብትደፍረን ነው እንደዛ የምታስበው? እንዴት ብትደፍረን ነው ሚዛናዊ አስተሳሰብ የምትይዘው? እንዴት ብትደፍረን ነው ጽንፍ የማትይዘው? ትባላለህ።
ከዚህ ጽንፍ ረጋጭነት ወጥተን ሚዛናዊ ሰው የምንሆነበት ቀን መምጣት አለበት። ከእውቀቱም ከሃይማኖቱም ወስደን የምንሄድበት ዘመን መምጣት አለበት። ለነገሩ ዘመን ይመጣል ይሄዳል። እኛ ነን መለወጥ ያለብን። ያን አይነት አቋም መያዝ አለብን። ትንሽ ተማርን ብለን ሃይማኖትን አለመናቅ። ሃይማኖትና ባህል አለ ብለን ቴክኖሎጂና ስልጣኔን ሃብትን አለመናቅ። ያንን ማድረግ አለብን። ያንን ማድረግ የቻለን ቀን ነው ለኢትዮጵያ ትንሳኤ የምንበቃው።
0 Comments