ደምሴ ገረመው
በትዳር ውስጥ የሴትና የወንድ ሚና የሚወሰነው በሥነሕይወታዊ (Biological) ልዩነት ብቻ ሳይሆን በጥልቅ ሃይማኖታዊ፣ ሞራላዊና ባሕላዊ መሠረቶች ላይ ነው። ከመጽሐፍ ቅዱስ አንጻር ሲታይ፣ ጋብቻ በሁለት እኩል ባልሆኑ አካላት መካከል የሚደረግ ውል ሳይሆን፣ ልዩ ልዩ ስጦታና ኃላፊነት ባላቸው ሁለት አካላት የሚፈጠር አንድነት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ወንድን የቤት ራስ፣ ሴትን ደግሞ ረዳት አድርጎ ሲያቀርብ (ኤፌሶን 5፡22-33)፣ ይህ የሚያመለክተው የበላይና የበታችነትን ሳይሆን የሥራ ክፍፍልንና የኃላፊነት ቅደም ተከተልን ነው። ወንድ ለቤተሰቡ መሥዋዕት የሚሆን ፍቅርን እንዲያሳይ፣ ሴት ደግሞ ለባሏ ተገቢውን ክብርና ድጋፍ እንድትሰጥ የታዘዘው የቤተሰብ መዋቅር እንዳይፈርስና ሰላም እንዲሰፍን በማሰብ ነው። ይህ መለኮታዊ ሥርዓት በኢትዮጵያ ባሕልና ሞራል ውስጥም ትልቅ ስፍራ አለው። ባሕላችን ወንድን እንደ ጠባቂና ሁሉን ለቤቱ የሚያስፈልግ ነገር አቅራቢ፣ ሴትን ደግሞ እንደ ቤት መሠረትና አሳዳጊ በማየት የቤተሰብን ህልውና ለዘመናት ጠብቆ አቆይቷል።
ይሁን እንጂ በቅርብ ዐሥርተ ዓመታት ውስጥ ከምዕራባውያን አገራት የሚመነጨውና “የፆታ እኩልነት (Gender Equality)" የሚለው ጽንሰ ዐሳብ፣ ከላይ የተጠቀሱትን መለኮታዊና ባሕላዊ ዕሴቶች የሚንድ አጀንዳ ይዞ ብቅ ብሏል። ይህ አስተምህሮ ወንድና ሴት በባሕርይና በክብር እኩል መሆናቸውን ከማረጋገጥ አልፎ፣ በመካከላቸው ያለውን የተፈጥሮና የተግባር ልዩነት ጭልጥ አድርጎ በመካድ “ሁለቱም አንድ ዓይነት ናቸው” የሚል ዕሳቤን ያራምዳል። ይህ አካሄድ በምዕራባውያን ዘንድ እንደ ሥልጣኔ ቢቆጠርም፣ ብዙ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ግን በትዳር ውስጥ ግጭቶችን፣ የሥልጣን ሽኩቻንና የቤተሰብ መፈራረስን አስከትሏል። በተለይም “ራዲካል ፌሚኒዝም” የሚባለው አስተሳሰብ ሴቶችን ከቤት ውስጥ ኃላፊነት በማራቅና ወንድን እንደ ተቀናቃኝ እንዲያዩ በማድረግ፣ በትዳር ውስጥ ሊኖር የሚገባውን የመደጋገፍና የመከባበር መንፈስ በመርዝ እየበከለው ይገኛል። ይህ ሴራ ተፈጥሮአዊውን የቤተሰብ መዋቅር በማፍረስ ግለሰባዊነትን (Individualism) ማስፈንና ማኅበረሰባዊ ትስስርን ማላላት ላይ ያተኮረ ይመስላል።
በጥልቀት ሲተነተን፣ የምዕራባውያን የፆታ እኩልነት አስተምህሮ በብዙ መልኩ የሰውን ልጅ የተፈጥሮ ዝንባሌና መለኮታዊ ትእዛዝ የሚቃረን ነው።
መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ የፆታ ሚናዎች በግልጽ ባልተቀመጡባቸው ማኅበረሰቦች ውስጥ የፍቺ መጠን በከፍተኛ ሁኔታ የጨመረ ሲሆን፣ የልጆች አስተዳደግና ሥነ-ምግባርም አደጋ ላይ ወድቋል። ይህም የሆነው በቤት ውስጥ “ሁለት ራስ” ሊኖር ስለማይችልና አንዱ ሌላውን የመተካት ግዴታ ውስጥ ሲገባ የሚፈጠረው አለመግባባት የቤተሰቡን መረጋጋት ስለሚያናጋው ነው። ስለዚህ፣ በባሕልና በሃይማኖት የተቀመጡትን የወንድና የሴት ሚናዎች ማክበር ማለት ሴትን መጨቆን ሳይሆን፣ እያንዳንዱ አካል በተሰጠው ጸጋና አቅም ቤተሰብንና አገርን የሚገነባበትን ጥበብ መከተል ማለት ነው። የፆታ እኩልነት በሚል ስም የሚመጡ ባዕድ አስተሳሰቦችን በጥንቃቄ መመርመርና የራሳችንን የተቀደሰ የትዳር እሴቶች መጠበቅ ለቀጣዩ ትውልድ ደኅንነት ወሳኝ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል።
0 Comments