ሚካኤል ዘኢትዮጵ
አቡ ሀይደር በክፍል ሁለት ጽሑፋቸው "አል-ባዒሥ (ላኪ/አስነሺ)" የሚለውን ስም በመተንተን ኢየሱስ ክርስቶስን ተላኪና ተነሺ ብቻ በማድረግ ከአምላክነት ተራ ለማውጣት የሞከሩበት መንገድ የክርስትናን ምሥጢረ ሥጋዌ ትምህርት ካለመረዳት የመነጨ ነው። ክርስቶስ ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው ነው፤ በመሆኑም ጸሐፊው "ተላኪ" እና "ተነሺ" በማለት የጠቀሷቸው ጥቅሶች የክርስቶስን ትስብዒት የሚገልጹ እንጂ መለኮታዊ ባሕርዩን የሚነጥቁ አይደሉም። ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናንዙ እንዳስተማረው "እንደ ሰው ተላከ፤ እንደ አምላክ ግን እርሱ ራሱ ይልካል"። ክርስቶስ "አብ እኔን እንደ ላከኝ እኔ ደግሞ እልካችኋለሁ" (ዮሐንስ 20:21) በማለት ራሱ ላኪ መሆኑን አረጋግጧል። አብና ወልድ በፈቃድና በሥራ አንድ በመሆናቸው፣ አብ ሲልክ ወልድ ደግሞ "በፈቃዱ" ይላካል እንጂ እንደ ባሪያ ተገዶ የሚላክ አይደለም። ስለዚህ ክርስቶስን "ተላኪ ብቻ" አድርጎ ማቅረብ የአካልና የባሕርይ አንድነቱን መካድ ነው።
ጸሐፊው "ኢየሱስን ያስነሣው እግዚአብሔር ነው" የሚለውን ጥቅስ የክርስቶስን አምላክነት ለማፍረስ ቢጠቀሙበትም፣ ነገር ግን ትንሣኤው የሥላሴ የጋራ ሥራ ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ "ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት በሦስተኛውም ቀን አነሣዋለሁ" (ዮሐንስ 2:19) በማለት ራሱን በራሱ እንደሚያነሣ የተናገረው ትልቅ ምሥጢር አለው። እርሱ ሕያው ቃል በመሆኑ በሥጋ ቢሞትም በመለኮቱ ግን ሞትን የገደለና መቃብርን የከፈተ "ትንሣኤና ሕይወት" እርሱ ራሱ ነው። አቡ ሀይደር "ተቀስቃሽ እንዴት ቀስቃሽ ይሆናል?" በማለት የጠየቁት ጥያቄ፣ መለኮትና ሥጋ የተዋሐዱበትን "አንድ አካል አንድ ባሕርይ" የመሆን ምሥጢር ካለመረዳት የመጣ ነው። ክርስቶስ በሥጋ ተነሣ ሲባል፣ በሥልጣነ መለኮቱ ራሱን አስነሣ ማለት ነው። በመሆኑም ሙታንን የሚቀሰቅሰው "አል-ባዒሥ" አላህ ብቻ ነው የሚለው የጸሐፊው ድምዳሜ፣ መጽሐፍ ቅዱስ "በመቃብር ያሉት ሁሉ የሰው ልጅን (የክርስቶስን) ድምፅ የሚሰሙበት ሠዓት ይመጣል" (ዮሐንስ 5:28) በማለት የትንሣኤው ጌታና አስነሺው ክርስቶስ መሆኑን ከሚመሰክረው እውነት ጋር ይጋጫል።
ሲጠቃለል አቡ ሀይደር "አል-ባዒሥ" የሚለውን ስም ለኢየሱስ መስጠት አግባብ አይደለም ማለታቸው፣ የክርስቶስን የባሕርይ አምላክነት ከመካድ የመነጨ "የአርዮሳውያን" ክርክር ቅጂ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ክርስቶስ የትንሣኤ ባለቤት እንጂ እንደ አልዓዛር በሰው ጸሎት የተነሣ አይደለም። እርሱ ሞትን በሞቱ የገደለ፣ ሲዖልን የበዘበዘና የሰው ልጆችን ሁሉ በቀጠሮው ቀን ከመቃብር የሚያስነሣ የክብር ጌታ ነው። ጸሐፊው የቋንቋ ትንተና ላይ ትኩረት በማድረግ "አል-ባዐት" የሚለው ቃል ስም አይደለም ቢሉም "ትንሣኤ (Resurrection)" የሚለው ቃል በባሕርይው ክርስቶስን ይወክላል፤ እርሱ ትንሣኤ ነውና።
Michael Z Ethiop
05/05/2018 ዓ/ም
0 Comments