የሩሲያዉ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን የሚከተለውን መልእክት መናገራቸው በማኅበራዊ ሚዲያ እየተዘዋወረ ይገኛል፦ "አንድ የአፍሪካ ሰው ሃብታም ሲሆን የባንክ ሒሳቦቹን ወደ ስዊዘርላንድ ይልካል፤ ለሕክምና ወደ ፈረንሳይ ይጓዛል፤ ወደ ጀርመን ሄዶ ኢንቨስት ያደርጋል፤ ምርቶችን ከዱባይ ይገዛል፤ የቻይና ቁሳቁስ ይጠቀማል፤ እሱ በሮም ወይም በመካ ይጸልያል፤ ልጆቹ በአውሮፓ ይማራሉ፤ ወደ ካናዳ፣ አሜሪካና አውሮፓ ሄደው ይጎበኛሉ።"
ይህ አባባል በይፋዊ መንገድ ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የወጣ መሆኑን የሚያረጋግጥ የታመነ መረጃ አላገኘሁም። በማኅበራዊ ሚዲያ ግን እየተዘዋወረ ነው። እርግጥ ነው በመልዕክቱ ውስጥ የተካተቱት ነጥቦች ግን የአፍሪካን ወቅታዊ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እውነታዎች በጥልቀት የሚነኩ ናቸው። አባባሉ አፍሪካን "የመቃብር ስፍራ" በማለት የገለጸበት ዋና ምክንያት፣ የአሕጉሪቱ ልሂቃንና ባለሃብቶች በገዛ አገራቸው ላይ ያላቸውን እምነት ማጣትና የሃብት ሽሽትን ለማሳየት ነው። አንድ አገር ሊያድግ የሚችለው ዜጎቿ በተለይም ባለሃብቶችና የተማሩ የሰው ኃይሎች ዕውቀታቸውንና ጥሪታቸውን በአገር ውስጥ ኢንቨስት ሲያደርጉ ብቻ ቢሆንም፣ የአፍሪካ ተጨባጭ ሁኔታ ግን ከዚህ ተቃራኒ መሆኑን አብዛኞቻችን የምንስማማበት ሐቅ ነው። የተከማቸ ሃብት ወደ ስዊዘርላንድ ባንኮች መፍሰሱ፣ የአፍሪካ ባንኮች ለልማት የሚሆን ብድር እንዳያቀርቡና የፋይናንስ ሥርዓቱ ደካማ ሆኖ እንዲቀጥል ሲያደርግ፣ ባለሃብቶቹም በአገራቸው የኢንዱስትሪ መዋቅር ከመዘርጋት ይልቅ የውጭ ምርቶችን ማራገፍ ላይ ማተኮራቸው አሕጉሪቱን የፍጆታ ማዕከል እንጂ የአምራችነት መናኸሪያ እንዳትሆን አድርጓታል።
ይህ ሥነልቦናዊና መዋቅራዊ ጥገኝነት በጤና እና በትምህርት ዘርፎች ላይም በግልጽ ይስተዋላል። የአፍሪካ መሪዎችና ባለጸጎች ጥቂት ሕመም ሲሰማቸው ወደ ፈረንሳይና አውሮፓ ለሕክምና መጓዛቸው፣ በአገር ውስጥ ያለውን የጤና ተቋም ለማሻሻል ትኩረት እንዳይሰጡ ከማድረጉም በላይ፣ የአገር ውስጥ የሕክምና ባለሙያዎች ተስፋ ቆርጠው እንዲሰደዱ (Brain Drain) ምክንያት ሆኗል።
በተመሳሳይ መልኩ የባለሥልጣናት ልጆች በአውሮፓና በአሜሪካ እንዲማሩ መደረጉ፣ በአፍሪካ ውስጥ ያለውን የትምህርት ጥራት ለማስተካከል የሚደረገውን ጥረት ያዳክመዋል። የፑቲን ንግግር ተብሎ በቀረበው አባባል ውስጥ "አንድ የመቃብር ስፍራ እንዴት ሊለማ ይችላል?" ሲል የጠየቀው ጥያቄ፣ ዜጎች ጉልበታቸውን፣ ዕውቀታቸውንና ትርፋቸውን ለሌላው ዓለም ገዝተው፣ ሕይወታቸው ሲያልፍ ብቻ ወደ ትውልድ መንደራቸው ለአፈር መመለሳቸው ለአገሪቱ ምንም ዓይነት የልማት ፋይዳ እንደማይኖረው ለማሳየት ነው።
ከዚህም በተጨማሪ፣ ንግግሩ የአፍሪካን መንፈሳዊና ባሕላዊ ጥገኝነት ጭምር ይዳስሳል። ዜጎች ለጸሎት ወደ ሮም ወይም መካ መጓዛቸውና ለግዢ ዱባይን ምርጫቸው ማድረጋቸው፣ አሕጉሪቱ በራሷ እግር ለመቆም ያላትን ሥነልቦናዊ ዝግጁነት ጥያቄ ውስጥ ይከተዋል። የመቃብር ስፍራ ተምሳሌትነት የሚያሳየው፣ አፍሪካ ለዜጎቿ የሚንቀሳቀስና የሚያድግ ሕይወት የምትሰጥ ሳይሆን፣ መጨረሻ ላይ በክብር ለማረፍ ብቻ የምትፈለግ "የማይንቀሳቀስ ንብረት" እየሆነች መምጣቷን ነው። በአጠቃላይ ይህ ትችት አፍሪካውያን ከጥገኝነት ወጥተው፣ የራሳቸውን የትምህርትና የጤና ተቋማት እንዲገነቡ፣ ሃብታቸውን በአገር ውስጥ ኢንቨስት እንዲያደርጉና አሕጉሪቱን ከመቃብርነት ወደ ህያው የዕድገት ምድር እንዲቀይሩ የቀረበ የነቃ ንግግር ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።
Michael Z Ethiop
27/04/2018 ዓ/ም
0 Comments