✍ ሔኖክ ኃይለገብርኤል
የፍቺ ወረርሽኝ ያስከተለው የቤተሰብ መፍረስ፣ የልጆች መበተን፣ የአባወራነት መክሰም የትውልድም መረን መውጣት!
ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት በ1992 ዓ.ም. በሀገራችን በኢትዮጵያ በወቅቱ በነበረው፦ የካርል ማርከስ የብሶት ጽንሰሃሳብ ወዳጅ በኾነው፤ መንግሥት “በእኩልነት፣ መብትና ነፃነት” ሰበብ ኢትዮጵያውያን ላይ በተለይም ሙስሊሙ ሲቀር ሌላው ማኅበረሰብ ላይ መቅሰፍት ወረደ!
በእርግጥ ይህንን መቅሰፍት ጥቂቶች፣ በተለይም ሆዳደር የነበሩ የጠላት ቅጥረኞች “የሴቶች እኩልነት፣ መብትና ነፃነት እውን ኾነ” ሲሉ አወድሰውታል!
ነገር ግን ዛሬ ላይ ቆመን ያንን ክፉ ቀን፣ የኾነብንንም ስናስታውሰው፦
🚨 ኢትዮጵያን ከመሰረቷ የናዳት፣
🚨 ከቤተሰብ አልፎ ሀገርን ሊመራ፣ ሊጠብቅ፣ ሊገነባ ያለውን የወንዱን ወኔ የሰለበ፣
🚨 ትውልድን መረን አውጥቶ ለሥነ-ልቦናዊ ቀውስም የዳረገ፣
🚨 ከታላቅ ብሔራዊ ሀገራዊም ክብርና ጥቅም ይልቅ የግል ጥቅሙን ወዳጅ ሆዳደርን ያተረፈ “የፍቺ ወረርሽኝን” አስከትሏል።
የዚህ ሁሉ መነሻ ጥንስሱ “የቤተሰብ ሕግ ይሻሻል” ብለው ያስገቡት “እርሾ” ነው። እርሱም ያለ ምንም ጥፋትም ቢኾን (ጥፋት ባይገኝም) “በቃኝ” በማለት ትዳርን የማፍረስ “ነፃነት” መስጠቱ ነው።
በዚህም ደግሞ ትዳር እንደማንኛውም የንግድ ስምምነቶች(ውሎች) መቆጠሩ ብቻ አይደለም፤ ከእነርሱም በባሰ የተዋዋዮቹን ግዴታ ማስገደድ የማይችል ተራና ተርታ እርባናቢስም መደረጉ እንጂ።
በዚህ ደግሞ ከውሉ ይልቅና ይበልጥ ተዋዋዮቹ ፣ ውሉን በተለይ የሚያፈራርሙት ተቋማት ለምሳሌ ቤተክርስትያን፣ የውሉ አስገኝ አመንጭ የነበረው አባታችንም የተናቁበት እንደኾነ ግልጥ ማሳያ ነው።
ይህ ሁሉ ግን በካርል ማርክስ ሰይጣናዊ መንገድ፣ እርሱንም በተከተሉ በሚከተሉም አፍቃሬ ማርክሳውያን ለትውልዱ “እኩልነት፣ መብትና ነፃነት” በሚል ሰበብ ተፈጸመ፤ ዛሬም የጥፋት መቅሰፍቱ ቀጥሏል።
ከዚህ በፊትም እንደጻፍኩት አንድ ተቋም ምን ትልቅ፣ ግዙፍ፣ አለማቀፍ ቢባል አንድ መሪ፣ ተጠሪ፣ አስተዳዳሪ አለው። ሸፍጠኞች ማርክሳውያን፣ አባታችንን እና የእርሱ የኾነውን ሁሉ የማይወዱ የጥፋት መልእክተኞች ግን ሁለት አባላት ብቻ ያሉትን ትዳር-ተቋም “በሁለቱም እኩል ይመራ” ይሉታል።
ይህን ማለታቸው ለትውልዱ አስበው፣ በተለይም እነርሱ እንደሚሉት ለሴቷ ተቆርቁረው አይደለም። ነገር ግን የሐሰት አጥማቂያቸው(ካርል ማርክስ) እና ለሐሰት አባቱ ሰይጣን የተሻረኩበትን ጥንታዊና “ውጤታማ” የውጊያ ስልት ሲጠቀሙ እንጂ!
ቤተክርስትያን እንኳ የትዳር መሪው አባወራው መኾኑን ማስተማር፣ ማሠልጠን፣ መምከር እስክትተው ድረስ የዚሁ አጥፊ ሕግና የ”ሊቃውንቱ” የጥፋት ተባባሪነት ቀጥሏል።
ዛሬ የቅድመ ጋብቻ ትምህርት ልትማሩ ብትሄዱ ተምታቶባቸው፣ የሚያምታቱ፤ አንድም ተከፍሏቸው የሚያምታቱ አሠልጣኞች ባልና ሚስት እንዴት “ተከባብረውና ተመካክረው” ትዳር እንደሚመሩ ይነግሯቹኋል እንጂ በጭራሽ የወንዱን ራስነት፣ መሪነት፣ ውሳኔ ሰጪነት መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገር አያስተምሯችሁም!
እነርሱም አይኖሩትምና አያውቁትም፤ በተግባር በሕይወት አያውቁትምና የላቸውም፤ በልብ በልማዳቸው የላቸውምና ሊሰጧችሁም አይችሉም!
ቢሰጧችሁ እንኳ ያንኑ በልባቸው ሞልቶ የፈሰሰውን፤ በእኩልነት፣ መብትና ነፃነት ተሳቦ የሰለባቸውን፣ ግዳጅ መፈጸም የማይችለውን፣ ካገኘ በልቶ ካጣ ተደፍቶ የሚያድረውን፤
🚨 ከሁሉም የሚከፋው ደግሞ እነዚህን ሁሉ በመንፈሳዊነት ስም ለብጦ የታጀረውን፣ በዚያም በታጀረበት እብሪት ትዕቢቱ የሚጠፋውን እንከፍ፣ ምስኪን፣ ጃንደርባ፣ አልጫ ማንነት ነው!
የፉክክር ቤት ሳይዘጋ ያድራል እንዲሉ! ዛሬ የክርስትያኑ ቤት የፉክክር እንዲኾን ራሳቸው ባፍጢም የተደፉ ሆዳደር ልሂቃን አድርገውታል።
“በእኩልነት፣ መብትና ነፃነት” ስም በተሰጣቸው ራስን በራስ ማጥፊያና ማምከኛ መሣሪያ ሚናቸውን የሳቱ፣ ግዴታቸውን የዘነጉ፣ ኃላፊነታቸውን የረሱ፤ ስጦታቸውን የናቁ፣ መክሊታቸውን የጣሉ፣ ተፈጥሮአቸውን የቀበሩ ሁለቱ(ባልና ሚስት) ጠዋትና ማታ ፉክክርን ቀለባቸው አድርገረውት ራሳቸውም ኾኑ ትውልዳቸው ጠፉ!
ልሂቃኑ ለትውልድ-ማኅበረሰቡ ሕልውና ካልተጨነቀ፣ ተጨንቆም ሳይቀር “ይህ ለማኅበረሰባችን አይበጅም” ብሎ ካልሞገተ፣ በዚያም የሚመጣበትን የመከራ ጽዋ ካልጨለጠ፤ እርሱ የማዕረግ ድርድር መስቀያ፣ የዩቲዩብና የመድረክ ሸቃላ እንጂ ምን ይባላል?
እርሱ ትውልዱ ድኅነት የሚያገኝበትን መንገድ ካልጠቆመ፤ ጭራሹን ደግሞ የሚፈርስ የሚጠፋበትን መንገድ ካመለከተ፣ ልክ እንደ ሰይጣን ከትውልዱ ሔዋንን ፈልጎ በዚሁ የተንኮል ሃሳብ ካጠመደ፤
ከማኅበረሰቡ መካከል ያልተገኘው፣ ሕልውናውም የማይገደው ባዕድ፤ አጥፊውን፦ ሥራና መሣሪያ ለዚያ ትውልድ ቢያቀብለው ለምን ይደንቀናል? የተመቻቸንለት እኛ! ወደሽ ከተደፋሽ ቢረግጡሽ አይክፋሽ ይላሉ!
ማርክሳውያን በሁለት ሰዎች የሚመራ ማንኛውም ተቋም መጨረሻው መፍረስና መጥፋት እንደኾነ ያውቁታል። አባወራዊው ቤተሰብ ሳይፈርስ “የሴቶች እኩልነት፣ መብትና ነፃነት” እውን እንደማይኾን፤ አባወራው ሚስቱን ከማምረቻ መሣሪያ ለይቶ እንደማያያት ስለዚህም ይህ ቤተሰቡ መፍረስ የተገባው እንደኾነ ይናገራል።
ይህንን ደግሞ “ትዳራችንን ለሁለት በእኩልነት፣ መብትና ነፃነት ተጠቅመን እንምራ” ያሉት ሁሉ የደረሰባቸውን የቤተሰብ መፍረስ ከምዕራባውያን ሀገራት ጀምረህ እስከ ቤትህ ድረስ ተመልከት!
ጀግናው ይህ ዛሬ ዛሬ ትውልድን ከሚታደግ ሊቅነት ይልቅ ፌዘኛነትና ኮሜዲያንነት በሚያጠቃቸው የዘመኔ ዓይን አውጣዎች ይፈጸማል፤ ነገር ግን እግዚአብሄር ያያል፣ ትውልድም ይነሳል፦
🚨 ትውልድ እያጣን ነው!
🚨 ቤተሰብ እየፈረሰ ነው!
🚨 ልጆቻችን እየተበተኑ ነው!
🚨 ጋብቻ ትዳራችን መጠቋቆሚያ እየኾነ ነው!
🚨 ትዳርን ታናናሾቻችን እየፈሩት እየጠሉትም ነው!
🚨 ምን ቢማር “ዶክተርና ኢንጂነር፣ ሊቅና ሊቀ ሊቃውንት” ቢባልም አልጫና አስመሳይ፣ አድርባይና ሆዳደርም ትውልድ እያፈራን ነው!
🚨 የጠላቶቻችን መሳቂያና መሳለቂያም እየኾንን ነው!
🚨 ማኅበረሰባችን እየመከነ ነው!
ወንድምዓለም! ትዳርን ታናናሾቼ ቢፈሩት እኮ አይገርመኝም! የፈሩት ተፈራርሞ ማግባቱን አይደለም! ነገር ግን “ላልተዋትን” ሲፈርሙ፤ “በበቃኝ” ባዷቸውን ሊሰናበቱ የሚችሉበትንም የመጥፊያቸውን ውል አብረው እንደሚፈርሙ ስለሚያውቁ እንጂ!
የመጀመሪያው የፍቺ ጥሪ፦
“ወይዘሮ *** ይህ የሚወስኑት ውሳኔ እጅግ ከባድ ነው። በልጆችዎ ላይም ከፍተኛ የሥነ-ልቦና ጠባሳ ያስከትላል። ያልተግባባችሁበትን ጉዳይ በሽማግሌ ብትመክሩበት።
ወይዘሮ *** “እኔ በቅቶኛል፣ ከዚህ በላይ አልችልም...”
ዳኛው ለሌላ ቀን ቀጠሩ!
በሌላ ቀን ቀጠሮ ከሳሽና ተከሳሽ ተጠሩ ተከሳሽ ቀርበዋል ከሳሽ አርፍደዋል፤ ዳኛው ጥቂት ቆዩና የክሱን መዝገብ ወደ መዝገቤት መሩት።
የሁለተኛው የፍቺ ጥሪ(ከሳሽ እንደገና ሌላ አቤቱታ ከወራት በኋላ አቅርበዋል)፦
ዳኛው ተከሳሽን ፦
አቶ ሄኖክ ወይዘሮ *** በቃኝ ፍቺ እፈልጋለሁ ብለዋል እርሶ ምን ይላሉ።
አቶ ሄኖክ፦ መፋታትን እንቢ ብል ሕጉ ይፈቅድልኛል?
ዳኛ፦ አይፈቅድም! ሕጉ አንደኛው ወገን በቃኝ ካለ የትዳር ውሉ እንደሚፈርስ አስቀምጧል!
አቶ ሄኖክ፦ እና ምንም ማድረግ እንዳልችል በተደረግኩበት መጠየቄ ጥቅም የለውምና ሕጉ የፈቀደላትን ስጧት!
ዳኛ፦ ከዛሬ ጀምሮ ፍቺው በሕግ የጸና ይኾናል!
ለተወለዱት ሦስት ልጆች መከራ!
አባት-እግዚአብሄር ተለምኖ ከቸርነቱ ማማ በፈለቀ፣ በሞላ በተትረፈረፈ ለጋስነቱ ለወላጆች በአደራ ልጆችን ቢሰጥ፤ ለልጆቹም ቤተሰብን፣ አባትን እናትን ቢሰጣቸው እነርሱ ግን ያለምንም ጥፋት በ”በቃኝ” ተነፈጉበት፣ ቤተሰብ ፈረሰበት!
በዚህ መንገድ የጸና፣ ጸንቶም ያደገ፣ አድጎም የበለጸገ፣ በዚያ ብልጽግና መንገድም የቀጠለ መንግሥት፣ ሀገር፣ ማኅበረሰብ የለም፦ ሁሉም ከንቱ ኾነው ቀርተዋል! ምክንያቱም መገንቢያ ጡቡ ቤተሰብን በዓላማ እንዲጸና ከማድረግ ይልቅ በስሜት እንዲፈርስ ፈቅደዋልና!
“በቃኝ” በሚል ቃል፤ አልያም ትዳር ከተቋቋመበት ዓላማ አንጻር ኢምንት በኾነ ምክንያት ቤተሰብን ማፍረስ ለጊዜው የተቀጣጠለ ስሜትን ያስደሰተ ይምሰል እንጂ ሁላችንንም የሚያፈርስ “ጅምላ ጨራሽ” መሣሪያ ነው።
“በቃኝ” ብሎ ትዳር ማፍረስ ለእድገትና ብልጽግና (ባዕለጸጋ ለመኾን) ልምድና ጥበብ የጎደለው ያላዋቂ ትውልድ ውሳኔ እንጂ በምንም ዓይነት መልኩ ጀብድ ጀግንነትም አይደለም።
ትውልዱንም “በቃኝ” ብሎ ቤተሰብን አፍርሶ፣ ልጆችን በትኖ፣ በዚያም ሥነ-ሥርዓትና ምግባርን የማያውቅ ነገር ግን “የተማረ” መረንና ሆዳደር ትውልድ እንዲፈራ፤
ትውልድ እንዲጠፋ፣ ማኅበረሰብ እንዲመክን፣ ሀገርም በቤተሰብ በታነጸ ትውልድ ከመገንባት ይልቅ “የተማረና በቁሳዊ ሀብት የናጠጠ” ነገር ግን መረን ትውልድ እንድትፈርስ መዳረግ ነው!
ይህ በሀገራችን አፍቃሬ ማርክስ በኾኑት ተፈጽሟል!
የመገናኛ ብዙኃን፣ በማኅበራዊ ትስስር ገጽ መንደር ያሉ “ተጽዕኖ ፈጣሪዎች” ስለ ቀጣዩ የዐለም ጦርነት፣ የኒውክለር ቦንብ ባለቤትነት ይጨነቃሉ እንጂ ሀገር ተረካቢውን ትውልድ ገና በእንጭጩ እያደረቀ፣ ከሰውነት ማንነቱ እያራቀ፣ ማኅበረሰቡን እያመከነ ስላለው “ጅምላ ጨራሽ መሣሪያ”፦ ፍቺ ለማውራት ፈቃደኛ አይደሉም።
ይህ ጥፋት እንደ የኒውክለር ቦንቡ ሁሉ ዘር፣ ቋንቋ፣ ብሄር፣ መደብ ሳይመርጥ ትውልድን የሚያጠፋ ቢኾንም ቅሉ በተለይ ግን የራሳቸውን ማኅበረሰብ እንዲያጠፋ የክርስትናው “ሊቃውንት” መንገዱን ወደ ትውልዱ አድልተው ደልድለውታል።
በዚያም ለጥፋቱ ወደር፣ ወሰን፣ ድንበር ጠፍቶለት ኁልቁ መሳፍርት የሌላቸውን ቤቶች አፍርሷል፣ ልጆችን በትኗል፣ ለቤተክርስትያንና ለሀገር ሸክም የኾነ ትውልድ አትርፏል፤ ነገር ግን ሁሉም ዝም ጭጭ!
የጃንደርባው ያልኾነ የአባወራው ትውልድ ግን ታሪክን ይቀይራል፤ ይህንንም ይቀለብስ ዘንድ ይቀሰቀሳል፣ ይነሳልም! ምንም እንኳ ይመለከታቸዋል ብለን የሄድንባቸው ያማከርናቸው “ልሂቃን”፣ ለጊዜው ተደማጭነት አላቸው የምንላቸው እንኳ በራቸውን ቢዘጉብንም፤
አንዳንዶቹንም በጥፋቱ መንገድ የጠላት ቅጥረኛ ኾነው “ደመወዛቸውን” ለሚቆጥሩበት ጊዜ አጥተው ብናገኛቸውም፤ የትውልዳችን፣ የሀገራችን ነገር ግድ የሚለን አርበኞች፣ አባወራዎች ነንና ስለ እነርሱ ስንል ወደ ጽድቁ እንፋጠናለን!
0 Comments